Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Entertainment
Viewing all articles
Browse latest Browse all 261

ጥቂት ስለ አርቲስት ሰብለ ተፈራ (እማማ ጨቤ)

$
0
0

በያሬድ ቁምቢና ውብዓለም ተስፋዬ

የአዲስ አመት ዋዜማ ጳጉሜ 5 ቱሉ ዲምቱ አቃቂ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ‹የመዳን ቀን ዛሬ ነው› እና‹ የጅራፍ ንቅሳት› የተሰኙ ሁለት የራሷን ግጥሞች አቅርባለች፡፡
sebele tefera
ገና በስራዋ ስትታይ ድንቅ የትወና ብቃትና ፈጠራዋ የብዙዎችን ቀልብ መሳብ የቻለች ብርቅዬ ድንቅ አርቲስት ነበረች …ሰብለ ተፈራ፡፡ ፍጹም ባልተጠበቀ እና ድንገተኛ አደጋ ህይወቷ በማለፉ ቁጭትና ጸጸቱ የሚፋጅ ሆኗል፡፡ እጇ የነካው የጥበብ ስራ ሁሉ ያማረ የተዋጣለት ስለመሆኑ ሁሉም የሚስማማበት ጉዳይ ነው፡፡ አርቲስት ሰብለ ተፈራ (እማማ ጨቤ) አዲስ አበባ ከተማ ወሎ ሰፈር በተለምዶ አይቤክስ ሆቴል አካካቢ በ1968 ግንቦት 18 ዓ.ም ነው የተወለደችው፡፡በተወለደች በ40 ዓመቷ ትላንት ከሰዓት 10 30 ገደማ በድንገተኛ የመኪና አደጋ ህይወቷ አልፏል፡፡ ሰብለ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በንፋስ ስልክ ትምህርት ቤት ያጠናቀቀች ሲሆን ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ በንፋስ ስልክ አጠቃይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች፡፡ ዛሬ ላይ አብርቶና ደምቆ ለመታየት የበቃው የጥበብ አቅምና ብቃቷ የተጠነሰሰው ገና የ14 ዓመት ልጅ እግር እያለች ነበር፡፡ ከዚያም በ1984 ዓ.ም በዶክተር ተስፋዬ አበበ የቲያትር ሙያ ስልጠና አግኝታለች፡፡ የቲያትር ትምህርቷንም በመቀጠል በራክማኖፍ ኮሌጅ በትወና ዲፕሎማ በመያዝ ድንቅ ብቃቷን በትምህርት አግዛለች፡፡በዚህ ብቻ አላቆመችም እስክትለየን ድረስም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቲያትሪካል አርት ትምህርት ክፍል የዲግሪ ትምህርቷን እየተከታተለች ነበር፡፡ አርቲስት ሰብለ ከ20 በላይ ፊልሞች እንዲሁም ከ30 በላይ ቲያትሮች ላይ በመተወን ከመድረኮቹ ፈርጦች መካከል አንዷ ሆናለች፡፡ ጓደኛሞች ፣ላጤ፣ ሰቀቀን ፣ የሰርጉ ዋዜማ፣ ህይወት በየፈርጁ ፣እቡይ ደቀመዝሙር ፣ አምታታው በከተማ፣ የክፉ ቀን ደራሽ ፣አንድ ቃል፣ ወርቃማ ፍሬ፣ እንቁላሉ፣ 12 እብዶች በከተማ፣ ሩብ ጉዳይ፣ አብሮ አደግ፣ እነዚህ ቲያትሮች በሰብለ ተፈራም የተተወኑ ናቸው፡፡

አርቲስት ሰብለ ተፈራ በቲያትር አፏን የፈታችው ከአርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬ ጋር በ‹ጭንቅሎ› ቲያትር ነው፡፡

ከተወነቻቸው ፊልሞች መካከልም ፈንጅ ወረዳ፣ ያረፈደ አራዳ፣ትንቢት፣ የሚሉት ፊልሞች ሰብለ ተፈራ ብቃቷን ያሳየችባቸው ናቸው፡፡

እንግሊዝ፣ አሜሪካ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የእኛ ዕድር የሚለው ቲያትር በሰብለ ተፈራ ቀርቧል፡፡ በእስራኤል ‹ሴት ወንድሜ› የተሰኘ ቲያትር ይዛም ቀርባለች፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቀዋል ተብሎ በድፍረት የሚነገርለትና በዮናስ አብርሃም ተደርሶና ተዘጋጅቶ በፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት ለአምስት አመታት ገደማ በቀረበው ‹‹ ትንንሽ ፀሐዮች›› ተከታታይ የሬድዮ ድራማ እማማ ጨቤን አለማወቅ አይቻልም ፡፡ አዎ እማማ ጨቤ አራዳዋ፣ ዘመናዊዋ፣ ጨዋታ አዋቂዋ፣ ሞጃዋ ፣ጠርጣራዋ ፣ንግግር አዋቂዋ፣ ሆነው ይታወቃሉ፡፡ ‹እማማ ጨቤ› ያች ‹ሁሉ ሴት› ‹‹ብዙዋ ሴት›› ስጋ ለብሳ ነፍስ የዘራችው በአርቲስት ሰብለ ተፈራ ነው፡፡፡፡ በቤቶች የቴሌቭዥን ድራማ በመብልም በንግግርም አፏ ስራ የማይፈታው ድንቡሼዋ፣ ቦርቧራዋ፣ የማዕድ ቤቷ ንግስት ‹ ትርፌ › በሰብለ ተፈራ ውስጥ ነበረች፡፡ በአዲስ አበባ ባሉ ቲያትር ቤቶች የትወና አቅም ብቃቷን አሳይታለች፡፡ ልቆ የሚበልጠው የሰብለ ተፈራ ባለውለታነት ከአዲስ አበባ ውጪ ቲያትር ማቅረብ በማይታሰብበት፤ መንገዱ በሚፈትንበት፤ አዳራሽ እንደልብ በማይገኝበት፤ የጸሃዩ ሀሩር፣ ዝናቡ፣ ብርዱና ቆፈኑ መድረሻ በሚያሳጣበት በዚያን ወቅት በተለያዩ የክልል ከተሞች ለሚገኙ የጥበብ አፍቃሪዎች ቲያትርን እየተዟዟሩ ካሳዩት ለጥበብ ከተፈጠሩ ጥቂት አርቲስቶቻችን እና መስዋዕትነት ከከፈሉት መካከል አርቲት ሰብለ ተፈራ አንዷ ናት፡፡ አርቲስት ሰብለ ‹‹አልበም ›› የተሰኘውን ፊልም አዘጋጅታለች፡፡ ‹እርጥባን› በተሰኘው ቲያትርም ላይ በዳይሬክተርነት ሰርታለች፡፡ በርካታ የሬድዮና የቴሌቭዥን ማስታወቂዎች አርቲት ሰብለ ተፈራን ሲጋብዙ አይተናል ሰምተናል፡፡

sebele

ቅንነት፣ ደግነት፣ መልካምነት፣ አዛኝነት በተለይም ሰው መርዳት ለተቸገረ መድረስ የአርቲት ሰብለ ተፈራ የሰርክ ባህሪያት ናቸው፡፡አልችም አይሆንም የሚሉት ሃሳቦች በሰብለ ተፈራ ዘንድ የሉም፡፡ በተግባቢነት፣ በቀልድ አዋቂነት፣ ጥርስ ባለማስከደን ሰብለ ተፈራን የሚስተካከላት የለም፡፡

ሰብለ ተፈራ ከዓለማዊ ህይወቷ ይልቅ በመንፈሳዊ ህይወቷ የሚበልጥ ተሳትፎ ነበራት የሚባልላት አርቲስት ናት፡፡ በተለያዩ ቤተ ክስቲያናት በመገኘት በሙያዋ ታገለግል ነበር፡፡ የቅርቡን ብናነሳ የአዲስ አመት ዋዜማ ጳጉሜ 5 ቱሉ ዲምቱ አቃቂ ደብረ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ‹የመዳን ቀን ዛሬ ነው› እና‹ የጅራፍ ንቅሳት› የተሰኙ ሁለት የራሷን ግጥሞች አቅርባለች፡፡

አርቲስት ሰብለ ተፈራ ሚያዝያ 27 1999 ትዳር የመሰረተች ሲሆን ልጆች እንዳላፈራች ነው ለማወቅ የተቻለው፡፡

የአርቲት ሰብለ ተፈራ የቀብር ስነ ስርዓት ፡በካቴድራል ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ነገ ሰኞ መስከረም 3 2008 ከቀኑ 9 ሰዓት ወዳጅ ዘመዶቿና አድናቂዎቿ በተገኙበት ይፈጸማል፡
ለቅሶ ለመድረስ መልካም ፍቃድዎ ይሁንና፣ ላንቻ ግሎባልን አለፍ እንዳሉ ኮንኮርድ ሆቴል ሊደርሱ ጥቂት ሲቀርዎት በስተቀኝ ባለው መታጠፊያ ገባ እንዳሉ ያገኙታል ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 261

Trending Articles