(ዘ-ሐበሻ) በሕዝብ ዘንድ “ልማታዊ አርቲስት” በሚል የመሽሟጠጫ ስያሜ ከሚጠሩት አርቲስቶች መካከል የቀድሞው የደርግ ወታደርና የአሁኑ የወያኔ ስርዓት ዋነኛ አቀንቃኝ አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ፤ ለመንግስት በሚያደርጋቸው የአጎብዳጅነት ተግባራት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ላይ የቶክ ሾው ፕሮግራም እንዲያዘጋጅ የዓየር ሰዓት ተፈቅዶላት ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል። ከአዲስ አበባ የዘ-ሐበሻ ምንጮች እንደጠቆሙት አርቲስቱ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ላይ ያቀርበው የነበረው ቶክ ሾው ውለታው ተዘንግቶ እንዲታገድ ተደርጓል።
“ግራና ቀኝ” የሚል ቶክ ሾው ከሌላኛው ‘ልማታዊ’አርቲስት ሽመልስ በቀለ ጋር ላለፉት 6 ወራት ሲያቀርብ የቆየው የደርጉ ወታደር ሰራዊት ፍቅሬ ይህን የዓየር ሰዓት ያገኘው ለመንግስት ባለው ታማኝነት እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም ድንገት ያቀርበው የነበረው ፕሮግራም በወያኔ ካድሬዎች በሚመራው ኢቲቪ እንዲታገድ መዳረጉ አስተተያየት ሰጪዎችን “ፍቅር አለቀ ወይ?” የሚሉ ግምቶችን እንዲሰጡ በር ከፍቶላቸዋል።
የአቶ መለስ ዜናዊ ሕልፈት ከተሰማ በኋላ አርቲስቶች ጥቁር በጥቁር ለብሰው “ባለ ራዕዩን መሪ” እንዲቀብሩ በማስተባበር እንዲሁም ጥቁር በጥቁር አንለብስም ያሉና ለቅሶ አንደርስም ያሉ አርቲስቶችን “ሲያስጠቁር” (ለመንግስት በማቃጠር) ነበር እየተባለ የሚተቸው አርቲስቱ 6 ወር በቴሌቭዥን ያቀረበው “ግራና ቀኝ” ቶክ ሾው እንዲታገድ የተደረገው “አዝናኝ ፕሮግራም” አይደለም በሚል ምክንያት ነው ተብሏል። ይህ እገዳ እስከመቼ ሊቀጥል እንደሚችል እንደማያውቁ የሚገልጹት የዘ-ሐበሻ ምንጮች ከባለፈው እሁድ ጀምሮ መታየት አቁሟል ብለዋል።
ኢቲቪ ወትሮም አዝናኝ ፕሮግራም አቅርቦ የት ያውቅና ሲሉ የሚተቹ አስተያየት ሰጪዎች አዝናኝ ፕሮግራም አይደለም በሚል ቶክ ሾው እንዲታገድ መደረጉ በቂ ምክንያት አይደለም በሚል ከእገዳው በስተጀርባ አንድ ነገር እንዳለ ይገምታሉ። በተለይም እንደሪፖርተርን ያሉ አፍቃሬ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ያሉ ጋዜጦች “በአቶ መለስ ስም መነገድ ይቁም” በሚል በረዥሙ ሲተቹ የከረሙት እንደሠራዊት ያሉትን ሆዳም አርቲስቶች ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች የኢቲቪ ካድሬ መሬዎች የሰራዊትን ማንነት በግልጽ ተረድተው ይሆናል ያገዱት ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
በዚህ ዜና ዙሪያ ዘ-ሐበሻ አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬን ለማነጋገር ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።
አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ በቅርቡም በአስገድዶ መድፈር አቤቱታ እንደቀረበበት መዘገቡ ይታወሳል።
የአስገድዶ መድፈር አቤቱታውን ዜና ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
ለግንዛቤ ደግሞ የታገደውን የሰራዊት ፍቅሬ ሾው አቅርበናል።
የ’ልማታዊው አርቲስት’ሠራዊት ፍቅሬ የኢቲቪ ፕሮግራም ታገደ
Tower in the Sky (የሰማይ ላይ ግንብ) –የመጽሐፍ ግምገማ
ድምጻዊ አበበ ከፈኒና ኤርሚያስ አስፋውን ሳስታውሳቸው
(በግርማ ደገፋ ገዳ)
ድምጻዊ አበበ ከፈኒ (ጄኔቭ) የሚገኝ እና ኤርሚያስ አስፋው ናዝሬት የሚኖር፤ የእነዚህን ሁለት የናዝሬት ድምጻውያንን ሙዚቃ ስሰማ አንድ ትዝ የሚለኝ ሁኔታ አለ። እ.ኤ.አ. 1998 በናዝሬት (አዳማ) ከተማ፣ ፋሲል ሆቴል ውስጥ በከተማዋ የሚገኙ ድምጻውያንን ለውድድር በአንድ መድረክ ላይ አቀረብናቸው። ሃሳቡ የዳንኤል ክፍሌና የመስፍን አስገዶም ነበር። ዳንኤል በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ምክንያት አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ከርቸሌ ከርሞ የመጣ ጋዜጠኛ ነው።
በእለቱ በናዝሬት ከተማ ይደረግ የነበረውን የመኪና ውድድር ኮካኮላ ፋብሪካ ስፖንሰር አድርጎ ስለነበር፣ እኛንም ስፖንሰር እንዲያደርገን አድርገን፤ ከአዳማ የመምሕራን ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ የሙዚቃ አስተማሪ የነበሩት መምህር ጉልቴ በመሃል ዳኝነት ውድድሩን ዳኙልን። ለመምህር ጉልቴ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ድረስ ሄጄ የትብብር ጥየቃ ደብዳቤያችንን የሰጠዋቸውም እኔ ነበርኩ። ወደ ዝግጅቱ ለመግባት አቅም ያለው እየከፈለና በነጻ እንዲታደም በደብዳቤ የጋበዝነውና አክብሮን የመጣው ብዙ በመሆኑ፤ መቀመጫ ጠፍቶ ዝግጅቱ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ለመቆም የተገደደ እድምተኛ ነበረን።
“የሆዴን አውጥቼ ልንገርሽ” የሚባለውን ምርጥ የጥላሁን ገሰሰን ዘፈን የተጫወተውና በውድድሩ አንደኛ የወጣው፤ ኤርሚያስ አስፋው ነበር። አበበ ከፈኒና ሰለሞን ዘሥላሴ ሁለተኛና ሶስተኛ ወጡ። ያን ጊዜ አበበ ባገኘው ውጤት አልተደሰተም ነበር። ይሁንና ከትንሽ ጊዜያት በኋላ አውሮፓ የሚወጣበት አጋጣሚ ተፈጠረና ለማሳተም ያዘጋጀውን ካሴት ናዝሬት ለሚገኙ ሙዚቃ ቤቶች አድሎ በዚያው ድምጹ ጠፍቶ ቀረ።
ዛሬ፤ አበበ ተቀማጭነቱን አውሮፓ አድርጎ ከአውሮፓውያን ሙዚቀኞች ጋር ልዩ ልዩ ዝግጅቶቹን ለፈረንጅም ይሁን ለአፍሪካውያን ከማሳየቱም ባሻገር ሲዲም ለገበየ ካቀረበ ሰነባበተ። “ናዝሬት አዳማዬ” የተባለ የናዝሬት ልጆችን ልብ የሰበረ ዘፈን ተጫውቷል። “ያርግልህ በሉኝ” በጥሩ ሙዚቃው የሚጠቀስ ነው። በቅርብ ጊዜ የአሊ ቢራን “ሂያዲኒ” የተሰኘ የኦሮምኛ ዘፈን ተጫውቷል፤ ዩቱብ እና የሙዚቃ ነገር ይመለከተናል ያሉ ዌብ ሳይቶችም አስተናግደውለታል። በቅርብ ቀን የሚወጣ የነጥላሁን ዘውገ የኮመዲ ቪሲዲ ላይም የራሱ የሆነ ድርሻ እንዳለው ከተለጠፈው ፖስተር ላይ እያየን ሲሆን፤ በኮመዲው ላይ ድርሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ቪሲዲው ገበያ ሲወጣ የምናውቀው ይሆናል። የዚህ ቪሲዲ አሳታሚና አከፋፋይ ዘውገ አርት ፕሮሞሽን ነው።
ኤርሚያስ አስፋውም ጥሩ ዘፈኖች የተሰባሰቡበት ሲዲ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ገደማ ለገበያ አውሏል። በተለይ “ልረሳሽ አልቻልኩ” በጣም ጥሩ ዘፈኑ ነች። ዩቱብ ላይም ትገኛለች። የግጥም ደራሲውም ዳንኤል ክፍሌ ነው። ኤርሚያስ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ባላውቅም ጥሩ የሙዚቃ ሰው በመሆኑ በዚያው የቀጠለ ይመስለኛል።
በእለቱ አንጋፋ ጋዜጠኛ የነበሩትን አቶ ያለው በለውን በክብር እንግድነት ጋብዘን ስለጋዜጠኝነት ለታዳሚው የሚሉትን ብለዋል። ድራማ፣ አስቂኝ ጭውውቶችና ግጥሞች ቀርበዋል። የፋሲል ሆቴል ባለቤት ልጅ የነበረው ወጣቱ ፋሲል ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ እጅግ ሰነባበተ። ብዙ የረዳን እሱ ነበር።
ዛሬ እንደዚህ ዓይነት ነገር ናዝሬት (አዳማ) ላይ አለ ወይ? አበበ ከፈኒ ለሥራ ጉዳይ ወደ ናዝሬት መመላለሱ አልቀረም፤ ስለዚህ ከኔ የተሻለ የሚያውቀው ይኖራል።
http://www.youtube.com/watch?v=2zu28SQFyfQ “የሆዴን አውጥቼ ልንገርሽ”
http://www.youtube.com/watch?v=aGkfV63IEdI “ናዝሬት አዳማዬ”
http://www.youtube.com/watch?v=QGH-0PmvD2k “ያርግልህ በሉኝ”
http://www.youtube.com/watch?v=t6ivqTKyLtI “ሂያዲኒ”
http://www.youtube.com/watch?v=04CGqQliWaY “ልረሳሽ አልቻልኩ”
የአሊ ቢራ 50ኛ ዓመት የሙዚቃ አገልግሎት ሊከበር ነው
(ዘ-ሐበሻ) በኦሮሚኛ ሙዚቃ ታሪክ ላይ ግዙፉን ቦታ የሚይዘው ድምጻዊው አሊ ቢራ በሙዚቃው ዓለም የቆየበት 50ኛ ዓመት በዓል እዚህ ሚኒሶታ ውስጥ ጁላይ 4 ቀን 2013 እንደሚከበር ምንጮች ለዘ-ሐበሻ ጋዜጣ አስታወቁ።
በሚኒሶታ የሚደረገውን የዘንድሮውን የኦሮሞ ስፖርት ፌስቲቫል ተከትሎ ከሚደረጉ በርከት ያሉ ዝግጅቶች መካከል አንዱ እንደሚሆን የሚነገርለት ይህ የአሊቢራ የሙዚቃ ሕይወቱ የቆበት 50ኛ ዓመት በዓል የሚከበረው በራት ግብዣ እንደሚሆን ተገልጿል። በእለቱ ድምጻዊው ሥራውን እንደሚያቀርብ የሚናገሩት ምንጮቹ በተለይም በኦሮሚኛ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ከማህበራዊ ሕይወት አንስቶ እስከ ፖለቲካ ጉዳዮች በማንሳት የተጫወታቸው ሥራዎች ይዘከራሉ ተብሏል።
አሊ ቢራ ሜይ 26 ቀን 1948 በድሬደዋ ተወለደ። ለእናቱና ለአባቱም ብቸኛ ልጅ ነው።S
ለአርቲስት አበበ መለሰ ገቢ ማሰባሰቢያ 9 ዘፋኞች በአ.አ የሙዚቃ ኮንሰርት አዘጋጁ፤ ኤፍሬም ታምሩ?
(ዘ-ሐበሻ) ለዜማና ግጥም ደራሲው አበበ መለስ መርጃ የሚውል ታላቅ የሙዚቃ ድግስ በአዲስ አበባ እንደተዘጋጀ ታወቀ። በዚህ ሰኔ 8 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይደረጋል በተባለው ኮንሰርት ላይ 9 ዘፋኞች ለአርቲስቱ መርጃ በሚውለው ኮንሰርት ላይ በነፃ ለመሥራት ቃል ሲገቡ ኤፍሬም ታምሩ ግን ተጠይቆ ፈቃደኛ ሳይሆን መቅረቱን ከአስተባባሪዎቹ አካባቢ ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
እንደ ደረሰን መረጃ ከሆነ ለአርቲስት አበበ መለሰ መረጃ፦
1ኛ. ቴዎድሮስ ካሳሆን (ቴዲ አፍሮ)
2ኛ. ግርማ ተፈራ
3ኛ. ሀመልማል አባተ
4ኛ. ፀሐዬ ዮሐንስ
5ኛ. ማዲንጎ አፈወርቅ
6ኛ. ጸጋዬ እሸቱ
7ኛ. ሃይልዬ ታደሰ
8ኛ. ዳዊት መለስ ሥራዎቻቸውን ለማቅረብ ፈቃደኛ ሲሆኑ ድምጻዊ ኤፍሬም ታምሩ ግን በኮንሰርቱ ላይ እንደማይገኝ ተናግሯል። ለኤፍሬም ታምሩ በርከት ያሉ ዜማዎችን መስጠቱን የሚያስታውሱት አስተያየት ሰጪዎች አሁን ይህ ዝነኛ ሰው የሰው እጅ ለማየት በተገደደት ወቅት ኤፍሬም ፊቱን ማዞሩ ብዙዎችን እያነጋገረ መሆኑን ከአዲስ አበባ የመጣው መረጃ ያመለክታል። በዚህ ጉዳይ ድምጻዊ ኤፍሬም ታምሩን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
አበበ መለሰ እስራኤል ሃገር ከሚገኝ አንድ ቲቪ ጋር በቅርቡ ያደረገውን ቃለ ምልልስ ይመልከቱ።
ወ/ሮ ንፁህብር ጥላሁን ገሠሠ ታማኝ ለአባቷ ስላደረገው ውለታ ስትናገር – Video
“ታማኝ ለጥላሁንዬ የዲፕሬሽን መድሃኒቱ ነበር”
ከስንታየሁ በላይ
በቨርጂኒያ አካባቢ ቴሌቭዥን በጥላሁን ገሠሠ ስም የከፈተውና ጥላሁን ገሠሠ “ካገባቸው” በጣት ከሚቆጠሩት ሚስቶች መካከል የአንዷ የወ/ሮ ሮማን በዙ ወንድም ነኝ የሚለው መስፍን በዙ ከወያኔ ፍርፋሪ አገኛለሁ በሚል ከንቱ ህልም የጀግናውን ታማኝ በየነ ስም ሲያጠፋ ቆይቷል። መስፍን በዙ በኢሜይልና በዩቲዩብ በታማኝ በየነ ላይ እያደረሰ ያለውን በሃሰት የስም ማጥፋትን እስከዛሬ ድረስ ዝም ብዬ ንቄው ትቼው ነበር። ለዚህም ምክንያቴ የዚህን ጀግና አርቲስት ከተኛበት መቀስቀስ ይሆናል በሚል ነው። ሆኖም ግን አቶ መስፍን በጥላሁን ገሠሠ ስም መነገዱን ስለቀጠለበት ከአሁን በኋላ ግን ዝም የምልበት መንገድ አይታየኝም። ለዛሬው የጥላሁን ገሠሠ ልጅ ወ/ሮ ንጹኅብር ታማኝ ለአባቷ ስላደረገው ውለታ በህዝብ ለተወደደው አርቲስት ታማኝ በየነ ክብር ተዘጋጅቶ በነበረው የራት ምሽት ላይ የተናገረችውን ቪድዮ አቀርብላችኋለሁ። በተከታታይ ደግሞ ጥላሁን ገሠሠ አንድ እግሩን ካጣ በኋላ በቨርጂኒያ ውስጥ እየኖረ በነበረበት ወቅት በር እየተዘጋበት ሥራ እየተሄደ፤ በረሃብ ስለተጎዳባቸውና ስላዘነባቸው ጊዜያት፣ ሚኒሶታ ላይ በተደረገ ኮንሰርት የስኳር በሽታ እያለበት በአንድ ቀን 7 “ሬድቡል” (ሃይል ሰጪ መጠጥ) ማን እንዳጠጣው፣ እግሩን ባጣበት ወቅት “አንተ ሰውዬ እዚህ ተወዝፈህ ሶፋው ተቀደደ እኮ..” እያሉ በሞራሉ ሲረማመዱበት ስለነበረው፣ ሌሎችንም ታሪኮችን በማስረጃ በተደገፈ መልኩ “ሆድ ይፍጀው” ስል በውስጤ ይዤው የነበረውን ምስጢሮች ሁሉ አጋልጣለሁ።
የሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ንብረት እያወዛገበ ነው
ከመታሰቢያ ካሳዬ
1ሚ. ብር አበድሬአቸዋለሁ የሚል ድርጅት ክስ ሊመሰርት ነው የአዋሣው ቤታቸው ተሸጦ ስም መዛወሩ እያነጋገረ ነው
እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ንብረት እያወዛገበ ነው፡፡ አርቲስቱ በሕይወት ሳሉ አንድ ሚሊዮን ብር አበድሬአቸዋለሁ የሚል ድርጅት ለክስ ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱን ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ሎሬት አፈወርቅ በህይወት ሳሉ የስዕል ሥራዎቻቸውን፣ ቪላ አልፋንና ሙሉ ንብረታቸውን ለመንግስት ማውረሳቸውን ተከትሎ፣ መንግስት ንብረቱን ለመረከብ እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የእኚሁን ታላቅ አርቲስት ንብረት ለማጣራትና ለመመዝገብም ከፍርድ ቤት፣ ከታዋቂ ሰዎችና ከሙያ ባልደረቦች የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ ምዝገባና ቆጠራ ቢጀመርም ፍፃሜ ሣያገኝ ተቋርጧል፡፡ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ በህይወት ሣሉ የአክሲዮን ባለ መብት ለመሆን አንድ ሚሊዮን ብር ወስደዋል በሚል የአርቲስቱን ስዕሎች ይሸጥ በነበረ አንድ የማስታወቂያ ድርጅት ክስ ሊመሰረት መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ጉዳዩ በፍርድ ቤት እልባት እንዲያገኝ ለኮልፌ ምድብ ችሎት ተመርቶ እየታየ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፤ ለጊዜው የንብረት ምዝገባና ቆጠራው መቋረጡን ገልፀዋል፡፡ በአዋሣ ከተማ የሚገኘውና በሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ስም የተመዘገበው ቤት በቀድሞ ባለቤታቸው አማካኝነት መሸጡን የጠቆሙት ምንጮች፤ የቤቱ ስም የተዛወረበት አሠራር ሕጋዊነት አነጋጋሪ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡ በሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ስም በለንደንና በስኮትላንድ ባንኮች ያለ ገንዘብ እንዲመለስ ጥረት እየተደረገ ሲሆን በተለያዩ አገራት ያሉ ስዕሎችና ንብረቶችን ለማስመለስም እየተሞከረ ነው ተብሏል፡፡ የአርቲስቱ ንብረት ካለባቸው አገራት መካከልም ንብረቱንና ገንዘባቸውን ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑና በመመለስ ሂደት ላይ የሚገኙ እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡
የሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ቪላ አልፋ፤ በኮሚቴዎቹ ሲከፈት በሺዎች የሚቆጠር ፓውንድ በካዝናቸው ውስጥ መገኘቱንና ይህም በንብረት ዝርዝር ላይ ተመዝግቦ መያዙን ምንጮች ገልፀዋል፡፡ በፍርድ ቤት ጉዳይ የተቋረጠው የሎሬት አፈወርቅ ንብረት ቆጠራና ርክክብ መዘግየት በንብረቱ ላይ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል የጠቆሙት ምንጮች፤ እጅግ ውድ ዋጋ ያላቸው ስዕሎቻቸውና የአርቲስቱ የመኖሪያ ቤትና የስዕል ስቱዲዮ የሆነው ቪላ አልፋም የመበላሸት አደጋ አንዣቦበታል ብለዋል፡፡ የሎሬት አፈወርቅ ተክሌ የቀብር ሥፍራ ምንም አይነት የማስታወሻ ሐውልት ሣይሰራበት መቅረቱን የጠቀሱት ምንጮች፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የቀብራቸው ሥፍራ ሊጠፋ ይችላል የሚል ሥጋት መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡
ምንጭ፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ የዛሬ ሰኔ 1 ቀን 2005 ዕትም
የታማኝ በየነ ሾው –በኢሳት
የድምጻዊት አበበች ደራራ መታሰቢያ ፕሮግራም በእስራኤል የኢትዮጵያ ቲቪ ቀረበ
የምህረት ደበበ መፅሃፍ – (ከተስፋዬ ገብረአብ)
“ጥቁር አንበሶች” ተብለው የሚታወቁት የአማርኛ ስነፅሁፍ አማልክት አብዛኞቹ ለዘልአለሙ አርፈዋል። ጥቂቶቹ በህይወት ቢኖሩም ከመድረክ ጠፍተዋል። ስብሃት ገብረእግዚአብሄር – በአሉ ግርማ – ፀጋዬ ገብረመድህን – መንግስቱ ለማ – ብርሃኑ ዘርይሁን – ሃዲስ አለማየሁ – አቤ ጉበኛ – ደበበ ሰይፉ – እና ሌሎችም ብዙ ብእረኞች ዛሬ ታሪክ ሆነዋል። ሲሳይ ንጉሱ – ሃይለመለኮት መዋእል – ፍቅረማርቆስ ደስታ እና ሌሎችም በርካቶች ድምፃቸው ብዙም የለም። በእውቀቱ ስዩም – ኑረዲን ኢሳ – እና ኤፍሬም ስዩም የተዳከመውን የአማርኛ ስነግጥም የቀሰቀሱ ቢሆንም፣ ከአቅማቸው በታች በመስራት ላይ መሆናቸው ያሳዝናል።
እነሆ! በቅርቡ አንድ ደራሲ ወደ መድረክ ብቅ ብሎአል – ምህረት ደበበ።
ምህረት ደበበ እንደ አንቶን ቼኾቭ በሙያው ሃኪም ነው። በአሜሪካን አገር የተማረ የአእምሮ ህክምና ስፔሺያሊስት ቢሆንም፣ ውጭ ሃገር በስደት የደረቀ መሶብ ሆኖ አልቀረም። የውስጥ ጥሪውን አዳምጦ፣ ከባህር የወጣ አሳ ላለመሆን በመጣር ላይ ስለመሆኑ በመፅሃፉ ሽፋን ላይ ተገልፆአል። ምህረት በቅርቡ ያሳተመውን “የተቆለፈበት ቁልፍ” የተባለ ልቦለድ ድርሰት አንብቤ ካበቃሁ በሁዋላ ስለመፅሃፉ አንድ ነገር ማለት እንዳለብኝ አወቅሁ። 447 ገፆችን የያዘው የምህረት ደበበ የፈጠራ ስራ ባለቤት ያጣውን የአማርኛ ስነፅሁፍ በማነቃቃት ረገድ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
ምህረት ደበበ በመፅሃፉ በራሱ መንገድ የኢትዮጵያን ቁልፍ ችግር ሊገልፅ የፈለገ ይመስለኛል። እንደ ምህረት ትረካ ችግሩ ያለው አእምሮአችን ላይ ነው። የግለሰቦች አእምሮ ካልተለወጠ በአገር ደረጃ ለውጥ ሊመጣ አይችልም። የተቆለፈበት እና ቁልፉ የጠፋበት አእምሮ ምን ሊሰራ ይችላል?
“ላሊበላን ማን ገነባው?” ብሎ ይጠይቃል ምህረት።
ኢትዮጵያውያን “እኛ ገነባነው” ብለው አያውቁም። “መላእክት ሰሩት” ይላሉ። “ላሊበላን የገነባሁት እኔ ነኝ” ብሎ ራሱን ማሳመን ያልቻለ ህዝብ ከቶውንም ለሌላ ፈጠራ ሊነሳሳ አይችልም። ምህረት እንዲህ ያሉ አመራማሪና አንቂ ጥያቄዎችን ማንሳት የቻለ ባለተሰጥኦ ብእረኛ ነው።
ምህረት ደበበ የገፀባህርያቱን ብሄር በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ እየተናገረ መዝለቁ የዘመናችን የዘር ፖሊቲካ ተፅእኖ እንዳሳደረበት ያሳያል። ዋናው ገፀባህርይ መላኩ ሃሰን የአፋርና የምንጃር ቅልቅል ነው። ፍቅረኛው ሰሎሜ ከኦሮሞ፣ ከአማራና ከትግራይ ትወለዳለች። የመላኩ ጓደኛ ማርቆስ ጉራጌ ነው። ሳራና ምንተስኖት ተጋብተው ሶስት ልጆች ወልደዋል። ሳራ ትግራይ ስትሆን፤ ምንተስኖት አማራ ነው። እነዚህ ባልና ሚስት ግን ሊግባቡ አልቻሉም። ችግራቸው ምን ይሆን? ምንተስኖት ተቃዋሚ ነው። ሳራ ገለልተኛ ብትሆንም፣ ትግሬ ስለሆነች፣ “ወያኔ ሆንሽ!” ብሎ ይጨቀጭቃታል። ሶስት ልጆች ቢወልዱም ትዳራቸው ውስጥ ፖሊቲካ ወይም ሰይጣን ገብቶባቸው ተበጣብጠዋል።
ደራሲው ተጨንቆ ይታየናል። ገፀባህርያቱን ኢትዮጵያውያን ለማድረግ መከራውን ያያል። ገፀባህርያቱ በዘር መደባለቃቸው ልጅ እያሱ ሚካኤል በጋብቻ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የሞከረበትን ስልት ያስታውሳል።
“በተቆለፈበት ቁልፍ” መፅሃፍ ላይ ተወዳጅ ካልሆኑት ገፀባህርያት አንዱ ክብሮም ይባላል። ክብሮም ኤርትራዊ መሆኑ፣ ደራሲው ወቅታዊውን ፖሊቲካ እያሰበ የገፀባርያት ድልደላ ማድረጉን ይጠቁማል። በዘመናችን የፈጠራ ስራ ድርሰት ውስጥ የገፀባህርያት የብሄር ወይም የጎሳ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መጥቶአል። ሰርቅ ዳንኤል፣ “ቆንጆዎቹ” በተባለ መፅሃፉ ለገፀባህርያቱ ሁሉ የመፅሃፍ ቅዱስ ስም በመስጠት ከዚህ ችግር ማምለጡ ትዝ ይለኛል። ጥሩ ዘዴ ነው። የዮሃንስን ወይም የራሄልን ብሄር በስማቸው ብቻ መለየት አይቻልም።
“የተቆለፈበት ቁልፍ” ከልቦለድ ድርሰትነቱ ይልቅ ወደ ፍልስፍና ያዘነብላል። ደራሲው ገፀባህርያቱን በቀጥታ መልእክቱን ለማስተላለፍ ተጠቅሞባቸዋል። ለብዙ መፅሃፍት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ አንኳር ጭብጦችን በየምእራፉ ማየት ይቻላል።
ሰዎች ለምን ድሃ ይሆናሉ? የሙስና አመለካከት፣ ጥላቻና ፍቅር፣ ቤተሰባዊ አለመግባባት፣ መርህ አልባነት፣ የአእምሮ ዝግመት፣ እና ሌሎችም እነዚህን የመሰሉ ጭብጦችን አንስቶ ምንጫቸውን ይቆፍራል። የመፅሃፉ ደራሲ ዶክተር ምህረት ደበበ የአእምሮ ህክምና ስፔሺያሊስት እንደመሆኑ፣ የአእምሮን ጓዳ እየበረበረ የሰው ልጆችን ባህርይ ለማወቅ ሙያውን ተጠቅሞበታል። እንዲህ ያሉ ሙያዊ ጉዳዮች በሃተታ መልክ ሲቀርቡ ተነባቢነታቸው ይቀንሳል። ምህረት ደበበ ልብ በሚያንጠለጥል ልቦለድ ድርሰት በኩል መልእክቱን ለማስተላለፍ በመመኮሩ በርግጥ ተሳክቶለታል።
ርግጥ ነው፣ “የተቆለፈበት ቁልፍ” ደካማ ጎኖችም አሉት።
እነዚህ ደካማ ጎኖች የመፅሃፉን ደረጃ ሊጎዱ መቻላቸው አይካድም። አንዳንድ ቦታ ገፀባህርያት በረጃጅሙ ሲናገሩ ያሰለቻሉ። የገፀባህርያቱ መልክና ጠባይ ጎልቶ አልወጣም። ተመሳሳይ ቃላት ይጠቀማሉ። ምህረት ደበበ በአፃፃፉ ቃላት ቆጣቢ አይደለም። በአምስት ቃላት ሊገለፅ የሚችለውን በ15 ቃላት ያብራራል። ፅሁፉ ፈጣን አይደለም። በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ አይገባም። ገፀባህርያቱ በመብዛታቸው አንዳንዶቹን በስማቸው ለመያዝ ያስቸግራል። እንዲህ ሲገጥመኝ ተመልሼ እያነበብኩ ለመረዳት ሞክሬያለሁ። መፅሃፉ ዲያሎግ ያንሰዋል። ሃተታ ይበዛዋል። ልቦለድ ድርሰት ዲያሎግ ማለት ነው። ገፀባህርያት በራሳቸው የአነጋገር ስልት ሲነጋገሩ መደመጥ መቻል አለባቸው። ከዚህ አንፃር ስንክሳር እና ምንተስኖት የተባሉት ገፀባህርያት የራሳቸውን ሰብእና መያዝ ችለዋል። መላኩና ሶሎሜ ግን በንግግራቸው መለየት እስኪያስቸግር ተመሳሳይ ጠባያትና የንግግር ስልት አላቸው። ርግጥ ነው፣ “የተቆለፈበት ቁልፍ” ከማሳየት ይልቅ መንገር ያበዛል። አንድን ገፀባህርይ አንባቢው ራሱ እንዲወደው ወይም እንዲጠላው እድሉን አይተውለትም። ደራሲው የወደዳቸውን እንድንወድለት፣ የጠላቸውን እንድንጠላ ይጫነናል። እንዲህ ያሉ ደካማ ጎኖች ቢኖሩትም፣ እነዚህ ህፀፆች ከመፅሃፉ ዋና ጭብጥና መልእክት በላይ ገዝፈው የመፅሃፉን ተነባቢነት የሚያሳጡ ግን አይደሉም። የደራሲው ዋና መልእክት ስለሚገዛን፣ የሚያነሳቸውን ጥልቅ አሳቦች ስለምናከብር ህፀፆቹ እንቅፋት አይሆኑብንም።
ምህረት ደበበ እምቅ አሳብ ያለው ደራሲ መሆኑ እውነት ነው። ብእሩ አብዮተኛ ነው። ብእሩ ዘረኛ እና አድርባይ አይደለም። ለውጥ ጠያቂ ነው ብእሩ። ከሶስት በላይ መፅሃፍ ሊወጣቸው የሚችሉ አሳቦችና ጭብጦችን በአንድ መፅሃፍ ዘርግፎልናል።
ከምስጋና ጋር እንደሚደግመን ተስፋ አደርጋለሁ።
በ “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” የሚወዳደረው በአምላክ ለአገሩ ያለውን ፍቅር እየገለፀ ነው ተባለ
ከግሩም ሠይፉ
ዘንድሮ የ “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” አብሮ የመኖር ውድድር፣ በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት ወሲብ በመፈፀም አነጋጋሪ ሆና የሰነበተችው ኢትዮጵያዊቷ ቤቲ ከውድድሩ ተሰናበተች፡፡ ውድድሩ ከተጀመረ አራተኛ ሳምንቱን የያዘ ሲሆን እስካሁን ቤቲን ጨምሮ ስድስት ተባርረው 20 ተፎካካሪዎች ቀርተዋል፡፡ ከእነሱም መካከል ሌላው ኢትዮጵያዊ በአምላክ ተስፋዬ (ቢምፕ) ይገኝበታል፡፡ ቢምፕ ለውድድሩ የሄደው አገሩን ስለሚወድና በተገኘው አጋጣሚ ስለ ኢትዮጵያዊነቱ ለመግለፅ ነው ያሉት እናቱ ወይዘሮ ደብሪቱ ሰለሞን፤ ባለፈው አንድ ወር በነበረው ቆይታ ይህንኑ ፍላጎቱን ሲያንፀባርቅ መቆየቱን ተከታትያለሁ ብለዋል፡፡ ‹‹ልጄ የአገር ፍቅር ስላለው በቢግ ብራዘር አፍሪካ ውድድር ፍቅሩን ለመግለፅ እድል አግኝቷል፡፡ ባንዲራው አብሮት ነው፡፡ ሁልጊዜም በሚለብሰው ካኒተራ ወይ ኮፍያ አሊያም በእጁ ላይ የአገሩ ባንዲራን ትቶ አያውቅም፡፡
የሚኖርበት መኝታ ቤቱ እንኳን በባንዲራ ያጌጠ ነው›› በማለት እናቱ ወይዘሮ ደብሪቱ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ልጃቸው በአኗኗሩ እያሳየ ያለው ባህርይ ከልጅነቱ ጀምሮ ያደገበት ስብእናው እንደሆነ የገለፁት እናቱ፤ ባለፉት አራት የውድድር ሳምንታት እንዲባረር አንድ ድምፅ ብቻ እንደተሰጠበት ገልፀው፤ የውድድሩን ውጣውረድ በመቋቋም ሳይሰላችና ለሌሎች ተወዳዳሪዎች እንክብካቤ ሳይነፍግ እስከመጨረሻው ምእራፍ ሊዘልቅና ሊያሸንፍ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ በ “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” ውድድር የኢትዮጵያውያን መሳተፍ ጠቀሜታ አለው የሚሉት ወይዘሮ ደብሪቱ፤ ውድድሩ የአገርን ባህል ለማስተዋወቅ እና ገፅታ ለመገንባት ሁነኛ መድረክ መሆኑን አስረድተው፤ ልጃቸው አብረውት ከሚኖሩት ተወዳዳሪዎች ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ጥያቄዎች እንደሚቀርቡለት እሱም ስለ ባህሏ ፤ስለ ታሪኳ፤ የሰው ዘር መገኛ ስለመሆኗ፣ ስለ ቡና፤ ስለእንጀራውና ስለሽሮው ሳይሰለች ሲያስረዳ ተመልክተነዋል ብለዋል፡፡ ከውድድሩ በወጣች ማግስት አስተያየት የሰጠችው ቤቲ ስላሳለፈችው ጊዜ ስትናገር ቤቱን ለቅቆ መውጣት ከባድ ነው፡፡
ቦልት እና እኔ ጥሩ ወዳጆች ነበርን፡፡ ከውድድሩም በኋላ በወዳጅነት እንደምንቀጥል እርግጠኛ ነኝ” ብላለች፡፡ በውድድሩ ላይ እስከ መጨረሻው እዘልቃለሁ ብዬ አስብ ነበር ያለችው ቤቲ በውድድሩ፤ ምርጥ ተሳትፎ እንደነበራት፤ በዚህም መኩራቷን እንደተናገረች “ስዌታን” የተባለው የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ ቤቲ “ዘ ቼዝ” የሚል ልዩ ስም በተሰጠው የዘንድሮ “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” አብሮ የመኖር ውድድር ገና በመጀመርያው ሳምንት ቦልት ከተባለው ሴራሊዮናዊ ተወዳዳሪ ጋር በፈፀመችው ወሲብ ትኩረት ስባ ስታወዛግብ ቆይታለች፡፡ በ “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” የስምንት አመት ታሪክ በቀጥታ ስርጭት የታየ ወሲብ ሲፈፀም የቤቲ እና የቦልት የመጀመርያው ነበር፡፡ ቤቲ ለአገሯ ባህልና ወግ ክብር አልሰጠችም በሚል በማህራዊ ድረገፆች እና በብሎግ መድረኮች ላይ ስትብጠለጠል መሰንበቷም ይታወቃል፡፡ ቤቲ በ “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” ኢትዮጵያን አትወክልም በሚል ለተቃውሞ በተከፈተ የፌስ ቡክ ድረገፅ ላይም በአገር ውስጥ እና በዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ትችት ተሰንዝሮባታል፡፡
የቤቲ ከውድድሩ ድንገት መባረር ፍቅረኛዋ ሆኖ ለሰነበተው ሴራሊዮናዊ ቦልት መርዶ እንደሆነበት ዘገባዎች ጠቁመዋል፡፡ ስንብቷን ባረጋገጠችበት ምሽት ሁለቱም በሃዘኔታ ተውጠው ሲተቃቀፉ እና ሲሳሳሙ መታየታቸውንም እነዚሁ ዘገባዎች አውስተዋል፡፡ ቦልት ምስጢረኛው፤ የልብ ወዳጁ እና ፍቅረኛውን ቤቲ በማጣቱ ብቸኝነት እንደሚያስቸግረውና እሱም ቢሆን በውድድሩ የማሸነፍ እድሉ የጠበበ እንደሆነ “ዘ ስታንዳርድ ዲጂታል ኒውስ” ጽፏል፡፡ ለሴራሊዮናዊው ቦልት ከዚህ በኋላ የሚኖረው የ “ቢግ ብራዘር አፍሪካ” ቆይታ ማራኪ እንደማይሆን እየተነገረ ሲሆን ፋቲማ ከተባለች ማሊያዊት ጋር የጀመረው ግንኙነት መፅናኛው ሊሆን እንደሚችልም ከወዲሁ ተተንብይዋል፡
(ምንጭ፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ የዛሬ ቅዳሜ ጁን 29 ዘገባ)
የድምጻዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ አዲስ አልበም እየተጠበቀ ነው
ድምፃዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ “ስጦታሽ’’ የተሰኘውን አዲሱን እና ሁለተኛውን አልበም ሊያወጣ ነው፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውን የሙዚቃ ባለሞያዎች የተሳተፉበትና ዐሥራ አምስት ዘፈኖችን የያዘው “ስጦታሽ’’ የተሰኘው አዲስ የሙዚቃ አልበም በቅርብ ቀን ወደ ሕዝብ ጆሮ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአልበሙ ውስጥ የተካተቱን ሰባት ዘፈኖች ያቀናበረው ታዋቂው የሙዚቃ ባለሞያ አበጋዙ ክብረወርቅ ሺወታ ሲኾን የአልበሙን ሙሉ ሚክሲንግ እና ማስተሪንግ የሠራውም እርሱ ነው፡፡ ወጣቱ የሙዚቃ አቀናባሪ ካሙዙ ካሳ ከአዲሱ የሸዋንዳኝ አልበም ውስጥ አምስት ዘፈኖችን አቀናብሯል፡፡ግሩም መዝሙር ሁለት ዘፈኖችን ሲያቀናብር ሚካኤል ኃይሉ አንድ ዘፈን በማቀናበር ተሳትፏል፡፡
ሸዋንዳኝን ጨምሮ ሞገስ ተካ፣ቴዎድሮስ ካሳሁን፣አማኑኤል ይልማ፣ጌቱ ኦማሂሬ፣አለማየሁ ደመቀ፣ጌትሽ ማሞና ብስራት ጋረደው በአጠቃላይ ስምንት አንጋፋ እና ወጣት የዜማ ደራሲያን በዚህ አልበም ላይ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡በግጥምም ይልማ ገ/አብ፣ቴዎድሮስ ካሳሁን ፣መሰለ ጌታሁን፣ጌትሽ ማሞ እና ታደሰ ገለታ ተሳትፈውበታል፡፡
የሙዚቃ አልበሙን በአገር ውስጥ አሳትሞ የሚያከፋፍለው በሙዚቃ ኢንደስትሪው የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው ‹‹ኤሌክትራ›› ሙዚቃ ቤት ሲኾን ከኢትዮጵያ ውጭ ደግሞ ‹‹ናሆም ሪከርድስ›› መኾኑ ታውቋል፡፡
ሸዋንዳኝን በጨረፍታ
አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው ድምጻዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ የአንደኛ ደረጃ ትምሕርቱን በ‹‹ምስካየኅዙናን››፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን ደግሞ በሴንጆሴፍ ካጠናቀቀ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመግባት ለሦስት ዓመታት የማኔጅመንት ትምሕርቱን ተከታትሏል፡፡ለማጠናቀቅ የአንድ ዓመት ጊዜ ሲቀረውም በልጅነት ዕድሜው ለጓጓለት ሙዚቃ በማድላቱ በሙዚቃ ፍቅር ተሸንፎ ትምሕርቱን አቋርጦ ወጥቷል፡፡
ሸዋንዳኝ ኃይሉ የልጅነት ዕድሜውን ባሳለፈበትና የትውልድ መንደሩ በኾነው፤ በአሁኑ ወቅት በተለምዶ ‹‹መስቀል ፍላወር›› እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በጊዜው አብረውት ላደጉ የዕድሜ አቻዎቹና ለትምህርት ቤት ጓደኞቹ የተያዘለትን ወይም ያጠናውን ዘፈን በማንጎራጎር ነበር መዝፈን የጀመረው፡፡በሴንጆሴፍ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን መከታተል ሲጀምርም የመዝፈን ፍላጎቱ በመጨመሩ ችሎታውን አሻሽሎ በትምሕርት ቤቱ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ በድምፃዊነት መሳተፍ ጀመረ፡፡
በወቅቱ የነበረው የትምህርት ቤቱ አስተዳደር በተለየ መልኩ ለሙዚቃ ጥበብ ከፍ ያለ ግምት የሰጠ ነበር፡፡ ለሙዚቃ ዝንባሌ ያላቸው ተማሪዎች እንዲበረታቱ በማሰብ የሙዚቃ ቡድኑን በሙሉ በዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያ አደራጅቶት ነበር፡፡ በቂ የሙዚቃ ዕውቀት ያለው መምሕር በመቅጠርም ተማሪዎች ለኾኑት የቡድኑ አባላት ከፍተኛ እገዛ አድርጎላቸዋል፡፡ ሸዋንዳኝ በትምሕርት ቤቱ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ እያለም የተለያዩ የእንግሊዘኛ ዘፈኖችን በመጫወት ቢታወቅም ለአርቲስት ጌታቸው ካሳ ዘፈኖች ልዩ ፍቅር ነበረው፡፡ በአጠቃላይ ሸዋንዳኝ በሴንጆሴፍ ዘመናዊ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ የነበረው ቆይታ ከሁለት ዓመታት ዕድሜ የዘለለ ባይኾንም የትምሕርት ቤቱ እገዛና ድጋፍ ለዛሬው ሞያዊ ሕይወቱ የራሱ የኾነ ቦታና ዋጋ እንዳለው የድምፃዊው የሙዚቃ ዕውቀት፣ ክህሎት እና ጥንካሬው ማረጋገጫ ነው፡፡
ሸዋንዳኝ ዐሥራ ሁለተኛ ክፍልን ተሻግሮ ወደ ዩኒቨርስቲ በዘለቀ ጊዜም ከሙዚቃ ጋር አልተቆራረጠም፡፡ ይልቅስ ከኢትዮ ስታር ባንድ ጋር በመኾን በሳምንት ለሁለት ቀናት እየሠራ ለጥቂት ጊዜያት ያህል ቆየ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሞያዊ ክህሎቱ እያደገ እና የምሉዕ ድምፃዊነቱ ቦታ እንደተረጋገጠ ዕውቅናው እየጨመረ፡፡ ይህኔ የተለያዩ ባንዶችን በመቀላቀል ተወዳጅነት ያተረፈለትን ሥራ ማቅረብ ጀመረ፡፡ ‹‹መዲና›› ፣ በአንጋፋው ድምጻዊ መሐሙድ አሕመድ ተመስርቶ የነበረው ‹‹ስሪ ኤም››፣ ‹‹ሩትስ ኤንድ ካልቸር››፣ ‹‹አዲስ››፣ ‹‹ሴቫንስ›› እና ‹‹ኤክስፕረስ›› የተሰኙት የሙዚቃ ባንዶች ሸዋንዳኝ በተለያዩ ጊዜያት ከእውቅ ድምጻውያን ጎን የሠራባቸው ናቸው፡፡ ድምጻዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ ‹‹በሴቫንስ እና ኤክስፕረስ›› የሙዚቃ ባንድ ውስጥ በነበረው ቆይታ ከእነ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ)፣ ትዕግስት በላቸው፣ አብዱ ኪያር፣ ሽመልስ አራርሶ፣ ጸደንያ ገብረማርቆስ እና ሌሎችም አርቲስቶች ጋር ሠርቷል፡፡
‹‹ጽጌረዳ›› የተሰኘው የግርማ በየነ ዘፈን የሸዋንዳኝ የመጀመሪያ ነጠላ ዜማ ሥራው ሲኾን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ስቱዲዮ የቪዲዮ ክሊፕም ሠርቶለት ነበር፡፡ አስከትሎም ‹‹ ስቅ አለኝ›› የተሰኘውን የመጀመሪያውን ተወዳጁን አልበም ለሕዝብ ጆሮ በማድረስ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡ ሸዋንዳኝ እ..ኤ.አ በ2004 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተካሄደው ‹‹ኮራ›› ሙዚቃ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ከጸደንያ ገብረማርቆስና ኃዴ ኃይሌ ጋር በመኾንም በዕጩነት ለውድድር ቀርቦ ጥሩ ደረጃን አግኝቷል፡፡
ድምፃዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ ‹‹አፍሮ ሳውንድ›› የሙዚቃ ባንድን ከመሠረቱት ሦስት ባለሞያዎች አንዱ ነው፡፡ ከአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) እና ከሙዚቃ ባለሞያው ግሩም መዝሙር ጋር በመኾን በጋራ ያቋቋሙትን ይህን ባንድ ለዘጠኝ ተከታታይ ዓመታት በፍቅር በመምራት እና ተናበው በመሥራት ውጤታማ ኾነውበታል፡፡ ‹‹ዛየን›› ሸዋንዳኝ ከሦስት ዓመት በላይ በፍቅር የሠራበት ሌላው ባንድ ነው፡፡
ድምፃዊ ሸዋንዳኝ በተለያየ ጊዜያት ከተጠቀሱት ባንዶች ጋር በመኾን፤ በቡፌ ደላጋር፣ በኢሉዥን፣ በሂልተን፣ በሸራተን ጋዝላይት፣ በኮፊ ሃውስና በሃርለም ጃዝ መድረኮች ላይ የሙዚቃ ሥራን በማቅረብ ወዳጅና አድናቂዎችን አፍርቷል፡፡ የመጀመሪያ አልበሙን ካወጣ በኋላም ከድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ጋር በአንድ ላይ በመኾን በቦሌ መንገድ ላይ ይገኝ የነበረውንና በወቅቱ በርካታ እንግዶችና ታዳሚዎችን በማስተናገድ በከተማው ተጠቃሽ የምሽት ክለብ የነበረውን ‹‹ላየን ክለብ›› በመከራየት ለስድስት ወራት ያህል በትጋት ሠርተውበታል፡፡ ሸዋንዳኝ ይህንኑ የምሽት ክለብ ሥራ ገፍቶበት ከሌሎች ሁለት ጓደኞቹ ጋራ በመኾን በቦሌ መድኃኒያለም የሚገኘውን ታዋቂው ‹‹ፋራናይት›› የምሽት ክለብን በመክፈት በዋና ሥራ አስኪያጅነት መምራት ከጀመረ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ሸዋንዳኝ ከሰው ጋር ተግባብቶ እና ተከባብሮ መሥራት የሚያስችለው መልካም ባህሪ እና ብቃት ያለው አመራር መስጠት የሚችል በመኾኑ ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከባለድርሻዎቹ ጋር በፍቅር ተስማምቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም አገር ውስጥ ባለበት ጊዜ ኹሉ ዘወትር ሐሙስ እና ቅዳሜ ቀደም ሲል ከዛየን ባንድ ጋር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከመሐሪ ብራዘርስ ጋር በመኾን እንግዶቹን በሙዚቃ ያዝናናል፡፡ከተለያዩ ባንዶች ጋር በመኾን ያለማቋረጥ የመድረክ ሥራን መሥራት በመቻሉ ችሎታውን ዕለት ከዕለት እንዲያዳብር እና በየትኛውም ቦታ ብቁ የኾነ ድምፃዊ መኾን አስችሎታል፡፡ በዚህ ብቃቱም በመላው ኢትዮጵያ በተዘጋጁ በርካት የሙዚቃ ዝግጅቶች፣ ለማኅበራዊ አገልግሎት በዋሉና በዕርዳታና መሰል የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍ ሥራዎቹን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡
ድምጻዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ የመጀመሪያውን አልበም ከማውጣቱ ቀደም ብሎ በነበረው ዕውቅና እና ተወዳጅነት ከአገር ውስጥ የመድረክ ሥራዎች በተጨማሪ ወደ ጣልያን፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ እና ዱባይ ተጉዞም የተለያዩ መድረኮች ላይ በመሥራት ችሎታውን አስመስክሯል፡፡ የመጀመሪያውን አልበም ካወጣ በኋላም ከኢትዮጵያ ውጪ፤ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ባህሬን፣ ዱባይ፣ አቡዳቢ፣ እስራኤል፣ ስዊድን፣ እንግሊዝ፣ ኖርዌይ፣ ሆላንድ፣ በአሜሪካ ከዐሥራ ሁለት ግዛቶች በላይ እና ሌሎች አገሮች በተደጋጋሚ ለኮንሰርት እየተጋበዘ ሥራዎቹን አቅርቧል፡፡ የሸዋንዳኝ የመጀመሪያ አልበም ከወጣ ጊዜ ጀምሮ ተወዳጅነቱ ለስምንት ዓመታት የዘለቀ በመኾኑ ለኮንሰርት ሥራ ወደተለያዩ አገራት መጋበዙ እስከአሁንም አልተቋረጠም፡፡
ሸዋንዳኝ ኃይሉ ምንም እንኳን አብዛኛው ሙዚቃዊ ሕይወቱ በውጭ ሀገር የሙዚቃ ስልቶች እና የአዘፋፋን ስታይሎች የተቃኘ ቢሆንም ተወዳጅ አገርኛ ቃና ያለው ድምጻዊ ነው፡፡ በአገራችን የሙዚቃ ኢንደስትሪ ውስጥ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ እየተደመጠና ተወዳጅነትንም እያገኘ ያለውን ዘመናዊ የአዘፋፈን ስታየልን በመፍጠር ረገድ ተጠቃሽ ከኾኑት አርቲስቶች መካከል ድምጻዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ አንዱ ነው፡
ድምጻዊያን አምና በዳላስ ዘንድሮ በሜሪላንድ
ጥበቡ ተቀኘ
ባለፈው አመት የአሜሪካን እትዮጵያዊያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሁለት በተከፈለበት ጊዜ ብዙ አርቲስቶቻችን ጥሩ ጥሩ ዳጎስ ያለ ብር በአላሙዲን ተከፍሏቸው ዲሲ ሲመጡ ያዩትን ውርደትና ቅሌት እነሱም ብሩን የሚያፈስላቸውም የማፍያ ግሩፕ የሚረሱት አይመስለኝም:: በተቃራኒው ደግሞ ዳላስ የነበረውን ዋናውን ፌዴሬሽን ለማገዝ ጥበብን ከህዝብ ጋር ካልሆነ በምንም አይነት ለብር አንገዛም በማለት የፈጣሪ ስጦታቸውን ተጠቅመው ህዝቡን ያዝናኑት እና ከጎኑ የቆሙት ያዩትን ደስታ እና አለም ታሪክ ሁልጊዜ በመልካም ሲያነሳው ይኖራል::
የጥበብ ባለሙያዎች ከህዝብ ውጭ ሌላ ምንም ሃብት እንደሌላቸው የታወቀ ነው:: ሲዲያቸውን የሚገዛው ኮንሰርታቸውን የሚታደመው በጭብጨባ የሚያበረታታቸው ህዝብ ብቻ ነው:: አላሙዲን የሚባለው ክፉ ጦስ ኪሳቸውን በጉርሻ ሲያሳብጠው ህዝብ ምን ያደርጋል? ብለው ለሃብታሞች ብቻ ለመዝፈን መወሰናቸው በጣም የሚያሳፍርና የሚያኮላሽ ተግባር ነው:: ዛሬ እንዲህ አይነት ተራ አስተሳሰብ ይዘው የሚጓዙትን እድሜ ይስጠንና እናያቸዋለን ነገ ስራዬን አድምጡልኝ ማለታቸው አይቀርምና::
ባለፈው አመት ዳላስ ከህዝባቸው ጎን በመቆም መከፋፈልን ሳይሆን አንድነትን ሲዘምሩና ሲዘፍኑ ከነበሩት ስመ ጥር ድምጻዊያን መካከል ማህሙድ አህመድ ጸሃይ ዮሃንስ አብዱ ኪያር እና ጎሳዬ ተስፋዬ ይጠቀሳሉ:: እነዚህ ታላላቅና ዝነኛ የኪነ ጥበብ ሰዎች የሚከፈላቸው ተራ የአላሙዲን ጉርሻ ሳያዝጎመዣቸው ህዝቡን ሲያዝናኑና አደራቸውን ሲወጡ ምን ያህል ክብርና ፍቅርን እንደሚያካብቱ ማሰብ የሚከብድ አይመስለኝም:: አንዳንዶቹ ድምጻዊያን ደግሞ ከሁለቱም ኳስ አንወግንም ብለው እንዳልሰሩ የማይካድ ሃቅ ነው ዛሬ ግን ድል ከህዝቡ ጋር እንደሆነ አውቀው ተቀላቅለውናል እናከብራቸዋለን:: ለክፉ ጊዜ ባይሆኑም ከመሰሪው አላሙዲን ጋር ባለመሆናቸው አስደስቶናል::
ዘንድሮ ያለፈውን ውርደት ለመድገም ወደ ዲሲ የመጡት ድምጻዊያኖችም ዲሲ አካባቢ በነጻነት የሚዟዟሩ አይመስለኝም ምክንያቱም ግልምጫውንና ስድቡን የሚችል አቅም ያላቸው ስለማይመስለኝ ነው:: ለነገሩ እንኳን እነሱ ዋና አዘጋጆቹም ቢሆን የአበሻውን ተቃውሞ እንደ ጦር እየፈሩ እንደሚጓዙ በአይናችን እያየነው ነው:: እንደውም እዚ ጋር አንድ ወዳጄ ያጫወተኝ ትዝ አለኝ:: ባለፈው መለስ ዜናዊ እዚህ አሜሪካ በአበበ ገላው ድምጽ እንደደነገጠ በዛው ሞቷል አሁን ደግሞ አላሙዲን ይሰደብና ደንግጦ አገር ቤት ሲመለስ ይሞታል ተብሎ እነደሚቀለድ ነግሮኛል:: ይህ መቼም የሚያሳየው ሰዎቹ ምን ያህል ህዝብን አንቀጥቅጠው እንደሚገዙ ነው አንድ ሰው እነሱን ክፉ መናገር አይፈቀድለትም:: ወይኔ ያገሬ ሰው!!
የኔ እምነት ማንም ሰው የፈለገውን የመደገፍና የመቃወም መብት እንዲሰጠው ነው ግን 30 አመት ያደረገን አንድ የኢትዮጵያውያን መገናኝ ኳሳችንን ለመበተን ለመከፋፈል እና ለወያኔ አላማ ለማዋል የሚደረገውን ጥረት እቃወማለሁ:: የሚደግፉትም አምነውበት ከሆነ ግድ የለኝም ውጤቱ እንዲህ 30 ሺ ለ ዜሮ መሆኑን ሲያውቁት ስህተት መሆኑን ሊረዱት ይገባል ባይ ነኝ::
የመደገፍና የመቃወም መብቴንም እያየሁት ያለሁት እዚህ አሜሪካ ነው እንጂ አገር ቤትማ ያለው ኢትዮጵያዊ በሙሉ ይህን እድል አላገኘውም የኢህአዴግ ደጋፊ ወይም አባል ካልሆነ አይማርም ቢማርም አይመረቅም ቢመረቅም ስራ አያገኝም ቢያገኝም አያድግም…. ኢህአዴግን መቃወም ሙሉ በሙሉ ወንጀል በመሰለበት በዚህ ጊዜ የአገር ውስጡ አልበቃ ብሏቸው ውጭ አገር ያውም አሜሪካ መጥተው ያልንህን ታደርጋለህ በሚል ማን አለብኝነት ሊበትኑን እና አፋችንን ሊያዘጉ ሲፈልጉ በጣም ይገርመኛል:: ታዲያ እነዚህን በመናቅና በብዙ ሚሊዮን ዶላር ያዘጋጁትን ድግስ ባለመሄድ ኢትዮጵያዊው ሁሉ ሲቀጣቸው ማየትና የታሪክ ምስክር መሆን እንዴት ደስ ይላል?
የተቆጣን እና በአላሙዲን የክፋት ተግባር የተናደድን ህዝቦች በመተባበር የምናደርገው ነገር ሁሉ ስሜት የሚነካ ነው ባለፈው አመት ዳላስ ላይ ስታዲየሙ በህዝብ ሞልቶ ሆ ሲል በአይኔ አይቻለው አሁን ደግሞ ሜሪላንድ የመክፈቻውን ስነስርአት የነበረው ዝናብና የተፈራው ስቶርም ሳይበግረው ይሄ ሁሉ ህዝብ ባንዲራውን ለብሶና ይዞ ሲከታተለው አይቻለው:: በጣም የሚይስደንቅና በቃላት ሊገለጽ የማይችል ከባድ የአገር ፍቅር ስሜትም ተሰምቶኛል::
መቼም ፈጣሪ ለኪነጥበብ ሰዎች የሰጣቸው የተፈጥሮ ስጦታ ይገርመኛል:: ያንን ሁሉ ሺ ህዝብ እያስደሰቱ መኖር ምን ያህል መታደልን እንደሚጠይቅ መቼም ለሁሉም ግልጽ ነው:: ባለፈው አመት ዳላስ ላይ ገጣሚ የዜማ ደራሲ እና ድምጻዊው አብዱ ኪያር እየዘፈነ የተሰማኝን ስሜት በምንም መልኩ ልገልጸው አልችልም:: መላ አካላቴን ውርር አድርጎኝ እንባ እንባ ይለኝም ነበር:: ህዝቡ በሙሉ ከዘፈኑ ጋር ያሳየው የነበረው እንቅስቃሴ ሁሉ አይኔ ላይ አለ::
ያልገቡበት የለም ያልገቡበት የለም
ሙቀትና ብርዱን ችለው በዚች አለም
ይቺ ቀን ታልፋለች እያሉ በማለም
ስትጣሪ ያልመጡት ጠልተውሽ አይደለም
እናቱን ሚጠላ ካንቺ አልተፈጠረም
የከዳማ እናቱን
እንጃ አበሻነቱን…..
ዘንድሮ ደግሞ በሜሪላንድ የመክፈቻው ስነ ስርአት ላይ እነዛን በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አርንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ያላቸው አፉፋዎች የባህል ቡድኑ ወደ ሰማይ ሲለቋቸው ሳይ ይኸው ከባድ የአገር ፍቅር ስሜት መልሶ ነፍሴን ሲተናነቃት ይታወቀኝ ነበር:: ስሜቴን ደግሞ ይባስ ያወጣው የድምጻዊው ብርሃኑ ተዘራ(ያምቡሌ) የዘፈን ግጥም ነበር
ይሄ ሰው አማራ እረ ሚለው ማነው
ይሄ ሰው ኦሮሞ እረ ሚለው ማነው
ይሄ ሰው ከትግራይ እረ ሚለው ማነው
ይሄ ሰው ከደቡብ እረ ሚለው ማነው
ቢለያይም ቋንቛው ደማችን አንድ ነው
በናቴም አንድ ነኝ ባባቴም አንድ ነኝ
ከኢትዮጵያ አገሬ የለም የሚለየኝ….
የጥበብ ሰዎች ይህን ሁሉ የአምላክ ስጦታ ይዘው ከህዝባቸው ጎን ካልቆሙ በጣም የመሸማቀቅና የውርደት እድሜ እንደሚገፉ በታሪክ ያየነው ነው:: አላሙዲንም ወያኔም ያልፋሉ ያኔ ከህዝብ ፊት እንዴት ልትቆሙ ነው ምንስ ልትሉ ነው ማለት ይኖርብኛል ብዬ አምኛለሁ::
ይሄንን ጽሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት ኳስና ዘፈን እንዲህ የህዝቡን ልብ ማማለል ከቻሉ ፖለቲከኞቻችንም ይህንን ጥበብ ሊካኑት ይገባል ባይ ነኝ:: መልካም የፍቅር እና የደስታ ኳስ ያርግላችሁ::
ጥበቡ ተቀኘ
July 01 2013
ኢትዮ-እስራኤላዊቷ ድምጻዊት በሙዚቃው ኢንዱስትሪ መድመቅ ጀምራለች
ከግሩም ሰይፉ
በቅርቡ “ላይፍ ሃፕንስ” የተባለ አዲስ አልበም በእስራኤል ለገበያ ያበቃችው ቤተእስራኤላዊቷ ድምፃዊት ኤስተር ራዳ፤ በእስራኤል የሙዚቃ ኢንዱስትሪ መድመቅ ጀምራለች ተባለ፡፡ የኤስተር ራዳ አዲስ አልበም አርቲስቷ ኢትዮጵያዊ የዘር ግንዷን ሙሉ ለሙሉ የገለፀችበት ነው ያለው “ኒውስፖይንት አፍሪካ” ፤ “ላይፍ ሃፕንስ” በተባለው ዘፈኗ ዋሽንትና ማሲንቆን እንደተጠቀመች ጠቅሷል፡፡
የ28 አመቷ ድምፃዊት፤ የዘፈን ግጥም ደራሲ እና ተዋናይቷ በአዲሱ አልበሟ ውስጥ “ላይፍ ሃፕንስ” የተሰኘውን የአልበሙን መጠርያ ጨምሮ “ሞንስተርስ”፤ “ኤኒቲንግ ፎር ዩ” እና “ኩድ ኢትቢ” የተባሉ ዘፈኖችን አካትታለች፡፡ በኢትዮ ጃዝ እና በሶል የሙዚቃ ስልቶች የተሰሩት የድምፃዊቷ ዘፈኖች በእስራኤላውያኖቹ እውቅ የሙዚቃ ባለሙያዎች ኩቲ እና ሳቦ የተቀናበሩ እንደሆኑ
ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኤስተር ቤተሰቦች እ.ኤ.አ በ1983 ዓ.ም በተከሰተው ረሃብ ሳቢያ ኢትዮጵያን ለቅቀው ወደ እስራኤል የተሰደዱ ሲሆኑ ኤስተር የተወለደችው ቤተሰቦቿ እስራኤል ገብተው ኪራያት ኡባ በተባለ
ስፍራ መኖር ከጀመሩ ከአንድ አመት በኋላ ነው፡፡ ኤስተር እና ቤተሰቧ 10ኛ ዓመቷን እስክትይዝ ድረስ በሄብሮን ዳርቻ የኖሩ ሲሆን እድሜዋ ለእስራኤል የውትድርና አገልግሎት ሲደርስ ወደ ውትድርናው ገብታ እግረመንገዷን እዚያው በነበረ የሚሊታሪ ባንድ ድምፃዊ በመሆን ሰርታለች፡፡ ቤተእስራዔላዊ ብትሆንም በፀጉረ-ልውጥነቷ ብዙ አሳዛኝ ገጠመኞችን በወጣትነቷ ያሳለፈችው ኤስተር፤የሚሰማትን የመገለል ስሜት በሙዚቃዋ ስትከላከልና ስትዋጋ እንደኖረች አልደበቀችም፡፡
የውትድርና አገልግሎቷን ከጨረሰች በኋላ ኑሯዋን በቴል አቪቭ በማድረግም ወደ ትወና ሙያ እንደገባች ትናገራለች፡፡ በተዋናይነቷ የቴሌቭዥን ፊልሞች የሰራችው ኤስተር፤ ከአራት በላይ የሙሉ
ጊዜ ፊልሞች ላይ መተወኗንና “ስቲል ዎኪንግ” እና “ዘ ሩቫቤል” የተባሉት ሁለት ፊልሞች በእስራኤል ፊልም አፍቃሪያን ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፉ መሆናቸውን ገልፃለች፡፡
(ምንጭ አዲስ አድማስ ጋዜጣ)
የብርሃን ልክፍትን በጨረፍታ (ደረጀ ሀ.)
የመጽሐፉ ርዕስ፦ የብርሃን ልክፍት(ስብስብ ግጥሞች)
ደራሲ፦ ዮሐንስ ሞላ
የሽፋን ምስል ዳዊት አናጋው
ገጽ፦108
የተካተቱት ግጥሞች፦72
ዋጋ፦ 28 ብር (18 ዶላር)
ብዙ ጸሀፍያን (ገጣምያን) የራሳቸው የአፃጻፍ ዘይቤ እንዳላቸው ሁሉ ፤ ዮሐንስ ሞላም የራሱን ዘይቤና ስልት ይዞ በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ መድረክ ብቅ ያለ ወጣት ገጣሚ ነው። ከሚያነሳቸው ጭብጦች፣ በአጭር ግጥሞች ጥልቅ መልዕክቶችን ከመግለጹ እና ዘለግ ባሉ ስንኞች ቃላትን እያነሳና እየጣለ ከማጫዎቱ አንፃር ከየትኞቹ የአገራችን ገጣሚያን ጋር እንደማመሳስለው አላውቅም። በስወድሽ ግጥሞቹ ገብረክርስቶስን የሚያስታውሰኝ ዮሐንስ ሌላ ቦታ ሌላ መሰሎ ይከሰትብኛል። ስለዚህ የማን ተጽዕኖ እንዳለበት ወይም የማንን ፈለግ እንደሚከተል ራሱ ዮሐንስ ቢነግረን ይመረጣል።በኔ በኩል ግን ዮሐንስ እየገጠመ ያለው፤ እንደ ዮሐንስ ነው ብዬ ማለፉን እመ ጣለሁ-አንደ ዮሐንስ አድማሱ ሳይሆን እንደ ዮሐንስ ሞላ።
ብዙውን ጊዜ ሥነ- ግጥም በአንባቢያን ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው በውስጡ የጠራ ሀሳብ ሲይዝ እና ያም ሀሳብ ስርዓቱንና ምቱን(rhythm) ጠብቆ በተገቢው ቃላት ሲገለጽ ነው። ከዚህ አንፃር አንዳንዶች የጥሩ ሀሳብ ባለቤቶች ሆነው ያን ሃሳባቸውን የሚያዋቅሩበት ቃላት ሲቸገሩ፤ ሌሎች ደግሞ የቃላት ሀብታሞች ሆነውና የስንኝ አጣጣሉን አግኝተውት ሳለ፤ በሀሳብ ድርቀት ይሰቃያሉ።በዚህም ምክንያት ይመስላል አልፎ አልፎ ሀሳብ የሌላቸው ወይም መልዕክታቸው ያልጠራ ግጥሞች – ቤት ስለደፉ ብቻ ግጥም እየተባሉ ወደ መድረክ ሲወጡ የምናየው።
የዮሐንስ ግጥሞች በሀሳብም፣ በቃላትም፣በስንኝ አወቃቀርም የተጠቀሰው ዓይነት ህጸጽ አይታይባቸውም።
የኳስ አፍቃሪዎች፦”ቀ ቁ ቂ ቃ
አንድ ጎል በደቂቃ “ እያሉ እንደሚጨፍሩት ፤ ዮሐንስ ትርጉም የለሽ ቃላትን ለቤት መምቻ ብቻ በዘፈቀደ አልተጠቀመባቸውም።ቃላትን በተገቢውና በትክክለኛው ቦታ እየሰካ ነው ያጫዎታቸው፦
ለምሳሌ” የእኔ ፍቅር ላንቺ “ በተሰኘው ግጥሙ ላይ፦
“…እንደ ሸማ ጥለት፣ ካሎስ-ሳባ ጥምረት፣
እንዳ’ደዋወሩ፣እንደ ድር ማግ ሥምረት፣
ሞያ እንደጎበኘው፣ እንደ ድርብ ኩታ፣
እንደ ቀጭን ፈትል፣እንደ ልስልስ በፍታ…
እንደ እስረኛ ባሪያ፣ እንደ ፍች ናፋቂ፣
ፍርድ እንደሚፈልግ ዝም ያልኩኝ ጠባቂ…..
እንደ እመጫት ድመት፣ ሙጭሊት እንደራባት፣
እንደ ክረምት ውሻ፣ ባሏ እንደናፈቃት…”
እያለ እንደ ጅረት ባፈሠሰው የግጥም ጎርፍ ላይ የተጠቀማቸውን ቃላትና የገቡበትን ስፍራ ስንመለከት ፤ዮሐንስ የቃላት ሐብታም ብቻ ሳይሆን የቃላት ሀብቱን በተገቢው ቦታ የሚጠቀም(የማያባክን) ገጣሚ መሆኑን እንረዳለን።
ገጣሚ መንፈሳዊና ደፋር ነው።መንፈሳዊ ስል ከውስጡ የሚያፈልቃቸው ሀሳቦች ከሰውኛውና ከሳይንሳዊው አስተሣሰብ ያፈነገጡ ናቸው ማለቴ ነው።በባህር ላይ መራመድ፣ተራራን በእምነትና በቃል ማፍለስ፣ በእሳት ላይ መሄድ…የመሣሰሉት በመንፈሳዊ መጽሕፍት የተጠቀሱት ተኣምራት፤ ለአንድ ዓለማዊ ወይም ሳይንሳዊ ሰው ቀልዶች ሊሆኑ ይችላሉ። ለገጣሚ ግን አይደሉም። ገጣሚው ራሱ እነዚህን ተዓምራት በየስንኞቹ ሢያደርጋቸው ይስተዋላልና። አንድ ገጣሚ በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኝ ፍቅረኛውን ሲናፍቅ ስለ ቪዛ፣ስለትኬትና ስለትራንስፖርት ዋጋ ሲጨነቅና ሲያስብ አይታይም።
፦”ባሳብ ፈረስ ሆኜ-እየገሰገስኩኝ ፣
ጋራውን አልፌ- ወዳንቺ መጣሁኝ “ ሲል ነው የምንሰማው። በቃ በተመስጦ ወዳሰኘው ይከንፋል።የአገር መለያየት፣ የተራራ መግዘፍ፣ የአድማስ ርቀት…አያግደውም። እንደ በቅሎ እየሰገረ፣ እንደ ፈረስ እየጋለበ፣ እንደ አሞራ እየበረረና እየተሽከረከረ ዱሩን፣ጢሻውንና ባህሩን..እየሰነጠቀ በሀሳብ ይነጉዳል።አንዳች የሚያስፈራው ቅጥር ሳይኖር ውስጡ የተሰማውንና አምጦ የወለደውን ይዘረግፈዋል።
ዮሐንስ፤”ጨዋታ ዝክረ-ዋልድባ ወዝቋላ” በሚለው ግጥሙ ላይ፦
ከጠቆረው ሰማይ፣
አፍጥጬ ወደ ላይ፣
ተአምር ተማጽኜ፣ትልቅ ተስፋ አዝዬ፣
ዳገቱን ወጥቼ..ቁልቁለት ወርጄ፣
ከላይ ታች ታግዬ፣
ከእሳቱ ጋር ልፊያ፣
ከአየሩ ጋር ግፊያ፣
ከነፋስ ጋር ግጥሚያ….. “እያለ፤ ማንም ዓለማዊ ሰው ሊገዳደራቸው ከማይችል ተፈጥሮዎች ጋር ግብግብ ገጥሞ እናየዋለን።
…ፍሙን ረግጬ፤እቶኑን ጨብጬ፣
ከእሳት ተሯሩጬ ከፍም ተፋጥጬ፣” እያለ የፍልሚያውን ከባድነት ከዘረዘረ በሁዋላም፦
……
እሪ በል ጠላቴ፣
እልል በል ወዳጄ፣
ገባሁ ረትቼ ፣ድል ቆመ ከደጄ” በማለት ከነፋስ ተጋፍቶ፣ ከእሳት ተላፍቶ፣ ፍም ጨብጦና እቶን ረግጦ በስተመጨረሻ ማሸነፉን ይነግረናል።ይህኔ የነ ሱዛን ኮሊን Catching Fire ትዝ ሊልዎት ይችላል።
ከላይ እንዳልነው ገጣሚን ጋራ አያግደውም፣ባህር አያሰጥመውም፣ እሳት አያቃጥለውም ።የሚረታው፣ የሚያቃጥለውና የሚያሰምጠው ፍቅር ብቻ ነው።እውነተኛ ገጣሚ መንፈሳዊና ደፋር ነው ስንል ግን ይህን ብቻ ማለታችን አይደለም። ከውስጡ የተወለደውን እንዳለ ለመዘርገፍ የማያመቻምች፣ የህረተሰቡን የልብ ትርታና የያየውን እውነታ ለማውጣት የማያፈገፍግ፣”እነ እገሌ ይከፋሉ፤እነ እገሌ ይደሰታሉ”በሚል ስሌት የወለደውን ልጁን(ግጥሙን) በጥገና የማያንሻፍፍ እና ብዕሩ አድርባይ ያልሆነ ማለታችን ጭምር ነው።
ለምሳሌ በብርሃን ልክፍት መድብል ውስጥ “ምንዱባን” የተሰኘው ግጥም፤ ዮሐንስ የሚያየውን እውነታ አምጦና የህዝብን የልብ ትርታ አዳምጦ የወለደውን ግጥም እንደወረደ የሚያቀርብ ደፋር ገጣሚ መሆኑን ያመላክተናል፦
የሰጡትን ማብቀል እየቻለ አፈሩ፣
ዘር እየመረጡ፣ዘር እየቆጠሩ፣
ዘር እየለቀሙ፣ዘር እየሰፈሩ፣
ዘር እያቀለጡ፣ዘር እያነጠሩ፣
ዘር እያንጓለሉ፣ዘር እያበጠሩ……” እያለ ነው ዮሐንስ በምንዱባን ላይ የተቀኘው።ዮሀንስ በዚህ ቅኔያዊ ግጥሙ ዘረኝነትን -በእህል ዘር አስመስሎ በመግለጽ፤ የዘሩ (የዘረኝነት)መጨረሻ ሊያምር እንዳልቻለ ይነግረናል።ገጣሚው ከዚህም ባሻገር፦ዘር መምረጥ፣ዘር መቁጠር፣ዘር መልቀም፣ዘር መስፈር፣ዘር ማንጓለል ፣ዘር ማበጠር…እያለ አንድን ቃል አብረውት ከሚሄዱ ብዙ ቃላት ጋር እያሰናሰለና እያዋደደ በመግጠም ፤ልዩ ችሎታውንም ያሳየበት ግጥም ነው።
በ”ግርማ ሞገሳ’ሟ እቴ” ፣ በ “ሀ ሁ/አ ኡ፣ እና በ “እንጉርጉሮዎቹ”ም ዮሐንስ ደፋርና ቀጥተኛ ብዕር እንዳለው፣ በህብረተሰቡ ልብ ውስጥ ያለውን ነገር ወደ አደባባይ ለማውጣት የማያንገራግር ገጣሚ መሆኑን ነው የምናየው።
ዮሐንስ፤ በብርሃን ልክፍት የዳሰሳቸው ቁም ነገሮችና ማህበራዊ ጉዳዮች በርካታ ናቸው። የቱን አንስቼ የቱን እንደምተው አስቸግሮኛል። ሁሉንም እንዳንዘረዝረውም የወረቀት ገጽና የአየር ሰዓት ይወስነናል። ስለዚህ እንደ አጀማመራችን አልፎ አልፎ በጣም በጥቂቱ መቃኘታችንን እንቀጥላለን፦
የሰው ልጅ ብዙ ጊዜ የሚፈልገው የሌለውን፣ የሚያሳድደውም የሚሸሸውን ለመሆኑ ብዙዎቻችን የማናስተውለው እውነታ ነው። ዮሐንስ ይህን እውነታ “ምናልባት ከቀረሽ”በሚለው ግጥሙ ላይ በሚገባ ገልጾታል። ዮሐንስ በዚህ ግጥሙ ያፈቀራትንና ቃል የገባችለትን ፤ሆኖም የእሱ ለመሆኗ ገና እርግጠኛ ያልሆነባትን ልጅ በናፍቆት ተውጦ በጉጉት ሲጠብቃት እናያለን።እሱ ወደሷ አንጋጦ በተስፋ ሲጠብቅ-በአንፃሩ ከሁዋላው እሱን ያፈቀረች ሌላ ሴት ልትኖርና ልትጠብቀው እንደምትችልም ጠርጥሯል።እሱ አንዿን ሲያሣድድ፣ ሌላዋ እሱን እያሳደደችው እንዳይሆን ሰግቷል፤ሸክኳል።
እናም፦
የፈጀውን ፀሐይ፣ ያሻውን ጨረቃ፣…ይፍጅና መምጣትሽ፣
ምጭልኝ ዓለሜ፣ በዕድሜዬ ድረሽ፣ መሞቴ ሳይቀድምሽ፣
የኔ ቃል አንቺ ነሽ! ሌላ የታ’ውቃለሁ?
ቃልሽኝ ከጠበቅሽ…እጠብቅሻለሁ!
ሆኖም በምናልባት…
ድንገት ‘ማትመጪ እንደሁ፣ ሀሳብሽን ቀይረሽ፣ጉዞሽ ከታጎለ፣
አደራ ላኪብኝ!..ማስጠበቅ ጡር አለው፣ ‘ሚጠብቀኝ ካለ። “ሲል እንሰማዋለን።
ዮሐንስ በግጥሙ ያነሳው ሌላ ነጥብ ጊዜን ይመለከታል።አብዛኞቻችን ኢትዮጵያውያን 7 ሰ ኣት ተቀጣጥረን 10 ሰ ዓት የምንገናኝ ዜጎች ብንሆንም ወጉ አይቀርምና በየጓዳችንና በየታክሲዎች ሳይቀር የሚለጠፍ፦
”ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ፣
ጊዜ ታክሲ አይደለም፣አይጠብቅም ቆሞ”የሚል የቆየ ስንኝ አለን። የዚያኑ ያህልም የአገራችን ጸሀፊዎችም ስለ አላፊው ጊዜ፣ስለ አላፊው ዘመን በየራሳቸው አተያይና አገላለጽ ብዙ ነገር ብለዋል።ለምሳሌ ጋዜጠኛና ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም “ኗሪ አልባ ጎጆዎች” በተሰኘው ተወዳጅ የግጥም መድበሉ ይህን ነገር የገለጸው፦
“እኛ’ኮ ለዘመን፣
ክንፎቹ አይደለንም፣
ሰንኮፍ ነን ለገላው፣
በታደሰ ቁጥር፣ የምንቀር ከሁዋላው።” በማለት ነው። ዮሐንስ ደግሞ በራሱ አተያይ “ምኞት” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ግጥም ፦
የሰዓት ቆጣሪው፣
የጊዜ ቀማሪው፣
ያ ቀጭኑ ሽቦ፣
ስንዞር አብሮን ዞሮ፣
ስንበርም በ’ሮ፣
አብሮን እንደዋለ…
ስንተኛም እንደኛ፣
ምናለ ቢተኛ “ እያለ ስለጊዜ የቁጭት ምኞቱን ሲገልጽ ይታያል።የዮሐንስ የጊዜ ቁጭት ግን በዚህ አይበቃም። በህብረተሰባችን ዘንድ የሚታየው፦ ጊዜን በአግባቡ ያለመጠቀም ነገርም ገጣሚውን አሣስቦታል።ዮሐንስ በብዙዎች ዘንድ ፦ “ጊዜውን እንግፋው፣ ጊዜውን እንግደለው…”የሚለውን አባባል በገጣሚ ዓይኑ አይቶ በዝምታ ሊያልፈው አልፈለገም፦
እናም፦”ሆድ ሲያውቅ “ በሚለው ግጥሙ፦
በቧልት ላላገጠ፣በፌዝ ለዘለለ፣
ብሩህ ተስፋን ነፍጎ፣ጸጸትን ካደለ፣
የሰው ፊት ካሳዬ፣ዝቅ አ’ርጎ ካዋለ፣
ጊዜ ገደለ እንጂ፤መቼ ተገደለ?!”ይለናል።
ሌላው በዮሐንስ መድበል የተዳሠሰው ቁም ነገር እንባን ወይም ለቅሶን የሚመለከት ነው።
ዮሐንስ፦ “አታልቅሽ” በሚለው ግጥሙ በታሪክ ስህተት ሳቢያ የሚወለድ ፀፀትና ቁጭት፤ ስህተትን ለማረምና ለማስተካከል እስካልጠቀመ ድረስ ከተራ የለበጣ ለቅሶነት የዘለለ እንዳሆነ ይነግረናል። የዚህ ዓይነቱ፦ ልባቸውን ሳይሆን ልብሳቸውን ከቀደዱ ሰዎች የሚወጣ እምባ ደግሞ መጣ ቀረ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ይነግረናል። ሎሬት ጸጋዬ የቴዎድሮስ ስንብት በመቅደላ በተሰኘውና ዓፄ ቴዎድሮስን ባናገሩበት ግጥማቸው፦
“…ሰለዚህ ለራስሽ እንጂ፥ ልቅሶሽ ለኔ ምን ሊረባ?
ብቸኛ ምሬት ነው ኃይሉ፥ ወኔ መሰለቢያው ነው እንባ፡፡” እንዳሉት ሁሉ፤ዮሐንስም አታልቅሽ በተሰኘው ግጥሙ፦
የዐይን ኳስ ተጨምቆ፣
ሽፋሽፍት ተላቆ፣
ቁልቁል ተሸምድዶ፣
ከጉንጪ ላይ ወርዶ…
የታሪክ ቋጠሮ ለይቶ ካልፈታ፣
ተስፋን አቀራርቦ፣ካልቸረ እፎይታ፣
ፈሰሰ፣ደረቀ…እንባ ቀረ መጣ፣
ከቶ ምን ሊረባ? “ ይለናል።
በብርሀን ልክፍት ከተሰባሰቡት 72 ግጥሞች አንዷ “ረቡኒ”ነች። ረቡኒ ቃሉ ዕብራይስጥ ሲሆን ትርጓሜው፦”መምህር ሆይ!” ማለት ነው።ታላቁ መጽሀፍ፤ ማርያም መግደላዊት በትንሳኤ ማግስት ኢየሱስን በዚህ ቃል እንደጠራችው ይነግረናል።
ዮሐንስ “ረቡኒ”በተሰኘችው ውብና አጭር ግጥሙ ፦
ቤትህ የማር ሀገር፤ልብህ የማር ቀፎ፣
ጣ’ም የሚበስልበት፣ ቀለም ተንጠፍጥፎ፣
ፍቀድልኝና ልዋል ከእግሮችህ ስር፣ ላንጋጥ አሰፍስፌ፣
ካ’ፍህ ማር ጠብ ሲል፣እንዳይወድቅ ካፈር፣
እንዲገባ ካ’ፌ” በማለት ለዕውቀት ወይም ለአዋቂዎች ያለውን አክብሮት እንዲሁም ፤ እሱም ከአዋቂዎች እግር ስር ሆኖ አብዝቶ የመማርና የማወቅ ጉጉቱን ቅኔ ባዘሉ ስንኞቹ ሲገልጽ እናየዋለን።
“የትውልድ ጠባሳ፣ሥጋ ደካማ፣አተርፍ ባይ አጉዳይ…ወዘተ” በአጭር ስንኞች ታላላቅ ቁም ነገሮች የታጀሉባቸው የዮሐንስ ውብ ግጥሞች ናቸው።ወጣቱ ገጣሚ የመጀመሪያ በሆነው የብርሃን ልክፍት የግጥም ስብስብ በተለያዩ የስንኝ አጣጣሎችና ምቶች አያሌ ጭብጦችን ለመዳሰስ ሞክሯል።አጠቃላይ መጽሐፉን አገላብጠን ስናነበው ዮሐንስ የበሰለ እንጂ ጀማሪ ደራሲ አይመስለንም።በመጀመሪያ ሥራው ይህን ያህል ከሰጠን ለወደፊቱ ምን ያህል ሊያበረክትልን እንደሚችል መገመት አይከብድም። እናም እንትፍ፣እንትፍ፣ እደግ ተመንደግ ብለን ልንመርቀው ይገባል።
በመጨረሻ የማነሳቸው ነጥቦች
-የመጽሐፉ ርዕስ የብርሃን ልክፍት ቢሆንም፤ ይህ ግጥም በመጽሐፉ ውስጥ አልተካተተም። ይህ ነገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ መምጣቱ ቢገባኝም፤ በኔ በኩል ግን የብርሃን ልክፍት የተሰኘችውና በፌስ ቡክ አስፍሯት ያየሁዋት ግጥም በስብስቡ ብትካተት፣አለያም በስብስቡ ከተካተቱት ግጥሞቸ አንድኛቸው የመጽሐፉርዕሶች ቢሆኑ እመርጣለሁ።ሆኖም ከመጽሐፉን ርዕስ ማራኪና ሳቢነት አንፃር ከነዚህ ሁለት አማራጮች የኔ የመጀመሪያው ምርጫ የብርሃን ልክፍት ግጥም ብትካተት የሚል እንደሆነ መጠቆም እፈልጋለሁ።
-ዮሐንስ በግጥሞቹ አዲስ የቃላት አጠቃቀምን ይዞ መጥቷል። ለምሳሌ “ፍቅሬ ሙዚቃዬ” በተሰኘው ግጥሙ “ወርቅ ቢሆን” ለማለት ፦ቢወረቅ፣ ጨርቅ ቢሆን ለማለት፦ “ቢጨረቅ” ሲል እናየዋለን። ከዓመታት በፊት እነ ዶክተር (ተባባሪ ነፕሮፌሰር) ፈቃደ አዘዘ አንዳንድ የእንግሊዝኛ ቃላትን በዚህ መልክ እያመጣን በአማርኛ ብንጠቀምባቸውስ? የሚል ሃሳብ ሲያነሱ ሰምቻለሁ። ለምሳሌ “ክላሲፊኬሽን” የሚለውን ቃል “ክልሰፋው እያልን እንጠቀም የሚል ነበር የነ ዶክተር ፈቃደ ሃሳብ። ይህ ሃሳብ በህብረተሰቡ ወይም በጸሀፍያን ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ምን ያህል ርቀት እንደሄደ አላውቅም። አንድ የማውቀው ሀቅ ቢኖር፤ በአገራችን እንደዚህ ዓይነት አዳዲስ ሃሳቦችን ለመቀበል የሚፈቅዱ እንዳሉ ሁሉ፤ በአንፃሩ “ሀ”ይሌ ገብረሥላሴን ወይም ኢንጂነር “ሀ”ይሉ ሻውልን እንዴት በፎሌው “ሀ” ትጽፋቸዋለህ? ብለው የሚቀየሙ ሰዎችም ጭምር መኖራቸውን ነው። ስለዚህ ዮሐንስ ይዟቸው የመጣቸው እነዚህ የቃላት አጠቃቀም ተቀባይነት ማግኘታቸውን ወይም አለማግኘታቸውን ወደፊት የምናያቸው ይሆናል። አለያም በጉዳዩ ዙሪያ የሥነ-ጽህፍ ሰዎች ሊነጋገሩበት ይችላሉ።
-በብርሃን ልክፍት ያስተዋልኩት ሌላው ነገር ገጣሚው “ይጠጥራሉ”ብሎ ላሰባቸው ቃላት-የቃላት መፍቻ ማዘጋጀቱን ነው። በኔ በኩል ለግጥም መጽሐፍ የቃላት መፍቻ ማዘጋጀቱ አስፈላጊ ሆኖ አልታየኝም።ግጥም-ግጥም ነው። አንባቢ ደጋግሞ በማንበብ እንዲመራመርበት ዕድል ሊሰጠው ይገባል።አንዳንድ ግጥም ተደጋግሞ እየተነበበም ሊጠጥር ይችላል። ይህ የግጥም አንዱ ባህርይ ስለሆነ ደራሲውን ሊያስጨንቀው አይገባም።ዮሐንስ የቃላት መፍቻ ያዘጋጀው ለአንባቢ ከመጨነቅ እንደሆነ ግልጽ ነው። “አይገባቸው ይሆን?” የሚለው ይህ ጭንቀቱ፤ በ አንዳንድ ግጥሞቹ ሳይቀር አልፎ አልፎ ሲከሰት ይታያል።ለምሳሌ “አደራ” የተሰነችውን የዮሐንስን ውብ ግጥም እንቃኛት፦
ሥጋዬ ሲበላ…ፈቀድኩ አባያቸው፣
ደሜንም ሲጠጡት፣ይሁን አጣጪያቸው፣
አጥንቴም ሢሰበር፣ ከቻልሽ አሳብሪያቸው፣
ልቤን ሲጠጉ ግን፣
ውስጥ አንቺ አለሽና፣ ሰው አለ በያቸው።” ይላል። እንደ እኔ በመጨረሻው ስንኝ ላይ፦ “ውስጥ አንቺ አለሽና” የሚለው ሀረግ አስፈላጊ አልነበረም ባይ ነኝ። “ውስጤ ሲጠጉ ግን፣ሰው አለ በያቸው” በቂ ነበር። “ሰው አለ” የሚለው፤ ከውስጥ ያለ ሰው መሆኑ ግልጽ ነው።ማለትም ወደ ልቡ ሲጠጉ ‘ሰው አለ!’ ካለች-እሷ በልቡ ውስጥ ለመኖሯ በቂ ማረጋገጫ ነው። ከዚህ በላይ ሄዶ ለማረጋገጥ መሞከር አይጠበቅበትም። “ውስጥ አንቺ አለሽና” የምትለው ሀረግ ዮሐንስ ነገሩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ መጨነቁን ነው የምታሳየው።የዚህን ያህል ርቀት ሄዶ ለ አንባቢ መጨነቅ፤ በግጥሙ ላይ አላስፈላጊ ልባሰን መደረብ ስለሚያስከትል ለወደፊቱ በጥንቃቄ ማየት የስፈልጋል። ይህም ሆኖ ፤በልቤ ከቀሩት የዮሐንስ ግጥሞች አንዷ ይህችው ፦ “አደራ” የተሰኘችው ናት።
ዮሐንስ ከፈቀደልን፦”ውስጥ አንች አለሽና” የምትለውን ሀረግ አውጥተን እስኪ እንድንደግማት ፦
“ሥጋዬ ሲበላ…ፈቀድኩ አባያቸው፣
ደሜንም ሲጠጡት፣ይሁን አጣጪያቸው፣
አጥንቴም ሢሰበር፣ ከቻልሽ አሳብሪያቸው፣
ልቤን ሲጠጉ ግን፣ ሰው አለ በያቸው። “ ይበል ብለናል ጆ!!!
ቅኝቴን በየትኛው ግጥም ልቋጨው? በአሻም እቴ? በጸጸት? ወይስ በእውነት እናውራ ካልሽ?…ምርጫው ከባድ ነው። ግዴለም በ”የቸገረ ነገር”ልሰናበታችሁ መሰል፦
የቸገረ ነገር
በአፈርማ ምድር፣
ባቄመ ሰማይ፣
እውር እየመራ፣
ይዘለቃል ወይ?!
ዮሐንስ ሞላ፤ እደግ ተመንደግ! ኑርልን!ፃፍልን!
ESFNA 2013፡ ፍቅር እንጂ ገንዘብ የማይገዛው ሕዝብ በአንድ ላይ ዘመረ (Video)
ሕዝቡ በስታዲየሙ እንዲህ ሲል ከዘፋኙ ጋር ዘመረ፦
“ገንዘብ ፍቅር ከሌለበት
የማይጠቅም ከንቱ ነው
ለጊዜው ያስደስት እንጂ
ሲረግፍ እንደጤዛ ነው”
ጃ ሉድን ምን ነካው? (ቪድዮ)
ስለሺ ደምሴ እና ፈንድቃ የባህል ቡድን በሚኒሶታ የኢትዮጵያን ሙዚቃና ዳንስ አስተዋወቁ (ሙሉውን ቪድዮ ይዘናል)
(ዘ-ሐበሻ) በሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ The Cedar Cultural Center’s የ”African Summer series” በሚል የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራትን ሙዚቃዎችና ባህል ባሳየበት በዚህ የበጋው ወራት ዝግጅቶች ኢትዮጵያን በመወከል አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) እና ፈንድቃ የባህል ቡድን ረቡዕ ጁላይ 10 ቀን 2013 በተዘጋጀው ወርክሾፕ ላይ ዝግጅታቸውን በማቅረብ የሃገራቸውን ሙዚቃ፣ ዳንስ እና ባህል አስተዋውቀዋል።
በዚህ በርከት ያሉ የውጭ ሃገር እና ኢትዮጵያውያን ዜጎች በተገኙበት የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) እና ፈንድቃ የአዝማሪ ባህል ቡድን በሚኒያፖሊስ የኢትዮጵያን ሙዚቃና ባህል በሚገርም መልኩ አቅርበው ከታዳሚው አድናቆትን አግኝተዋል። ጋሽ አበራ ሞላ በክራሩ አስቂኝ ግጥሞችን በመደርደር ህዝቡን ሲያዝናናው ያመሸ ሲሆን ፈንድቃዎች ደግሞ በውዝዋዜ፣ ትግርኛውን፣ አማርኛውን፣ ኦሮሚኛውን፣ ወላይትኛውን፣ ጉራጊኛውን እና ሌሎችንም ሲያስነኩት ነበር። ይህ 1:20 ደቂቃ ቪድዮን ዘ-ሐበሻ ቀርጻዋለች። ቪድዮውን ለእረፍት ቀንዎ ማየት ከፈለጉ ይኸው። ላላዩት ቢያሳዩት፤ በተለይም በውጭ ሃገር የሚያድጉ ህጻናትና ወጣቶች ቢያዩት መልካም ነው እንላለን። ወደ ቪድዮው፦
Art: ሁለገቧ አርቲስት አዳነች ወ/ገብርኤል
በማስረሻ መሀመድ
አርቲስት አዳነች ከአባቷ ወ/ገብርኤል ገብረ ማርያም እና ከእናቷ ፋና አምባው በ1952 ዓ.ም ይህችን አለም ‹‹ሀ›› በማለት ይፋትና ጠሞ በሚባል አውራጃ ካራቆሬ በተባለ ትንሽ ከተማ ውስጥ ተወለደች፡፡ እንደማንኛውም ልጅ እናትና አባቷን በቤት ውስጥ በማገልገል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በዚችው ካራቆሬ በተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ ተከታተለች፡፡ ከዛም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደብረሲና ከተማ ውስጥ ከተከታተለች በኋላ 9ኛ ክፍል ሠንዳፋ ጅማ ሰንበቴ ትምህርት ቤት ከታላቅ እህቷ ኮማንደር ብርቄ ወ/ገብርኤል ጋር በመሆን እዛው ትምህርቷን እንድትከታተል ሆነ፡፡ ይሁንና የነበሩበት ከተማ በተለያዩ ምክንያቶች ስላልተስማማቸው አዳነችና እህቷ ብርቄ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ተገደዱ፡፡
አዲስ አበባም አጎቷ ሻንበል ባሻ ተረፈ አንባ ጋር በመሆን ያቋረጠችውን ትምህርቷን ማለትም ከ9ኛ ክፍል በግዜው የፈጥኖ ደራሽ ካንፕ (ሙዚቃ ክፍል) አጠገብ ከነበረው ቅዱስ ጳውሎስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መማር ቀጠለች፡፡ ‹‹እንዴት ነበር ለትምህርት የነበረሽ ፍላጎት››? የሚል ጥያቄ አቀረብኩላት ‹‹ኦ ይሄ ነው ልልሽ አልችልም ብቻ ተመጣጣኝ ነው ማለቱ ይቀለኛል፡፡ እኔ በተለይ በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ቤት ስማር በግዜው በጣም ወጣት ነኝ ፍላጎቴ በሙሉ የነበረው ስፖርት ላይ ነው፡፡ እንዲሁም
ከዚሁ ትምህርት ቤት በፊት በተማርኩባቸው ት/ቤቶች በጠቅላላ ስፖርት ከመስራቴ ባሻገር ውድድር ውስጥ ሁሉ እገባ ነበር፡፡ እንደውም ጅማ ሰንበቴ ትምህርት ቤት ስማር ለስፖርት ተመርጬ ለውድድር ወደ አዲስ አበባ ስቴድየም የመጣሁበት ግዜ ሁሉ አለ፡፡ የምድር ዝላይ፣ ሪሌይ፣ 100 ሜትር ሩጫ እና ሌሎችንም ተወዳድሬ ወደ አራት ሜዳሊያዎችን ለትምህርት ቤቴ ያስገኘሁበትን ግዜ አልረሣም›› የሚል መልሷን ሠጠችኝ፡፡
ከዚህ በኋላ አዳነች በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርቷን እየተከታተለች ቢሆንም ከፈጥኖ ደራሽ ካንፕ ሙዚቃ ክፍል የሚንቆረቆረው የባንድ ዜማ እና ከፍተኛ ድምቀት የነበረው የማርሽ ቡድኑ ጣዕመ ዜማ ከግዜ ወደ ግዜ ቀልቧን እየገዛ መጣ፡፡ ታዲያ በዚህ መሀል ፈጥኖ ደራሽ የሥራ ማስታወቂያ ለጠፈ፡፡
ይህን በመከተል ታዲያ 1968 ዓ.ም አዳነች በ16 አመቷ ትምህርቷን በማቋረጥ ፈጥኖ ደራሽ ያወጣውን መስፈርት በብቁነት በማለፍ ወደ ውትድርናው አለም ‹‹በእድሜ ትንሽ ብትሆንም እዚሁ ታድጋለች›› በማለት የሙዚቃ ክፍሉ ሀላፊ ኮረኔል አያሌው አበበ፣ ተስፋዬ አበበ እና ኮረኔል ግርማ በተወዛወዥነት እንድትቀላቀል አደረጓት፡፡ በዚህም ግዜ ፒያኖ፣ የማርሽ ሙዚቃና የተለያዩ በካንፑ ይሰጡ የነበሩ ትምህርቶችን በፖሊስነት ተምራና ሠልጥና ብቁ ሆና ተመረቀች፡፡ የፖሊስ ተወዛዋዥ ሆና ለስድስት ወር ሠልጥና ከተመረቀች በኋላ በህጉ መሠረት በግዜው የሚሞላ ቃል የመግቢያ ፎርም ነበረና በፎርሙ መሠረት ለሠባት አመት ላታገባ፣ ላትወልድና፣ የሰውነት አቋሟ ላይለወጥ ቃል ገባች፡፡ በህይወት ላይ መቼም አንዳች አይጠፋምና አዳነች ስራዋን ለተወሠኑ ግዜያት ከሠራች በኋላ በውዝዋዜው በግዜው ያሠለጥናት የነበረው ሻንበል ባሻ ጌታቸው አንዳርጌ በፍቅሯ በመውደቁ ጠልፏት እቤቱ ይዟት ገባ፡፡ ይህ ሲሆን ታዲያ በካንፕም በመሠማቱ ከፍተኛ ቁጣን አስነሣ፡፡ ይህን ተከትሎም የህግ ጥሠት ተካሄዷል ተብሎ አዳነችና ጌታቸው ቻርጅ እንዲሞሉ ተደረገ፡፡ ቅጣትም ተላለፈባቸው፡፡ ቅጣቱ በግዜው ጦርነት ወደነበረበት አስመራ ክፍለ ሀገር ጌታቸው ባሰልጣኝነት አዳነች ደግሞ በረዳት አሠልጣኝ ሆነው ወደ አስመራ ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል እንዲዘዋወሩ ተደረገ፡፡
‹‹ለግዜው ቅጣቱ ሲወሰንብሽ ምን አይነት ስሜት ተሠማሽ›› የሚል ጥያቄ አነሣሁላት ‹‹እንደማንኛው ሰራዊት ህጉን በመጣሴ ቅጣት ተላልፎብኛል፡፡ ለምን ቅጣቱ ተላለፈብኝ ብዬ አላዛንኩም፣ ቅሬታም አላሠማሁም፣ ጥፋቴንም አምኛለሁ፣ ለመቀጣትም ዝግጁ ነበርኩ›› በማለት በራስ የመተማመን ስሜቷ ፊቷ ላይ በግልፅ እያሣየችኝ ለጠየኳት ጥያቄ መልሷን ለገሠችኝ፡፡
አዳነች በአዲስ አበባ ፈጥኖ ደራሽ ሙዚቃ ክፍል የተወሠኑ ጊዜያት ብቻ የቆየች ቢሆንም ኤርትራ ክፍለ ሀገር አስመራ ፖሊስ ሙዚቃ ክፍል ግን ብዙ ግዜያትን አሣልፋለች፡፡ ከዛም አልፎ ከሌሎች ለየት ባለ ብዙና አጥጋቢ እንቅስቃሴዎችን ታደርግ ነበር፡፡ ይህን የምታደርገው ታዲያ አንደኛ በፖሊስነት ሌላም ደግሞ በሲቪልነት ነበር፡ ፡ ታዲያ ከምታደርገው ጠንከር ያለ እንቅስቃሴ የተነሣ የአራት ሲኒማ ቤቶች ማለትም ሲኒማ ካፒቶል፣ ሲኒማ ኢትዮጵያ፣ ሲኒማ ሮማ እና ሲኒማ አባ አሉላ አባ ነጋ አዳራሽ የተባሉ ሲኒማ ቤቶችን አስተዳድራለች፡፡
በዚህ ግዜ ታዋቂ አርቲስቶች የተባሉ አርቲስት አማኒ ኢብራሂም፣ ይገዙ ደስታ እና ሌሎች ሌሎችም ከአዲስ አበባ ራስ ቲያትር እየመጡ እሷ የምታስተዳድራቸው ሲኒማ ቤቶች ዝግጅታቸውን በሚያቀርቡ ሠዓት የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች የምታቀርብላቸው እሷ ስለነበረች ከነሱ ጋር የመተዋወቅ እድሉ ተከፍቶላታል፡፡
አዳነች ከ1969 እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ በኤርትራ ከላይ የጠቀስኳቸው ሲኒማ ቤቶችን ስታስተዳድር አያሌ የሚባሉ አስደማሚ ግዚያቶችን ማሳለፏን ትናገራለች፡፡
አዳነች ሲኒማ ካፒቶል እያለች ‹‹ጭቁኗ ሴት ተነሽ›› የሚል ድርሠት በመፃፍ ለእይታ አብቅታለች፡፡ በሠዐቱ አስመራ ውስጥ 107 ቀበሌዎች የነበሩ ሲሆን በነበራት ጠንከር ያለ እንቅስቃሴዎች ከሚሊተሪ ውጪ የሴቶች ሊቀመንበር በመሆን አገልግላለች፡፡ ታዲያ በወቅቱ ስለነበረው የሻዕብያ ጦርነት ቤት ለቤት በመዞር ሴቶችን በማነሣሣትና የተለያዩ ኪነ ጥበብ ነክ ስራዎች በመስራት የማነቃቃት ስራዎችን ሠርታለች፡፡ ይህ ታዲያ ታይቶ ከተራ ወታደርነት የ50 አለቃ ማዕረግን ለማግኘት በቅታለች፡፡ በግዜው ጀነራል ግርማ አየለ የማዕረግ ሽልማቱን (አበርክተውለታል፡፡)
ከዚህ በኋላ አዳነች አስመራ የነበራትን እንቅስቃሴ ወደአዲስ አበባ ለመቀየር በማሰብ ለአራቱም ሲኒማ ቤቶች ባለቤት አቶ ሀይሉ የስራ መልቀቂያ በማስገባት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሲኒማ ራስ ተቀጥራ ማገልገል ጀመረች፡፡ ከ1974 በኋላ ወሩን በትክክል ባታስታውሰውም ከላይ እንደጠቀስነው በአሁኑ ራስ ቲያትር ቤት በቀድሞው ስሙ ራስ ሲኒማ ማገልገል ጀመረች፡፡ ወደዚህ የመጣችበትን ዋና ምክንያት ብላ እንደገለፀችው አዲስ አበባ ያለው ሲኒማ ኢትዮጵያና ራስ ቲያትር ከተስፋዬ አበበ ጋር ግንኙነት ስለነበራቸውና ደሞዟም ሞዴል እየተባለ ከአስመራ እየተላከ ይከፈላት ስለነበር ነው፡፡
‹‹በዚያን ግዜ ደሞዝ ስንት ይከፈልሽ ነበር?›› የሚል ጥያቄ አነሣሁላት እሷም እየሳቀችና የአግራሞት ስሜትን እያንፀባረቀች ‹‹የያኔ ብር እንዳሁን ግዜ አልነበረም፤ እኔ እንዳውም ትልቅ ደሞዝ ይከፈላቸው ከነበሩት ውስጥ አንዷ ነበርኩኝ፤ 375 ብር ይከፍሉኝ ነበር›› የሚል መልስ ሠጠችኝ፡፡
ከዚህ በኋላ አስቴርዬ ክለብ ማገልገል ጀመረች፡፡ ክለቡ በሲሊንደር ፍንዳታ ምክንያት በመቃጠሉ በራስ ቲያትር የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ በመሆን ተቀጥራ በዚሁ ቦታ ላይ ለ15 ዓመታት ያህል አገለገለች፡፡ ከዚያም ወደ ሀገር ፍቅር ቲያትር በመዘዋወር ከ1994 ዓ.ም እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ በዚሁ ሞያዋ አገለገለች፡፡
ከ1996 ዓ.ም በኋላ በኢትዮጵያ መገናኛ ኤጀንሲ ውስጥ ተቀጥራ የፕሮሞሽን ስራዎችን ፣ መፅሔቶችንና የተለያዩ ኪነ ጥበብ ነክ ስራዎችን በመስራት ለተወሰኑ አመታት ካገለገለች በኋላ ከመስሪያቤቱ በግሏ ስራ የመልቀቅ ፍላጎቷን በመግለፅ ከስራዋ ለቀቀች፡፡
ከዚህ በኋላ እንግዲህ አዳነች ስራዎቿን ሁሉ ከተቀጣሪነት ይልቅ በግሏ ለመስራት በመወሠን ‹‹ጀአዲ አርት ፕሮሞሽን›› የሚል ድርጅት መሠረተች፡፡ በዚህ ድርጅት ውስጥ ታዋቂ የነበረውንና የመዝናኛና የኪነጥበብ ስራዎች ይቀርብት የነበረውን ‹‹ጠብታ›› የተሠኘውን መፅሔት በ2000 ዓ.ም መሠረተች፡፡ ይህ መፅሔት በአዲስ አበባ ውስጥ ጎልተው ከወጡ መፅሔቶች ውስጥ አንዱ የነበረ ሲሆን በውስጡም እነ ፕሮፌሠር አብይ ፎርድር ፣ሀይሌ ገሪማ፣ የሼክ አላሙዲን ባዬግራፊና ሌሎች ታዋቂ ሠዎችን
ይዞ የሚወጣ መፅሔት ነበር፡፡ መፅሔቱን አዳነች ለሁለት አመታት አሣትማ ለህዝብ ያቀረበች ቢሆንም በወቅቱ የነበረውን የህትመት ዋጋ መቋቋም ባለመቻሏ በ2002 ዓ.ም መፅሔቷን ከመታተም እንዲቆም አደረገች፡፡ ከ2002 ዓ.ም ላይም ‹‹ሳሎን ኢትዮጵያ›› የተባለ ጋዜጣ በበአሜሪካ ሲያትል ከተማ ውስጥ በየ15 ቀኑ አሳትማ ለኢትዮጵያውያን ታቀርብ የነበረ ቢሆንም ከአሳታሚዎች ጋር በነበራት አለመስማማት ጋዜጣዋን ልታቆም ችላለች፡፡
‹‹በነገራችን ላይ እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ፣ መሠረት እንድጥልና በራሴ እንድተማመን ያደረገኝ የፖሊስ ሠራዊት ቤት ነው፡፡ ትልቁን በስነ ምግባር እንድታነፅና ህይወቴን እንድመራ ያደረገኝ ይሄው የፖሊስ ቤት ስርዓት ነው፡፡›› የምትለው አዳነች እሷ የነበረችበት ግዜ የነበረው የፖሊስ ሥነ ስርዓት እንዲህ በቃላት ልትገልፀው እንደማትችል ታስረዳለች፡፡ በሚሊተሪ ውስጥ የማትረሣው ነገር አዳነች ሙዚቃ ክፍል እያለች የነበረው መተሣሠብ፣ መፈቃቀርን፣ መከባበሩንና ሰርዓቱን ነው፡፡ ‹‹እስከ ዛሬም ድረስ በፈጥኖ ደራሽ ነባር የነበሩትን መኮንን መርሻን፣ እና ዳንኤልን ሣይ እንባዬ ይመጣል›› ትላለች፡፡
አዳነች በአሁኑ ሠዓት በራሷ ድርጅት ‹‹ጀአዲ አርት ፕሮሞሽን›› ላይ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡ በቅርቡም የልጇ ባለቤት የሆነው አርቲስት አለማየሁ ታደሠ የደረሠው ድርሰት ላይ አብራ ለመስራት እንቅስቃሴ እያደረገችም ትገኛለች፡፡ ‹‹በቅርቡ የሠው ለሠው ድራማ ላይ እየተወንሽ ትገኛለሽ እንዴት ነው እንቅስቃሴው?›› አልኳት ‹‹ኦው! የሰው ለሰው ቤተሠቦች እጅግ ጎበዝና የቀልጣፋ ተዋናዬች ስብጥር ሲሆን አንጋፋና ወጣት ተዋንያን የተሣተፉበትም ጭምር ነው፡፡ እንዳውም ‹የአስናቀ ሚስት› እያሉ መንገድ ላይ ስሜን ቀይረውት ይጠሩኛል፡፡
በይበልጥ በድራማው ታዋቂነትን አትርፌያለው ብዬ አስባለሁ›› የሚል መልስ ሰጠችኝ፡፡ አዳነች ከባለቤቷ ጋር የነበራት ኑሮ እጅግ መራራ እንደነበረ ትገልፃለች፡፡ እሷ ወጣት በመሆኗና ባለቤቷ ሻንበል ባሻ ጌታቸው በእድሜ ስለሚበልጣት እንደ ልጅ በየግዜው ይደበድባት እንደነበር ትገልፃለች ይህ ያማረራት አዳነች፤ ቢኒያም ጌታቸው እና ማርታ ጌታቸው የተሠኙ ልጆቿን ከወለደች ከተወሰኑ አመታት በኋላ ከባለቤቷ ጋር ልትለያይ ችላለች፡፡ ባለቤቷም ሌላ ቤተሰቦችን መስርቶ ልጆችን ያፈራ ቢሆንም ከዚህ አለም በሞት የተለየ መሆኑና ልጆቹንም እንደ ልጆቿ እያየች እንዳሳደገች ታስረዳለች፡፡ ሻይና ዳቦ ከማንኛውም የምግብ አይነቶች የምታስበልጥ ሲሆን እስፓርታዊ እንቅስቃሴንም አሁንም ድረስ አላቋረጠችም፡፡
አርቲስት አዳነች ወ/ገብርኤል በቲቪ ድራማዎች ላይ ያልተሄደበት መንገድ፣ ቅብብል እንዲሁም አሁን በሚታየው የሠው ለሰው ድራማ ላይ የተሣተፈች ሲሆን የራሷ ድርሰት በሆነው የሳት ዕራት፣ ክብረነክ፣ ኮሞሮስ፣ አልደወለም፣ አልነግራትም እንዲሁም ፊደል አዳኝ የተሠኙ ፊልሞችን ሠርታለች፡፡ አማጭ፣ ዲያስፖራ፣ ሩብ ጉዳይ እንዲሁም የብዕር ስም የተባሉ ቲያትሮች ላይም ተውናለች፡፡ ከዚህ በተረፈ የሸዋንዳኝ ሀይሉን፣ የሄኖክ አበበን፣ የሄሎ አፍሪካ ጄሪን፣ የነዋይ ደበበን (አሜን)፣ የፀሐዬ ዩሀንስን (ሳቂልኝ) አልበሞችን ፕሮሞት ያደረገች ሲሆን የቴዲ አፍሮን እና የሸዋንዳኝን፣ ኮፒ ራይት ማህበር ያዘጋጀውን፣ የከተሞች ቀን የተከበረበትን፣ ስፖርት ለሠላም የተሠኙ ኮንሰርቶችን ፕሮሞት አድርጋለች፡፡ ቻቺ ታደሰ እንዲሁም የሌሎች ታዋቂ አርቲስቶች ፕሮሞተር በመሆን ሠርታለች፡፡ ‹‹ሥራዬን መቼም አላቆምም ወደፊትም ለህዝብ የማቀርበው ሥራዎች አሉኝ›› በማለት የወደፊት ዕቅዷን ነግራኛለች፡፡ እነሆ አዳነች 53ኛ ዓመት ዕድሜዋን በደመቀ ሁኔታ አክብራለች፡፡ በእርግጥም የብዙ ሙያዎች ባለቤት መሆኗን አስመስክራለች፡፡
ቸር እንሠብት፡፡S
Art: አማኑኤል ይልማ –ከታዋቂ ድምፃዊያን ጀርባ ያለ ታላቅ የሙዚቃ ሰው
ዘርፈ ብዙ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ነው፡፡ የሙዚቃ አቀናባሪ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ፣ የሙዚቃ ፕሮዲውሰር፣ የቪዲዮ ክሊፕ ፕሮዲውሰርና የፊልም ተዋናይ! አማኑኤል ይልማ፡፡
ለጌዲዮን ዳንኤል፣ ኃይልዬ ታደሰ፣ ሸዋንዳኝ ኃይሉ፣ አለማየሁ ሂርጶ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ማዲንጎ አፈወርቅ፣ ብርሃኑ ተዘራ፣ ጸሐይ ዮሐንስ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ማቲያስ ተፈራ፣ ጥበቡ ወርቅዬ፣ ግርማ ተፈራ፣ አቦነሽ አድነው፣ ፋሲል ደመወዜና ሌሎችም በርካታ ድምፃዊያን በአልበማቸው ውስጥ በግጥም፣ በዜማና በቅንብር ተሳትፎ አለው፡፡ እንዲሁም የተለያዩ ድምፃዊያንን ሙሉ አልበም አቀናብሮ ፕሮዲውስ አድርጓል፡፡ በቅርቡ ‹‹ዜማ አማን›› በሚል ኃይለየሱስን፣ ትዕግስትን፣ ህብስትን፣ ብዙአየሁን፣ ግርማ ተፈራን፣ ገረመውንና ፀጋዘአብን ያካተተ ኮሌክሽን አልበምም በፕሮዲውሰርነት አቅርቧል፡፡ በሚዲያዎች ራሱን ለማስተዋወቅ እንብዛም ግድ የሌለውን አማኑኤል ይልማን አነጋግረነዋል፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ጊዜ የነበረውን በአል ለማክበር ከ50 በላይ ድምፃዊያን የተለያዩ ሙዚቃዎችን አውጥተው ነበር፡፡ ነገር ግን ከሁሉም ጎልተው የወጡት አንተ ያቀናበርካቸው የቴዲ አፍሮ ‹‹ጊዜ ለኩሉ›› እና የብርሃኑና ማዲንጎ ‹‹አንበሳው አገሳ›› ነበሩ፡፡ ያ እንዴት ሊሆን ቻለ?
አማኑኤል፡- እንዳልከው የ2000 በአልን ለማክበር ህዝቡን ለማንቀሳቀስ ብዙዎች ዘፈኖችን ሰርተዋል፡፡ በዚያ አጋጣሚ አንዱ ሆኜ እንደዜማ ደራሲና እንደ አቀናባሪ ተሳትፌ ነበር፡፡ ዕድለኛ ያደረገኝ እኔ የሰራሁት ዘፈን ህዝቡ የተቀበለው ሆነ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የቴዲ አፍሮ ‹‹ጊዜ ለኩሉ›› ወይም ‹‹አበባ አየህ ወይ›› የሚለው ዘፈን ሲሆን፣ ከዛ በመቀጠል ‹‹አንበሳው አገሳ›› የሚለው በብርሃኑ ተዘራና ማዲንጎ አፈወርቅ የተዜመው ነው፡፡ በጊዜው በታዋቂ ድምፃዊያን ጭምር የተሰሩ ብዙ ዘፈኖች ውድድሩ ውስጥ ነበሩ፡፡ ከእነዛ ውስጥ ግን በተለይ ‹‹አበባአየህ ወይ›› በአንድ ጊዜ ሒት ሆኖ ወጥቷል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የምነግርህ ያኔ ከቴዲ ጋር ብዙ አብረን ስንጓጓዝ ‹‹ቴዲ አትዘፍንም ወይ?›› እያሉ ይጠይቁት ነበርና በጣም የተጨነቀበት ወቅት ነበር፡፡ ምን ይዤ ልምጣ? ብሎ በተጨናነቀበት ወቅት ሌሎች ስራዎችን ስንሰራ ቆይተን አበባአየህ ወይን ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ነበር የጀመርነው፡፡ ወደ 11፡00 ሰዓት ላይ ጨረስነው፡፡ ከዚያ በኋላ ምንም ግጥም አልጨመረም፡፡ ድጋሚም አልዘፈነውም፡፡ አንዴ ስቱዲዮ ውስጥ የተሰራ ስራ ነው፡፡ ዜማና ግጥሙ የቴዲ አፍሮ ነው፡፡ ቅንብሩ ከእነሚክሲንጉና ማስተሪንጉ የእኔ ነው፡፡ ከዛ በኋላ የብርሃኑና የማዲንጎ ‹‹አንበሳው አገሳ›› ወጣ፡፡ (ዜማው የህዝብ፣ ግጥሙ የመሰለ ጌታሁን ሲሆን ቅንብሩ ሙሉ በሙሉ የእኔ ነው) ሁለቱም ላይ የሰቀሉ ዘፈኖች ነበሩ፡፡ እኔን የሚሊኒየሙ ዕድለኛ ያደረገኝ ሁለቱም ዘፈኖች ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር የምንሰማቸው ማለትም ድሮ ከነበሩት ከእነጥላሁን ገሠሠ፣ ከእነ ብዙነሽ በቀለ የአመት በአል ዘፈኖች ጋር በማይተናነስ መልኩ እየተሰሙ ዘመን ተሻጋሪነታቸውን በማስመስከራቸው ነው፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- በተለይ የቴዲ አፍሮን ‹‹ጊዜ ለኩሉ›› ቢዮንሴ አዲስ አበባ መጥታ በሰራችው ኮንሰርት መድረክ ላይ ተጫውተው ደንሳበታለች፡፡ ያ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ብታጫውተኝ?
አማኑኤል፡- በወቅቱ እኔም እዚያው ሚሌኒየም አዳራሽ ነበርኩ፡፡ እና ሰርፕራይዝ ያደረገች ጊዜ እንደማንኛውም አድማጭ ደንግጫለሁ፡፡ በጣም አሪፍ ነበር፡፡ ሙዚቃውን የመረጠችው ሳውንድ ማኗ ናት የሚል ነገር በኋላ ሰምቻለሁ፡፡ እርግጥም በዚያን ጊዜ የሳውንዱ ግሩቭ (Groove) በጣም ሒት ነበረ፡፡ ብዙ ጊዜ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እንደዚያ አይነት ሚክሲንግ አልተሰራም ነበር፡፡ በመሆኑም ሳውንድ ማኗ ወደደችው፡፡ በሳውንድ በኩል በጣም ብዙ የሚጠበቅብን ነገር ያለ ቢሆንም በወቅቱ ግን ያ ሳውንድ በቂ እንደነበረ አምናለሁ፡፡ በተጨማሪም ያን ጊዜ በመላው ኢትዮጵያ ይለቀቅ የነበረው ይህ ዘፈን ነበር፡፡ ህዝቡ ያብድበት የነበረ በመሆኑ የቴዲ አዘፋፈንም ምርጥ ስለነበረ መርጠውታል፡፡ በአጠቃላይ በዚያ የሚሌኒየም ወቅት ለቢዮንሴ ይመጥን የነበረ ሙዚቃ ስለሆነ ነው ብለን ብንወስደው ደስ ይለኛል፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- ብዙ ጊዜ በግጥምና ዜማ ስራዎችህ ላይ እውነተኛ ታሪኮችን ወደ ሙዚቃ እየቀየርክ እንደምታቀርብ ይሰማል፡፡ ይህን ስታይል የመረጥከው ለምንድን ነው?
አማኑኤል፡- ይሄን ጥያቄ ለመመለስ ትንሽ ወደኋላ መለስ ብዬ ልጀምርልህ፡፡ ከያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት የተመረቅኩበት መሳሪያ ደብል ቤዝ ይባላል፡፡ ፒያኖ ማይነሬ ሲሆን፣ በባህል መሳሪያ ማሲንቆን ተጫውቻለሁ፡፡ ማሲንቆ በጣም ዜመኛ ያደርጋል፡፡ ከዚያ ውጭ ደግሞ የአዝማሪ ግጥሞችን መስማት በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ረጅም ጊዜ እየሄድኩኝ የእነሱን ስራዎች እከታተላለሁ፡፡ አንድ የአዝማሪ ስራንም ፕሮዲውስ አድርጌያለሁ፡፡ እንደነዚህ አይነት በድሮ ጊዜ የሚሰሩ ነገሮች ሪያሊቲ አላቸው፡፡ ለምሳሌ ከድሮ ድምፃዊያን የማደንቀው የጋሽ ባህሩ ቀኜ ግጥሞችን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ‹‹አንጣላ›› ብሎ የሚዘፍን የለም፡፡
ልቤን ጅብ በበላው ባወጣው አጥንቱ፣
ተጣልቶ መታረቅ አይሆን እንደ ጥንቱ፡፡
የመሳሰሉ ግጥሞች ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ቀድመው የሚነግሩህ ናቸው፡፡ እንደዚህ አይነት ፍልስፍና ውስጥ ስትገባና ይህን እያዳበርከው ስትሄድ፣ ላይፍን ወደ ሙዚቃ አምጥተህ የሰውን ታሪክ ስትፅፍ ከዛ የበለጠ ቀድመህ ሁሉ መድሃኒት ታዘጋጃለህ፡፡ እኔ ደግሞ ፊት ለፊት ያሉኝን ችግሮች ወደ እውነተኛ ታሪክ ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ለምሳሌ በአንድ ዘመን እሰራቸው የነበሩት ስራዎች በአብዛኛው አፍቅሮ የተጎዳ ሰው ላይ ያመዝን ነበር፡፡ የተወሰኑትን ብጠቅስልህ ‹‹እንዳረከኝ አድርገኝ፣ ሳታመሀኝ ብላ፣ ኋላ እንዳይቆጭሽ፣ በአይኔ ላይ ዋልሽሳ በአይኔ፣ የማታ ማታ…›› ሌሎችም አሉ፡፡ በሴት ደግሞ የነፃነት አየለ ‹‹ላያገባኝ›› አለ፡፡ ማለትም እንዴት ይሄ ሁሉ ጊዜ አልፎና ዛሬ ከእኛ አልፎ ለሰው ተርፎ፣
ለካ ይሄን ሁሉ ጊዜ እያለፋኝ ነበረ ለካ
ሳያገባኝ እያለች የምትጫወተው ማለት ነው፡፡
ይህም አንዲት ሴት ረጅም ዓመት አንድ ወንድ ይዟት ሄዶ ጊዜዋን ሁሉ ገድሎ በመጨረሻ ሳያገባት ሲተዋት ያመላክታል፡፡ የብዙ ሴቶችን፣ ችግር ያሳየሁበት ነው፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- በጎሳዬ ተስፋዬ የተዘፈነውን ‹‹ሳታመሀኝ ብላ›› ግጥም የፃፍከው ከእውነተኛ በምታውቀው ሰው ላይ ከደረሰ አጋጣሚ ተነስተህ መሆኑም ይነገራል፡፡
አማኑኤል፡- ልክ ነህ፡፡ ‹‹ሳታመሀኝ ብላ›› ትልቅ ታሪክ ነው፡፡ በአንድ የቅርብ ጓደኛዬ የደረሰ ታሪክ ነው፡፡ አንድ ሰው የሚወደውን ጓደኛውን በምን መንገድ እንደሚያጣው፣ ሚስቱን ደግሞ በጓደኛው እንዴት እንደሚያጣ የሚገልፅ ነው፡፡ የክሊፑ አለመሰራት ዘፈኑን በውስጥ ደረጃ አስቀረው እንጂ ትልቅ ታሪክ ያለው ነው፡፡
የሚገርምህ ከዚህ ዘፈን ጋር በተያያዘ ብዙ ገጠመኝ አለኝ፡፡ ለምሳሌ ‹‹እንዴት ሰውን ጅብ ትላለህ?›› ያሉኝ ሰዎች ነበሩ፡፡ እኔ ግን ‹‹ጅብ›› ስል በልመናና በጨዋነት ነበረ የገለፅኩት፡፡
አንቺም ትዳሬ ነሽ እሱም ጓደኛዬ፣
ጥፋቱ የማን ይሆን ስሄድ አንችን ጥዬ፣
አወይ ክፉ ዘመን ልቤ አዘነብሽ
እሱም ተሳሳተ የእኔ እናት አንቺም አልታመንሽ
ታማኝ ያንቺ ገላ ያለኔም አያውቅም
ምነው ደከመሳ አነሰው ወይ አቅም
ስደተኛ ታርገኝ ደሞ ብላ ብላ
ጅብ ረሃብ አይችልም ብለህ ወንድሜ ሳታመሀኝ ብላ
አየህ ‹‹ወንድሜ›› ነው ያልኩት፡፡ ጭካኔ የለውም፣ ግን መልዕክቱ ሃያል ነው፡፡ በጓደኛዬ ላይ የደረሰው ህመም ነው ያንን እንድፅፈው ያደረገኝ፡፡ ብዙዎች ይህ የእኔ ስራ መሆኑን ሲያውቁ የኔ ታሪክ መስሏቸው ደውለው ሀዘናቸውን የገለፁልኝ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ‹‹የእኔን ታሪክ ነው የሰራህልኝ›› ያሉኝም አሉ፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- አንተ በጥሞና ዜማውን የሰራኸውና ኤፍሬም ታምሩ የተጫወተው ‹‹ኋላ እንዳይቆጭሽ›› ሙዚቃም እውነተኛ ታሪክ ነው አይደል?
አማኑኤል፡- ኋላ እንዳይቆጭሽ እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ የሰራሁት ስራ ነው፡፡ ታሪኩን በዝርዝር ባልነግርህም የዚያን ጊዜ የተፈጠሩት ‹‹ኋላ እንዳይቆጭሽ››፣ የጌዲዮን ዳንኤል ‹‹እንዳደረግከኝ አድርገኝ››፣ የፀሐዬ ዮሐንስ ‹‹ፍቅርሽ እንደ ጥላ፣ አንድ በይኝ…›› ወዘተ እውነተኛ ታሪክን መሰረት ያደረጉ ናቸው፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- አማን አንተ ሌላ የምትታወቅበት ‹‹ለታናሿ ልስጋ›› በሚለው የሙዚቃ ቪዲዮ ነው፡፡ ይህንን ቪዲዮ ግጥምና ዜማ ሰርተህ ከማቀናበርህም በላይ ራስህ ፕሮዲውስና ዳይሬክት አድርገህ ያቀረብከው መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ለመሆኑ ይህን ስራ ለማቅረብ እንዴት ተነሳሳህ? ከአድማጭ ያገኘኸው ምላሽስ?
አማኑኤል፡- የምር ለመናገር ደራሲ ስትሆን፣ በሰው ችግር ውስጥ ማለፍ ስትጀምር፣ ዘፈኖችን ወደ ሪያሊቲ ስታመጣና ወደ እውነተኛው በሄድክ ቁጥር አርቱም ይሳካልሃል፡፡ የምትፅፈው ነገር ይሳካል፡፡ ዳይሬክት የምታደርገው ነገር ሁሉም ወደ እውነት ይቀርብልሃል፡፡ ከቅንነት ከተነሳህ ማለት ነው፡፡ እና የሚገርምህ ነገር በቡና ቤት ሴቶች ላይ፣ በጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ፣ በአላቻ ጋብቻ ላይ እንደዚህ አይነት ነገሮችን ለመስራት እያሰብኩ ባለሁበት ሰዓት ወደ ገጠር ውስጥ እየሄድኩ፣ በቀንም በማታም ያለውን ሁሉ እያየሁ እየቀረብኩ እፅፍ ነበር፡፡ እና በዚህን ወቅት አንዲት ልጅ በጣም አዝና አየሁኝ፡፡ ያቺ ልጅ በሀዘን አገጯን የያዘች፣ ከንፈሯ የሚንቀጠቀጥ፣ እንባ ያቀረረችና ደንግጣ የተቀመጠች ነበረች፡፡ እኔም የፃፍኩት ያንኑ ነው፡፡ ግጥሙንም ስፅፈው፤-
እንባ አዝሎብኝ አይኖቿ፣
መዳፏ አልፎ ከጉንጮቿ
እንባዋ ይፈሳል ሳያባራ
ብቻውን ያወራል ከንፈሯ
እያልኩ ጀመርኩት፡፡ ከዚያ ይህችን ህፃን ሊድሯት፣ ቤተሰቦቿም ፈረዱባት፣ እያልኩ ዘፈኑን እየሰራሁት ይህን ዘፈን በደንብ ሊጫወተው የሚችለው ማነው? የሚለው ውሳኔ የኔ ነበር፡፡ ጎሳዬን መረጥኩት፡፡ እንደውም ለጎሳዬ ክፍያ ስከፍለው ‹‹እንዴት እንደዚህ አይነት አይዲያ?›› ሲለኝ ግድየለህም ብዬ አስጀመርኩት፡፡ ከዚያ ቡሬ አንድ ጥጃ አጠገቧ ስለነበረች ‹‹ቡሬ ቡሬ ቀናችን አይደለም እኔና አንቺ ዛሬ፣ አለጊዜው ታርደሽ አለጊዜው ተድሬ›› የሚለው በመስታወት አራጋው ተቀረፀ፡፡ ታገል ሰይፉም ገባበት፡፡ በእንደዚህ አይነት ተቀረፀ፡፡ ዘፈኑን ከቀረፅን በኋላ የዚህን እውነተኛ ታሪክ ሰው ጭፈራ ይመስለዋል፡፡ ምክንያቱም ሲሰማው እንደዘፈን የሚያደምጠው ነው፡፡ ስለዚህ ክሊፑን በመስራት መልዕክቱን ህዝቡ እንዲረዳው ማድረግ ያስፈልግ ነበር፡፡ የዚህንም ሪስክ ወስጄ ወደ 50 ሺ ብር በማውጣት ክሊፑን አሰርቼዋለሁ፡፡ እዛ ውስጥ ያለ ሁሉ ድምፃዊ፣ አንባቢ ተከፍሎታል፡፡ ይሄ ሁሉ አልፎ እስካሁን ከሰራኋቸው በርካታ ስራዎችና ሙዚቃዎች በላይ በየሄድኩበት ዓለም ሁሉ ‹‹ለታናሿ ልስጋ›› ነው የሚሉኝ፡፡ ምክንያቱም በህዝብ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት ያገኘሁበት በዚህ ስራ ነው፡፡ እንደምታውቀው የአላቻ ጋብቻን በተመለከተ ብዙ ወረቀቶች፣ ብዙ ወርክሾፖች፣ ብዙ ስብሰባዎች ተደርገዋል፡፡ ግን በሰባት ደቂቃ አንድ የሙዚቃ ክሊፕ ብዙ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መሆኑን ብዙዎች መስክረውለታል፡፡ ሰውን እያዝናና ለቀጣዩዋ ለታናሿ ደግሞ ይታሰብበት በሚል መንገድ የቀረበ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓም፣ በአሜሪካም፣ በካናዳም አውስትራሊያም፣ አረብ አገር ጭምር ያሉት የወደዱትና እንዲዘፈን ደጋግመው ያዩት ክሊፕ ሊሆን ችሏል፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- በቅርቡም ሌላ ይህን መሰል ክሊፕም ሰርተሃል? ይህኛውስ?
አማኑኤል፡- አዎ፣ በቅርብ ጊዜ ድጋሚ ከጎሳዬ ጋር ሰርቻለሁ፡፡ ያቀናበረው አበጋዝ ነው፡፡ ግን ዜማውም ግጥሙም የእኔ ነው፡፡ ‹‹ፍጥረትን እንደቀላል›› የሚል ነው፡፡ ይህኛው ደግሞ ህፃናቶችን ብዙ ጊዜ ከገጠር እያመጡ ዘመድ ጋ ይቀመጡ በሚልና በተለያየ መንገድ በማምጣት ትልልቅ ስራ ከአቅማቸው በላይ ያሰሯቸዋል፡፡ እኔም የሰራሁት ያንን በመቃወም ነው፡፡ ይህም ስራ አስተማሪ፣ ትልቅ ተቀባይነት ያገኘና ማህበረሰቡን የሚነካ፣ ለውጥና ዕድገትን የሚያመጣ የህፃናትን ኃላፊነት እኛ መውሰድ እንዳለብን የሚያስገንዘብ ሆኗል፡፡ እንደ አጋጣሚ ይህን ያሰራኝ አንድ ድርጅት ነው፡፡ ለታናሿ ልስጋን አይተው በዚያ መንገድ እንዲሰራላቸው ፈልገው ጠይቀውኝ ቦታው ድረስ ሄጄ፣ እንዴት ሽመና እንደሚያሸምኗቸው እህል እንዴት እንደሚያስፈጯቸው ከባባድ ስራ ሲያሰሯቸው አይቼ በጣምም እንዳይከፉ አድርጌ ቀለል አድርጌ የሰራሁት ነው፡፡ ግን ያለው ሁኔታ በዚህ መንገድ ብቻ የሚገለፅ ሳይሆን ሁለትና ሶስት እጥፍ የበለጠ መገለፅ የሚችል ነው፡፡ እኔ ግን የማምነው ማንኛውንም አይነት ችግር ነገሮችን በማቅለል ማህበረሰቡ በሚረዳበት መንገድ ማስተማርና ማዝናናት እንዳለብን ነው፡፡ በመሆኑም ያቀረብኩት በዚህ ሁኔታ ነው፡፡ ከሁለቱ ስራዎቼ በተጨማሪ በቀጣይነት እንደዚህ አይነት ስራዎችን ማለትም ማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር እየፈለፈልኩ የማውጣት አቋም አለኝ፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- እስቲ ስለዜማ ላሰታስ ባንድስ እናውራ፡፡ እንዴት ተቋቋመ? እንዴትስ ሊፈርስ ቻለ?
አማኑኤል፡- እኔ ዜማ ላስታስ ባንድ ለሙዚቃ ዕድገት አንድ መሰረት ነው ብዬ የማምንበት ነው፡፡ ከያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት የተመረቅን ልጆች ማለትም ኤልያስ መልካ፣ ሁንአንተ ሙሉ፣ ሚካኤል መላኩ፣ ምስጋናውና እኔ ሆነን ያቋቋምነው ሲሆን፣ ስንጀምር ድምፃዊዎች ትዕግስት በቀለ፣ ሚካኤል በላይነህ፣ እዮብ መኮንን፣ ኃይሌ ሩትስ ባንዱ ውስጥ ነበሩ፡፡ ባንዱ ትልቅ የሳውንድ ለውጥ ይዞ የመጣና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነበር፡፡ ባንዱ ሊፈርስበት የቻለው ዋንኛ ምክንያት ሁላችንም ወደየስራችን ስቱዲዮ መበታተናችን ነው፡፡ መጀመሪያ ኤልያስ መልካ፣ ቀድሞን የራሱን ስቱዲዮ ሲከፍት ሁንአንተ ተከተለው፡፡ ከዚያ እኔም ወደ ስቱዲዮ ገባሁ፡፡ ከዚያ የየራሳችንን የስቱዲዮ ስራ ስንሰራ ወደ ባንዱ ለመስራት ስላልቻልን ሊፈርስ ችሏል፡፡ ይሁንና ባንዱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዓለማየሁ እሸቴ፣ የባህት ገ/ህይወት፣ የፍቅር አዲስና የመሳሰሉትን የድሮ ሙዚቃዎች አምጥተን በጥሩ ሁኔታ ቀርፀን ሰው በሚገርም ሁኔታ ተቀብሎታል፡፡ በዚያ ሳውንድም ባንዱ በጣም አሪፍ ከሚባሉት ባንዶች ስሙን አስቀምጦ ለማለፍ ችሏል፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- አንተ በሙዚቃ ስራ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ለመዞር የቻልክ ነህ፡፡ የአቡጊዳ ባንድ ውስጥ ተካተህም ከቴዲ አፍሮ ጋር ብዙ መድረኮች ላይ መስራትህን አውቃለሁ፡፡ የሙዚቃ ጉዞህን በተመለከተ እናውራ?
አማኑኤል፡- የሚገርምህ ከታዋቂ ድምፃዊያን ጋር ወደ ውጭ አገራት ከመሄዴ በፊት ከያሬድ ት/ቤት እንደተመርቅኩኝ አንድ ‹‹ፎርኤቨር ያንግ›› የሚል የባህል ቡድን አቋቁሜ ነበር፡፡ ከዚያ ቡድን ጋር ሀኖቨር የባህል ኤክስፖ በተዘጋጀበት ወቅት ከዛሬ 13 ዓመት በፊት በመሄድ ጀምረን በተከታታይ ለአንድ 6 ዓመታት የተለያዩ ቦታዎች ሰርተናል፡፡ ከዚያ ስቱዲዮ ከመግባቴ በፊት ከእነፍቅር አዲስ፣ ኃይልዬ፣ ይርዳው፣ ህብስት ቴዲ አፍሮን ጨምሮ ራሴ ፕሮሞተር እየሆንኩኝ ከአገር ውስጥ እስከ አረብ አገሮች እሰራ ነበር፡፡ የመጨረሻ ጉዞዬን ያደረግኩት ደግሞ ከቴዲ አፍሮ አቡጊዳ ባንድ ጋር በመቀላቀል ነው፡፡ ከአቡጊዳ ጋር ከ24 ሾው በላይ ሰርቻለሁ፡፡ ይህም በመላ አውሮፓ፣ አረብ አገራት፣ እንዲሁም አሜሪካና ካናዳ ዞሬያለሁ፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- ምንም አልበም ሳይኖረው በመላው ዓለም ታዋቂ ለመሆን የበቃው ጃኪ ጎሲ (ጎሳዬ ቀለሙ) ከዚህ ቀደም በዚሁ ዘ-ሃበሻ ጋዜጣ ቃለ ምልልስ ሲያደርግ አንተን አመስግኗል፡፡ ከስኬቱ በስተጀርባ ያለህ ቁልፍ ሰው መሆንህንም ተናግሯል፡፡ ለመሆኑ ከጃኪ ጋር የነበራችሁ የስራ ግንኙነት ምን ይመስላል?
አማኑኤል፡- ጃክ ከጥቂት ዓመታት በፊት እኔ ጋር ሊሰራ በአጋጣሚ ወደ ስቱዲዮ መጥቶ ነበር፡፡ ይዞት የመጣው ስታይልም ትንሽ ወጣ የሚል ነው፡፡ ማለት ከአማርኛ ሙዚቃዎች ወጣ ያለና እንደ ሒፕ ሆፕ አይነት ነገር ነበር፡፡ እና የሒፕ ሆፕ ስታይሉን በሚያሰማኝ ጊዜ ልጁ አንድ ቃናና በጣም የሚገርም ድምፅ እንዳለው ተረዳሁ፡፡ ይሄን ድምፁን ደግሞ በእርግጠኝነት የሌላ ዜማ ስታይል ቢሰራበት ጥሩ ይሆናል በሚል ትንሽ ደቂቃ ተነጋገርን፡፡ ልጁም ጥሩና ቅን ስለሆነ ወዲያው ተመለሰ፡፡ ምክንያቱም የዜማ ደራሲ ስትሆን የመጀመሪያው ነገርህ ሰው መፍጠር ነው፡፡ አንድን ድምፃዊ አምጥቶ መስራት እንደማለት ነው፡፡ እንደፊልም ለዚህ ተዋናይ ይህን ካራክተር ብሰጠው ይዋጣለታል ብሎ መቅረፅ ነው፡፡ ስለዚህ በዚያ መንገድ የመጀመሪያውን ‹‹ጭራሽ›› የሚለውን ሰራሁለትና ይዞት ወደ አገሩ ሄደ፡፡ እዛ ከለቀቀ በኋላ አቀባበሉ የሚገርም ሆነ፡፡ እኔ መልዕክቱንም ስፅፈው ውጭ አገር ስላሉ ሰዎች በመለያየትና በመነፋፈቅ ውስጥ እንዴት እንደሚተሳሰቡ በሚያደርግ ስሜት ነበር፡፡ በመሆኑም ውጭ አገር ያሉ ሰዎች በጠቅላላ ወደዱት፡፡ ከዚያ ከስድስት ወር በኋላ ደወለልኝና ‹‹ዘፈኑ በጣም ቡም ብሏል›› አለኝ፡፡ አላመንኩም፡፡ ‹‹እውነትህን ነው?›› አልኩና ዩቲዩብ ላይ ሳየው ደነገጥኩኝ፡፡ የሚገርምህ ወደ 2 ሚሊዮን 800 ሺ ህዝብ አይቶለታል፡፡ በደወለልኝ ጊዜ ሌላ ዘፈን እንዳዘጋጅለት በጠየቀኝ መሰረት ‹‹ደሞ አፌን›› ሰራሁለት፡፡ የመጀመሪያው የባህል ዘመናዊ ሲሆን ይህ ግን ችክችካ አይነት ለመድረክ የሚሆን ነው፡፡ ከዚያ፣ በየኮንሰርቶች ተመራጭ ለመሆንና ለመስቀል ቻለ፡፡ ቀጥሎ ‹‹ሰላ በይ›› የሚለውን በሌላ ስቱዲዮ መጥቶ ሰራው፡፡ እሱም ውጤታማ ሆነለት፡፡ ይሄ ልጅ የተሾመ አሰግድን ‹‹የእኔ አካል›› የሚለውን ድጋሚ በመዝፈን አንድ ዘፈን ጨምሮ በአራት ዘፈን በዓለም ላይ እየተዘዋወረ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
እኔ ለጃክ የመጀመሪያውን ሙዚቃ ግጥምም ዜማም ቅንብርም ስለሰራሁለት ሊያመሰግነኝ ቢችልም፣ እኔ ደግሞ በጣም ብልህ ልጅ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ለምን ብትል በደራሲ ያምናል፡፡ የድሮዎቹን ትልቅ ደረጃ የደረሱት እነ ኤፍሬም ታምሩን ብትመለከት ለረጅም ጊዜ የሰሩት ደራሲዎችን ይዘው በመምጣታቸው ነው፡፡ ልጁ በዚሁ ከቀጠለ ታዋቂዎቹ የደረሱበት ቦታ የማይደርስበት መንገድ የለም፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- ብዙውን ጊዜ የድሮ ድምፃዊያንን በተለያዩ መንገዶች ታነሳለህ፡፡ ለምንድን ነው?
አማኑኤል፡- ያለጥርጥር እኔ የድሮዎቹ ድምፃዊያን አድናቂ ነኝ፡፡ ከ50ዎቹ ጀምሮ የነበሩት በተለይ ባህሩ ቀኜ፣ አሰፋ አባተ፣ ወደዚህ ስትመጣ ጋሽ ይርጋ ዱባለ በጣም ድምፃዊ ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜ የሚያገኙት ግጥምም ሆነ ዜማ ያስገርመኝ ነበር፡፡ በተለይ ጋሽ ባህሩ የሚፈጥረው ዜማና ግጥም በጣም ለኢትዮጵያ ሙዚቃ መሰረት የነበረና ለረጅም ዓመት የተደመጠ ነው፡፡ ወደዚህ ስንመጣ ደግሞ የእነ ጥላሁን፣ የእነ ብዙነሽ፣ የእነ ሒሩት ዘመን አለ፡፡ ሲቀጥል ሮሀ ባንድ፣ በ70ዎቹ እነ ኤፍሬም ታምሩ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ አስቴር አወቀ እያልን መዘርዘር እንችላለን፡፡ እነዚህ ሰዎች ሙዚቃን ለ40 እና 30 ዓመታት ያሻገሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ እንደቀላል አይታዩም፡፡ አሁን የእኛ አገር ሙዚቃዎች ለሶስትና ለአራት ወር ተሰምተው ሲቆዩ እንደትልቅ ነገር የምናይበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ስለዚህ እኔ የዚያን ጊዜ ሰዎች በምን መንገድ ቢሰሩት ነው ቴክኖሎጂ በሌለበት ሰዓት፣ በአናሎግ ሲስተም እየቀዱ፣ ኮምፒውተር ሳያግዛቸው፣ ላይቭ እየቀዱ፣ ወጣቱ በእነሱ ዘፈን እየተማረከ እኛ እንዴት እንደነሱ መስራት አቃተን? የሚሉ ጥያቄዎች ስላሉኝ ያኛው ትውልድ ይበልጥብኛል፡፡ ይሄ የእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የአድማጭ፣ የህዝብና የአርቲስቱ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- የዚህ መፍትሄው ምንድን ነው ትላለህ?
አማኑኤል፡- አንደኛው ነገር ራሳችንን እየሆንን አይደለንም፡፡ ራሳችንን መሆን መቻል አለብን፡፡ ሁሉም በየፊናው የተለያየውን ዓለም ሙዚቃ ይሰራል፡፡ አይስራ አልምም፡፡ በስታይሉ ውስጥ ደግሞ ስራውን በማቅለል ደረጃ በአንድ ሞኖ ስቱዲዮ (ሆም ስቱዲዮ) ውስጥ በመሰራቱ አንድ ሰው ሙዚቃውን እንደፈለገው ማድረግ ጀመረ፡፡ ድምፃዊያኑም ስለቀለለው ገባ፡፡ መአት ድምፃዊያን ተፈጠሩ፡፡ ግን ከዚያ ውስጥ ምን ያህሉ ድምፃዊ ነው? ብለህ ብታስብ ሁሉም አይደሉም፡፡ ስለዚህ ህዝቡንም አሰለቸነው፡፡
እኛ የእኛነት የምትለው ነገር የለም፡፡ ሬጌው ምን ያህል በኢትዮጵያ ሄዷል? ብትል የለም ገና መጀመሩ ነው፡፡ ሒፕ ሆፕ አለ ወይ? ብትል ሒፕ ሆፕ የሚባል ሙዚቃ የት አለ? ሌላው ዓለም መጥቶ ሲሰማን በጣም ያዝንብናል፡፡ በየስቱዲዮው ነጮቹ ጥቁሮቹ መጥተው አይተው የተሰማቸውን ስሜት አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በዚህ ትውልድም እንደድሮው የራሳቸውን ቀለም ይዘው መስራት እንዳለባቸው ይሰማኛል፡፡ ኢንዱስትሪው እንዲያድግና አድማጭ እንዲሰማን ከፈለግን ጥሩ ዜማ፣ ለግጥሙም መጨነቅ፣ ለአሬንጅመንቱም መጨነቅና ጥሩ ድምፃዊም መስራት ያስፈልገናል፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- የሙዚቃ አቀናባሪ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ፣ የሙዚቃ ቪዲዮ ክሊፕ ዳይሬክተር ፕሮዲውሰር ስለመሆንህ እስካሁን በነበረን ቆይታችን ስናወራ ቆይተናል፡፡ አሁን ደግሞ በፊልሙ ዓለም ስላለህ ተሳትፎ እናውራ፡፡ እንችላለን?
አማኑኤል፡- ይቻላል፡፡ ስለፊልም ካነሳን የመጀመሪያው ‹‹የማያልቀው መንገድ›› ነው፡፡ እንኳን እኔ ኢትዮጵያ ውስጥም ፊልም ገና እየገባ በነበረበት ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ነበረ፡፡ የያኔው ከነበረው ሁኔታ አንፃር ጥሩ ነው፡፡ ወደ አሁኑ ዘመን ስንመጣ ‹‹ፔንዱለም›› እና ‹‹ከመጠን በላይ›› የሚሉ ፊልሞች ላይ ሰርቻለሁ፡፡
የፔንዱለም ፕሮዲውሰር ቶማስ ጠርቶ ሲፈትነኝ ሌሎች ዳይሬክተሮችም ይዞ ነበር፡፡ ከተፈተንኩ በኋላ የተቀረፅኩትን በቪዲዮ ስመለከተው እውነቴን ነው የምልህ ጠላሁት፡፡ እናም ‹‹እኔ መግባት የለብኝም፡፡ እኔ አልሆናችሁም›› አልኳቸው፡፡ ግን ዳይሬክተሩ ለዚህ ቦታ አማን ይሆናል ብሎ ከወሰነ ሪስኩን ይወስዳል፡፡ ስለዚህም ‹‹ይህን ልጅ እለውጠዋለሁ፣ በዚህ አይነት ፎርም አመጣዋለሁ›› ብሎ ስላሰበ ዳይሬክተሩንም አምኜ ገባሁበት፡፡ እውር አሞራ እንደማለት ነው የማታውቀው ነገር ውስጥ መግባት፡፡ በዚህ መንገድ ሰራሁ፡፡ ፊልሙ እስኪያልቅ ድረስ ስቱዲዮ ዘግቼ ነው የሰራሁት፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- የፔንዱለም ፊልም ምርቃት ከተማውን ሁሉ በነቀነቀ ሁኔታ ነበር የተከናወነው፡፡ በዚህ ረገድ የአንተም ወሳኝ ድርሻ እንደነበረበት ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?
አማኑኤል፡- ፊልሙ ከተጠናቀቀ በኋላ በአንዳንድ ቦታዎች ማስታወቂያውን ሰማሁ፡፡ ያኔ ለፕሮዲውሰሩ ቶም ደወልኩለትና መተዋወቅ ያለበት በዚህ አይነት መንገድ አይደለም አልኩት፡፡ ምክንያቱም እንደ አበባዮሽ አይነት እን ደጃኪ አይነት ስዎች ጎልተው ሲወጡ ደስ ይለኛል፡፡ ዘፈን ከተሰራ ጎልቶ መውጣት አለበት፡፡ ፊልምም ቢሆን እንደዚያው ነው፡፡ ስለዚህ የሚዲያውን ስራ ሁሉ ጠቅልዬ ያዝኩት፡፡ እንደውም የማልረሳው ለሳውንድ ትራኩ ብዙአየሁ ብዙ ብር ጠየቀ፡፡ እኔ ‹‹በቃ ራሴ እገዘዋለሁ›› ብዬ አሰራሁትና ጨርሼ ቶምን ሰራሁት፡፡ ቶምም ሲሰማው ዘፈኑን ሳላጋንን ከ30 ጊዜ በላይ ቆሞ ሰማው፡፡ ፊልሙን ግልፅ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ ዘፈን ይሄን ያህል ፓወር አለው ወይ? ብሎ ደነገጠ፡፡ ከዚያ ተጀመረ፡፡ ቶም ሁሉንም ወጪ አወጣለሁ በማለቱ ወደ ሚዲያ መጥተን ሬዲዮኑን ተቆጣጠርነው፣ ጋዜጦችን ተቆጣጠርን፡፡ ቀጥሎ የሚሊኒየም አዳራሽ ሀሳብ መጣ፡፡ ቀይ ምንጣፍ ታሰበ፡፡ እኔ ወደ ባንድ መጣሁኝ፡፡ ሔለን በርሄ ገባች፡፡ በዚህ ጊዜ ሰዎችን ሳማክር ‹‹እናንተ እብድ ናችሁ ወይ፤ እንዴት ዘፈንና ፊልም አንድ ላይ ይታያል? በዚያ ላይ ሚሊኒየም አዳራሽ›› ብለው አልተቀበሉኝም ነበር፡፡ ግን ነገሮችን ትልቅም ትንሽም የምታደርገው አንተ ነህና በውጥናችን ገፍተንበት በስተመጨረሻ 14 ሺ ሰው መጥቶ ፊልሙን ሊያየው ችሏል፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- ለዚሁ ፊልም ማጀቢያነት ሔለን በርሔ የተጫወተችውን ሙዚቃ በግጥምም በዜማም በማቀናበርም ሰርተሀል፡፡ ይሄ ሙዚቃዋ ደግሞ ከፊልሙም በኋላ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲደመጥ ይታያል፡፡ ሙዚቃውን ስታዘጋጅላት ከፊልሙም ውጭ ይደመጣል ብለህ አስበህ ነበር?
አማኑኤል፡- ይኸውልህ አንድ ምሳሌ ልንገርህ፡፡ ‹‹ለካ ለካ ያንተ ዓለም፣ ወዲህ ወዲያ ፔንዱለም›› የምትለዋ የዘፈኑ ግጥም ኤዲት ሲደረግ ነበርኩኝ፡፡ እና ያኔ ‹‹በናታችሁ ልብስ ስለካ እዚህች ቦታ አስገቡኝ›› አልኩ፡፡ ፊልሙ ላይ የምሰራው ልብስ ሰፊ ሆኜ ነው፡፡ እና ለካ፣ ለካ ማለት ልብሱን ለካ እንደማለት ነው፡፡ በፊልሙ ላይ ግን ዝም ብለህ ፊልሙን ባታየውም ደግሞ ‹‹ለካ ከእኔ ጋር አልነበርክም›› የሚል ትርጉም ይሰጥሃል፡፡ የውጪዎቹን ስራዎች እያደነቅንና የእነሱን ተሞክሮ እየቀሰምን መሄድ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ታይታኒክ ፊልም ለእኔ ምርጥ ፊልም ነው፡፡ የፊልሙን ማጀቢያ ሙዚቃ የሰራችው ሴሊንዲዮን ናት፡፡ ይህ ማጀቢያ ሲሰራ ስሎው ነው፡፡ ከፊልሙ ጋር ልክክ ብሎ ገብቶ እንዳትወጣ አድርጎ ዘፈኑን በሰማህ ቁጥር ብዙ የፍቅር ትውስታ እንዲኖርህ ያስችላል፡፡ ይሄ ዘፈን ቴክኖና ሐውስ ሆኖ ወጥቷል፡፡ ወደ ጭፈራ ዘይቤ ሆኖ ቀርቧል፡፡ እኔ የሄለን በርሔንም ሙዚቃ እኔ አንዳንዴ ሲጨፍሩበት አያለሁ፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ይሄ ከፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው መነሳሳትን የሚፈጥር ይመስለኛል፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- ከሰሞኑ ‹‹ዜማ አማን›› በሚል ርዕስ አዲስ አልበም በፕሮዲውሰርነት አቅርበሃል፡፡ በዚህ አልበምህ ካመጣኸው ድምፃዊያን ኃይለየሱስ አንዱ ነው፡፡ ኃይለየሱስ ከሙዚቃው አካባቢ ጠፍቶ ነበርና የት አገኘኸው?
አማኑኤል፡- የኃይለየሱስ ነገር እንደማንኛውም አድማጭ እኔንም ይቆጨኝ ነበር፡፡ ተማሪ ሆኜ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት እያለሁ እሱን ለማየት ለመስማት ስል ኤግዚቢሽን ማዕከል ድረስ እሄድ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ያንን የመሰለ ድምፅ ይዞ ጠፋ፡፡
‹‹ይለፍ ዕድሜ፣ አንችን ስል ቆሜ›› የሚለው ወረድ ብሎ ጀምሮ በኋላ ላይ በጣም ከፍ የሚል ነው፡፡ ሀይለየሱስን ውስጤ ሁሌም ስለሚያስበው በቀጥታ እሱ ነው ይህን የሚዘፍነው ብዬ ወስኜ ደወልኩለት፡፡ እሱም ለረጅም ጊዜ ይፈልገኝ ነበርና ተነጋገርን፡፡ ዘፈኑን ሰጠሁት፡፡ በአጭር ጊዜ ይዞት ሰራው፡፡ አድማጭም በጣም የእሱን ዘፈን ወዶታል፡፡ ኃይለየሱስ የሚገርም ድምፃዊ ሲሆን፣ አብሬው በመስራቴ ደስተኛ ነኝ፡፡
ዘ-ሃበሻ፡- በአልበምህ የተካተቱት ድምፃዊያን በአሜሪካና በኢትዮጵያ የሚኖሩ ናቸውና እነሱን ማሰባሰቡና መጠበቁ አላስቸገረህም?
አማኑኤል፡- በጣም ተስፋ የሚያስቆርጥ ደረጃ ያደርሳል፡፡ አንዳንዴ ምን ውስጥ ነው የገባሁት? እስከማለት ደርሼ ነበር፡፡ ሙዚቃ ግን ከገባህበት አይለቅህም፡፡ አንዳንዴ ፈተና ቢበዛብ ህም በእልህ ተስፋን ሰንቄ ለአድማጭ ላበቃው ችያለሁ፡፡ ወደ አምስት ዓመት ያህል የፈጀብኝም ለዚህ ነበር፡፡S