Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Entertainment
Viewing all articles
Browse latest Browse all 261

“ጥሬ ሥጋ መብላት ካቆምኩ በኋላ ውፍረቴ ቀንሷል…”ድምፃዊ ታምራት ደስታ (ቃለምልልስ)

$
0
0

ከቁምነገር መጽሔት ጋር የተደረገ

ታምራት ደስታ ከዚህ ቀደም ለአድናቂዎቹ ባደረሳቸው የሙዚቃ አልበሞቹ ይታወቃል፡፡ በተለይ አንለያይም የተሰኘ አልበሙ በብዙ አድናቂዎቹ ተወዶለታል፡፡ ከዚህ ቀደም ከሰራኋቸው ዘፈኖች በተሻለ የተዘጋጀሁበት ነው ያለውን ‹ከዛ ሰፈር› የተሰኘ አዲስ አልበም በያዝነው 2007 ዓ.ም ለገበያ ባቀረበበት ማግስት የመሿለኪያ አምዳችን እንግዳ አድርገነዋል፡፡
Tamrat Desta
ቁም ነገር፡- ሰሞኑን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳልነበርክ ሰምተናል፡ ፡ የት ነበርክ?
ታምራት፡- በስራ ጉዳይ እና በግል ምክንያት አውሮፓ ነበርኩኝ፡፡
ቁም ነገር፡- ምን ያህል ጊዜ ቆየህ?
ታምራት፡- ብዙ አይደለም፡፡ አንድ ሶስት ወር ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ከዛ ሰፈር የሚለው አዲሱ አልበምህ የወጣው እዛው ሆነህ ነው ማለት ነው?
ታምራት፡-አዎ
ቁም ነገር፡- አልበሙ ከወጣ በኋላ እዚያ የነበረው ስሜት ምን ይመስል ነበር?
ታምራት፡- በጣም ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም እዚያ ካሴቶች ቶሎ ይደርሳሉ፡፡ ሲጀመር አሳታሚውም ናሆም ሪከርድስ ስለሆነ ናሆም ብዙ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ በአውሮፓም በአሜሪካም በተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራትም ብዙ ማከፋፈያዎች ስላሉት አቀባበሉ በጣም አሪፍ ነው፡፡ ስዊዘርላንድ ጀርመን ጣልያን አካባቢ ነበርኩኝ፡፡
ቁም ነገር፡- እዚህ ኢትዮጵያ ከመጣህ በኋላስ አልበምህ ያለበትን ደረጃ እንዴት አገኘኸው? እየተደመጠ ነው?
ታምራት፡- አውሮፓ ሆኜ እዚህ የአልበሙ ፕሮሞሽን ስላልተሰራ ብዙ ሰዎች ጋ እንዳልደረሰ ሰምቼ ነበር፤ አሁን ከመጣሁ በኋላ ግን ያው ቪዲዮዎ ክሊፖችን አዘጋጃሁኝ ነው፡፡ እ…የተለያዩ ሬዲዮ ጣቢያዎች ጋር አንዳንድ ማስታወቂያዎችን ሰራን፤ ከዛም ባለፈ ግን ራሴ ቃለመጠይቅ እየተደረግኩኝ ስለ አልበሙ ተናግሬያለሁኝ፡፡ በሙዚቃ ቤቱም በኩል ያለው ነገር በጣም አሪፍ ነው፡፡ ወደ ህዝቡ እየደረሰ ነው፡፡ ስራዎቹ ሲሰሙ ያምራሉ፡፡ የሚያምርና ቆንጆ የሆነ ስራ ባልሰራ ወደ ህዝቡ አልመጣም፡፡ ያልሰሙትም ሰዎች ካሉ ሰምተው ወደዉት አስተያየታቸውን እንደሚሰጡኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- አልበምህን ለማዘጋጀት ምን ያህል ጊዜ ወሰደብህ?
ታምራት፡- ዝግጅት ሳደርግ እንግዲህ ብዙ ጊዜ ቆይቼአለሁ፡፡ ለነገሩ የቆየሁት ዜማዎችና ግጥሞችን በመምረጥ ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች ስራዎች ስለነበሩኝ፤ እንደገና በዚህ በቅጂ መብት በኮፒ ራይት ዙሪያ ደስ የሚል ነገር ስላልነበረ ያ ነገር ከዛሬ ነገ ይሻሻላል ለውጥ ይመጣል በሚል ጊዜዬን ተሸሻምቶብኛል፡፡
ቁም ነገር፡- ሁለተኛ አልበምህ ከወጣ ስንት ዓመት ሆነህ?
ታምራት፡-ሁለት ሺህ ላይ ነው ያኛውን አልበም ያወጣሁት፤ በመሃል ግን ዘፈኖች አሉ፡፡ አዳዲስ ዘፈኖች ክሊፖች ምናምን ሰርቼያለሁ፡፡በዚያኛውና በዚህኛው አልበም መካከል የሰባት ዓመት ልዩነት አለ፡፡ የዚያኔ የምሰራቸው አልበሞች ደግሞ የዚያን ዘመን አሻራ ጥለው እንዳለፉ ሁሉ ይሄም ደግሞ የራሱ ዘመን አለው፤ የምትሰራበትም ስሜት ደግሞ እንደዛሬ እንጂ እንደትናንት አትኖርም.. (ሳቅ…) ምን ለማለት ፈልጌ ነው ያመንኩበትን ስራ ነው ወደ ህዝቡ ያመጣሁት፡፡ እርግጠኛ ነኝ ደግሞ አሪፍ አልበም ነው፡፡
ቁም ነገር፡- በቀደሙ አልበሞችህ ውስጥ ለፍቅር ዘፈኖች የምትሰጠው ትኩረት ከፍ ያለ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በአሁኑ አልበምህስ ለፍቅር የሰጠኸው ቦታ ምን ይመስላል?
ታምራት፡-ከፍቅር በላይ ምን አለ ብለህ ነው (ሣቅ…) ፍቅር ማለት በእኔ እይታ ራስን ለሌላው አሳልፎ መስጠት ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍም እንደምናውቀው የፍቅር ጥጉን አይተነዋል፡፡ ስለዚህ ማህበራዊ ሕይወትና ፍቅር ላይ ትኩረት አደርጋለሁ፡፡ እነሱን መስበክ ያስደስተኛል፡፡ ምክንያቱም ሰው መጀመሪያ አስተሳሰቡን ነው መቀየር ያለበት፡፡ ከጥላቻ ይልቅ ወደ ፍቅር መምጣት አለበት፡ ፡ አንድ ድርጊት እንኳን ከማድረጋችን በፊት መጀመሪያ አዕምሮአችን ለክፋትም ይሁን ለቅንነት ለጥላቻም ይሁን ለፍቅርም አዕምሮአችን ውስጥ ነው የሚታሰበው፡ ፡ ስለዚህ ሁልጊዜ አስተሳሰባችንን ሊለውጥ የሚችል እ…በዘፈንም ይሁን በተለያዩ ጥበብ ነክ ነገሮች ማህበረሰቡን መደገፍና ምናልባት ተናግረው ማሳመን የማይችሉ ብዙ ሰዎች ይኖራሉ ፤አንደበታቸው ቢዘጋ ያው እንግዲህ በዘፈን ስታቸውን ይገልፃሉ፡፡ …የተለያየ ይህን ፊልም እይልኝ ይህን ዘፈን አዳምጪልኝ የሚባሉ ነገሮች አሉ፡፡ ፍቅር የማያረጅ ነገር ነው፤ አያረጅም፡፡ ከፍቅር ውጪ ሁሉ ነገር ከንቱ ይመስለኛል፡፡ ለዛነው እኔም እዚህ ላይ ትኩረት አድርጌ የምዘፍነው፡፡ ይህንን ስል ደግሞ ሌሎች ነገሮችን አላነሳም ማለት አይደለም፡፡ ብዙ የተነሱ ጉዳዮች አሉ፡፡ አዲስ አበባ ሌላ ጉዳይ ነው፤ የጎጃም የባህል ዘፈን አለ(የፍቅር ቢሆንም)፤ ማማዬ የሚለውም ስለእናት ይሆንና ከሴትና የወንድ ግንኙነት ወጣ ይላል፡፡እናት ላይ ያተኮረ ዘፈን ነው፡፡ ትራክ(ቁጥር) አስራ አራት ላይ ብታይ ደግሞ ለምኔ የሚል ዘፈን አለ፡፡ እዚያ ላይ የአንት ፍልስፍና አንተን አመለካከት ነገሮችን ሁሉ እንዴት ወደ ቅንነት እንዴት ወደ በጎ ምግባር ማምጣት እንደሚቻል የሚያሳይ ዘፈን ነው፡፡
ቁም ነገር፡- አንድ አልበም ሲዘጋጅ ከፍተኛውን ተጽእኖ መውሰድ ያለበት ማን ነው ድምጻዊው ነው ወይስ የግጥምና ዜማ ደራሲው?
ታምራት፡-ዘፈን ማለት የጋራ ስራ ነው እንደ እግር ኳስ በጋራ የሚሰራ ስራ ነው፡፡ ስለዚህ የግጥምና የዜማ ደራሲዎቹ መኖር አስፈላጊ ነው፤ቅንብሩ የድምጽ ጥራቱ እነዚህ ሁሉ መጉደል የለባቸውም፡፡ የሁሉም አስተዋጽኦ አለበት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የጋራ ስራ እንደመሆኑ ተስማምተን ነው የምናደርገው፡፡ ወደ ድምጻዊው ስትመጣ ዜማና ግጥሙን የመምረጥ መብቱ የድምጻዊው ነው፡፡ የማይፈልጋቸው ዜማና ግጥሞች ከሆኑ አይመርጣቸውም፡፡ አቀናባሪም ደግሞ አንተ የሚመችህን አይነት ነገር ትንሽ ፍንጭ ከሰጠኸው አሪፍ አድርጎ ሊሰራልኽ ይችላል፡፡ ስለዚህ የብዙ ሰው እጅ ይጠይቃል፡፡

ቁም ነገር፡- ምናልባት ይህንን ያነሳሁት የአሁኑ አልበምህ በተለመደው የዜማና ግጥም ደራሲ የተሰራ ስላልሆነ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በነበራችሁ ግንኙነት ታምራት ደስታ ሲነሳ የብዙ ግጥምና ዜማዎቹ ደራሲ የሆነው ሀብታሙ ቦጋለ ይነሳል፡፡ የእርሱ ስራዎች ለምን አልተካተቱም? ከዚህ ጎነን ለጎንም ከእርሱ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ሰላማዊ ነው?
ታምራት፡-አይ… ያው ሀብታሙም አለ ዳግማዊ አሊ አለ፡፡ እነዚህ ሰዎች ማለት ለኔ እዚህ ጋ መድረስ ትልቁን ሚና የተጫወቱ ናቸው፡፡ እ… ምንድነው እርሱ አሁን ወደዚህ አልበም ስመጣ አንደኛ ሳውንድ ለመቀየርም ነው፡፡ ማለት በተለመደ ነገር ከመሄድ ውጪ የሰው ጆሮ አዲስ ነገር መስማት ይፈልጋል፡፡ የሰው ዓይን ደግሞ ሁሌም አዲስ ነገር ማየት ይፈልጋል፡፡ ከዚህ አንጻር የራሴን ምልከታ ዓይቼ ይሄን ነገር እንዲህ ባደርግ ይሻላል በሚል እንጂ ከእነርሱ ጋር እንደቀድሞው ሳልገናኝ ወይም በሌላ ምክንያት አይደለም፡፡ በአዲሱ አልበም ውስጥ የተካተቱት ሰዎችም ቢሆኑ ለተለያዩ ሰዎች ግጥምና ዜማ የሰሩ ናቸው፡፡ ጌትሽ ማሞ አለ፤ አማኑኤል ይልማ አለ፤ መሰለ ጌታሁን አለ፤ ኤፍሬም ዳምጠው አዲስ ልጅ ነው፡፡ እዮቤል ብርሃኑ …እነዚህ እነዚህ ጎበዝ ልጆች ናቸው፡፡ እድሉንም ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ለእነርሱም መስጠት ጥሩ ነው፡፡ ሁል ጊዜ አንድ አቅጣጫ ብቻ የምናይ ከሆነ መልካም አይደለም፡ ፡ ሌሎች አቅጣጫዎችን መመልከት አለብን፡፡ እኔ ደግሞ የዜማም ደራሲ ነኝ፡፡ እኔ ራሴ አልተሳተፍኩም፤ ሀሳቤን ብቻ አክያለሁኝ እና አንዳንድ የዜማ ማጠፊያዎችን፤ አዝማች፤ አንዳንድ የመሃል ዜማዎችን የማስተካከል፤ ወደ መሃል የማምጣት… እንጂ ከዚያ ውጪ ሁሉንም ስራ ሌሎች ሰዎች ናቸው የሰሩት፡፡ ትልቁን ቦታ የሚወስደው ጌትሽ ማሞ ነው፡፡ ከዚያ አማኑኤል አለ፤ መሰለ ጌታሁን አለ፤ እዮቤል ብርሃኑ አለ በግጥም፡፡ እና ኤፍሬም ዳምጠው፡፡ እነዚህ ሁሉ ልጆች ጎበዞች ናቸው፡፡ ከእነርሱም ጋር በመስራቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

ቁም ነገር፡- በዚህ አልበምህ ላይ አዲስ አበባን አንስተሃል፡፡ ከዚህ በፊት ደግሞ በጋራ በተሰራ ነጠላ ዜማ ወላይታን አንስተሃል፡፡ እ… የጎጃምና የወሎ ዜማዎችን እንዲሁም ስለ ድሬዳዋም ዘፍነሃል፡፡ ከዚህ በኋላስ የሚዘፈንለት ተረኛው ከተማ ማን ይሆን?
ታምራት፡-አሁን ለምሳሌ ስለዚህ ከተማ እዘፍናለሁ ብለህ አይደለም የምትዘፍነው፡፡ በወቅቱ እዛ ከተማ ላይ ሄደህ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይ ደግሞ ኖረህ ሊሆን ይችላል፡፡ እ…እንደገና ደግሞ የተለያዩ ገጠመኞች ይኖሩሃል፡፡ እንግዲህ ከምታነበውም ከምታየውም ነገር የተነሳ ማለት ነው፡፡ ሀዋሳን ብትል ሀዋሳ እና ሻሸመኔ የትውልድ አካባቢዎቼ ናቸው፡፡ ድሬዳዋ ደግሞ የኖርኩበት በልጅነቴ ሄጄ ሙዚቃም የጀመርኩበት ሃገር ነው፡፡ የተለየም ፍቅር አለኝ፡ ፡ አዲስ አበባ ብትል ደግሞ ሰርቼ የተለወጥኩበት፤ ከህዝቡ ጋር ተስማምቼ የኖርኩበት፤እ..ብዙ ፈተናም የተፈተንኩበት ፤በፍቅርም ህይወቴ ይሁን በተለያዩ ነገሮች ብዙ ነገር ያየሁበት ከተማ ነው፡፡ ስለዚህ የዚህ ከተማ ትዝታው እና አሻራው በውስጤ አለ፡ ፡ ከተማውን ስታስብ ህዝብ አለ፡፡ ህዝብ ደግሞ ተቀብሎ እዚህ አድርሶኛል፡፡ ነገም እንግዲህ በተለያዩ አጋጣሚዎቸች ማንሳት የምፈልጋቸው ጉዳዮች ካሉ እ… በዘፈን መልክ አንስቼ ለሰዉ ላቀርብ እችላለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- በዕድል ታምናለህ ታምራት?
ታምራት፡-እ.. አስራ አምስት በመቶ ምናምን፤ እንጂ እኔ ሰማኒያ አምስት በመቶ በስራ ነው ብዬ ነው የማምነው፤ ከመሬት ተነስቶ የሚፈጠር ነገር የለም፡፡ እጅህን አጣጥፈህ ቁጭ ብለህ ከሰማይ መና እንዲወርድልህ የምትጠብቅ ከሆነ ምናልባት ሌላኛውን ዓለም መምረጥ አለብህ፡ ፡ ምክንያቱም ሰው ጥሮ ግሮ እንዲበላ ነው ከአዳም ጀምሮ የምናውቀው እና በመስራት አምናለሁኝ፡ ፡ እ… በመስራት የማመኔ ትልቁ ምክንያት ደግሞ ያለፍኩትን ጎዳና ስለማውቅ ነው፡፡ ስለዚህ ለዕድል ከሃያ እና ከሰላሳ በመቶ የበለጠ አልሰጠውም፡፡
ቁም ነገር፡- ስመ ሞክሼህ ከሆኑ ታዋቂ ሰዎች መካከል እነማንን ታውቃለህ?
ታምራት፡-ዘፋኞች
ቁም ነገር፡- ማንኛውም ሙያ ውስጥ ያሉ?
ታምራት፡- ለምሳሌ ራሱ የዚህ መጽሔት አዘጋጅ ታምራት ነው፡፡እ..ከአንጋፋ አርቲስቶች ደግሞ ታምራት ሞላ፤ ታምራት አበበ አለ የድሮ ዘፋኝ ነው፡፡ እንደገና ደግሞ ሌላ ጋዜጠኛም አለ መሰለኝ፡፡

ቁም ነገር፡- በዘንድሮ አልበምህ ውስጥ ከተካተቱት ዘፈኖች መካከል የአንተ ስሜት የበለጠ የሚያደላው ለየትኛው ነው?
ታምራት፡- ዘፈኖቼን ስሰራ አንዱን ከአንዱ 35 አበላልጬ የማይበት መንገድ ብዙም የለም፡፡ ግን ያው ጣቶቻችንም አንዱ ከአንዱ ይበላለጣሉ፤ቢሆንም አንዱ ያለ አንዱ አይኖርም፡ ፡ የአንዱ መጉደል አንዱን ያጎድለዋል፡፡ ዘፈኖቼ ውስጥ እንግዲህ እንደ ቴስት የምወዳቸው ዘፈኖች አሉ፡፡ከዛ ሰፈር አሪፍ ነው፤ ራሱ ፍፁም ሰላም፤ ማማዬ የተለየ ነገር አለው፤ተአምር ያስፈልጋል የሚል ዘፈንም አለ፡፡ ጌትሽ ማሞ ግጥሙን የጻፈበት እይታው ያስገርመኛል፡ ፡ እና በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ብቻ አንድ ነው ሁለት ነው ሶስት ነው አልልህም፡፡ ሁሉንም ነው እኔ የምወድደው፡፡

ቁም ነገር፡- ከሌሎች ድምጻውያን ጋር በጋራ በሰራኸው አንድ የወላይትኛ ዘፈን የሙዚቃ ቪዲዮ ላይ ልጆችህ የሚታዩ ይመስለኛል፡፡ በቅርቡ ደግሞ አብነት አጎናፍር ባወጣው አዲስ አልበም በአንድ ዘፈኑ ላይ ልጆቹን አሳትፏል፡፡ ልጆችህን በሙዚቃ ስራዎችህ ላይ የማሳተፍ ሃሳብ አለህ?
ታምራት፡- ከልጆቼ መካከል እኔን የሚመስሉ አሉ፡፡ ድምጽም ያላቸው አሉ፡፡ በተለይ አንዱ ልጅ በጣም ጎበዝ ነው፡፡ ግን እስካሁን በአልበምም ሆነ በሙዚቃ ደረጃ አሳትፌያቸው አላውቅም፡ ፡ራሳቸው በግል የሚያደርጉትን ነገር ግን ቤት ውስጥ እሰማቸዋለሁ፤ እቀርፃቸዋለሁ አንዳንድ ጊዜ፡፡ አሁን ለጊዜው ትምህርታቸው ላይ ትኩረት ቢያደርጉ እመርጣለሁኝ፡፡
ቁም ነገር፡- ከአልበምህ መውጣት በኋላ ኮንሰርት ለማዘጋጀት አላሰብክም?
ታምራት፡- በእርግጥ አልበም ሰርተህ ቶሎ ብለህ ኮንሰርት አታቀርብም፡፡ ዘፈኖቹ በሰዉ አዕምሮ ውስጥ በደንብ ገብተው ቦታ መያዝ አለባቸው፡፡ ሰዉ አጣጥሟቸው አብሮህ ማለት እስከሚጀምር ድረስ መጠበቅ አለብህ፡፡ የዚያን ጊዜ እንደ ማንኛውም ሰው ኮንሰርት ልሰራ እችል ይሆናል፡፡
ቁም ነገር፡- ሰሞኑን በሀገራችን የተለያዩ ሰዎች ሀብታቸው እየተመዘገበ ነው፡፡ ተራው ወደ አንተ ደርሶ ሀብትህን አስመዝግብ ብትባል የምታስመዘግባቸው ሶስት ነገሮች ምንድን ናቸው?
ታምራት፡- እ… አንደኛው ሕዝብ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ሀብቴ ልጆቼ ናቸው፡፡ (ሣቅ…) እንግዲህ ሌላ እኔ የማስመዘግበው ነገር የለኝም(ሣቅ…)፡፡
ቁም ነገር፡- እስካሁን ድረስ በህይወትህ ውስጥ ተመኝተኸው ያላገኘኸው ነገርስ ምንድን ነው?
ታምራት፡-እንደዛ እንኳን የለም፡፡እንግዲህ መፈልጋቸው የምመኛቸውን ነገሮች ሁሉ አግኝቼያቸዋለሁ፡፡ ምን አልባት ከዚህ በኋላ አገኘዋለሁ ብዬ የማስበው ነገር ይኖር ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንደሌሎቹ እርሱም ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡ እስካሁን የሚያጓጓ፤ እንቁልልጭ የሚያስብለኝ ምንም ነገር የለም፡፡
ቁም ነገር፡- በአንድ መድረክ ላይ ያገኘኸው ከፍተኛ ሽልማት ስንት ነው?
ታምራት፡- በሽልማት ደረጃ የተለያዩ ሽልማቶች ይኖራሉ ፤ ሰዎች ሲደሰቱ የሚሰጡህ ስጦታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ጊዜ ወደ መካከለኛው ምስራቅ የተባበሩት አረብ ኤምሬት ሀገር ውስጥ አንድ ጊዜ ለስራ ሄጄ ከፍተኛ የሆነ ስጦታ ተሰጥቶኛል፡፡ ሽልማቱ ሰዓት ነበር፡፡ ሰዓቱ ውድ ሰዓት ነው፡፡ ትልቁ ችግር ሠዓቱን መሸጥ አትችልም፡፡ ልሽጠው ብትል እንኳን ሰዓቱ በአንተ ስም አይደለም የተገዛው፡፡ እና እስከ ስልሳ ስምንት ሺህ ብር የሚደርስ ነበር ግን ምንታደርገዋለህ (ሣቅ…) እጅህ ላይ አድርገኸው ስትሄድ ራሱ የመክበድ ስሜት አለው፡፡ እኔ በተፈጥሮዬ ከባድ ነገር ብዙም አይመስጠኝም፡፡ ህይወቴ ራሱ ቀለል ያለ ነው፡፡ እንደ ማንኛውም ሰው የሚያስፈልገኝን ነገር አደርጋለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- ሕይወቴ ቀለል ያለ ነው ስትል… ታምራት ለምሳሌ በቀላሉ ተፈልጎ ይገኛል? ስልኩንስ በስንተኛው ጥሪ ነው የሚያነሳው?
ታምራት፡- እ…(ሣቅ…) አዎ! እኔ እ… ውጪ ካልሄድኩኝ ወይም ደግሞ ስራ ላይ ካልሆንኩኝ በስተቀር አካባቢዬም ሆነ ከአካባቢዬ ውጪ ከድሮም ጀምሮ ከማውቃቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት አለኝ፡፡ እገናኛለሁኝ፡፡ ማድረግ ያለብኝን ነገር ሁሉ ከጎረቤቶቼም ይሁን ከዘመዶቼም ከጓደኞቼም ጋር እገናኛለሁኝ፡፡ እንደዚህ ወጣ ብዬ ራሴን አግልዬ ምናምን አልኖርም፡ ፡ያው ከሰው ውጪ የሚሆን ነገር ስለሌለ ማለት ነው፡፡ ብትደምቅ ያለ ሰው አያምርም፡ ፡ ሁሉ ነገር ከሰው ጋር ሲሆን ነው ደስ የሚለው፡፡ እና ስለዚህ እንደ አርቲስት ታዋቂ ነኝ ብዬ ራሴን በጣም አግልዬ የምኖርበት ላይፍ ስታይል የለኝም፡፡ ምናልባት አንዳንድ ጊዜ በፊት በጣም የምታደረጋቸውን ነገሮች ላትጠቀም ትችላለህ፡፡ ከዛ ውጪ ግን ከሰዎች ጋር በስራም ሆነ በተለያየ መልክ እየተገናኘሁ ከእያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል ጋር ለምሳሌ ፊልም ቤቶች ሄጄ ፊልም አያለሁ፡ ፡እንደገና ደግሞ መጽሔትም ጋዜጣም ገዝቼ አነብባለሁ፡፡ ሻይ መጠጣት ካለብኝ የሆነ ቦታ ገብቼ ሻይ እጠጣለሁ፡፡ እኛ ሀገር ደግሞ ህዝቡ መልካም ነው፡፡ ወጥተህ ተጫውተህ ትገባለህ፡፡
ቁም ነገር፡- ደም ሰጥተህ ታውቃለህ?
ታምራት፡- የሚገርምህ ነገር ሁልጊዜ አስባለሁ፡፡ ግን የኔ ደም ራሱ ደም ያስፈልገዋል(ሣቅ…)፡፡ የደም አይነቴ ምን አይነት የሚሆን ይመስልሃል ስታስበው?
ቁም ነገር፡- ኦ ይሆን?
ታምራት፡- ኦ ፕላስ ነኝ፡፡ እንዲያውም ነጌቲቭ ሳልሆን አልቀርም… ቆይቷል ቼክ ካረግኩት፡፡ አንድ ነገር ቢያጋጥምህ የደም አይነትህ ኦ ከሆነ ብዙ ሰዎችን ያለማግኘት ችግር አለ ይባላል፡፡ እና ስልክ ቁጥር ራሱ መዝግቤ የያዝኩበት ጊዜ አለ፡፡ እንግዲህ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ነገር ስላልገጠመኝ ያው ቅድመ ዝግጅት አድርጌያለሁ፡፡ ለሌሎች ግን ደም አልሰጠሁም፡፡ ብሰጥ ግን ደስ ይለኛል፡፡
ቁም ነገር፡- እንቅልፍ ላይስ እንዴት ነህ? በጣም እንቅልፋም ነህ ወይስ መደበኛ የመኝታ ልምድ ነው ያለህ?
ታምራት፡- በፊት የተዛባ የእንቅልፍ ስርዓት ነው የነበረኝ፡፡ ምክንያቱም ማታ ሠርቼ ጠዋት ነው የምተኛው፡፡ አስፈላጊ ከሆነ አንዳንድ ጊዜ የምቀሰቀስበት ጉዳይ አለ፡ ፡ የኤምባሲ ጉዳይ ሲሆን እና ሌላም ሌላም ነገር ሲኖር ተቀስቅሼ እነሣለሁ፤ በዚህ ሁኔታ ይዛባል፡፡ የአመጋገብ ሰዓቴ ራሱ የተዛባ ነበረ፡፡ ቁርስ ምናምን ላይ ብዙ አላተኩርም፡ ፡ ምሣና እራት ነው የምበላው፡፡ ይሄ ሁሉ ከስራዬ አኳያ የመጡ ችግሮች ናቸው፡ ፡ አሁን ግን የምሽት ሥራ ካቆምኩኝ ወደ አራት አምስት ዓመት ስለሆነኝ የእንቅልፍ መዛባት የለም፤ ቁርሴንም በሰዓቱ እበላለሁ፡ ፡ እንደማኝኛውም ሠው ጠዋት ተነስቼ፤ የጠዋት ፀሐይ ሞቄ፤ ሻይ ጠጥቼ፤ ከዚያ በፊት ስፖርቴን ሰርቼ… ያው አሁን እንደምታየኝ ኪሎዬ ጨምሯል (ሣቅ…)
ቁም ነገር፡- በነገራችን ላይ ኪሎህ ስንት ደረሠ?
ታምራት፡- አሁነ አንዳየህ ጥሬ ስጋ (መብላት) ካቆምኩ በኋላ ቀንሷል ኪሎዬ (ሣቅ!)፡፡ ጥሬ ሥጋ ምናምን፤ አንዳንድ ነገሮችን ክትፎ ነገር እወድ ነበር፡፡ አለርጂ እየሆነብኝ ስለተቸገርኩ ባልወስደው ይመረጥ ነበር፡፡ አሁን ጥሬ ስጋ ከተውኩ ረጅም ጊዜ ሆኖኛል፡፡ እ…. ስፖርት ዱቡ ዱብ ማለት ጀምሬያለሁኝ አሁን፡፡ በፊት ሠማንያ ሁለት ኪሎ ሆኜ ነበር፡፡ እንግዲህ ከየት ተነስቼ ሠማንያ ሁለት እንደደረስኩ አንተ መገመት ትችላለህ (ሣቅ!)
ቁም ነገር፡- አዎን ቀጭኑን ታምራት እናውቀው ነበር (ሣቅ…)
ታምራት፡- እንግዲህ የበፊቱ ቀጭኑ ታምራት ነው ይሄኛውን ታምራት የወለደው የዛኔ የነበረው አስተሣሠብህ፤ ለምሣሌ በወቅቱ ከፍተኛ የሆነ ጉልበት ባይኖር ኖሮ የመለወጥ… አሠርቶ የማደግ ጉልበት በቀጭኑ ታምራት ውስጥ ባይኖ ኖሮ ይሄኛውን ታምራት ማግኘት ይከብዳል፡፡ ለማንኛውም በጣም ወደ ቀጭኑ ታምራት መመለስ እንኳን ባልችልም… አሁን ወደ ሠባ አምስት ኪሎ ሆኜያለሁ፡፡ ቀስ ብዬ ደግሞ ሠባ ኪሎግራም ለመግባት ነው ሀሣቤ፡፡ ቁመቴ አንድ ሜትር ከሠባ ሶስት በመሆኑ በእኔ ቁመት በሀኪም የሚመክረው ከስልሣ ስምንት እስከ ሰባ ኪሎ ግራም ክብደት እንዲኖረው ነው፡፡
ቁም ነገር፡- የሌሎችም ድምፃውያንን ዘፈን የመጫወት ሀሣብ ቢኖርህ ለየትኛው ዘፈን ነው ስሜትህ የሚያደላው፡፡ በጣም ስሜትህን የሚገዛው ዘፈን የትኛው ነው?
ታምራት፡- ከወጣትም ከአንጋፋም ድምፃውያን መካከል በጣም ደስ የሚሉኝ ብዙ ድምፃውያን አሉ፡፡ ስለዚህ እኔ ከድምፄ ጋር ሊሄድ የሚችል መርጩ የምዘፍንበት ብዙ ጊዜ አለ፡፡ ከእነዛም መካከል ለምሳሌ የኤፍሬም፣ አሊቢራ፣ የነዋይም… ከዚያ ውጪ ደግሞ በራሴ መንገድ የጋሽ ጥላሁን ዘፈኖችም እሠራለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- ቆይታችንን እያጠናቀቅን ነው በምን እንሠነባበት?
ታምራት፡- እንግዲህ እንደከዚህ ቀደሙ የቀደሙት አልበሞቼን ሰምታችሁ አስተያየት እንደሠጣችሁኝ ሁሉ ይህንንም አልበም ሠምታችሁ እንድታጣጥሙት በዚህ አጋጣሚ እጋብዛለሁ፡፡ ዘፈኖቹ መልዕክታቸውም ሆነ ውስጡ ያለው የዜማው፣ የሙዚቃው፣ የድምፁ ጥራት ሁሉ ከአሁኑ በፊት ካወጣኋቸው አልበሞች በተሻለ መልኩ የመጣሁበት ነው፡፡ የእኔ ሀሳብ ይህ ነው የእናንተን ሀሳብ ደግሞ እንድታጋሩኝ እጠብቃለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- አመሠግናለሁ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 261

Trending Articles