ከኢየሩሳሌም አረአያ
አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ አሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት ይገኛል። በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ከአርቲስት ጥላሁን ጋር ቃለምልልስ አድርገናል። መልካም ንባብ፤
ጥያቄ፥ እንኳን ደህና መጣህ!
ጥላሁን፥ እንኳን ደህና ቆያችሁኝ! ለነገሩ እኔም እንኳን ደህና መጣችሁ ማለት ይገባኛል። (ሳቅ)
ጥያቄ፥ ለምንድነው እንኳን ደህና መጣችሁ የምትለን?
ጥላሁን፥ አንዳንዶቻችሁ ከእኔ በኋላ ስለመጣችሁ (ሳቅ) እንደዛ ማለት ግን ሁሉንም ሰው አሜሪካ በመምጣት እቀድማለሁ ማለቴ አይደለም።
ጥያቄ፥ ለመጀመሪያ ጊዜ አሜሪካ የመጣኸው መቼ ነው?
ጥላሁን፥ አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣሁት እ.ኤ.አ በ2003 ነው፤ እንግዲህ ለ11 አመት ያህል ወጣ ገባ እያልኩ ነው ያየሁት።
ጥያቄ፥ የቤቶች ድራማ ክፍል 62 እዚህ አሜሪካ ሀገር የተሰራ ነው። አሜሪካ የመጣኸው እሱን ለመስራት ነው እንዴ?
ጥላሁን፥ አይ እኔ በዋነኛነት አሜሪካ ሀገር የመጣሁት ቤተሰቦቼ እዚህ አገር ስለሚኖሩ እነሱን ለማየት ነው። የድራማውም ታሪክ ከእኔ ጋር ተያይዞ ወደዚህ ወደ አሜሪካ የመጣ በመሆኑ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖልኛል።
ጥያቄ፥ እዚህ የሚሰራው ድራማ ይቀጥላል ማለት ነው?
ጥላሁን፥ እንድምታውቁት እዚህ አሜሪካን ሀገር በተለይም ዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ብዙ ኢትዮጵያውያኖች ስለሚኖሩና የተለያዩ የህይወት ገጠመኞችና ታሪኮች ስላሉ ብዙ መስራት ይቻላል። ሆኖም ግን የድራማው ዋና ታሪክ የተመሰረተው ኢትዮጵያ በሚኖሩ ቤተሰቦች በመሆኑ ከተወሰነ ክፍል በላይ መሄድ አይቻልም።
ጥያቄ፥ በአሜሪካ ቆይታህ በቤቶች ድራማ ክፍል 62 የሰራኸው እንዳለ ሆኖ በአጠቃላይ የኢትዮጵያውያንን ኑሮ እንዴት አገኘኸው?
ጥላሁን፥ አሜሪካ በጣም በርካታ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ። እንዲህ ብዙ ኢትዮጵያዊ እዚህ አሜሪካ መኖራቸው በራሱ ደስ የሚል ነው። ከዚህ በተጨማሪ ብዙዎቹ በትምህርት፣ በስራ፣ በሃብት..ወዘተ ጭምር የተሳካላቸው ናቸው። እንዳውም አንዳንዶቹ አገርን በሚያኰራና ለሌሎች ህዝቦች ምሳሌ መሆን በሚያስችል አይነት በሳይንስና በምርምር ስራ ላይ የተሰማሩና በሙያው አንቱ የተባሉ ኢትዮጵያውያኖች አሉ።
ጥያቄ፥ ሌሎች የታዘብካቸው ወይም የገጠሙህ ይኖራሉ?
ጥላሁን፥ በእርግጥ ከቆየሁበት ጊዜና ከአጋጣሚ ሁኔታዎች ተነስቼ በጥልቀት ይሄ ነው ብዬ ለመናገር ባልችልም አብዛኛው ሃበሻ ጠንካራ ሰራተኛ፣ ተረጋግቶ የሚኖር፣ በቂ የሚባል ገቢ ያለውና ለሌሎችም መትረፍ የሚችል ይመስለኛል። ባጠቃላይ ብዙው ተሳክቶለታል። አንዳንዶች ደግሞ ከትምህርቱም፣ ከስራውም፣ ከቋንቋውም ያልሆኑ አሉ። አንዳንድ ወገኖች ጐዳና የወደቁና ለአዕምሮ ህመም የተዳረጉ አሉ። ያሳዝናል!
ጥያቄ፥ አንዳንዶቹ አልተሳካላቸው ብለሃል፤ ምን ይመስልሃል?
ጥላሁን፥ እንደሚመስለኝ አሜሪካ ሀገር ጥሩ ነገር ብቻ ያለበት ሀገር ሳይሆን ውጣ ውረድም ያለበት ነው። ስለዚህ ሁሉም ሰው ይህን ውጣ ውረድ ተቋቁሞ ማለፍ ይችላል ማለት አይደለም። ቋንቋውም እንደዛ ይመስለኛል። አንዳንዶች በተለያየ የህይወት ጫና ምክንያት መማር ያልቻሉ ሰዎች አሉ። አንዳንዶች ደግሞ ለመማርም ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች አሉ። ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት ተግዳሮቱን ጥሰው የወጡ በቁጥር በርካቶች ናቸው። ይሄን ማየት በራሱ እንደ ኢትዮጵያዊነት ያኮራል!
ጥያቄ፥ ወደ ቲያትር አለም እንዴት ገባህ?
ጥላሁን፥ ቲያትር ከልጅነቴ ጀምሮ ከኔ ጋር አብሮኝ ያደገ ነው። በአማተሪዝም ደረጃ ሙያው (ተሰጥኦው) እንዳለኝ ያረጋገጥኩት በቀበሌ ኪነት ውስጥ ነው። ያ የቀበሌ ኪነት የትያትር ሙያ ትወናዬ ብዙም ሳይቆይ ወደ ሀገር ፍቅር ቲያትር ወይም ወደ ፕሮፌሽናሊዝም እንዳመራ ረድቶኛል።
ጥያቄ፥ በቲያትር ሙያ ውስጥ እንድትገባና በውስጥህ ፍላጐቱን የጫሩብህ ባለሙያዎችን ታስታውሳለህ?
ጥላሁን፥ ወጋየሁ ንጋቱና ደበበ እሸቱ ውስጤ ያስቀመጡት ነገር እንዳለ አስባለሁ። በይበልጥ ደግሞ በቀበሌ አብረን ከምንሰራቸው የኪነት አባላቶች ጋር የጸጋዬ ገብረመድኅንን “መልዕክተ ወዛደር”ን በተመለከትኩ ጊዜ ፍላጐቱ ይበልጥ በውስጤ ተቀጣጠለ። ከዚያም እጄን ይዘው ወደ ቲያትር ቤት በመውሰድ ለተዋናይነት መንገዱን የጠረጉልኝ አርቲስት መላኩ አሻግሬ ነበሩ።
ጥያቄ፥ መላኩ አሻግሬ የት አገኙህ? ችሎታህንስ እንዴት አወቁ?
ጥላሁን፥ ከአቶ መላኩ ጋር የአንድ ቀበሌ ነዋሪዎች ነን። በዚያው ቀበሌ ቲያትር ስሰራ ነው የሚያውቁኝ። ከዚያም ወደ ቲያትር ቤት ወሰዱኝ።
ጥያቄ፥ መጀመሪያ መድረክ ላይ የወጣኸው የት ነበር?
ጥላሁን፥ ከቀበሌ በኋላ ለመጀሪያ ጊዜ ቲያትር የሰራሁት በሃገር ፍቅር ነው።
ጥያቄ፥ ቲያትሩ ምን የሚል ነበር?
ጥላሁን፥ የቆሰለች ስጋ..
ጥያቄ፥ ከቀበሌ አማተር ከያኒነት ወደ ፕሮፌሽናል መድረክ መውጣቱ ቀላል ነበር?
ጥላሁን፥ የሚገርምህ ነገር እኔ ሀገር ፍቅር ለመጀመሪያ ጊዜ ቲያትር የሰራሁት እንደአጋጣሚ ነው። አቶ መላኩ ፕሮፌሽናል ቲያትር ሲሰራ ቁጭ ብለህ ተመልከት ብለውኝ ሲለማመድ እያየሁ አጋጣሚ የሚሰራው ተዋናይ ቀረ፤ እሱን የሚተኩት ሁለት ሰዎች ቀሩና ሰው ሲጠፋ አንተ ስራ ተብዬ ወጣሁ። እኔ እየሰራሁ እያለ የቲያትር ቤቱ ስራ አስኪያጅ መጥተው አዩኝና ይህንን ፓርት ከዛሬ በኋላ ይሄ ልጅ ነው መስራት ያለበት ብለው ወሰኑ። እኔም በዛው መድረክ ላይ ቀረሁ።
ጥያቄ፥ በወቅቱ ስትቀጠር ደመወዝህ ስንት ነበር?
ጥላሁን፥ ደመወዜ በመድረክ 25 ብር፣ በወር 100 ብር ነበር የሚከፈለኝ።
ጥያቄ፥ ለረጅም አመት በመድረክ ላይ በርካታ ቲያትሮችን ሰርተሃል። አሁን ደግሞ በፊልም ሙያ ተሰማርተሃል፤ ለመሆኑ ከቲያትርና ፊልም የቱን ታስበልጣለህ? የትኛው ሙያ የአርቲስቱን ችሎታ የበለጠ ይፈትናል ትላለህ?
ጥላሁን፥ እኔ ሁለቱም ሙያ ደስ ይለኛል። የበለጠ ግን የትያትሩን ሙያ እወደዋለሁ። የትኛው የባለሙያውን ችሎታ ይፈትናል ላልከው..ፊልም ስትሰራ ብቻህን እየተቀረጽክ፣ ስህተትም ሲኖር እያረምክ ነው የምትሰራው። ቲያትር ግን አንድ ጊዜ መድረክ ላይ ከወጣህ በኋላ ፊት ለፊትህ ያለው ተመልካቹ ነው። ጥንካሬህንም፣ ድክመትህንም እዛው መድረክ ላይ የምታስመሰክርበት ነው። እናም ቲያትር የባለሙያውን ችሎታ የበለጠ የሚፈትን ይመስለኛል። ባጠቃላይ ፊልም ብዙ አጋዥ አለው። መድረክ ግን ፈተናውም ያንተ ነው፤ የምትወጣውም ራስህ ነህ።
ጥያቄ፥ በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ፊልሞች ይሰራሉ።በርካታ ተመልካቾችም አሉ። ሆኖም የሚሰሩት ፊልሞች እንደብዛታቸው ጥራት የላቸውም እየተባለ ሲተች ይደመጣል። ይህን እንዴት ታየዋለህ?
ጥላሁን፥ ጥራት ሲባል ከምን አኳያ?..ከካሜራ ኤዲቲንግ፣ ከድምጽ.. ባጠቃላይ ከፕሮዳክሽን መሳሪያዎች ነው? ወይስ ከድርሰቱ ነው? አሊያም ከገፀ ባህርይው፣ ከወከለው ተዋናይ ነው?..የቱን ለማለት ነው?
ጥያቄ፥ ሁሉም ላይ የጥራት ችግር ይስተዋላል፤ በተለይ የፊልሙ ታሪክና ፊልሙን ማሳመርና ማስተካከል ያለበት ዳይሬክተሩ ላይ ችግሩ የጐላ ይመስለኛል..
ጥላሁን፥ የፕሮዳክሽን መሳሪያ በተመለከተ በአሁኑ ጊዜ የሰለጠነው አለም የሚጠቀምበትን ስታንዳርድ መሳሪያዎችን እየተጠቀምን ነው። ከቴክኖሎጂው ጋር የተቀራረቡ ባለሙያዎች አሉ። ያልደረሱትም በቅርቡ ወደዚያ ይደርሳሉ ብዬ አስባለሁ። ድርሰትን በተመለከተ እኔም እንደምሰማው አብዛኛው ፊልም ሮማንስ ኰሜዲ ነው ይባላል፤ እዚህ ላይ ሶስት ነገሮችን ማንሳት እንችላለን..
ጥያቄ፥ ምንና ምን ናቸው?
ጥላሁን፥ አንደኛው የሚቀርቡት ፊልሞች በሙሉ ሮማንስ ናቸው ነው የሚባሉት። በእርግጥ ፊልሞቹ ሮማንቲክ ኰሜዲ ናቸው ወይ? ሁለተኛው- ከሆኑስ ደግሞ ተመልካቹ ያለሮማንቲክ ኰሜዲ አያይም ወይ? የመጨረሻው የተለያዩ ቅርፅ ያላቸው የፊልም አፃፃፍ ዘዴዎችን ለምን ማቅረብ አልቻልንም?. የሚሉት ናቸው።
ጥያቄ፥ የሚቀርቡት ፊልሞች ታሪካቸው አንድ ዓይነትና ተመሳሳይ ናቸው ይባላል፤ ይህ ድግግሞሽ ለምን ሆነ?
ጥላሁን፥ እንደሚመስለኝ የሚጽፉት ሰዎች የተወሰኑ መሆናቸው፣ ጥሩ ጥሩ ፀሐፊዎችን ወደ ሙያው ልናስገባ አለመቻላችን ወይም ለሌሎች ፀሐፊያን በራችን ክፍት ያለመሆኑ ይመስለኛል። ሌላው የራሳችንን መንገድ ከመፈለግ ይልቅ አንድ ስኬታማ ፊልም በከፈተው በር ሌሎቻችን እሱን ተከትለን ለማለፍ መሞከራችን ነው። እነዚህ ነገሮች ለታሪኩ መመሳሰል ዋና ምክንያቶች ይመስሉኛል።
ጥያቄ፥ አንዳንድ ጊዜ የፍላጐትና ችሎታ ያለመጣጣም ያለ ይመስለኛል፤ ይህ ነገር በፊልም ስራ ላይ ችግር የፈጠረ አይመስልህም?
ጥላሁን፥ ትክክል ነው! ፍላጐትን ብቻ መሰረት አድርጐ የተነሳ ሰው ባለሙያ አይደለም። ችሎታ፣ ተሰጥኦ ወይም እውቀቱ ሳይኖረው ፊልም ለመስራት የሚነሳ ሰው ህልሙ ዝነኛ መሆን፣ ገንዘብና ክብር ማግኘት ነው። ይሄ ደግሞ የፊልሙን ኢንዱስትሪ ከሚያጫጩት ምክንያቶች ዋነኛው ይመስለኛል።
ጥያቄ፥ አንዳንዶች የፊልሙን ስራ ጠቅልለው ሲይዙ ይታያል። ይሄ ትክክለኛ አካሄድ ነው?
ጥላሁን፥ ለኔ ትክክል አይደለም። አንድ ፊልም ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ የብዙ ባለሙያዎች ሃሳብ፣ ልምድና እውቀት፣ ትምህርትና ችሎታ ሊካተትበት ይገባል እላለሁ። አንድ ሰው ፕሮዲውሰር፣ ዳይሬክተር፣ ተዋናይ፣ ደራሲ ከሆነ በአንድ ሰው ጭንቅላት አንድ ፊልም እንዴት ውጤታማ ሊሆን ይችላል? ባለሙያ ግን ይህን ያደርጋል ብዬ አላስብም።
ጥያቄ፥ ተደጋግሞ የሚሰማው አንዳንድ ሰዎች ገንዘብ ስላላቸው ብቻ ፊልም ለመስራት ይነሳሉ። አንድ ሰው ገንዘብ ስላለው ብቻ ፊልም መስራት ይችላል ማለት ነው?
ጥላሁን፥ ገንዘብ ያለው ሰው እንደ ፕሮዲውሰር ፊልም ቢሰራ መልካም ነው። የፊልሙን ኢንዱስትሪ ማበረታታት ነው። ነገር ግን ገንዘቡን ያወጣው ፕሮዲውሰር “እኔ የፊልሙ ዳይሬክተር ነኝ” ካለ ነው ችግሩ። በአሁኑ ጊዜ ጐልቶ የሚታየውም ችግር ይሄ ይመስለኛል።
ጥያቄ፥ የአገራችንን የፊልም ኢንዱስትሪ በተመለከተ ሁለት አይነት አስተያየቶች ሲሰጡ ይደመጣል። አንዱ- የፊልም ኢንዱስትሪው ገና ጀማሪ ስለሆነ ችግሮች ቢኖሩበትም ወደፊት እያስተካከለ ጥሩ – ጥሩ ፊልሞች ሊመጡ ይችላሉ ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ የጥራት ችግሩ በአፋጣኝ ካልታረመ ተመልካች እየሰለቸና እየራቀ ሊመጣ ይችላል ይላሉ። አንተ እነዚህን ነጥቦች እንዴት ታያቸዋለህ?
ጥላሁን፥ በእርግጥ አንድ አገር ውስጥ የፊልም ኢንዱስትሪን ለማሳደግ ጊዜ ሊሰጠው ይገባል። ፊልሙም ቢሆን በተሰጠው ጊዜ ማደግና ጥራቱን መጠበቅ ያለበት ይመስለኛል። እኔ ይህን ነገር የማየው አንድ ህፃን ተወልዶ ፣ በአንድ ጊዜ ቆሞ አይሄድም። ዳዴ የሚልበት ወቅት ያስፈልገዋል። ልጁ ግን እስከ ስምንት አመቱ ዳዴ ሊል አይገባውም። እናም በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለን ሰዎች ፊልሙ ጥራቱን እየጠበቀ የማደጉን ነገር ልናስብበት ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን እንደተባለው ተመልካቹን ልናጣ እንችላለን። አንድ ጊዜ ህዝቡን ካጣነው ደግሞ ወደፊት ጥሩ ፊልም እንኳ ብናመጣ ተመልካች ልናጣ እንችላለን የሚል ስጋት አለኝ።
ጥያቄ፥ የቤቶች ድራማ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እየተላለፈ ይገኛል። ድራማው ከሌሎች ለየት የሚያደርገው ምንድነው?
ጥላሁን፥ ቤቶች ድራማ የሲቲ ኮም ኰሜዲ ዘውግ የተከተለ መሆኑ ከሌሎች ለየት ያደርገዋል። ይሄ ማለት እያንዳንዱ ክፍል የራሱ የሆነ መልእክት ያለው፣ እያዝናና ቁም ነገር የሚያስጨብጥ ማለት ነው። ታሪኩም በአንድ ቤተሰብ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሆኖ በዛ ቤተሰብ ውስጥ በተለያየ እድሜ ክልል በተለያየ የትምህርትና የእውቀት ደረጃ የግል ባህርያትና የኢኮኖሚ አቅም በአንድ ተጣጥመው የሚጓዙበት የድራማ ቅርፅ ያለው ነው።
ጥያቄ፥ ቤቶች ድራማን ለመስራት ያነሳሳህ ምንድነው?
ጥላሁን፥ አንደኛ በሙያው ያለኝን የረጅም አመት ልምድና ሙያውን ለሚወዱና ለሚያደንቁ ሰዎች ለማስተላለፍ..ሌላው ትልልቅ ሰዎች፣ በመካከለኛ እድሜ የሚገኙ ወጣቶችና ህፃናት ያለ ልዩነት፣ ያለመተፋፈርና ያለመሳቀቅ ሊያዩት፣ ሊመለከቱት የሚገባ ድራማ ያስፈልጋል ብዬ አምን ስለነበረ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ጤነኛ ቤተሰብ የህብረተሰባና የሀገር መሰረት ነውና በዚህ ድራማ በመጠኑም ቢሆን ዜጋን መቅረፅ ይቻላል ብዬ ስላሰብኩ ነው።
ጥያቄ፥ በቤቶች ድራማ ውስጥ የምትወደውና የምታደንቀው ገፀ ባህርይ ማነው?
ጥላሁን፥ በይበቃልና በምዕራፍ መካከል ምን ልዩነት አለ? በርስቴና በበዛብህስ መሃከል እንዴት ልዩነት ይፈጠራል? እንዳልክንም አትርሳ። ዋናዋስ አዛልዬ? ትርፌም እኮ ስጋዬ ናት። ሻሾስ ብትሆን ምንዋ ይጠላል? የእከ’ንማ ነገር ተወኝ.. እኔ ከምወደው በላይ ሳይወደኝ ይቀራል!?..ጋሼ እኮ ከአፉ አይጠፋም። ..ለማንኛውም ሁሉንም እኩል እወዳቸዋለሁ!
ጥያቄ፥ ከአርሰናሉ ኢንተርናሽናል ተጨዋች ጌዲዮን ዘላለም አባት ጋር ስታወሩ ነበር። ስለምንድን ነበር የምታወሩት?..በቤቶች ድራማ ላይ አሳትፈኸዋል።
ጥላሁን፥ አዎ ተገናኝተን በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ አውርተናል። ቤቶች ድራማን በተመለከተ ያለውን አስተያየት ሰጥቶኛል። ወደፊት እንደሁኔታው የሚቀርብ ይሆናል።
ጥያቄ፥ እዚህ አሜሪካ ብዙ ህፃናቶችና ታዳጊ ወጣቶች አብረውህ ፎቶ ሲነሱና “ዘሩ ቀለጠ..እውነት አሜሪካ መጥተሃል?” እያሉ በአድናቆት እንደሚያናግሩህ ሰምተናል። ምን ተሰማህ?
ጥላሁን፥ ብዙ ኢትዮጵያውያን በተለይም ህፃናቶችና ታዳጊ ወጣቶች ይህን ድራማ በመከታተላቸው በጣም ደስ ብሎኛል! እዚህ አሜሪካ የተወለዱና ያደጉ ህፃናቶች ስለሀገራቸውና ስለማንነታቸው የማወቅ ፍላጎት አድሮባቸው በማየቴ በጣም አስደስቶኛል።
ጥያቄ፥ ከድራማው ጋር በተያያዘ ብዙ አድናቂና ተከታይ ይኖረኛል ብለህ አስበህ ነበር?
ጥላሁን፥ ያሁኑ በጣም የተለየ ነው። ለምሳሌ እናንተም አሁን አብረን ሆነን እንደሰማችሁት በቤቶች ድራማ ምክንያት አማርኛ ቋንቋ መልመድ የጀመሩም ህፃናትና ታዳጊ ልጆች እንዳሉ ተረድቻለሁ። ሌላው ያስደሰተኝ ደግሞ አንዲት አማርኛ የማይችሉ ኤርትራዊት እናት ቤቶች ድራማን እያዩ አማርኛ ቋንቋ እየለመዱ መሆናቸው ነው።
ጥያቄ፥ የሙያህ አድናቂዎችና አፍቃሪዎች እንዳሉ ሁሉ አንዳንዶች ደግሞ ቅሬታ ያላቸው አሉ..
ጥላሁን፥ ቅሬታ ስትል ምን ማለትህ ነው? ከሙያው ጋር የተገናኘ ነው ወይስ በግል?..አልገባኝም፤
ጥያቄ፥ ቅሬታ አቅራቢዎቹ አንድ ድራማ ላይ ስለ ኦርቶዶክስ አባቶች የማይገባ ንግግር ተናግረሃል በሚል ነው።
ጥላሁን፥ አንደኛ በቅርቡ የሚለው ስህተት ነው። ይሄ የተባለው ድራማ የተሰራው በ1993ዓ.ም ነው። ከዛሬ 13 አመት በፊት ማለት ነው። ይሁንና ከ13 አመት በፊትም ቢሆን በማንም ላይ ያልተገባ ንግግር መናገር አለብኝ ብዬ በጭራሽ አላምንም። አልተናገርኩምም።
ጥያቄ፥ እንዳውም “የኦርቶዶክስ አባቶች ገዳዳ ነገር ይዘው- ትውልዱን አንጋደዱት” ብላሃል ነው የተባለው።
ጥላሁን፥ ፈፅሞ ስህተት ነው! ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቀደምትና ከክርስቶስ ልደት ጀምሮ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ጠብቆ ለዚህ ትውልድ ያስረከበ ሀይማኖት ነው። እኔም ሆንኩ ሌሎቻችን የተገኘነው ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነው። ባጠቃላይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የታሪካችን፣ የባህላችን፣ የማንነታችን መነሻ መሰረት ነው። እኔም ራሴ ከዛፍ ላይ የተሸመጠጥኩ ሳይሆን ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት የተገኘሁ ነኝ። ለኔ ኦርቶዶክስን መሳደብ ማለት ወልዳ ያሳደገችኝን እናት እንደመሳደብ ያክል እቆጥረዋለሁ! ሰው እናቱን ይሳደባል?..በጭራሽ!
ጥያቄ፥ ታዲያ ይህ ነገር ከየት መጣ?
ጥላሁን፥ የዛሬ 13 አመት የተሰራን ድራማ አንስተው ልክ ዛሬ እንደሆነ በማስመሰል፣ በጭራሽ ያላልኩትን “አለ” እያሉ..እኔን ከህዝቡ ጋር ለማጋጨትና ስሜን ለማጥፋት የሚሞክሩ ጥቂት ሰዎች ያቀነባበሩት ተንኮል ነው። እነዚህ ግለሰቦች የተለየ ፍላጐትና አላማ ያላቸው ናቸው። ….ያም ሆኖ የኦርቶዶክስ አባቶችና ሊቃውንቶች ይህንን ድራማ አይተው “ይህን የሚመስል ነገር አለው” ካሉኝ ለመታረምና በይፋ ይቅርታ ለመጠየቅ ዝግጁ ነኝ።
ጥያቄ፥ በድራማው ላይ እኮ “ትውልዱን ያንጋደድነው እኛ ነን” ብለሃል፤
ጥላሁን፥ ያ ማለት በድራማው በተፈጠረው ታሪክ ላይ ሁለት ውጭ ሀገር ያሉ አባቶች ሲነጋገሩ ትውልዱን አንጋደድነው ብለው ስለራሳቸው አባትነት ነው እንጂ የሚነጋገሩት ፈፅሞ የኦርቶዶክስ አባቶች አይልም። ሰው ያላለውን ነገር አለ በማለት ነገር እየሰነጠቁ በውሸት መክሰስና ስም ማጥፋት እግዜአብሄርም የሚወደው ነገር አይደለም። ደግሞም ኢትዮጵያ የሃይማኖት እኩልነት ያለባትና ሃይማኖቶች ተቻችለው የሚኖሩባት አገር ናት። ሀይማኖት የግል ነው፣ አገር የጋራ ነው እንደሚባለው፥ ሰው የፈለገውን ሃይማኖት የመከተል መብት አለው። ይህ ሲሆን የሌላውን እምነት ማክበር ግድ ነው። እኔ ግን በግሌ፥ ክርስቲያን- ክርስቲያን ነው ብዬ ነው የማምነው።
ጥያቄ፥ በአርቲስትነት ሙያህ ለረጅም አመት እንደማገልገልህ በነዚህ አመታት የሚይስቅ ወይም የማልረሳው የምትለው ገጠመኝ ካለ?
ጥላሁን፥ ከ26 አመት በፊት ቲያትር ለመስራት ወደ መተሐራ ሄድን። እኔ ፕሮግራም ለመስራት ወደ አዋሽ አርባ መጓዝ ነበረብኝ። ፕሮግራሙን ሰርቼ ስመለስ ትራንስፖርት አጣሁ። በእለቱ በሚቀርበው ቲያትር ላይ መሪ ገፀ ባህርይውን ወክዬ የምጫወተው እኔ ነኝ። ..በመጨረሻ አንድ አነስተኛ መኪና ተገኘች። እንዲጭኑኝ ሾፌሩን አናገሩት። ከሹፌሩ አጠገብ መቀመጫ የለውም። ከኋላ ደግሞ አስከሬን ነው የጫነው። አማራጭ ስላልነበረኝ ከኋላ አስክሬኑ አጠገብ ተቀምጬ 4 ኪ/ሜትር (ከበድን አስክሬን ጋር) ተጓዝን። ይህ የማልረሳው ገጠመኜ ነው።
ጥያቄ፥ በመድረክ ላይ የገጠመህ ይኖራል?
ጥላሁን፥ የዋርካ ስር ምኞት የተባለው ቲያትር ጣሴ የሚባል ሰፊ ቁምጣ የለበሰ ሞኝ ገፀ ባህርይ ወክዬ ነበር የምጫወተው። አንድ እሑድ ተመልካቹ እያየ ድንገት የእኔ ቤት ወደቀ፤ ከዛ..”አባባ..አባባ.. ጅል ነው ብለው ቤቴን አፈሩሱት..አባባ ድረሱልኝ ” አልኩኝ። መጋረጃው ተዘጋና ቤቱ እንደገና ተሰርቶ ቲያትሩ ቀጠለ። በሳምንቱ በድጋሚ የገቡ ተመልካቾች “ቤቱ ያልወደቀው ረስታችሁት ነው?” ብለው ጠየቁን። ቤቱ መፍረሱ የድራማው አንድ ክፍል መስሎአቸው ነበር ለካ።
ጥያቄ፥ ከቲያትር፣ ከፊልምና ማስታወቂያ ስራ ውጭ በትርፍህ ጊዜህ ምን ታደርጋለህ?
ጥላሁን፥ ብዙ ትርፍ የሚባል ጊዜ የለኝም። ትምህርት ቤት እሄዳለሁ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ አመት የቲያትርና የስነፅሑፍ ተማሪ ነኝ። ከዛ በተረፈ በትርፍ ጊዜዬ እግር ኳስ አያለሁ።
ጥያቄ፥ መጽሐፍ ማንበብ ላይ እንዴት ነህ?
ጥላሁን፥ ባገኘሁት አጋጣሚ መጻሕፍቶችን አነባለሁ። በተለይ መፅሐፍ ቅዱስ ማንበብ ደስ ይለኛል። የገባኝንም የወንጌል ቃል ለሌሎች አካፍላለሁ።
ጥያቄ፥ በመጨረሻ የምታስተላልፈው መልእክት…
ጥላሁን፥ እኛ አሁን ያለነው ትውልዶች በሁሉም መስክ የሚያስከፍለንን ዋጋ ከፍለን የተሻለች ኢትዮጵያን፣ ያደገችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ሁላችንም በተሰማራንበት መስክ- ነገን እያየን ባለመሰልቸትና ባለመታከት የሚጠበቅብንን በማድረግ የዜግነት ግዴታችንን እንወጣ እላለሁ።