ጌጡ ተመስገን ከአዲስ አበባ አክሱም ሆቴል እንደዘገበው:-
ፊታውራሪ ዐመዴ ለማ
የወሎ ጠቅላይ ግዛት ይባል በነበረው ግዛት፣ ወረሂመኑ ተብሎ በሚጠራው አውራጃ፣ መጋቢት 1913 ዓም ተወለዱ፡፡ አባታቸው በልጅነታቸው በሞት ስለተለዩዋቸው ኑሮ ከበዳቸውና ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር ዕንቁላልና ሌሎች ነገሮችንም መነገድ ጀመሩ፡፡ ደሴ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በማታው መርሐ ግብር እስከ ስድስተኛ ተማሩ፡፡ በ1936 ዓም ደግሞ ወ/ሮ ዘምዘም ኢብራሂምን አገቡ፡፡ ከእኒህ ወይዘሮ ጋርም ለስድሳ ዓመታት በጋብቻ ኖረዋል፡፡
ፊታውራሪ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በወቅቱ ከነበሩ ነጋዴዎች ልምድ ቀሰሙ፡፡ ይህንን ልምድ ተጠቅመውም ነግደው የሚያተርፉ፣አትርፈውም ለሌሎች የሚተርፉ ነጋዴ ሆኑ፡፡
ፊታውራሪ በሕዝብ ዘንድ ይበልጥ ያሳወቃቸውና ያስወደዳቸው ለሰው ልጅ ያላቸው ክብርና፣ ለሰውነት የሚሰጡት ዋጋ ነው፡፡ ይህም ለፓርላማ አስመርጧቸው በ1948 ፓርላማውን ሲቀላቀሉ ፓርላማው ከፍተኛ መሻሻል ያሳየበት ዘመን ሆነ፡፡ ለዚህም እነ ፊታውራሪ ዐመዴ ለማና ሌሎች ያደረጉት አስተዋጽዖ ወሳኝ ነበር፡፡ በኃላፊነት ዘመናቸው ኢትዮጵያ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች መብታቸው እኩል ተከብሮ በመፈቃቀርና በመከባበር የሚኖሩባት ሀገር እንድትሆን ተግተዋል፡፡ አንዳንድ በዓላት ቀርተው የሙስሊም በዓላት እንዲተኩባቸውም ጥረት አድርገዋል፡፡
በፍትሕ ሥርዓቱ የነበረው ፍርደ ገምድልነት ቀርቶ የተሻለ የፍርድ ሥርዓት እንዲኖር እርሳቸውና ስድስት ሌሎች የፓርላማ አባላት ያቀርቡ በነበረው ሐሳብና ትችት የተነሣ በንጉሡ ዘንድ ቅያሜ አስከትለው ከደረጃ ዝቅ ብለው እንዲሠሩ ተደርገው ነበር፡፡ ከፓርላማ እንዲወጡም ሤራ ተጎንጉኖባቸው ነበር፡፡ በፓርላማ አባልነታቸው ካነሡዋቸው ሐሳቦች መካከል የአክሱም ሐውልት መመለስ፣ የመሬት ይዞታ መሻሻልና የጤና ግብርን የተመለከቱት ይጠቀሱላቸዋል፡፡
ፊታውራሪ ዐመዴ በሕይወት ዘመናቸው ከሚደሰቱበት ሥራቸው መካከል የአክሱምን ሐውልት ለማስመለስ በተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ውስጥ ያደረጉት አስተዋጽዖ ለስኬት መብቃቱ ነው፡፡ ፊታውራሪ ዐመዴ የሀገራቸውን ጉዳይ ከምንም ጉዳይ በላይ የሚያስቀድሙ ናቸው፡፡
ለእርሳቸው ጉዳዩ የክርስቲያን ሆነ የሙስሊም አንድ ነው፡፡ መስጊድ ያሠሩትን ያህል ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል፡፡ ‹በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች› የሚለው ባዕድነት የሚያመጣ ስያሜ እንዲቀር የታገሉትን ያህል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚገኙ አባቶች መለያየታቸውን ባለመደገፍ ሁለቱንም አባቶች ቀርበው ይቆጡ፣ ይገሥፁና ‹‹ይህቺ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን የእናንተ ብቻ አይደለችም›› እያሉ ይናገሯቸው ነበር፡፡ በ1997 ዓም የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ የታሠሩትን የቅንጅት አመራሮች ለማስፈታት በተደረገው የሽምግልና ጥረትም ከሌሎች ወገኖች ጋር በመሆን ከላይ ታች ደክመዋል፡፡
ከዚህ ተግባራቸው ባሻገር የውኃ ዋና ፌዴሬሽን ሊቀ መንበር በመሆን ከ20 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፡፡ የአክስዮን ማኅበርን ባሕል እንዲሆን ሠርተዋል፡፡ የትራንስፖርት ኩባንያ እንዲቋቋም አስተባብረዋል፡፡ ፊታውራሪ ዐመዴ የእምነትና ዘር ገደብ የማይዛቸው፣ ሀገራቸው ሰላምና የበለጸገች ሆና የማየት ሕልም የነበራቸው፣ በሽምግልናቸው የማያፍሩ፣ እውነትን በብርቱ የሚደፍሩ ሁለገብ አባት ነበሩ፡፡ ያረፉት በ2001ዓም በሚያዝያ ወር ነው፡፡
***
በጎ ሠሪዎችን በማክበርና በማበረታት ሌሎች በጎ ሠሪዎችን እናፍራ!