በራሱ የሙዚቃ ስልት በመጫወት ተወዳጅነት ለማትረፍ የቻለ ድምፃዊ ነው፡፡ እስከዛሬም በተለያዩ አገራት እየዞረ የሙዚቃ ስራዎችን በማቅረብ አድናቂዎቹን በማዝናናት ላይ ይገኛል፡፡ ከድምፃዊነቱ በተጨማሪ ከአንድ ዓመት በፊት ‹‹ጆሲ ኢን ዚ ሃውስ›› (Jossy in the house) የሚል የራሱን ቶክ ሾው የኢቢኤስ የቲቪ ጣቢያ ማቅረብ ከጀመረ በኋላ የፕሮግራሙ ይዘት የብዙ የኢቢኤስ ተመልካቾችን አይን ሊስብ የበቃ ባለሙያ ለመሆን ችሏል፡፡
በተለይ በዚህ ዓመት በትንሣኤ በዓል ላይ አቅርቦት በነበረው ፕሮግራሙ ላይ የቀድሞዋን ተወዳጅ ድምፃዊ ማንአልሞሽ ዲቦ ልጆች ገጥሟቸው በነበረው የህይወት ፈተና ዙሪያ በሰራው ዘጋቢ ፊልም ምክንያት ልቡ ያልተሰበረ የፕሮግራ ተከታታይ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡
ዛሬ መተሳሰብና መረዳዳት እንደሰማይ በራቀበት ዘመን ዮሴፍ (ጆሲ) በፕሮግራሙ ላይ እንዲህ የተረሱና የወገን ድጋፍ የሚያሻቸው ወገኖችን ከህዝቡ ጋር በማገናኘት ህይወታቸው እንዲለወጥ ያደረገው አስተዋፅኦ የተከታተሉ ተመልካቾች እደግ፣ ተመንደግ፣ ተባረክ በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ዙሪያ ከድምፃዊና የቶክ ሾው አዘጋ ዮሴፍ ገብሬ ጋርየተደረገው ቆይታን እንሆ።
ጥያቄ፡- አዲሱ አልበምህ ከምን ደረሰ?
ዮሴፍ፡- አልበሙ ከሞላ ጎደል አልቋል፡፡ ለፋሲካ ይደርሳል የሚል ሃሳብ ነበረን፡፡ አንዳንድ የስፖንሰር ሺፕና ሌሎች ጉዳዮች ነበሩን፡፡ እነዚያን ጉዳዮች ፋሲካ ከመድረሱ በፊት ነበር የጨረስነው፤ ከዚያ በኋላ ያሉት ነገሮች ለማስተካከል እየሞከርን ነው ያለነው፡፡ የጆሴ ሾው ምዕራፍ 3 ልጀምር ስለሆነና ትንሽ ለየት ባለ መልክ ይዘን ለመውጣት ስለፈለግን ትንሽን ድካሞች ነበሩበት፡፡ ያንን አስተካክለን አልበሙ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለ1 ወር ከ15 ቀን ውስጥ ለአድማጭ ወደ መልቀቁ እንሄዳለን፡፡
ጥያቄ፡- አልበሙን ዜማ፣ ግጥምና ቅንብር ከእነማን ጋር ነበር የሰራኸው?
ዮሴፍ፡- በርካታ ሰዎች አሉበት፡፡ ይልማ ገ/አብ፣ ጌትሽ ማሞ፣ መለሰ ጌታሁንና ሙያው ላይ ይሰራሉ የሚባሉ የተለያዩ ሰዎች ጋር ነው የሰራሁት፡፡ ዜማውና በቅንብርም ሁሉም ጋር ነው የተሰራው ማለት ይቻላል፡፡
ጥያቄ፡- በዚህ አልበም ላይ የበፊቱን ስታይል ይዘህ ነው የመጣኸው ወይስ የተለየ?
ዮሴፍ፡- የበፊቱ እስታይል 6 ወይም 7 ዓመት በፊት ነው ይዤ የወጣሁት፡፡ ያኔ ደግሞ ወታት ነበርኩ፣ አሁን ወደ መብሰሉ ስለሆንኩ በዚያው ልክ በሰል ያሉ ዜማዎች ናቸው፡፡ ለበፊቱ አድናቂዎችም የሚሆኑና እንዲሁም አገራዊ ፋይዳ ያላቸው መልዕክት ማስተላለፍ የሚችሉ፣ ሀገርኛ ባህልን የሚያስተዋውቁ ሆነው የዕድሜዬን ያህል አልበሙም አድጎ ይወጣል፡፡
ጥያቄ፡- የአልበሙ ርዕስ ታውቋል?
ዮሴፍ፡- የተመረጡ ርዕሶች አሉት፡፡ ግን ሊወጣ ሲል ነው አንዱ ርዕስ የሚመረጠው፡፡
ጥያቄ፡- አልበሙን የገዛው ወይም የሚያከፋፍለው ማነው?
ዮሴፍ፡- ያንን ለጊዜው ምስጢር ላድርገውና ስፖንሰርሽፕ ከአንድ ካምፓኒ ጋር ጨርሰናል፡፡ ከዚ ባለፈ ግን የማከፋፈል ስራው እንዴት እንደሚሆን እያሰብንበት ስለሆነ ለጊዜው ይፋ አልሆነም፡፡
ጥያቄ፡- በአንተ እይታ አሁን እንደሚታወቀው የሙዚቃው ኢንዱስትሪ የገጠሙት ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
ዮሴፍ፡- ምክንያቶቹ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ሁልጊዜ እንደሚባለው የኮፒራይት ያለመከበር ችግር ዋነኛው ነው፡፡ ነገር ግን የሙዚቃው ኢንዱስትሪ ሙሉ ለሙሉ እንዳልተቀዛቀዘ የሚያመላክቱ እንደ ብዙአየሁ አይነት ስራዎች አሉ፡፡ የብዙአየሁ አልበም በደንብ ተሰምቶ ነበር፡፡ አልፎ አልፎም ቢሆን ተሰርተው መቅረብ የሚችሉ አልበሞች አሉና ከእነኛ አንዱ የመሆን ዕድል አልመህ ያለውን ስራ በደንብ አጠንክረህ ሰርተህ ማቅረብ እንጂ ከሙያው ጨርሶ መራቅ አያስፈልግም፡፡ ምናልባት ከሚሰሙ ስራዎች መካከል አንዱ ትሆናለህ፡፡ አለበለዚያም ሪስኩን ወስደህ የሚመጣውን መቀበል ነው፡፡
ሌላው ግን ሁሉ ነገር ጨምሯል፣ ዛሬ አንድ ማኪያቶ አንዳንድ ቦታ 13 ብር ገብቷል፡፡ ከጓደኛህ ጋር ሆነህ ሁለት ማኪያቶ ከጠጣህ 26 ብር ነው፡፡ የእኛን ሲዲ በ25 ብር ለመግዛት እንደ ከባድ ይቆጠራል፡፡ አብዛኛው ሰው ለሙያው የሚሰጠው ቦታ ከደብል ማኪያቶ በታች ሆኗል፡፡ ለሙያው ክብር ብንሰጥ መልካም ነው፡፡ ድሮ እኛ ልጅ እያለን አዲስ ዘፈን ሲወጣ በየሙዚቃ ቤቱ ደጃፍ እንሰባሰብ ነበር፡፡ ሌላው ችግር ብዙ በመፅሔትና ጋዜጦች ላይ አላግባብ የአርቲስቱ ይሰጥ የነበረው ያልሆኑ ስም ማጥፋቶች ይወጡ ነበር፡፡
ወደ መፍትሄው ስንሄድ ያንን ገፅታ ለመቀየር አርቲስቱ ዝም ብሎ ከመዝፈን ባለፈ በማህበራዊ ስራዎች ውስጥ ራሱን ማሳተፍ አለበት፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እኔም የጀመርኩት ነገር አለ፡፡ እኔ ብቻም ሳልሆን የሙያ ባልደረቦቼም በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፈው ያ ገፅታ ከተቀየረ በኋላ ህዝቡ ውስጥ የእኔነት ስሜት ፈጥሮ ገበያውን የመመለስ ነገር ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡
ጥያቄ፡- አንተስ ለአዲሱ አልበም ከአድማጮችህ ምን ትጠብቃለህ?
ዮሴፍ፡- መልካም ነገሮችን እጠብቃለሁ፤ ጥሩ ነገሮች ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ጥሩ ነገር ሰርቻለሁ፡፡ በተለያዩ ባለሙያዎች አሰምቼ በጣም ቀና የሆነ ምላሽ ነው ያገኘሁት፡፡ አድማጩ ሰምቶት ደግሞ የሚሰጠውን ምላሽ አብረን እናየዋለን፡፡
ጥያቄ፡- ‹‹ጆሊ ቶክ ሾው››ን እንዴት ጀመርከው?
ዮሴፍ፡- ት/ቤት ውስጥ እያለሁ ሚኒ ሚዲያ ውስጥ እሰራ ነበር፡፡ ከ9-12ተኛ ክፍል ስማር በጣም ታታሪ ጋዜጠኛ ስለነበርኩ ይመስለናል የሚኒ ሚዲያው ኃላፊ ጭምር ነበርኩኝ፡፡ 10ኛ ክፍል ላይ የህዝብ ግንኙነትና የተማሪዎች ተወካይ ተብዬ ከ3 መምህራን ጋር የሹመት ደብዳቤ ደርሶኛል፡፡
ጥያቄ፡- የት ነበር የምትማረው?
ዮሴፍ፡- ናዝሬት አዳማ አጠቃላይ 2ተኛ ደረጃ ነበር የምማረው፡፡ እዚያ ነበር የጋዜጠንነት ህይወት የጀመርኩት፡፡ በየእረፍቱ እየገባሁ አምስቱን ቀናት ሙዚቃ ማሰማት፣ ስነ ፅሑፍ ማቅረብና ፕሮግራም መምራት የመሳሰሉትን እሰራ ነበር፡፡
መርካቶ ከወንድሜ ጋር ቢዝነስ እየሰራሁ ኢትዮ-ኒውስ፣ ዘ ፕሬስ፣ አዲስ አድማስ ላይ ከ60 በላይ አርቲክሎችን ጽፌያለሁ፡፡ ስለዚህ ጋዜጠኝነት ከዚያ ጀምሮ ያደገ ሙያ ነው፡፡
ወደ ቶክሾው ስንመጣ ለምሳሌ ክዊን ላቲቫ ዘፋኝ ናት፡፡ የራሷ ቶክሾውም አላት፡፡ ሌሎችም እንደዚያው፡፡ እኔም የራሴ ቢኖረኝ ብዬ አልም ነበር፡፡ ኢቢኤስ ቲቪ ሲመጣ ፕሮግራሞች ይፈልግ ነበርር፡ ከባለቤቶቹ ጋር ተገናኝተን ለመጀመር አሰብኩኝ፡፡ በወቅቱ አልበሙ ትንሽ ያዝ ስላደረገና ልጀምር አልቻልኩም ነበር፡፡ ከቆይታዎች በኋላ ጀመርኩኝ፡፡
ጥያቄ፡- የፕሮግራሙ ፎርማት ምንድነው?
ዮሴፍ፡- ሲጀመር የታዋቂ ሰዎች የህይወት ሂደት ምን ይመስላል፣ አንድ ሰው ከመሬት ተነስቶ ታዋቂ አይሆንም፡፡ እነዚያ ታዋቂ ሰዎች እዚያ እውቅና ላይ የደረሱበት መንገድ እንዴት ነው? የሄዱበት መንገድ ለሌሎች መማሪያ መሆን በሚቻልበት መልኩ ማቅረብ ነው፡፡
ስለ አርቲስቶቹ የነበረን ገፅታ ጥሩ ስለነበር አርቲስት ከተጠቀምንበት በጣም ብዙ ነገር የማድረግ አቅም አለው፡፡ ብዙ ነገር ማድረግ ይችላል፡፡ የአርቲስቶችንና የታዋቂ ግለሰቦችን ያልታዩ ማንነቶችን እያሳዩ ያለውን መንፈስ ሊቀየር የሚችል መንፈስ ይዞ ነበር የተነሳው፡፡ ያንንም ስናደርግ የታመሙት፣ የተጎዱ፣ የተረሱትን፣ የትኛቸው ያሉት ብለን የመጠየቅ መንፈስ ይዘን መጣን፡፡ ከዚያም የበዓለት ዘመድ ጥየቃ የሚል ፕሮግራ ጀመርን፡፡ እያልን አሁን ያሉት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
ፕሮግራ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የተላበሰ፣ ከቋንቋ አጠቃቀም ጀምሮ፣ ከአቀማመጥ፣ በእያንዳንዱ ነገር ከልጅ እስከ አዋቂ የሚከተለው የቤተሰብ ፕሮግራም እንደሆነ ነው እየሰራን ያለነው፡፡
ጥያቄ፡- ምን ያህል ፕሮግራሞች ሰራችሁ?
ዮሴፍ፡- እስካሁን ዓመቱን ሙሉ ስንሰራ ነበር፡፡ ሶስት ልዩ የበዓል ፕሮግራሞች ሰርተናል፡፡ ለአዲስ ዓመት፣ ለገና እና ለፋሲካ፣ ከእነሱ ሌላ በእርግጠኝነት ከ3-4 ፕሮግራሞች ካልሆነ በስተቀር ዓመቱን ሙሉ አዳዲስ ፕሮግራሞችን ነበር ስናቀርብ የነበረው፡፡ ስኬታማ ያደረገንም ፕሮግራም ያለመድገማችን ነው፡፡ ዓመቱን ሙሉ አዲስ ነገር እያሳየን ነው እዚህ የደረስነው፡፡
ጥያቄ፡- ሰዎችን መርዳት እና ማገዝ የፕሮራሙ አካል እንዴት ልታደርገው ቻልክ?
ዮሴፍ፡- ሰዎችን የማገዝና የመርዳት ነገር አሪፍ ፕሮግራም አዘጋጅ ስለሆንክ ወይም እውቀት ስላለህ ስለዚህ ብቻ ሳይሆን ልብ ይፈልጋል፡፡ አንተ ትንሽ በመስጠት የምትደሰት ከሆንክ ያንን ትሰራለህ፣ ለምሳሌ 5 ብር ኖሮህ 1 ብር በመስጠት የምትደሰት ከሆንክ እንደዚህ አይነት ፕሮግራም ትሰራለህ፡፡ እንደዚህ አይነት ልብ ከሌለህ የፈለገው ጎበዝ ጋዜጠኛ ብትሆን አትሰራውም፡፡ ይሄ የልብ ነገር ነው፡፡
ጥያቄ፡- የማንአልሞሽ ቤተሰቦች ህይወትን በፕሮግራም ላይ ለማቅረብ ምን አነሳሳህ?
ዮሴፍ፡- የእኔ ታላላቆች ወይም በዘመዶቼና ቤተሰቦቼ በተለይ በዳግማይ ትንሣኤ ወቅት ‹‹አክፋይ›› በሚባለው ስነ ስርዓት ውስኪ እና በግ ይዘው ይጠይቃሉ፡፡ ይሄ የክብር መገለጫ ነውና ያንን ሃሳብ ይዤ ነው ወደዚህ ያመጣሁት፡፡
ፕሮግራሙ ላይ በዓል ከተለመደው ፕሮግራም ውጭ የተለየ ነገር መሰራት አለበት አልኩኝ፡፡ ትዝ የሚልህ ከሆነ ለ2006 አዲስ ዓመት እነ ማንአልሞሽ ቤተሰቦች ቤት ሄጄ ነበር፡፡ በሁኔታው እኔ ብቻ ሳልሆን ተመልካቾችም በጣም ነበር ያዘኑት፡፡ ከዚያ በኋላ የአባባ ተስፋዬም የአርቲስት ዘሪቱ (እንቁጣጣሽ) ጉዳይም ነበር፡፡ ስለዚህ የማንአልሞሽ ልጆች ጥሩ ኑሮ የሚኖሩ፣ አሪፍ ት/ቤት ይማሩ የነበሩ፣ የአንዲት ታዋቂ ዘፋኝ ልጆች ነበሩ፡፡ አሁን ያሉበት ህይወታቸው ሲታይ በጣም ያሳዝናል፡፡ ቤታቸው በጣም ሩቅ ነው፣ በተለይ የማንአልሞሽ ዲቢ ሁለተኛ ልጅ ምስጢረ የተናገረችው ንግግር በጣም ልብ ይሰብር ነበር፡፡ እንደማንኛውም ሰው እኔም ልብ ተነክቶ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የምችለውን ነገር ሁሉ አድርጌ ህይወታቸው የሚስተካከልበት ነገር ልፈልግ በማለት ተነሳሁ፡፡
ጥያቄ፡- ልጆቹ የት ነበሩ አሁን የት ደረሱ?
ዮሴፍ፡- የሚኖሩበት አካባቢ በጣም ሩቅ ነበር፡፡ የት/ቤት እና የመኖሪያ ቤት ችግር ነበረባቸው፡፡ አንደኛዋ ልጅ የጤና ችግር ነበረባት፡፡ ወንድየው ት/ቤት ቢገባም የመማሪያ ቁሳቁስ ችግር ነበረበት፡፡ ከዚህ አንፃር በቂ ነው ባይባልም ዛሬ ሩቅ ከሚባል ሰፈር ወጥተው እዘህ ግሎባል ሆቴል አካባቢ ከዋናው አስፋልት 150 ሜትር ገባ ብሎ ከሚገኝ ንፁህ ቤት ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ቤቱ አንዳንድ ነገሮች ቢቀሩትም እየተስተካከለ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎችም እያገዙን ነው፡፡ አሁን ህይወታቸውን ከሞላ ጎደል በጣም ደስ በሚል ሁኔታ ተቀይሯል፡፡ እነሱም ህይወታችን እንደ አዲስ ጀመረ ብለው ነው ደስታቸውን የገለፁት፡፡
ጥያቄ፡- ፕሮግራሙ ከተላለፈ በኋላ ምን ምላሽ አገኘህ?
ዮሴፍ፡- ከፕሮግራሙ በኋላ ያለው ነገር ማመን ያቅትሃል፡፡ ፕሮግራ የተላለፈ ቀን ባህሬን ዝግጅት ነበረኝ፡፡ ሰው ሾውን ካየ በኋላ ነው ማታ ወደ የሙዚቃ ዝግጅቱን ለመከታተል የመጣው፡፡ የነበረው ምላሽ በታም የሚገርም ነበር፡፡ በነጋታው ሰኞ ፌስ ቡክ ስከፍት ከነበረው የፌስ ቡክ ፋን ከነበረው 94 ሺ ገደማ በአንድ ቀን ልዩነት ወደ 106 ሺ ከዚያም በተከታታይ ቀናት ከ120 ሺ በላይ ሆነ፡፡
እዚህም ስመጣ በየመንገዱ የሚያልፈኝ ሰው አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር ይክበር ነው ያልኩት፡፡ ይሄ ብርታት ሆኖኝ እኔ ላይ የነበሩ ፕሮግራሞች የበለጠ እንድገፋበት ጉልበት ሆነኝ፣ የእናቶች ምርቃት ለእኔ ህይወት ሆኖኛል፣ ምርቃት በጣም ነው የምወደው፣ ያደኩበት ቤተሰብ እንደዚ ስላሳደገኝ ምርቃት በጣም ነው የምወደው፡፡ ከገንዘብ በላይ ምርቃት ደስ ይለኛል፡፡
አንዳንድ ሰዎች በቃል መግለፅ የማይችሉት ፍቅር አሳይተውኛል፡፡ የፍቅር አምላክ እግዚአብሔር ፍቅሩን በፍቅር ይመልስልኝ ነው የምለው፡፤ መልካም ነገር ስሰራ ለራሴ ብዬ ነው ያደረግኩት፡፡ እንደ ፕሮግራምም ስታየው ጥሩ ነገር እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ግን እንደዚህ ህይወትህ ግልብጥ ብሎ እስኪቄር ድረስ ይሆናል ብዬ በፍፁም አልጠበቅኩም ነበር፡፡ ይህን ክብር መልሼ ለእግዚአብሔር ነው የምሰጠው፡፡
ጥያቄ፡- ከዚህ በኋላ እኛም አግዘንህ እንርዳ ያሉ በጎ አድራጊዎች የሰጡ ካሉ?
ዮሴፍ፡- በቂ ነው ባይባልም የመጡ ሰዎች አሉ፡፡ የመጡትን እናመሰግናለን፡፡ አሁንም እጄ ላይ ያሉ ጥቂትም ቢሆኑ መታገዝ የሚገባቸው ሰዎች በእነዚህ ፕሮግራሞች ለመርዳት እንሞክራለን፡፡ እኔም አቅሜ በሚችለው ሁሉ ከማገኘው ነገር ላይ ለማገዝ እሞክራለሁ፡፡
ጥያቄ፡- የወደፊት እቅድህስ ምንድን ነው?
ዮሴፍ፡- ምዕራፍ 3 ባይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በተለያየ መልኩ የማህበረሰቡ ችግሮችን የሚቀርፉ ምክሮች ወይም ትምህርቶች፣ ምሳሌ መሆን የሚችሉ ፋይዳዎችን የፕሮግራማችን አካል ለማድረግና የበለጠ የፕሮግራሙን ይዘት አሳድጎ የማህበረሰቡ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ነገሮች እንዲሆኑ አቅደናል፡፡
እስካሁን የሠራናቸውን ፕሮግራሞች በተመለከተ ተመልካች አስተያየት እንዲሰጡን እናደርጋለን፡፡ የምዕራፍ 3 ፕሮራሞች በአዲስ አቀራረብ፣ በጥራት ሰርተን ለእይታ እናበቃለን፡፡
ጥያቄ፡- የማን አልሞሽ ልጆች የወደፊት ህይወት የት ሊሆን እንደሚችል ይታወቃል?
ዮሴፍ፡- ልጆቹ ጎበዝ ተማሪዎች ናቸው፡፡ በትምህርታቸው ታታሪ ናቸው፡፡ አንደኛው ልጅ የትምህርት መሳሪያ ያስፈልጉት ነበር፡፡ ላፕቶፕ በስጦታ አግኝተንለታል፡፡ ከዚያ ውጭ ደግሞ በትምህርቱ ሂደት ውስጥ የሚያስፈልጉት ነገሮች እንደ ወንድም አግዘዋለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ ምስጢረም ትምህርቷን እስክትጨርስ የስኮላርሺፕ እድል አግኝታለች፡፡ ፍቅርተም (የማንአልሞሽ ወንድም ልጅ) ጤናዋ ተስተካክሎ ወደ ትምህርቷ የምትመለስበት ሁኔታ ተመቻችቶላታል፡፡ ቲጂም (የማንአልሞሽ እህት) ያቋረጠችው የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ትቀጥላለች፡፡ መሰረታዊው ነገር እራሳቸውን ችለው ጥረው ነገ ለሰው የሚተርፉበት ህይወት ላይ ያቆምናቸው ይመስለኛል፡፡ ቀሪው ነገር የራሳቸው ጥረት ይሆናል ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፡- ስኬታማ ነህ?
ዮሴፍ፡- እንደ ጀማሪ ጥሩ ነው፡፡ ግን የስኬት መጨረሻ ይሄ አይደለም፡፡ ገና ብዙ ይቀረኛል፡፡ እዚያ ደረጃ ላይ ከእግዚአብሔር ጋር እንደምደርስ እምነት አለኝ፡፡
ጥያቄ፡- ደስተኛ ነህ?
ዮሴፍ፡- የምፈልገውን ነገር ስለምሰራ፣ የምፈልገውን ስላደርግ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በህይወት ውስጥ ስትመላለስ ማድረግ የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ፡፡ እኔ የምሰራው የህዝብ ስራ ነው፡፡ ከማህበረሰቡ የምታገኘው ምላሽ ደግሞ ጥሩ እየሆነ ሲመጣ ከዚህ በላይ ደስተኛነት የለም፡፡ ከራስህም አልፈህ በሰዎች ህይወት ውስጥ ምክንያት መሆንህ በራሱ ከማንም በላይ ደስተኛ ያደርግሃል፡፡
ጥያቄ፡- የምትጨምረው ነገር ካለ?
ዮሴፍ፡- በመጀመሪያ አክብራችሁ ስለጋበዛችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡ በአዲስ አልበም፣ በአዲስ የቲቪ ሾው ሲዝን ጥሩ ነገሮችን ይዘን ራሳችንን አሻሽለን የምናርመውን አርመን፣ የምናዳብረውን አዳብረን ለማህበረሰቡ ይጠቅማል በምንለውና ባደገ የስራ አካሄድ ወደ ህዝቡ እንመጣለን የሚል እምነት አለኝ፡፡