(ዘ-ሐበሻ) ማክሰኞ ማርች 13 ቀን 2013 ዓ.ም ዘ-ሐበሻ አዲስ አድማስ ጋዜጣን ጠቅሳ “አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ በአስገድዶ መድፈር አቤቱታ ቀረበበት” የሚል ዜና አቅርባ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በዚህ ልማታዊ አርቲስት ላይ የቀረበው ክስ አርቲስቱ ከስርዓቱ ጋር ባለው የጠበቀ ወዳጅነት የተነሳ ተድበስብሶ እንዲያልፍ መደረጉን የቅርብ ምንጮች ለዘ-ሐበሻ ገለጹ።
አንድ ሰው በተለይም ሴት ልጅ በሙያዋ ካለምንም አድልዎ እና ካለምንም የጾታዊ ግንኙነት ሙስና የመሥራት መብቷ የተጠበቀ ቢሆንም አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬ ግን ያለውን እውቅና በመጠቀም ሴትን ልጅ ጾታዊ ግንኙነት ለሥራ ማስገኛ መደለያ ተጠቅሟል በሚል በአንዲት ሴት አቤቱታ እንደቀረበበት ይታወሳል። በወቅቱ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ሁኔታውን ሲዘግብ የሠራዊት መልቲ ሚዲያ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ሠራዊት ፍቅሬ ላይ አንዲት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ለፖሊስ አቤቱታ ማቅረቧን የሚናገሩ ምንጮች፣ ባለፈው ቅዳሜ “ለማስታወቂያ ስራ እፈልግሻለሁ” ብሎ ፒያሳ አካባቢ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ለመሳምና ለማሻሸት ሲሞክር አመለጥኩ” የሚል ነው ብሎ እንደነበር ይታወሳል።
ሠራዊት በወቅቱ ጉዳዩን እንዳልፈጸመ የተናገረ ቢሆንም ልጅቷ ለፖሊስ አቤቱታ ብታቀርብም ጉዳዩ ተድበስብሶ እንዲያልፍ መደረጉን ብዙዎች በትዝብት ተመልክተውታል። በወያኔ ሥርዓት ናፋቂዎች የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ጉዳይ የዚህችን ወጣት አቤቱታ ሠራዊት ለስርዓቱ ባለው ተላላኪነት የተነሳ አንዳችም የሆነ ትኩረት ያልሰጠውና ክትትልም ያላደረገበት መሆኑ ያሳዘናቸው የቅርብ ምንጮች የመንግስት ሕግ አስከባሪዎችም ከበላይ በተለይም ከአቶ በረከት ስምዖን በመጣ ትዕዛዝ የሠራዊት የአስገድዶ መድፈር ክስ ተድበስብሶ እንዲያልፍ መደረጉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል የሚሰሩ የሥርዓቱ ተላላኪዎች በሕግ የሚጠየቁበት ሁኔታ በጣም አናሳ መሆኑና ለክስ የሚቀርቡትም ከሥርዓቱ ጋር ሲጣሉ መሆኑ ከዚህ በፊት የታዩ በመሆናቸው የሃገሪቱን የሕግ ሥርዓት ዘወትር እንዲወቀስ ያደርገዋል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች በርካታ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በርከት ያሉ የማስታወቂያ ሠራተኞች እና ፊልም እና ድራማ የሚያሰሩ አርቲስቶች ለትወና የሚመርጧቸውን ሴቶች ቅድሚያ ወሲብን እንጅ መንሻ እንደሚጠይቁ፤ ይህን የማያሟሉ ሴቶች ግን ብቃቱ እያላቸውም ቢሆን ለፕሮጀክቱ ብቁ እንደማይሆኑ በተደጋጋሚ መነገሩ አይዘነጋም።