ጌጡ ተመስገን ከአዲስ አበባ አክሱም ሆቴል እንደዘገበው:-
ፕሮፌሰር አበበ በጅጋ
ፕሮፌሰር አበበ በጅጋ የዓይን ሕመም ከፍተኛ ችግር በሆነበትና በቀላል ሕክምና ሊድኑ የሚችሉ የዓይን ሕመሞች ዓይነ ሥውርነትን በሚያስከትሉበት ሀገራችን ውስጥ ይህንን ችግር ለመፍታት በግንባር ቀደምነት ከተሰለፉ ባለሞያዎች መካከል ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕክምና(MD,)ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በኦፕታልሞሎጂ ስፔሻላይዝድ ያደረጉት ፕሮፌሰር አበበ በጅጋ አውስትራልያ ከሚገኘው ኒው ካስል ዩኒቨርሲቲ በክሊኒካል ኤፒዲሞሎጂና ባዮ ስታትስቲክስ ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚሠሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ይህም አገልግሎታቸው ከ30 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡
ፕሮፌሰር አበበ በጅጋ ሞያቸውን በተመለከተ በማስተማር፣ጥናት በማድረግና ልዩ ልዩ ሞያዊ ተቋማትን በማገልገል ይታወቃሉ፡፡ በሞያዊ ጆርናሎች አርታዒና አማካሪ በመሆን(ከአራት በላይ ቢሆኑ የኦፕቲሞሎጂ ጆርናሎች አባልና መሪ ተሳታፊ ናቸው)፣ በልዩ ልዩ ጉባኤያት አወያይና ተወያይ በመሆን(በሞያው ዘርፍ የተደረጉ ሁለት ሀገር አቀፍ ጉባኤያትን በመሪ ተወያይነት አገልግለዋል)፣ የሕክምና ማኅበራትን በመምራትና በቦርድ አባልነት በማገልገል(ከስድስት በላይ ሞያውን የተመለከቱ ማኅበራትና ሀገር አቀፍ ኮሚቴዎች ውስጥ በቦርድ አባልነትና በኮሚቴ አባልነት ያገለግላሉ)፡፡
እስካሁን ድረስ ኦፕቲሞሎጂን የተመለከቱ ከ30 በላይ ጥናቶችን በራሳቸውና ከአጋሮቻቸው ጋር ሆነው በመሥራት ያሳተሙ ሲሆን ላበረከቱት አስተዋጽዖም ልዩ ልዩ ሽልማቶችን ተቀብለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ኦፕቲሞሎጂካል ማኅበር (እኤአ በ2010) በጥናት መስክ ላበረከቱት አስተዋጽዖ የዕውቅና ሽልማት፣ እኤአ በ2012 በመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች የዓመቱ ምርጥ መምህር፣ እኤአ በ2014 የዓመቱ ምርጥ መምህር ተብለው ለስፔሻላይዜሽን በሚማሩ የክፍለ ትምህርቱ ተማሪዎች ተመርጠዋል፡፡
ዶክተር አበበ በጅጋ ከዚህ ሁሉ በላይ የሚታወቁት ዕውቀታቸውን ሳይሰስቱ ለመስጠት በሚያደርጉት ትጋትና ሕሙማኑን ለመርዳት በሚከፍሉት መሥዋዕትነት ነው፡፡ ከ1000 በላይ የሚሆኑ ሕጻናትን ከዓይነ ሥውርነት ታድገዋል፡፡ ተማሪዎቻቸው በዕውቀት ብቁ፣ በሥነ ምግባር ምስጉን፣ በሕዝብ አገልጋይነትም ታማኝ ሆነው እንዲወጡ ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ዕውቀታቸውንም፣ ምክራቸውንም ይለግሳሉ፡፡ ተማሪዎችን በማክበር ሕዝብ የሚያከብሩ የሕክምና ባለሞያዎችን ለመፍጠር ይተጋሉ፡፡ በተደጋጋሚ በተማሪዎቻቸው ተመራጭ መምህር ያደረጋቸውም ይኼው ነው፡፡ ሕሙማኑን እስከመጨረሻው በመርዳት መፍትሔ እንዲያገኙ ይተጋሉ፡፡ ከእርሳቸው እጅ ሕክምናን ለማግኘት ዕድል ያገኙ ሁሉ ከሞያዊ ችሎታቸው ባሻገር የአባትነትና የወንድምነት ጠባያቸውን፣ ችግሩን ፈትተው የዓይን ብርሃንን ለመመለስና የዓይንን ጤንነት ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ግብግብ ያስታውሳሉ፡፡ የሞያ አጋሮቻቸውና ተማሪዎቻቸው ‹ችግርን በመፍታት እንጂ ገንዘብን በማግኘት የማይደሰቱ› ይሏቸዋል፡፡