Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Entertainment
Viewing all articles
Browse latest Browse all 261

ድምፃዊ ስንታየሁ ጥላሁን-ሂቦንጎ

$
0
0


‹‹ሂቦንጎ›› የወቅቱ ተወዳጅ ዘፈን ነው፡፡ ይህንን ዘፈን የተጫወተው ደግሞ ድምጻዊ ስንታየሁ ጥላሁን ነው፡፡ በ1973 ዓ.ም እዚህ አዲስ አበባ የተወለደው ስንታየሁ የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ሲሆን፣ ከእሱ በታች አራት ልጆች አሉ፡፡ እስከ ስምንተኛ ሆሳዕና ውስጥ፣ ከዘጠነኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በጥቁር አንበሳ ት/ቤት ነው የተማረው፡፡
‹‹ሂቦንጎ›› የሚለው ዘፈን በሙያው አፍቃሪ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱ ምክንያት ሆኖን ነው ከድምፃዊ ስንታየሁ ጥላሁን ጋር ቃለ-ምልልስ ያደረግነው፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ዘሃበሻ፡- ድምፃዊ ስንታየሁ ጥላሁን ከሁሉ በማስቀደም ይህንን ቃለ ምልልስ ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆንህ አመሰግናለሁ፡፡

// ]]>
ስንታየሁ፡- እኔም እድሉን ስለሰጣችሁኝ ከልብ ነው የማመሰግነው፡፡
ዘሃበሻ፡- ስንታየሁ ጥላሁን ራሱን አጭር በሆነ ሁኔታ ያስተዋውቅ ተብሎ ቢፈቀድልህ ምን ብለህ ታስተዋውቃለህ?
ስንታየሁ፡- እኔ የተወለድኩት እዚሁ አዲስ አበባ ከፍላሚንጎ ጀርባ ነው፡፡ ትንሽ ልጅ ሆኜ ወደ ሆሳዕና ሄድኩኝ፡፡ ስለዚህ ያደኩት ሆሳዕና ነው ማለት ነው፡፡ ያደኩት ደግሞ በአያት እጅ ነው፡፡ ሆሳዕና ምንም አይነት የሙዚቃና የቴአትር ክበባት አልነበሩም፡፡ የሙዚቃ ፍቅሩ ግን ውስጤ ነበር፡፡ ሁል ጊዜ ቤት ውስጥ እዘፍናለሁ፡፡ ድምፄን የሚሰሙ ሰዎች መዝፈን እንደምችል ሲነግሩኝና ሲያበረታቱኝ ወደ አዲስ አበባ መጣሁኝ፡፡
ዘሃበሻ፡- መቼ ነበር ወደ አዲስ አበባ የመጣኸው?
ስንታየሁ፡- 1991 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ነው የመጣሁት፡፡ በ1982 ዓ.ም መጨረሻ ላይ አዲስ ከተማ ወወክማ በክረምት የሚሰጥ የሙዚቃ ስልጠና ነበር፡፡ ስልጠናውን ከጀመርኩ በኋላ እዛም ጥሩ ነገር እንዳለኝ ተነገረኝ፡፡ በጊዜው ወደ ሁለት መቶ የምንጠጋ ልጆች ነበርን ስልጠናውን እንወስድ የነበረው፡፡ እኔ አንደኛ ነበር የመጣሁት፡፡
ዘሃበሻ፡- ምን ነበር የሚሰጣችሁ ስልጠና?
ስንታየሁ፡- ስለ ድምፅ እንማር ነበር፡፡ ውዝዋዜም ሁሉ ሞክሬያለሁ፡፡ በቡድን በቡድን ተከፋፍለን ውዝዋዜ ሁሉ አቅርበን ነበር፡፡ ከዚያ ወደ ድምፅ ገባሁ፡፡
ዘሃበሻ፡- ከኢትዮጵያ የሙዚቃ አፍቃሪ ጋር ያስታወቀህ ‹‹ሂቦንጎ›› የሚለው ዘፈን ነው፡፡ ‹‹ሂቦንጎ›› ምን ማለት ነው?
ስንታየሁ፡- ሂቦንጎ ማለት ወንዶችና ሴቶች በቡድን ሆነው የሚዘፍኑት ዘፈን ነው፡፡
ዘሃበሻ፡- የሚዘፈንበት የተለየ ወቅት አለው?
ስንታየሁ፡- የተለየ ወቅት የለውም፡፡ ሠርግ ላይ ሊሆን ይችላል፣ አራስ ቤት ሊሆን ይችላል፣ የግርዛት በዓልም ላይ ሊሆን ይችላል ግን ወንዶችና ሴቶች በቡድን፣ በቡድን ሆነው የሚሞጋገሱበት፣ የሚተቻቹበት፣ የሚወራረፉበት፣ ብሎም የከንፈር ወዳጅነት የሚመሰርቱበት ነው፡፡ ግጥም የሚያወርደው ወንድ ከሴቶች መሀል የመረጣትን ያሞግሳታል፡፡ ወይንም ይተቻታል ሴቷም እንዲሁ፡፡ እንዳልኩህ በእዚህ መሀል የከንፈር ወዳጅነትም ይመሰረታል፡፡ ከንፈር ሲሳሳሙ ደግሞ የሴቷ ከንፈር ምልክት እስኪያወጣ ድረስ መሳሳም የሚደረግበት ነው ሂቦንጎ፡፡
ዘሃበሻ፡-‹‹ሂቦንጎ›› የሚለው ዘፈንህ ከኢትዮጵያም አልፎ በውጭ ሀገር እየተደመጠልህ ነው፡፡ ስትሰራው ይህንን ጠብቀህ ነበር?
ስንታየሁ፡- በፍፁም አልጠበኩም፡፡ በእውነት ነው የምልህ የስራው ውጤት እንዲህ ይሆናል የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ ከጠበኩት በላይ ነው የሆነው፡፡ በጣም ብዙ ስልክ ነው አሁን የሚደወልልኝ፡፡ ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎ ች ሁሉ ይደወልልኛል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ሁሉ ይደወልልኝ ነበር፡፡ የዓለም ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ ይካሄድ በነበረበት ወቅት ለስራ ብዙም አይወጡም ነበር፡፡ ‹‹አንድ ቤት ተሰብ ስበን ስራህን እየሰማን ነው›› ብለው የደወሉልኝ አሉ፡፡
ሃበሻ፡- ይህ ዘፈን አንተ በነፃ መስጠትህን አውቃለሁ፡፡ ተሸጧል የሚልም ነገር ሰምቻለሁ፡፡ ስለሽያጩ የምታውቀው ነገር አለ?
ስንታየሁ፡- እኔ አልሸጥኩም፡፡ በሀገራችን ላሉ የመገናኛ ብዙሃኖች ሰጠሁ፡፡ ከእዚህ ውጭ ሆሳዕና ለማውቃቸው ልጆች አንድ፣ ሁለት ሲዲ ሰጥቼ ነበር፡፡ የሚገርምህ ዘፈኑ በሶስት ቀን ውስጥ ነው የሆሳዕና ከተማን ያዳረሰው፡፡ በቅጂ ነው ከተማው የተዳረሰው፡፡ በስፋት የደረሰው በእዚህ ምክንያት ነው እንጂ እኔ አልሸጥኩም፡፡
ዘሃበሻ፡- ግን ደውሎ ያንተን ስራ እንደገዛ የነገረህ ሰው የለም?
ስንታየሁ፡- ገዛን የሚሉ ሰዎች ከሆሳዕናም ሆነ ከተለያዩ አካባቢዎች ይደውሉልኛል፡፡ ‹‹በሃምሳ ብር፣ በመቶ ብር ዛሬ ሲዲህን ገዛን ብለው ደውለው የነገሩኝ ሰዎች አሉ፡፡››
ዘሃበሻ፡- አንተ በነፃ የሰጠኸውን ሌሎች ሸጠው በገንዘቡ ተጠቃሚ በመሆናቸው ምን ይሰማሃል?
ስንታየሁ፡- በጣም ነው እኔ የምቆጨው፡፡ የለፋነው እኛ ነን፡፡ ስራውን በእዛ መልክ ለሙያው አፍቃሪ ለማድረስ ተጨንቀናል፡፡ እንዲህ ሆነን የሰራነውን ስራ ሌሎች እየሸጡ ሲጠቀሙበት እንዴት አይቆጭም? የሰራው እኮ ምንም አልተጠቀመበትም፡፡ የተጠቀመበት ሌላው ነው፡፡ ይህ መሆኑ በጣም ነው የሚቆጨው፡፡
ዘሃበሻ፡- በዘፈንህ ክሊፕ ላይ የውጭ ሀገር ዜጎች አሉ፡፡ እነሱን ማካተቱ ለምን አስፈለገ?
ስንታየሁ፡- ክሊፑ ላይ እንደተመለከትከው ካርታ አሳያቸዋለሁ፡፡ ሃዲያ ውስጥ ያሉ ሲታዩ የሚገባቸውን የቱሪስት መስህቦችን ማለት ነው፡፡ ያንን ለማሳየት ነው የፈረንጆቹን ለመጠቀም የቻልነው፡፡
ዘሃበሻ፡- እነዚህ የውጭ ሀገር ዜጎች በአጋጣሚ በቀረፃ ወቅት የተገኙ ናቸው ወይንስ ታስቦበት ነው እንዲገቡ የተደረገው?
ስንታየሁ፡- ታስቦበት ነው የሆነው፡፡ ካርታውን ለጎብኚዎች እያሳየን የቱሪዝም መስህቦችን የመጠቀም ሀሳቡ ሲመጣልን በእኛው ልጆች ነበር ለመስራት ያሰብነው፡፡ በኋላ ግን ለምን የውጭ ሀገር ሰዎች አይሆኑም የሚል ሀሳብ መጣና ፈረንጆቹን አስገባን፡፡
ዘሃበሻ፡- የ‹‹ሂቦንጎ›› ዘፈን መወደድ፣ ከጠበከው በላይ በሙያው አፍቃሪ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ስንታየሁን ለቀጣይ ስራው ምን ያህል አነሳስቶታል?
ስንታየሁ፡- በጣም ነው ለስራ ያነሳሳኝ፡፡ እኔ አዲስ አበባ ተወልጄ ያደኩት ሆሳዕና ነው፡፡ ቋንቋውን እችላለሁ፡፡ የሚገርምህ እንደ ሂቦንጎ ያልወጡ ጥሩ ጥሩ የባህል ዘፈኖች አሉ፡፡ እነዚህን በጥሩ ሁኔታ አቀናብሮ ወደ አድማጭ ለመስራት በጣም ተነሳስቻለሁ፡፡ ቀደም ሲል እንደነገርኩህ ሂቦንጎ የሚለው ዘፈን ይህንን ያህል ተቀባይነት ያገኛል ብዬ አልጠበኩም ነበር፡፡ የሂቦንጎን ውጤት ላይ ግን የበለጠ እንድሰራ አድርጎኛል፡፡ በቅርቡም አዲስ የሚወጣ ስራ አለኝ፡፡ ‹‹ሸምበላላ›› የሚል ነው ርዕሱ፡፡ በሃዲያኛ ‹‹ሸምበላላ›› ማለት ‹‹ብዙ›› እንደማለት ነው፡፡ የሙዚቃ ክሊፕ ላይ እንዳየኸው ከብቶቹ ላይ ማርና ወተት ነው የሚረጨው፡፡ የሃዲያ አርቢዎች ከብቶቻቸው በቁጥር መቶ ሲሞሉ፣ አንድ ሺህ ሲሞሉ ያስቆጥራሉ፡፡
ዘሃበሻ፡- የከብቶቹ ቁጥር ከመቶ በታች ከሆነ አይቆጠርም?
ስንታየሁ፡- አዎ! መቶ ሲደርስ ነው የሚቆጠረው፡፡ ‹‹ጢቤ ወገንማ›› ነው የሚባለው ሂቦንጎ… ወደ ገጽ 16 የዞረ
ስርዓቱ፡፡ ከብቶችህ መቶ ሲሞሉ ታስቆጥራለህ፡፡ ስታስቆጥር ግን የከሱ ከብቶችና በቅርብ የተወለዱ ጥጃዎች በቆጠራው አይካተቱም፡፡ ደህና ደህና ከብቶች ናቸው የሚቆጠሩት፡፡ በዛ ላይ ‹‹ሸምበላላ›› ይባላል፡፡ ከብቶቹ ብዙ ናቸው እንደማለት ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም የሚዘፈን ዘፈን ነው የሰራሁት፡፡ ‹‹ሸምበላላ›› የሚባል ማለት ነው፡፡ ይህ ዘፈን በቅርብ ይወጣል፡፡
ዘሃበሻ፡- እዚህ አዲስ አበባ የምሽት ክበብ፣ መድረኮች ትሰራለህ?
ስንታየሁ፡- አዎ! እሰራለሁ፡፡ ሠርጎችን፣ የመድረክ ዝግጅቶችንም እሰራለሁ፡፡ በሀበሻ ሬስቶራንትም የምሽት ክበብ እየሰራሁ ነው ያለሁት፡፡
ዘሃበሻ፡- በልጅነትህ ሆሳዕና እያለህ እረኝነት ሞክረሃል?
ስንታየሁ፡- እረኝነት ወጥቻለሁ፡፡ እርሻም አርስ ነበር፡፡ እንጨት እሰብር ነበር፡፡ አጥርም አጥር ነበር፡፡ ያደኩት ገጠር አካባቢ ስለሆነ የገጠር ልጆች የሚሰሩትን ሁሉ ሞክሬያለሁ፡፡
ዘሃበሻ፡- በአያት እጅ ሆሳዕና እንዳደክ ነግረኸኛል፡፡ በአያት እጅ ያደገ ደግሞ ሞልቃቀ ነው የሚባል ነገር አለ፡፡ ስንታየሁ ሞልቃቃ ሆኖ ነው ያደገው?
ስንታየሁ፡- እኔ አይደለሁም፡፡ የሚገርምህ አያቴ ያሞላቅቀኛል፡፡ ግን መቅጣት ካለበት ደግሞ ይቀጣኛል፡፡ በጣም ሀይለኛ ነው፡፡ ያሞላቀቅቀኛል ደግመም ይቀጣኝ ነበር፡፡ በጣም ነው ደግሞ የሚወደኝ፡፡ የሚገርምህ ትንሽ ልጅ ሆኜ አንድ ቀን አንድ ነገር አጥፍቼ ይቀጣኝ ነበር፡፡ እሱ ሲገርፈኝ ጎረቤት አካባቢ የነበረች ሴትዮ ‹‹ቅጣው ይሄ ባለጌ›› እያለች ታያለች፡፡ አያቴ እኔን ገርፎኝ ንዴቱ ከበረደለት በኋላ ቀጥታ ሄዶ ከሴትየዋ ጋር ነው መጣላት የጀመረው፡፡
ዘሃበሻ፡- ለምን?
ስንታየሁ፡- እኔ ተናድጄ ነው፡፡ ልጄን ስገድለው ለምን አትገላግይኝም ብሎ ነው የተጣላው፡፡ እንዳልኩህ አያቴ ቢያሞላቅቀኝም በስርዓቱ እንዳድግ ይቀጣኝ ይመክረኝም ነበር፡፡
ዘሃበሻ፡- ለመዝፈንም የሚያበቃኝ ድምፅ ስላለኝ ወደ ሙያው መግባት አለብኝ ብለህ የወሰንክበትን ጊዜ ታስታውሰዋለህ?
ስንታየሁ፡- እንዳልኩህ ሆሳዕና ከተማ ውስጥ ክበባት የለም፡፡ ችሎታህን የምታወጣበት ነገር የለም፡፡ እኔ ግን ቤት ውስጥ እዘፍን ነበር፡፡ እኔ ቤት ውስጥ ከሆንኩኝ ቴፑ በጭራሽ ዝም አይልም፡፡ የሚገርምህ ከማብዛቴ የተነሳ እናቴ የቴፑን ሶኬት ደብቃብኝ ሁሉ ትሄድ ነበር፡፡ በጣም ነበር የምዘፍነው፡፡ ከቤት ውጭም እዘፍን ነበር፡፡ ድምፄን የሰሙ ሰዎች ‹‹ለምን ዘፋኝ አትሆንም?›› ሲሉኝ ለካ መዝፈን እችላለሁ አልኩኝ፡፡ የወንድ የለ፣ የሴት የለ የሁሉንም ዘፋኞች ዘፈን ማጥናትና መዝፈን፣ እንዲሁም ራሴ መሞከር ጀመርኩኝ፡፡ በኋላ እዚህ አክስቴ ስለነበረች በቀጥታ እሷ ጋር ነው የመጣሁት፡፡ ወ.ወ.ወ.ክ ስልጠናውን ወሰድኩ፡፡ የሚገርምህ ‹‹ሪትም›› ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም፡፡ ግን ስዘፍን ከሪትም ወጥቼ አላውቅም ስዘፍን ‹‹ሜዠርህ›› ምን ላይ ነው? ተብዬ ስጠየቅ ሙዚቃውን አውቀዋለሁ ነበር የምለው፡፡ ‹‹ሜዠር›› ምን ማለት እንደሆነ አላውቅማ! ግን ሙዚቃውን ሲሰሩልኝ ከቅኝት ላልወጣ ነበር የምዘፍነው፡፡ አሁን ሳስታውሰው ለራሴ ይገርመኛል፡፡
ዘሃበሻ፡- ስለዘፈንክ ተብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ምን ያህል ተከፈለህ?
ስንታየሁ፡- በክበብ ውስጥ እያለን የመድረክ ዝግጅት ስንሰራ አስር ወይንም ሃያ ብር ነበር የሚሰጠን፡፡ ከዚያ በኋላ ሠርግ ሰርቼ ሠላሳ ብር ተከፍሎኛል፡፡
ዘሃበሻ፡- ትልቅ ገንዘብ ነበር?
ስንታየሁ፡- አዎ! እናቴ ገንዘብ ትልክልኝ ነበር፡፡ ግን እናቴ ከምትልክልኝ ገንዘብ ይልቅ ሠርግ ሰርቼ ያገኘኋት ሠላሳ ብር ለእኔ ትልቅ ነበረች፡፡
ዘሃበሻ፡- ስንታየሁ የሙሉ አልበም ስራህስ?
ስንታየሁ፡- ቀደም ሲል እንደነገርኩህ ሁለተኛውን ነጠላ ዜማዬን ጨርሻለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ሙሉ አልበም ስራዬ ነው የምሄደው፡፡
ዘሃበሻ፡- እስካሁን በኪነ-ጥበብ መንገድ የተጓዝክበት መንገድ አልጋ ባልጋ ነበር?
ስንታየሁ፡- ብዙ ፈታኝ ነገር ነበረበት፡፡ ጉዞው ቀላል አይደለም፡፡ የምሽት ክበብ ስጀምር የጀመርኩት ዲ-አፍሪክ ሆቴል ነበር፡፡ በሳምንት ሁለት ቀን ነበር የምንሰራው፡፡ ድሮ ስጀምርና አሁን ያለኝ ድምፅ ይለያያል፡፡ አሁን የተሻለ ድምፅ ነው ያለኝ፡፡ ድምፄ የተሻለ እንዲሆን መልፋት ያስፈልገኝ ነበር፡፡ አዲስ ከተማ ወወክማ ስንሰራ ለልምምድ የምንገናኘው ስምንት ሰዓት ነበር፡፡ እኔ ግን ሰባት ሰዓት ተገኝቼ የድምፅ ልምምድ እሰራ ነበር፡፡ ለአንድ ድምፃዊ የድምፅ ልምምድ መስራት የግድ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ እንዳልኩህ በብዙ ልፋት ነው አሁን የደረስኩበት ደረጃ የደረስኩት፡፡ የምሽት ክበብ ስትሄድ አንዱ ጋ‹‹ጥሩ ድምፅ አለህ›› ሊሉህ ይችላሉ፡፡ አንዱጋ ደግሞ ‹‹ዘፋኝ ነኝ ብለህ ነው?›› ሊሉ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን እንደ እሱ አይነት ነገር አላጋጠመኝም፡፡ ግን ልፋት አለው፡፡ ድካም አለው፡፡
ዘሃበሻ፡- ‹‹ሂቦንጎ›› ሙዚቃውንም ክሊፑንም ለመስራት ያወጣችውን ወጭ መልሰሃል?
ስንታየሁ፡- አልመለስኩም፡፡ የክልሉ መንግስት ግን የተወሰነ ግማሽ ብር ሸፍኖልኛል፡፡ ክሊፑ ላይ የለበስኩት ልብስ ደግሞ ውድ ነበር፡፡ መግዛት አልችልም፡፡ እሱንም የሆሳዕና የካቢኔ አባላት ናቸው አውልቀው የሰጡኝ፡፡ በእዚህ አጋጣሚ እነሱንም አመሰግናቸዋለሁ፡፡
ዘሃበሻ፡- እኔ ግን በ‹‹ሂቦንጎ›› ዘፈን መሬት ተሰጥቶታል የሚባል ነገር ሰምቻለሁ?
ስንታየሁ፡- አንተ መሬት ብቻ ነው የሰማኸው?
ዘሃበሻ፡- አዎ! ሌላም አለ?
ስንታየሁ፡- የሚባለው ነገርማ ብዙ ነው፡፡
ዘሃበሻ፡- ምን ምን ይባላል?
ስንታየሁ፡- እንዳልከው መሬት አግኝቷል ይባላል፡፡ ብዙ ብር በሽልማት አግኝቷል ይባላል፡፡ ኧረ ብዙ ነገር ነው የሚባለው፡፡ የሚባለውን ሁሉ ግን እኔ አላገኘሁም፡፡ ከሁሉ በላይ ደስ የሚለኝ ያደኩበትን አካባቢ ባህላዊ ዘፈን በእዚህ መልክ ለሙያው አፈቃሪ ማስተዋወቅ በመቻሌ ነው፡፡ መጀመሪያ የመሬት ሽልማቱን አስቤ አልሰራሁም፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩህም ዘፈኑ እንዲህ ይወደዳል ብዬም አልገመትኩም፡፡ በእርግጥ የሀዲያ ባህሉ፣ ታሪክ ብዙም አልወጣም፡፡ ግን ብዙ ሊያሰሩ የሚችሉ፣ ሊወጡ የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ካልተሰራው ብዙ ነገር እጅግ በጣም ጥቂቱን ለማውጣት ብዬ እንጂ የመሬት ሽልማትን አስቤ አልሰራሁም፡፡
ዘሃበሻ፡- መስከረም 13 እና 14 ሀዲያ ላይ የሚዘጋጅ አንድ ሲምፖዚየም አለ፡፡ እዚህ ላይ ትገኛለህ ብዬ አስባለሁ፡፡
ስንታየሁ፡- በእርግጥ እገኛለሁ፡፡ አዲሱ ነጠላ ዜማዬንም የሰራሁት ለእዛ ነው፡፡ ሰው ለበለጠ ስራ እንዲነሳሳ የሚያደርግም ስራ ነው፡፡ በሲምፖዚየም ላይ በትክክል እገኛለሁ፡፡
ዘሃበሻ፡- ክብደትህ ምን ያህል ነው?
ስንታየሁ፡- መጀመሪያ አንተ ገምት…
ዘሃበሻ፡- ከሰማኒያ እስከ ሰማኒያ አምስት ኪሎ ትሆናለህ ብዬ እገምታለሁ፡፡
ስንታየሁ፡- ክብደቴ አንድ መቶ ሶስት ኪሎ ግራም ነው፡፡
ዘሃበሻ፡- ከባድ አይደል?
ስንታየሁ፡- ቁመቴ ረጅም ነው፡፡ አንተ ገምት ስልህ እስከ ሰማኒያ አምስት ኪሎ ብለህ ነው የገመትከው፡፡ በእርግጥ በወተት ስላደኩ ከልጅነት የመጣ ክብደት ነው፡፡ እንደምታየው ቦርጭ የለኝም፡፡ ስፖርት እሰራለሁ፡፡ ስፖርት መስራት እወዳለሁ፡፡ ከሙያው ውጭ የእረፍት ጊዜዬን የማሳልፈው በማንበብና ስፖርት በመስራት ነው፡፡ ከቁጥር አንድ ጀምሮ የእናንተ መጽሔት አለኝ፡፡ ከፋይል የጠፋብህ ካለ ላውስህ እችላለሁ፡፡ ሌሎችም እንዲሁ አሉ፡፡ ከማንበብ በተጨማሪ የዋና ስፖርት እወዳለሁ፡፡ ጂም እሰራለሁ፡፡
ዘሃበሻ፡- ውፍረት ለጤና ጥሩ አይደለም የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ውፍረት የሟቾች ምልክት ነው የሚሉ ሰዎችም አሉ፡፡ በአንተ እምነት የየትኛው ሀሳብ ነው ልክ?
ስንታየሁ፡- እኔ ውፍረት የምቾት ምልክት ነው አልልም፡፡ ለጤናም ለእንቅስቃሴም ቀልጠፍ ሲባል ነው ደስ የሚለው፡፡ እኔ ስፖርት ስለምሰራ እንደ ክብደቴ አይደለሁም፡፡ ቀልጠፍ ብዬ ነው የምሰራው፡፡
ዘሃበሻ፡- በነገራችን ላይ ‹‹ሂቦንጎ›› የሚለው ዘፈንህ ሀዲያ ውስጥ በመድረክ ለተመልካች አቅርበህ ታውቃለህ? ወይንስ በክሊፑ ብቻ ነው የሚያውቅህ?
ስንታየሁ፡- ዝግጅት ተዘጋጅቶ አንድ ሁለት መድረክ ሰርቻለሁ፡፡ ብዙ ህዝብ የሚሰበስብበት ዝግጅት ነበር፡፡ በእዚህ ዝግጅት ላይ ነው ሆሳዕና ውስጥ የሰራሁት፡፡
ዘሃበሻ፡- እኔ ጥያቄዬን እየጨረስኩ ነው መታለፍ የለበትም የምትለው ነገር አለ?
ስንታየሁ፡- የሚፈቀድልኝ ከሆነ ማመስገን የምፈልጋቸው ሰዎች አሉ፡፡
ዘሃበሻ፡- እድሉን ሰጥቼሃለሁ ቀጥል…
ስንታየሁ፡- አሁን በህይወት የሌለችው ያሳደገችኝ እናቴን ኑራሜ ሎሚሳኮን፣ እንዲሁም እናቴን ቦጋለች ጥላሁንን፣ ወይንሸት ገለታን በጣም ነው የማመሰግናቸው፡፡ ሶስቱም የምወዳቸውና የሚወዱኝ ናቸው፡፡ እንደወለዱኝ ነው የምቆጥረው፡፡ እነሱን በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ሁሉንም አድምጠው በስልክና በአካል አስተያየት የሰጠኝንና መላውን የኢትዮጵያ ህዝብንም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ዘሃበሻ፡- እኔም ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 261

Trending Articles