ጌጡ ተመስገን ከአዲስ አበባ አክሱም ሆቴል እንደዘገበው:-
ሰዓሊ ታደሰ መስፍን
ሰዓሊ ታደሰ መስፍን በ1945 ዓ.ም በወልዲያ ነበር የተወለደው፡፡ ከእረኝነቱ ጀምሮ እጅና እግሩ ላይ በእንጨት በመሞንጨር ሥዕልን የጀመረው አዳጊው ምንም እንኳን ዝንባሌው ወደ ሥዕል ማጋደሉን ከልጅነቱ ቢረዳም መደበኛ ትምህርቱን ከመከታተል ወደ ኋላ አላለም፤ በዚሁ መሠረት በዕቴጌ ጣይቱ ብጡል ት/ቤት መደበኛ ትምህርቱን ጀምሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ቆይታውን እንዳጠናቀቀ የ6 ዓመቱ ታዳጊ ከአጎቱ ጋር ለመኖር ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላም በስዊዲሽ ሚሽን ት/ቤት ገብቶ መደበኛ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በበዕደ ማርያም ት/ቤት አጠናቀቀ፡፡ ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን ግን በትምህርት ቤቱ ውስጥ ለሚዘጋጀው መጽሔት “ኢሉስትሬሽን” የውጭ ሽፋን የመሳሰሉትን ይሰራ ነበር፡፡
ሰዓሊ የመሆን ጥልቅ ፍላጎትና ችሎታ ስለነበረው 1960 ዓ.ም ሥነ ጥበብ ት/ቤት ገባ፡፡ በአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ት/ቤት ቆይታው ታዋቂው ሰዓሊ ገ/ክርስቶስ ደስታ ያስተማረው ሲሆን እንደነ ዲዛይነር ታደሰ ግዛውን ጨምሮ በድንቅ መምህራን መማሩን የሚናገረው ሰዓሊ ታደሰ በተማሪነቱ ከሌሎች አቻዎቹ የላቀ ሥራ በመሥራት የከፍተኛ ትምህርቱን በማዕረግ አጠናቋል፡፡
የዛሬው አንጋፋው የያኔው ወጣቱ ሰዓሊ ከተመረቀ ከአምስት ዓመት በኋላ የብሔራዊ ቴአትር “አንድ ሰዓሊ መርጣችሁ ላኩልን” በማለት ለሥነ ጥበብ ት/ቤቱ በደብዳቤ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ሰዓሊ ገ/ክርስቶስ ደስታም በወጣቱ ችሎታ በመተማመን ሰዓሊ ታደሰን ወደ ብሔራዊ ቴአትር ላከው፡፡ በመድረክ ዲዛይን ሥራው የብዙዎችን አድናቆት የተቸረው ሲሆን በቅርበት ሥራውን የተከታተሉ ሙያተኞች “በዚያን ዘመን እሱ ይሰራቸው የነበሩት የመድረክ ዲዛይኖች ዛሬ እንኳ በዲጂታል ዘመን እንዳልተሠራ ይመሰክራሉ፡፡
ለተጨማሪ ከፍተኛ ትምሕርት ወደ ራሽያ ሀገር በማቅናት በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ በሚገኘው ሬፒን አካዳሚ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን ለመከታተል የቻለ ሲሆን በዚህ ተቋም በነበረው ቆይታ ከራሽያ ተማሪዎችም ሆነ ከሌላ ሐገር ከሄዱት ተማሪዎች እጅግ የላቀ ብቃት አሳይቷል፡፡ በዚህም ልዩ ብቃቱ በአካዳሚው ታሪክ የመጀመሪያው የውጭ አገር ዜጋ የክብር ተሸላሚ በመሆን ማስተርሱን ይዞ ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡ በከፍተኛ ውጤት በማዕረግ ተመርቆ ሐገሩ ከተመለሰ በኋላ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ስር የሚገኘውን እና ለሀገራችን ፋና ወጊ የሆነውን የአዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ት/ቤት ሰዓሊ ታደሰን እና ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህን ተቀብሎ በተቋሙ የነበረውን የኪነ ንድፍ(ድሮዊንግ) ደረጃ በጣም ከፍ ያደረጉበት ጊዜ ነበር፡፡
በደርግ ጊዜ በየጊዜው ለብሔራዊ ግዴታ በሚሉ እና በሌሎችም መነሻዎች ምንም ሳይከፈለው በነፃ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፖስተሮችንና ሥዕሎችን በመስራት፣ የሶሻሊስት ኢትዮጵያ ዓርማን በመቅረፅ፣ ለታላቁ የሕዝብ ለሕዝብ ትዕይንት የሚሆኑ የመድረክ እና የአልባሳት ዲዛይን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በማዘጋጀት፣ እንዲሁም የሀገራችን የመገበያያ ሳንቲሞች (25 ሳንቲም እና 50 ሳንቲም) ላይ የራሱን ሙያዊ አስተዋፅዖ በማድረግ አንጋፋው አስተማሪ እና ሰዓሊ ታደሰ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ግዴታ ሊወጣ ችሏል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በመንግሥት እና በሌሎችም አካላት ሙያዊ አስተዋጽዖን ሲጠየቅ ወደ ኋላ ብሎ የማያውቀው ሰዓሊው ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላም በተለያዩ የመታሰቢያ ሥራዎች ላይ ሙያዊ ተሳትፎን አድርጓል ከቅርብ ጊዜ ሥራዎቹ ውስጥም ትግራይ ላይ ያለውን የሰማዕታት ሐውልት የመጀመሪያውን ንድፍ ያጠናና የፈጠረ እንዲሁም በአማራ የሰማዕታት ሐውልት ሥራ ላይ የበዛ አስተዋፅኦ ያደረገባቸውን መጥቀሱ በቂ ይሆናል፡፡
ሰዓሊ ታደሰ መስፍን ገና በወጣትነቱ ከሥነ ጥበብ ት/ቤቱ በማዕረግ ሲያጠናቅቅ ጃንሆይ የወርቅ ሰዓት ሸልመውታል፡፡ የሥነ ጥበብ እና የመገናኛ ብዙኃን ሽልማት ላይ በምርጥ ሰዓሊነቱ መሸለሙ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ለበርካታ ዓመታት ሀገሩን ያገለገለው አንጋፋው ሰዓሊ የሚገባውን ያህል ቀርቶ ለሥራው መታሰቢያ የሚሆን እውቅናን እንኳን በተለይ ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቱ አልተሰጠውም፡፡ ከተቋሙ በተቃራኒው ግን በሥነ ጥበብ ት/ቤቱ ተማሪዎቹ በተደጋጋሚ ሊሸለምና ሊመሰገን ችሏል፡፡
በአሁኑ አጠራሩ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ጥሩ ጥሩ መምህራን ቢኖሩም ለተማሪዎች የምንጊዜም ምርጥ መምህራቸው በመሆን ሰዓሊ ታደለ መስፍን በእነርሱ የቃል ምስጋና ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ “ተማሪ በአንድ ድምፅ የሚወደውና የሚያደንቀው አንጋፋ ሰዓሊ ነው” በማለት የሚመሰክሩለት ተማሪዎቹ “ለመምህራቸው እና እውቁ ሰዓሊ ታደሰ መስፍን የማይገባው ሽልማት የለም” ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ታዋቂው ሰዓሊ መዝገቡ ተሰማ በበኩሉ “በሥነ ሥዕል እንደ ታደሰ መስፍን ለመንግሥት ሆነ ለአገሩ በሚገባ ያገለገለ ሰው የለም፡፡ እሱ እንደዚህ አድርግ ካሉት “እምቢ” የማይል ሰው ነው፡፡ በዚያ ላይ ቢያንስ እንኳን መልሳችሁ እንደዚህ አድርጉልኝ የማይል ነው፡፡” በማለት የአንጋፋውን ሰዓሊ ብቃት ይመሰክራል፡፡
አንጋፋው ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ በበኩላቸው “እንደ ታደሰ መስፍን ዓይነት ሠዓሊ በዘመናት ውስጥ አንድ ሁለት ሰው ነው የሚታየው” በማለት አድናቆታቸውን ካወሱ በኋላ የታደሰ ብቃትን የሚያህል የዕውቀትና የጥበብ ሰው የሌለን በመሆኑ ከእኛም አልፎ አፍሪካን የሚያስጠራ ነው፡፡ በማለት ስለሙያተኛው ብቃት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡