Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Entertainment
Viewing all articles
Browse latest Browse all 261

(አሁንም ስለአነጋጋሪው የጥላሁን መጽሐፍ) ሁለት ማንነት በአንድ ራስ –ጥላሁን ገሠሠ የሙዚቃው ንጉሥ

$
0
0

tilahun

ርዕስ፡ ጥላሁን ገሠሠ የሕይወቱ ታሪክ እና ምሥጢር
ጸሐፊ፡ ዘከሪያ መሐመድ

ሲሳይ ጫንያለው እንዳነበበው


የመጀመሪያ ስሜት እንደመንደርደሪያ “እንዲህ ካለ መራራ የሕይወት ገጽ ውስጥ ኮኮብ ሆኖ መፈጠር ፤ ንጉሥ ተብሎ መዘከር እንደምን ይቻላል?” የሚለው ጥያቄ አዕምሮዬ ውስጥ ብቅ ያለው የጥላሁን ገሠሠን የሕይወት ታሪክና ምሥጢር የሚተርከውን የዘከሪያ መሐመድ መጽሐፍ ካነበብኩ በኋላ ነው፡፡ ከጨቅላ ዕድሜው አንስቶ የሐዘን አንቀልባ እንዳዘለ ሃምሳ አመታትን በኢትዮጵያ ኪነት ውስጥ በክብር ለኖረ ሰው 69 ዓመት ትንሽ ዕድሜ ነው፡፡ ኅልፈተ ሕይወቱ በሚዲያ ሲነገር አገር በዕንባ ታጥቧል፡፡ ያኔ እኔም እርሜን አውጥቻለሁ፡፡ ከስድስት ዓመታት በኋላ የጥላሁንን ሁለት የማንነት ገጾች በፍካሬ ለማሳየት የተጋውን የዘከሪያን መጽሀፍ ሳነብ ደግሞ በስኬቱ ተገርሜ በስቃዩ ታምሜያለሁ፡፡

ጋሽ ጥላሁን የምር አሳዝኖኛል፡፡

በገጾቹ ምን ይዟል?

“ጥላሁን ገሠሠ የሕይወቱ ታሪክና ምስጢር” በዘከሪያ መሐመድ ተጽፎ ለንባብ
የበቃ አነጋጋሪ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ነው፡
፡ መጽሐፉ አቶ ፈይሳ ኃይሌ ሀሠና የተባሉ የጥላሁን ቅርብ የስጋ ዘመድ ከ1934 ጀምሮ ያሰፈሩትን የቤተሰብ ማስታወሻ ቀዳሚ የመረጃ ምንጩ አድርጓል፡፡ ጸሐፊው የትውልድ ሥፍራው ሶየማ ድረስ ተጉዞ የባለታሪኩን ዘመድ አዝማዶች ፣ አብሮ አደጎች እና ጎረቤቶች ቃለ መጠይቅ በማድረግ መረጃዎቹን አጠናክሯል፡፡ በተጨማሪም የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው እና የህትመት ሚዲያው ስለ ጋሽ ጥላሁን የዘገቡትን ፣ በሙዚቃው ንጉሥ ሕይወት ውስጥ የነበሩ ሌሎች ግለሰቦች የነገሩትን በመተንተንና በመፈከር በአራት ክፍሎች እና በሃያ ዘጠኝ ምዕራፎች የጥላሁንን ሕይወት ከልደቱ እስከ ኅልፈቱ ተርኳል፡፡

በአምስትምዕራፎችየተደራጀውና“መሠረት” የሚል ርዕስ የተሰጠው የመጀመሪያው ክፍል ከአቶ ፈይሳ ኃይሌ ሀሠና ዳራ ተነስቶ የጥላሁንን ልደት እና ቤተሰባዊ መሠረት የሚቃኝ ነው፡፡ ሁለተኛው ክፍል የጥላሁን የሙዚቃ አጀማመር ከኢትዮጵያ የዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ ጋር በማስተሳሰር ሙያዊ እና ግለሰባዊ ሕይወቱ ተሰናስለው በአስራ ስድስት ምዕራፎች ቀርበውበታል፡፡ ሰፋ ያለውን ገጽ የሸፈነውም “የሕይወቱ ሕይወት” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይኸው ክፍል ነው፡ ፡ ክፍል ሶስት በጥላሁን የመጨረሻ አልበም መጠሪያ የተሰየመ ነው ፤ አንዳንድ ነገሮች፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ጥላሁን ከግል ሕይወቱ ጋር የሚገናኙ ዜማዎች ፣ ስለሌሎች ድምጻውያን ያደነቀባቸውን ስሜቶች ፣ ስለድምጽ አጠቃቀሙና ብቃቱ ፣ ከመደበኛ መድረክ ውጪ ስለተጫወተባቸው አጋጣሚዎችና ስለግለሰባዊ ባህርይው የሚተርኩ አጫጭር ሁነቶችን የያዙ ሦስት ምዕራፎችን አካቷል፡፡ ክፍል አራት የሚተርከው የልጅነት ሕመሙ የፈጠረው ስነ-ልቦናዊ ቀውስ ግዘፍ ነስቶ የሚታይበትን የፍቅር ሕይወቱን ነው፡፡ ከመጀመሪያ የልጅነት ባለቤቱ ወ/ሮ ፈለቀች ማሞ አንስቶ በመጨረሻው የሕይወቱ ምዕራፍ ላይ አብራው እስከነበረችው ወ/ሮ ሮማን በዙ ድረስ አስራ ስድስት ልጆች ያፈራባቸውን ሰባት የትዳር ሕይወቶች ይቃኛል (ከፈለቀች ማሞ እና ከብርሃኔ ዘለቀ ብቻ ነው ጥላሁን ልጅ ያላገኘው)፡፡

tilahun Gesese
ደራሲው የጥላሁንን ሕይወት እንዴት ቀረበው የሕይወት ታሪክ እጅግ ጥንታዊ መሠረት አላቸው ከሚባሉ የስነጽሁፍ ዘሮች አንዱ ነው፡፡ በይዘቱ ኢ-ልቦለዳዊ ይሁን እንጂ የባለታሪኩን ሕይወት በመልሶ ፈጠራ በውብ ቃላት እየሳለ ከትክክለኛው የታሪክ እውነት ጋር በማይቃረን መልኩ አቀራረቡን ልቦለዳዊ ሊያደርግ ነጻነት አለው፡፡ ይህ ግን በባለታሪኩ የሕይወት ታሪክ አካሄድ እና በደራሲው ምርጫ የሚወሰን ነው፡ ፡ በዘመናዊ የሕይወት ታሪክ አጻጻፍ ውስጥ ደራሲው በአቀራረቡ ስነልቦናዊ ፣ ምግባራዊ እና ስነውበታዊ አካሄዶችን ሊያጤን እንደሚገባ ፖልሙራይን የመሰሉ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ፡ ፡ ባለታሪኩን የተመለከቱ ታሪካዊ መረጃዎችን በቅደም ተከተል መደርደር ብቻ የሁነቶችን ቢጋር እንጂ የግለሰቡን ሕይወት አያሳዩም፡፡ ስለዚህ ደራሲው አስፈላጊ የሚላቸውን መረጃዎች ከሰበሰበ በኋላ ጥልቅ የሆነ ስነልቦናዊ ፍተሻ በማድረግ መረጃዎቹን እያዛመደ በመተንተን እና በመተርጎም የባለታሪኩን ሰብዕና መገንባት ይጠበቅበታል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ዘመናዊ የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ የሚጋፈጠው ምግባራዊ ፈተና አለ፡፡ የተለያዩ የስነልቦና ንድፈ ሀሳቦችን ተግባራዊ አድርጎ በትርጓሜ ያገኘውን እውነት ሁሉ እንዲታተም ያደርግ ይሆን? ምን ያህሉን አውጥቶስ ምን ያህሉን ይተወው? እነዚህ ጥያቄዎች ከ18ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ በሕይወት ታሪክ ጥናት ውስጥ ሲነሱ የኖሩ ምላሽ አልባ ጥያቄዎች ይመስላሉ፡፡

ሌላው የሰበሰባቸውን ፣ የተነተናቸውንና የተረጎማቸውን ጥሬ መረጃዎች ሕይወት አከል እንዲሆኑ ምስል የመፍጠር እና ቅርጽ የማበጀቱ ጉዳይ ነው፡፡ እዚህ ጋር ሽግግር አለ በቅደም ተከተል የተሰደሩ የታሪክ እውነታዎችን የባለታሪኩን ሰብዕና ወደሚያሳይ ውብ ትረካ ማሸጋገር ያስፈልጋል፡፡ ጥሬ ሐቆቹን ልቦለዳዊ አድርጎ ሲያቀርብ ከእውነታው ሊጋጭ ይችላል፡፡ ልቦለዳዊ አቀራረቡን ትቶ ጥሬ ሐቆቹን ቢደረድር የሕይወት ታሪኩ ኪነት አልባ ይሆናል፡፡ አንድ የሕይወት ታሪክ ደራሲ የሚመዘነውም በዋናነት ለእነዚህ ጥያቄዎች በሚሰጠው የተመቻመቸ ምላሽ (compromised response) ነው፡፡
Tilahun Legend
ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ የነበረው ዘከሪያ መሐመድ እንደ ደራስያን ማህበሩ የደቦ ድርሰት ገራገር አቀራረብ ይዞ አልመጣም፡ ፡ ያገኛቸውን መረጃዎች በሙሉ በቅደም ተከተል ሲሰድር ታሪካዊ እና ስነልቦናዊ አንድነታቸውን እየፈከረ ነው፡፡ ልቦለዳዊ ውበቱ እና ታሪካዊ እውነቱም እርስ በእርስ እንዲደጋገፉ እንጂ አንዱ ከአንዱ ጋር እንዲቃረኑ አላደረገም፡፡ አልያም እንደ ደራስያን ማህበሩ ድርሰት የተነገረውን ብቻ የሚተፋ በቀቀን አልሆነም ፤ በፍጹም !

“ጥላሁን ገሠሠ የሕይወቱ ታሪክ እና ምሥጢር” በዋናነት ሦስት የማህበራዊ ሳይንስ ዲሲፕሊኖች ( ሙዚቃ ፣ ስነልቦና እና ታሪክ) እንደየአስፈላጊነቱ ተዛምደው የቀረቡበት መጽሐፍ ነው፡፡ የዚህ ዳሰሳ አቅራቢ ይበልጡን የተሳበው ግን በስነልቦናዊ ፍከራው ላይ ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ስነልቦናዊ ፍካሬ ያላቸው የሕይወት ታሪኮች ተቀባይነታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም ባለታሪኩ አውቆም ይሁን ሳያውቅ የደበቃቸውን ስውር የታሪክ ገጾች የማሳየት አቅም አላቸው፡፡ በዚህ ረገድ የሊዎናርዶ ዳቬንቺን እና የልጅነት ትዝታውን በፍካሬ ልቦና (psycho analysis) ያሳየው የሲግመን ፍሩድ መጽሐፍ ፈር ቀዳጅነቱ ይጠቀሳል፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ላይ የነበረውን የአዶልፍ ሂትለርን ሰብዕና የሚተነተነው የዶ/ር ሙራይ መጽሐፍም ከሚጠቀሱ ስነልቦናዊ የሕይወት ታሪኮች አንዱ ነው፡፡

የእኛው ዘከሪያ መሐመድ ከእነዚህ መጽሐፍት ጋር የቅርብ ዝምድና ያለው ይመስለኛል፡፡ የአቶ ፈይሳ ኃይሌ ሀሠና የቤተሰብ ማስታወሻ ያዘለውን የጥላሁንን የልጅነት ቀውስ የበዛበት ታሪክ መሳሪያ በማድረግ የጥላሁንን ሙሉ ሰብዕና በፍካሬ ለማሳየት የተጋው በእነዚህ መጽሐፍ ተጽዕኖ ይሆን ? መልሱን ለደራሲው ትቻለሁ፤

ሁለት ማንነት ለምን ?
መሳቁን ይስቃል ጥርሴ መቼ አረፈ፣
ልቤ ነው በጣሙን እጅግ ያኮረፈ፡፡
አልጠፋልህ ብሎኝ የልቤ ውስጥ እሳት፣
ጥርሴ እንዲያምር ብዬ ተወጋሁ ንቅሳት፡፡
ይሄ ነው ጥላሁን ማለት ! ልቡ ውስጥ የቀበረውን እውነት በአንደበቱ

ይሽራል፡፡ በአስታወሰው ቁጥር እሳት ሆኖ ይፈጀዋልና አርቆ ጥሎታል፡፡ በጨቅላነት ዕድሜ የእናቱን ጉያ እየሞቀ ማደግ ቢፈልግም ፣ በአባቱ መዳፍ እየተዳበሰ ልጅነቱን ማየት ቢሻም አልቻለም፡፡ እናቱ ስድስት ዓመት ሳይሞላው ጥላው ኮበለለች፡፡ አባቱ የእናቱን ፈለግ ተከትሎ አድራሻውን ሳይናገር ጠፋ፡ ፡ ጥላሁን በአያቱ እጅ ለማደግ ተገደደ፡፡ ይህን የልጅነት ቁስል ነው ላለፉት 50 ዓመታት ሲደብቅ የኖረው እና የዘከሪያ መሐመድ መጽሐፍ ይፋ ያደረገው፡፡ ጥላሁን መዘንጋት ፣ መተው ያመዋል፡፡ በልጅነቱ የተከሰተው ስነልቦናዊ ቀውስ በትዳሩም የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡ እናት እና አባቱ እሱን ጥለውት እንደኮበለሉ ሁሉ እሱም ሻንጣውን እየያዘ ያለበትን ሳይናገር የትዳር አጋሮቹን እስከነልጆቻቸው ጥሎ ሸሽቷል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ትንታኔ መሠረት ጥላሁን ከሰባት ሴቶች ጋር የፍቅር ሕይወት የመሠረተው ሴት የመቀያየር አባዜ ይዞት ሳይሆን የተዳፈነው የልጅነት ቁስል ውጤት ነው፡፡ የዚህ መጽሐፍ ትልቁ ትሩፋትም ይህን በትንታኔ ማሳየቱ ነው፡፡

ከጥላሁን አንደበት ያገኙትን በሙሉ በተዝረከረከ ቋንቋ የጻፉት የደራስያን ማህበር ጸሐፍት (ይህ ወቀሳ የሠርጸ ፍሬስብሐትን መጣጥፍ አይመለከትም) ከዘከሪያ መሐመድ ! ከአንዱ ግለሰብ ! ጥረት የሚማሩት በርካታ ነገር አለ፡፡

እንደ ደራስያን ማህበር መጽሐፍ ቢሆን ኖሮ ጥላሁን የተወለደው ጠመንጃ ያዥ ሠፈር ነው ፤ የጥላሁን ሕጋዊ ሚስቶች ቁጥር አምስት ብቻ ነው ፤ የመጀመሪያ ሚስቱም ወ/ሮ አስራት አለሙ ናት ፤ የእናቱ ሙሉ ስምም ወ/ሮ ጌጤነሽ ጉርሙ ነው፡፡ በዘከሪያ መሐመድ መጽሐፍ እነዚህ ስህተቶች እርማት ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ጥላሁን ገሠሠ የተወለደው ከወሊሶ 12 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ጉሩራ እልፍ ብሎ በሚገኘው ሶየማ የገጠር ቀበሌ ነው፡፡ እናቱም ወ/ሮ ጌጤነሽ ኢተአ ትባላለች፡፡ የጥላሁን ሕጋዊ ሚስቶች ቁጥር ስድስት ሲሆን የመጀመሪያ ባለቤቱ በአስራ ሰባት ዓመት ዕድሜው ያገባት ወ/ሮ ፈለቀች ማሞ ናት፡፡ በ1970ዎቹ አጋማሽም አራተኛ ሚስቱን ፈሪያል መሐመድን ከፈታ በኋላ ከወ/ሮ ብርሃኔ ዘለቀ ጋር ከሁለት ዓመት በላይ አብሮ ኖሯል፡፡ ይህም የሚስቶቹን ቁጥር ወደ ሰባት ከፍ ያደርጋል፡፡ እነዚህን ሁሉ አሳማኝ የታሪክ ሐቆች ነው የደራስያን ማህበሩ መጽሐፍ የገደፈውና የዘከሪያ መሐመድ መጽሐፍ ይፋ ያደረገው፡፡

ለሃምሳ ዓመታት ሲተረክ የነበረው የጥላሁን ተለጣፊ ማንነት በስነልቦናዊ ትንታኔ ሽሮ የእውነተኛውን የሙዚቃ ሰው ታሪክ ለአስኮመኮመን ዘከሪያ በእውነት ክብር ይገባዋል፡፡

የሆድ ይፍጀው ነገር

“ጥላሁን ገሠሠ የሕይወቱ ታሪክ እና ምሥጢር” የተሰኘውን መጠሪያ የተመለከተ ሰው ሁሉ የዚህ መጽሐፍ ትልቁ ምሥጢር አድርጎ የሚወስደው የሆድ ይፈጀውን ትረካ ይመስለኛል፡፡ ለእኔ ግን ከሆድ ይፍጀውም በላይ ትልቁ ምሥጢር ለሃምሳ ዓመታት ተደብቆ የኖረው የጥላሁን የልጅነት እና የትዳር ሕይወት ነው፡፡
ሚያዝያ 10 ቀን 1985 ዓ.ም የፋሲካ ዕለት የጥላሁን ገሠሠን በስለት የመወጋት ዜና ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ ጥላሁንን ሦስት ቦታ ወግቶ የመግደል ሙከራ ያደረገው ማን እንደሆነ ማወቅ አልተቻለም ነበር፡፡ ዘከሪያ መሐመድ ለዚህ ጥያቄ ዘወርዋራ በሆነ መንገድ ምላሽ ለመስጠት ሞክሯል ፤ ወንጀሉን የፈጸመው እና የፈጸመበትን መንስኤ በትርጓሜ ጠቁሟል፡፡ አብዛኛውን አንባቢ ምን ያህል ያረካል ? እርግጠኛ አይደለሁም፡፡

የመጨረሻው ቃል

በአንድ ኢትዮጵያዊ የኪነት ሰው ላይ በዚህ ደረጃ የሕይወት ታሪክ ተጽፎ ያነበብኩት የዘከርያ መሐመድን “ጥላሁን ገሠሠ የሕይወቱ ታሪክ እና ምሥጢር” የተሰኘውን መጽሐፍ ነው፡፡ የጥላሁን ገሠሠ ውስጣዊ ዓለም በቃላት ስሎ አሳይቶናል፡፡ ስነልቦናዊ ፍካሬው አንጀት ያርሳል ቅደም ተከተላዊ ታሪኩን የገለጸበት ቋንቋ ጥቃቅኖቹን ሁነቶች ሳይቀር ልቦና ውስጥ እንዲቀሩ ያደርጋል፡፡ ይህ መጽሐፍ ፈቃደኛ የሆኑ መረጃ አቀባዮችን ካገኘ የበለጠ እየፋፋና እየጎለበተ መሄድ የሚችል ይመስለኛል፡፡ ለአገራችን የሕይወት ታሪክ ጸሐፍትም ዘከሪያ መሐመድ “የተገኘውን ጥሬ መረጃ እንደወረደ መጻፍ ጸሐፊ አያሰኝም ፤ ጥሬውን መረጃ ከተለያዩ ዲሲፕሊኖች በተገኙ ንድፈ ሐሳቦች መተንተንና መፈክር ነው የስኬታማ የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ ብቃት መታያው፡ ፡” ያለ ይመስለኛል ፤ በሥራው፡፡

የዘከሪያን መጽሐፍ ማንበብ መታደል ነው ፤ ትርፉ ብዙ ነውና፡፡

ቁምነገር መጽሔት ላይ ታትሞ የወጣ

The post (አሁንም ስለአነጋጋሪው የጥላሁን መጽሐፍ) ሁለት ማንነት በአንድ ራስ – ጥላሁን ገሠሠ የሙዚቃው ንጉሥ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 261

Trending Articles