የአመቱ ምርጥ አርቲስት – ቴዲ አፍሮ
ቴዲ አፍሮ “ሚስማር በመቱት ቁጥር ይጠብቃል” እንደሚባለው ሆኗል:: በመንግስት የሚደርስበት ጫና ይበልጥ ተወዳጅ እንዲሆን እያደረገው ነው:: በዚሁ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ላይ 70 ደረጃ የሚለውን ነጠላ ዜማ ከለቀቀ ወዲህ የሕዝብ ጆሮን አግኝቶ ነበር:: ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ ውጭ ሃገር ለኮንሰርት ዝግጅት ላይ በነበረበት ወቅት ድንገት ፖሊሶች አስረውት ነበር:: ምክንያታቸውም ከዚህ ቀደም ቴዲ አፍሮ- ከዓመታት በፊት የጎዳና ተዳዳሪ ገጭቶ ገድሏል የተባለበት ቢኤምደብሊው የቤት አውቶሞቢል ቀረጥ ሳይከፈልበት የገባ ነው በሚል በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መርማሪ ቡድን በቁጥጥር ሥር ዋለ:: በ30 ሺህ ብር ዋስም ተለቀቀ:: የሚገርመው ይህ ክስ ከብዙ ዓመታት በፊት መመስረቱ ብቻ ሳይሆን መኪናው በአሁኑ ወቅት በአርቲስቱ እጅ አለመኖሩም ጭምር ነው::
ቴዲ አፍሮ በዚህ ዓመት ‘አልሄድ አለ’ እና ‘ኮርኩማ’ አፍሪካ የተሰኙ መል ዕክት ያላቸውን ተወዳጅ ዘፈኖቹን አበርክቶልናል:: ሁለቱም ዘፈኖቹ እጅግ ተወዳጅ ሆነውለታል::
በዚህ ዓመት በቴዲ አፍሮ ላይ ከፍተኛ ጫና የተደረገበት ሲሆን ከዚህም ውስጥ የአውሮፓው ኮንሰርቱ እንዲስተጓጎል የተደረገበት ነው:: ከሃገር ሊወጣ ሲል ፓስፖርቱን ከሕግ ውጭ በደህንነቶች የተቀማው ቴዲ በአውሮፓ ማቅረብ የነበረበትን ኮንሰርት በዚህ ሳቢያ በመሰረዙ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል:: በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሳይባል ደህነነቶች ‘ልክ እናስገባሃለን’ በሚል ፓስፖርቱን የተቀማው ቴዲ እየደረሰበት ያለውን ጫና ዘፈኑ ገልጾታል እየተባለ ነው:: “አልሄድ አለ” የሚለው ነጠላ ዜማውም ለራሱ የሰራው ነው እየተባለ ይነገራል::
ቴዲ በአዲስ ዓመት ዋዜማ በአዲስ አበባ ላፍቶ ሞል ሊያቀርበው የነበረው ኮንሰርቱ በፖሊስ ምክንያት እንዲሰረዝ ተደርጓል:: ለስርዓቱ ቅርብ የሆኑት ማዲንጎ አፈወርቅ እና አስቴር አወቀ ኮንሰርት እንዲያቀርቡ ሲፈቀድ ቴዲ በመከለከሉ የተቆጡት ኢትዮጵያውያን ኮንሰርቱን በፌስ ቡክ ለማድረግ ቆርጠው ተነስተዋል::
ቴዲ አፍሮ በዘ-ሐበሻ አንባቢዎች የአመቱ ምርጥ ሰው ሽልማትን አግኝቷል:: እንኳን ደስ ያለህ::