ቴዲ አፍሮ የሂልተኑ የሰርጉ ቀን እናቱ ራዬ ግጥም ለታዳሚው አቅርባ ነበር፡፡ ‹‹እንደ ልጄ ግጥም ባያምርልኝም አድምጡኝ›› ስትል ያቀረበቻቸው ለትውስታ ግጥሞች እነሆ፡-
ይህ ነው- ሽልማቴ
ባባትና ባያት………….. ቅድመ አያቶቻችን
ጥንት የሚታወቀው…………..ወጉ ባህላችን
ለአብራካቸው ክፋይ…………..የወላጅ ስጦታ
ነበር ቋሚ ንብረት…………..መሬትና ቦታ
እኔስ ግን ለልጄ…………..የጋብቻው ለታ
ባለበሰኝ ፍቅር…………..በሰጠኝ አለኝታ
በስስት ዓይኖቼ…………..በእናት አንጀቴ
ሌላ ምንም የለኝ………….. ይህ ነው ሽልማቴ
ቴዲዬን ስወልደው
ቴዲ በዚህች ምድር………….. ገና ሳይፈጠር
እኔና ካሳሁን………….. ተፋቅረን ስንኖር
ቤታችን ነበረ………….. ተድላ የደስታ
ፍፁም የተሞላ………….. በጥበብ ጠብታ
ታዲያ ያን ጊዜ …………..በጠባቧ ክፍል
ነበር ቁም ሳጥን ላይ………….. የአጤ ቴዎድሮስ ምስል
የግዜር ፈቃድ ሆኖ ………….. ወንድ ልጅ ከሰጠኝ
ስሙ ቴድሮስ ነው ………….. ብዬ ተመኘሁኝ
ፈጣሪም ደግ ነው………….. ልመናዬን ሰማ
ብላቴናው ቴዲ………….. ጥሪውን አሰማ
ህፃኑ ቴድሮስ………….. የካሳንም ይዞ
ረጅሙን መንገድ…………..ተጉዞ ተጉዞ
ይኸው እዚህ ደርሷል………….. ዛሬ በጥረቱ
ምን ልስጠው ለልጄ………….. ስም ነው ሽልማቱ
ቴዲን ስናንፀው
ምንጊዜም………….. ስምህ ያኮራኛል
ምኞትህ ተሳክቶ………….. ለዛሬ አብቅቶኛል
ልጅህን ቀርፀኸዋል………….. አናፂው አንተ ነህ
የድካምህን ፍሬ………….. ማየት ባያድልህ
ከመቃብር በላይ………….. ስምህ ገኖልሃል
የድካምህ ፍሬ………….. አጎምርቶልሃል
ቴዲዬን ሳስበው
እንደዛሬው ሳይሆን………….. ቴዲ ሳያገባ
እኔው እናቱ ቤት………….. ሲወጣ ሲገባ
እሳሳለታለሁ………….. በእናትነት ዓይኔ
ባይርቅ ደስታዬ ነው………….. ሁልጊዜም ከጎኔ
ቴዲን በዚያች ሰዓት
ቴዲዬ ነፍስ አውቆ…………..ዝናውም ሲመጣ
ያላሰብኩት ነገር………….. ድንገት ፈጥኖ መጣ
ብላቴናው ቴዲ…………..ከናቱ ተሽሎ
ችግር መከራውን………….. ወጣው ሁሉን ችሎ
ልጄን በዚያች ሰዓት………….. መልሼ እንዳልውጠው
ወይ እንደመቤት………….. ችዬ ሳልደብቀው
የህዝብ ፍቅር ሰጥቶት………….. እሱም ፍቅር ይዞ
ይኸው ለዚህ በቃ………….. ያን ሁሉ ተጉዞ
ሸክሜ ቀለለ
ልጄ በሙዚቃው………….. እንዳቀነቀነው
ምትክ ስጠኝ ብሎ………….. ፈጣሪን ለመነው
ብላቴናው ልጄ………….. በጠዋት ታደለ
የራዬን ስጦታ………….. ዛሬ ተቀበለ
ፈጣሪም ሰጥቶሃል………….. ጥሪህን አድምጦ
ፀባየ ሰናይ ልጅ………….. ለግሶሀል መርጦ
ቴዲ ከትላንቱ………….. ዛሬ ነፍስ አወቀ
በሄዋን ደም ግባት………….. ፀዳሏ ደመቀ
ምትኬ አምለሰት………….. ሰጠሁሽ አደራ
አንቺም በእሱ ኩሪ………….. ቴዲም በአንቺ ይኩራ
እናም በዚህች ዕለት…………..በመስቀል ዳመራ
ፍቅራችሁ ይፈንጥቅ………….. በቀንዲል ላይ ይብራ
ምኞቴን ተመኙት…………..ሀሳቤን ሙሉልኝ
በህይወት እያለሁ………….. የልጅ እናት አርጉኝ
ያብርሃም የሳራ………….. ይሁን ጋብቻችሁ
ይህ ነው ስጦታዬ…………..…………..እኔ የእናታችሁ፡፡
መስከረም 17 ቀን 2005
አዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ቀረበ