ከኢሳያስ ከበደ
‹‹ይህ ሰው እጅግ ብዙ ጥልቅ አሳቦችንና ጠንካራ ስሜቶችን በአንድ የሙዚቃ ሥራ ውስጥ መክተብ ችሏል፣ ለዛውም በአንዲት ትንሽ የሙዚቃ መሳሪያ ይሞዝቁ ዘንድ፡፡ ይህ ድንቅ ድርሰት በሚወለድበት ወቅት በፀሐፊው ቦታ ራሴን ከትቼ ሳስበው ከአቅሜ በላይ የሆነ ልዩ የሀሴት ስሜት ራሴን ሲያስተኝ ይታየኛል›› ይህ ጥቅስ ጆሃነስ ብራሃምስ የተባለ የ19ኛው ክፍለ ዘመን እውቅ ሙዚቀኛ የጆሃን ሰባስቺያን ባህ (በልዩ ተሰጥኦው ከምን ጊዜም የዓለም የሙዚቃ ሃያላን አንዱ) ድርሰት የሆነውን partita in D minor for Solo Violin አስመልክቶ የተናገረው ነው፡፡
ቻኮን የዚህ ድርሰት የመጨረሻ ክፍል ስያሜ ሲሆን ብራሃምስ ለግራ እጅ ብቻ የፒያ ጨዋታ እንዲሆን አድርጎ እንደገና አዘጋጅቶታል፡፡ ቻኮን ተጫዋቹን እጅግ በጣም የሚፈትንና አድማጩን በከፍተኛ የስሜት ማዕበል የሚያናውጥ ቅንብር ነው፡፡ ታዲያ ይህንኑ ውብ ስራ ለአዲስ አበባ ጆሮ ለማድረስ ኒኮላ ስታቪ የተባለ የተካነ ፈረንሳዊ ፒያኒስት ከጥቂት ወራት በፊት በጣልያን የባህል ማዕከል ተገኝቶ ነበር፡፡ ጣዕመ ሙዚቃውን በቦታው ተገኝቼ ካደመጥኩ በኋላ ሳይንቲስቶች የሚሰሩት ሥራ አርቲስቶች ከሚሰሩት ስራ ጋር ያለውን አንድነት የበለጠ ለማስተዋል ችያለሁ፡፡
መጀመሪያ ፈጠራን እንመልከት፡፡ ቻኮንን ለመድረስ ዓመታት ፈጅቷል፤ ምክንያቱም ጥልቅ አሳቦችንና ስሜቶችን የሚወክል ሙዚቃዊ መግለጫ ከራስ ጭንቅላት ማፍለቅ ጊዜ የሚወስድ፣ ትዕግስትንና ልዩ የፈጠራ ችሎታን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አንድን ንድፈ ሃሳባዊ ፊዚሲስት (Theoretical physicist) ለምሳሌ ብናነሳ፣ ውስብስብ የሆነ መስተጋብር ካላቸው ብዙ የተፈጥሮ ገፅታዎች መካከል ውስን የሆኑትንና ተፅዕኗቸው ተነጥለው መታየት የሚችሉትን ገፅታዎች መወከል የሚችሉ ሒሳባዊ ሞዴሎች አስሶ ማግኘት አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሌሎች ያላዩትን አድማስ ከተለመደው የአስተሳሰብ አጥር አሻግሮ ለማየት የሚያስችል አይነ ህሊና ይጠይቃል፡፡
አካባቢን ያለምንም መርጃ መሳሪያ (በአሁኑ ማሳያ፣ ያለ ሙዚቃ ወይም ያለ ሳይንስ) አተኩሮ በመመልከትና በማሰብ ብቻ ለመረዳት አዳጋች የሆኑ የተሸፈኑ ምስጢሮች ጊዜም ቦታም ሳይገድባቸው በብዛትና በየዓይነት ይገኛሉ፡፡ የሰው ልጅ ድንቅ የሆነ አዕምሮውን ተጠቅሞ ይኸው የራሱ አዕምሮ በሚገባ ማገናዘብና ማላወስ የሚችላቸውን ሞዴሎች (በአሁኑ ማሳያ፣ የሙዚቃ ድርሰት ወይም ሒሳባዊ ቀመር) ፈልስፏል፡፡ ይህ የፈጠራ ስራ ጥግ ነው፡፡ የፈጠራ ስራው አቀማመር ልቀት ደግሞ ለሰዎች ስሜት ቅርብ የሆነ ውበት አለው፡፡ ይህ ሃሳብ ውበትን ወደሚመለከተው ሁለተኛው ነጥብ ያሻግረኛል፡፡
ሊ ስሞሊን (ሳይንቲስትና የኖቤል ሽልማት ባለቤት) ‹‹The life of the cosmos›› በተሰኘው መፅሐፉ ውስጥ ሳይንቲስቶችና አርቲስቶች በውበት ላይ የሚጋሩትን አቋም እንዲህ ፅፎታል፡፡ ‹‹ሳይንቲስቶች ልክ እንደ አርቲስቶች ሁሉ ስለ ስራቸው ውበት ይጨነቃሉ፡፡ በተለይም ንድፈ አሳባዊ ፊዚሲስቶች እና የሒሳብ ሊቆች ተፈጥሮን በደፈናው በድጋሚ ከሚያስቀምጡና ከሚዘግቡ መግለጫዎች ይልቅ ተፈጥሮን በልዩ ልዩ መንገዶች መወከል የሚችሉ ፈጠራዎች ለስራቸው ድንቅ ውበት እንደሚያጎናፅፉላቸው ያምናሉ፡፡ አርቲስቶችም ይህንን ሀሳብ ይጋራሉ››
ሳይንስና ሙዚቃን የሚያዋድደው ሶስተኛው እሴት ስርዓት ይመስለኛል፡፡ ሰባስቺያን ባህ የሙዚቃ መሳሪያ ድምፅን በመጠቀም ልዩ ስሜት እና አስተውሎት ወደ አድማጭ አሻግሯል፡፡ ይህንን አይነት ስራ ለመስራት ሙዚቃው ከስሜት ጋር ያለውን ቁርኝት በሚገባ ከማወቅ ባሻገር ሙዚቃውን ለመናገር የሚያስችል ልዩ ቋንቋ አቀላጥፎ ማወቅ ያሻል፡፡ አንድ የልብ ወለድ ደራሲ ያዳበራቸው ብዙ የቋንቋ ክህሎቶችና የሚከተላቸው የሰዋሰው ህጎች እንዳሉ ሁሉ ሰባስቺያን ባህ ቻኮንን በዘፈቀደ አልደረሰውም፡፡
ለፒያኖ አጨዋወት የተመቸ፣ በዓመታት የሚዳብር የጣት ቅልጥፍና የስርዓቱ አንድ አካል ነው፡፡ የሞት፣ የቅኝት ወዘተ የሙዚቃ ለዛ መገለጫዎችን ሳያዛቡና በዘመኑ ከነበረው የባሮክ የሙዚቃ ስልት ህግጋት ሳይፈነግጡ የፈጠራ ስራ ማመንጨት መቻል ሰባስቺያን ባህ ጠንቅቆ ያከበረው ሌላኛው የስርዓቱ አካል ነው፡፡
ሪቻርድ ፋይንማን (ምናልባትም ከአልበርት አይንስታይን ቀጥሎ በንድፈ አሳባዊ ፊዚክስ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሮ ያለፈ) እንዳለው ከሆነ ‹‹ሳይንሳዊ ፈጠራ በመገደቢያ እርከን ውስጥ የሚገኝ አይነ ህሊና›› ነው፡፡ አሁንም እንደገና ከንድፈ አሳባዊ ፊዚክስ ሳንወጣ የዚህን ጥቅስ አንድምታ ማጤን እንችላለን፡፡ የመገደቢያው እርከን በቀጥታ ስርዓትን ይመለከታል፡፡ በምስልና በሀተታ አካባቢን የመግለፅ ችሎታ የሳይንስ ቋንቋ አጋዥ ክህሎቶች ቢሆኑም ቅሉ ዋናው መሳሪያ ሒሳብ ነው፡፡ ሒሳብ በተጠየቃዊና ምክንያታዊ አካሄድ ወይም ስነ አምክንዮ የተዋቀረና ተፈጥሮን የሚወክል ሞዴል ለመገንባት ፍፁም ተስተካካይ ያልተገኘለት የሰው ልጅ ድንቅ የፈጠራ ውጤት ነው፡፡ በሒሳብ ክህሎት በሚገባ ያልተካነ ግለሰብ ስኬታማ ፊዚሲስት መሆን አይችልም፡፡
ሰባስቺያን ባህ የሞት፣ የቅኝት ወዘተ የሙዚቃ ለዛ መገለጫዎችን ሳያጣርስና ከባሮክ የሙዚቃ ስልት ማዕቀፍ ሳያፈነግጥ ድንቅ ሥራዎችን በሙዚቃ መስራት እንደቻለው ሁሉ አንድ ንድፈ አሳባዊ ፊዚሲስት፣ እንበል አልበርት አይንስታይን፣ አዲስ ግኝት ለማድረግ ሲነሳ ቀደም ሲል ትልቁን የሳይንስን የእውቀት ማህደር መቀላቀል የቻሉ ንድፈ አሳቦችን በዘፈቀደ መናድ አይችልም፡፡
አልበርት አይንስታይን የሳይንስ የእውቀት ማዕቀፍን ሳይተላለፍ፣ አስገራሚ የዓይነ ህሊና ተሰጥኦውን ተጠቅሞ፣ ተፈጥሮን መወከል የሚችሉ ልዩ ሒሳባዊ ሞዴሎችን አበርክቷል፡፡ የብርሃን ጨረር በውስን ፍጥነት እንደሚጓዝ የሚገልፀው የማክስ ፕላንክ ንድፈ ሐሳብ በአንድ ወገን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ጋሊለዮ ጋሊለይ ያዊት (constant) ንፅፅራዊ ፍጥነት ያላቸው አካላት ተፈጥሮን ለመለካት ቢሞክሩ አንድ አይነት ልኬት እንደሚኖራቸው ያስረዳበት ንድፈ ሐሳብ፣ እርስ በእርስ የሚጣረሱ ቢመስሉም ሁለቱም በየፊናቸው ተፈጥሮን በትክክል መወክል የሚችሉ ንድፈ ሀሳቦች መሆናቸውን የሚያወላውል አልነበረም፡፡ ታዲያ አይንስታይን በዚህ ጨቋኝ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ሁለቱንም ውብ ሒሳባዊ ሞዴሎች ሳይሽር፣ በተቃራኒው ሁለቱንም ሞዴሎች አንድ ላይ ያዋሃደበት ‹‹Special Theory of Relativity›› የተሰኘው ንድፈ ሃሳብ ለሳይንስ ስርዓት የበላይነት ግሩም ማሳያ ነው፡፡
በሳይንስና በሙዚቃ ውህደት ላይ አራተኛና የመጨረሻ የማሰቢያ ነጥብ ልወርውር፡፡ እንደ ጆሃነስ ብራሃምስ ላለ የሙዚቃ ባለሞያም ሆነ እንደ እኔ ላለ ባለሞያ ያልሆነ ቀንደኛ የሙዚቃ አፍቃሪ ቻኮን በሁለት ደረጃ ትርጉም ይሰጣል፡፡ ሳባስቺያን ባህ እንዲህ አቀላጥፎ የሚያንበለብለው የሙዚቃ ቋንቋ የአድማጩን ስሜት እስር ድረስ ዘልቆ ይኮረኩረዋል፡፡ ይህ የሚሆነው የአድማጩ ጭንቅላት ቋንቋውን በሚገባ መረዳት በመቻሉ ነው፡፡ ይህ የመጀመሪያው ደረጃ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በዚህ የሙዚቃ ቋንቋ የተወከለውን የሰባስቺያን ባህ ልዩ ስሜት፣ አስተሳሰብ፣ አስተውሎት ወዘተ… መረዳት በመቻል የሚገኝ ልዩ ደስታ አለ፡፡ የእነዚህን ሁለት ደረጃዎች ተዛማጅ መገለጫዎች በሳይንስ ውስጥ ለመመልከት ወደ ሊ ስሞሊን ‹‹The life of the cosmos›› እንመለስ፡፡
‹‹የሰው ልጅ አዕምሮ የወለደውን ሒሳባዊ ሞዴል በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሞዴሉ የተወከለውን ገሃዳዊ ሁኔታ በተመሳሳይ ሰዓት መረዳት መቻል የሚያስገኘው አንዳች ሀሴት አለ›› ምንም እንኳን እስከ አሁን ድረስ ከሙዚቃ አቻው ጋር ሲነፃፀር በስሱ የተስተዋለ ክስተት ቢሆንም ሊ ስሞሊን የሚያወራለት ሃሴት ለሳይንቲስቱም ለሳይንስ አፍቃሪውም ስሜት ቅርብ ነው፡፡ ቀላል ምሳሌ፡- የፓይታጎራስን መክስት (pythagorean theorem) አመጣጥና ማረጋገጫ በተረዳንበት ቅፅበት መክሰቱ በዓለም ላይ ላሉ ቀጤ ጎን ሶስቶች (Ritht triangles) በሙሉ መስራት መቻሉን መገንዘብ ከቻልን የተባለው ልዩ ደስታ ይጎበኘናል፡፡
The post ሳይንስና ሙዚቃ appeared first on Zehabesha Amharic.