ቅዳሜ ሰኔ 28 ቀን 2006 ዓ.ም የተመሰረተበትን 60ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓሉን ያከበረው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ምረቃ ሥነ ሥርዓት አካሂዷል፡፡ በዚሁ የተማሪዎች የምረቃ ስነ ሥርዓት ላይ በተሰማሩበት ሙያ ለህብረተሰቡ አይነተኛ አገልግሎት አበርክተዋል ላላቸው አራት ሰዎች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷል፡፡ የክብር ዶክትሬት ከተሰጣቸው ሰዎች መካከል 3ቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ዝነኛዋ ድምጻዊት አስቴር አወቀ፣ አትሌት መሠረት ደፋር፣ የዩኒቨርሲቲው ምሩቅና የማህፀንና ፅንስ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ሙሉ ሙለታ እንዲሁም የኢህዴን ታጋይ የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ በዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ከነዚህ ሰዎች መካከል ስማቸው ለአብዛኞቻችን አዲስ የሆኑት ዶ/ር ሙሉ ሙለታ በማህፀንና ፅንስ ህክምና በርካታ ስራዎችን ያከናወኑ ሲሆን የዓለም አቀፉ ሬስቱላ ማህበር (International Fistula Assocaition ) ፕሬዚዳንት በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ወደ ጎንደር ከተማ እየተመላለሱ በፌስቱላ ህክምና ላይ እገዛዎችን ያደርጋሉ፡፡
በአጠቃላይ እነዚህ አራት ግለሰቦች በየሞያቸው ለሀገር ባበረከቱ አስተዋጽኦ ላይ ተመስርቶ ዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷቸዋል፡፡ ከአራቱ ሰዎች መካከል በስፍራው ተገኝተው የክብር ዶክትሬታቸውን የተቀበሉት ዶ/ር ሙሉ ሙለታና አቶ ተፈራ ዋልዋ ብቻ ናቸው፡፡
ድምጻዊት አስቴር አወቀና አትሌት መሠረት ደፋር በዚህ ወቅት የሚገኙት በአሜሪካ ሀገር በመሆኑ በጎንደር ዩነቨርሲቲው ስርዓት ላይ መታደም አልቻሉም፡፡ አስቴር ነዋሪነቷ በአሜሪካ ሲሆን መሠረት ደግሞ ወደስፍራው ያቀናችው በወሊድ ምክንያት ነበር፡፡
ድምጻዊት አስቴር አወቀ በ1951 ዓ.ም ደቡብ ጎንደር ውስጥ ሃሙሲት በተባለች ትንሽዬ የገጠር ከተማ ነው የተወለደችው፡፡ በ1960 ዎቹ ወደ አዲስ አበባ መጥታ ሙዚቃን የጀመረችው አስቴር ከ40 ዓመት በላይ በሙዚቃው ዓለም ላይ ነግሳበታለች፡፡ ዛሬም ድረስ ተወዳጅ ስራዎቿን ስቱዲዮ ገብታ እየሠራች ለአድናቂዎቿ ከመልቀቋ ባሻገር በተለያዩ ሀገራት በመዘዋወር የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ታቀርባለች፡፡
አስቴር ሙዚቃን የጀመረችው ገና የ13 ዓመት ታዳጊ እያለች እንደነበር ይገለጻል፡፡ በዝነኛው ሀገር ፍቅር ቴያትር ቤት ተቀጥራ ሙዚቃን መስራት የጀመረችው አስቴር ከተለያዩ የሙዚቃ ባንዶች ጋር ተወዳጅ ስራዎቿን በሆቴሎችና በምሽት ክበቦች ታቀርብ ነበር፡፡
አስቴር በ1960ዎቹ የሙዚቃ ስራዎቿን ስታቀርብ ካጀቧት ባንዶች መካከል ኮንቲኔንታል ባንድ፣ ሆቴል ዲ አፍሪክ ባንድ፣ ሸበሌ ባንድና አይቤክስ ባንድ ይገኙበታል፡፡
በአስቴር የሙዚቃ ህይወት ውስጥ ትልቁን ሚና ከተጫወቱ ሰዎች መካከል አሊ ታንጎ አንዱና ዋናው ነው ማለት ይቻላል፡፡ አሊ የታዋቂው ታንጎ ሙዚቃ ቤት ባለቤት የነበረ ሠው ሲሆን አስቴር አወቀ የመጀመሪያ የሙዚቃ ካሴቷን ለአድማጮች እንድታደርስ ያደረገው አቶ አሊ ነበር፡፡ የአስቴር አወቀ 5 የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሞች የተሠሩትና ለገበያ የቀረቡት በታንጎ ሙዚቃ ቤት በኩል ነበር፡፡
በፍጥነት ተቀባይነትትን ያገኘችው ተወዳጇ ድምጻዊት አስቴር አወቀ ወደ አሜሪካ ተጉዛ ኑሮዋን በዚያ ከመሠረተች ከ30 በላይ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በደርግ ጊዜ የነበረውን ፓለቲካዊ እንቅስቃሴ በመሸሽ ወደ አሜሪካ ያቀናችው አስቴር መጀመሪያ ኑሮዋን በካሊፎርኒያ አድርጋ የነበረ ሲሆን ኋላ ላይ ግን ብዙ ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩበት ዋሽንግተን ዲሲ ህይወቷን መስርታለች፡፡ በዚያም በመዝናኛ ቦታዎችና በሬስቶራንቶች እንዲሁም በምሽት ክበቦች ተዘዋውራ የሙዚቃ ስራዎቿን ታቀርብ ነበር፡፡
አስቴር አወቀ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ በ1989 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲም 50 ሺህ ገደማ የሚገመቱ ተመልካቾች በተገኙበት ያቀረበችው የሙዚቃ ኮንሰርት አይረሴ ነው፡፡ በ1995 ዓ.ም ደግሞ ለእርዳታና ለትምህርት ቤቶች ግንባታ የሚውል ገንዘብ ለማግኘት የሚያስችሉ ሁለት ኮንሰርቶች በአዲስ አበባ ስታዲየምና በሸራተን አዲስ ሆቴል አቅርባ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ በርካታ የሙዚቃ አልበሞችን ለገበያ ካበቁ ድምጻዊያን መካከል አንዷ አስቴር አወቀ ናት፡፡ ከክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ በመቀጠል በአልበም ብዛት ሁለተኛ ናት፡፡ 24 የሙዚቃ አልበሞችን ለሙዚቃ አፍቃሪዎች አድርሳለች፡፡ የመጨረሻ አልበሟ ባለፈው ዓመት ለጆሮአችን የደረሰው ‹‹እወድሃለሁ›› የተሰኘው አልበሟ ነው፡፡
አስቴር አወቀ በሙዚቃ ስራዎቿ ስኬታማ ጊዜን ብታሳልፍም፣ በብዙ ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ ብትቀመጥም ተገቢው ቦታና ክብር ግን የተሰጣት አይመስልም ነበር፡፡ አሁን የሚገባትን አግኝታለች፡፡የሚሉ አድናቂዎች ብዙ ናቸው፤ የጎንደር ዩነቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪን ሰጥቷታል፡፡ የተዘነጋችውን ዘመን ተሻጋሪ ድምጻዊ አስታውሷታል፡፡
የዩኒሴፍ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር የሆነችው አስቴር ከልጅነቷ ጀምሮ በሙዚቃው ዓለም ያደረገችው አስተዋጽኦና አገሯን በማስተዋወቅ የተወጣቸው ሚና ለዚህ ክብር እንድትበቃ እንዳደረጋት ዩኒቨርሲቲው ገልጿል፡፡
መሰረት ደፋር
የ30 ዓመቷ ውጤታማ አትሌት መሠረት ደፋር በተለይ በ3ሺና በ5ሺ ሜትር በተደጋጋሚ ሻምፒዮን መሆን የቻለች አትሌት ናት፡፡ በኦሎምፒክና በዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክላ የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሯ ማስገኘት ችላለች፡፡ በአቴንስና በለንደን ኦሎምፒክ በ5ሺ ሜትር የሩጫ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነች ሲሆን በዓለም ሻምፒዮናም ኦሳካና ሞስኮ ላይ የሀገሯን ባንዲራ እንዲውለበለብ አድርጋለች፡፡
ውልደትና እድገት
ህዳር 9 ቀን 1976 ዓ.ም በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ጉለሌ አካባቢ የተወለደችው መሠረት ደፋር እንደ እድሜ እኩዮቿ በሰፈር ጨዋታ ላይ ተሳታፊ የነበረች ሲሆን፤ ሩጫ ነክ ጨዋታዎች ያስደስቷት ነበር፡፡ አንድ ሜትር ከ55 ሳንቲ ሜትር ቁመት እና 46 ኪሎ ግራም የምትመዝነው መሠረት ለመጀመሪያ ጊዜ ለሩጫ በኢንተርናሽናል ውድድር ላይ ለመካፈል ወደ ትራክ ስትገባ ተፎካካሪዎቿን ጥላ ቀድማ ትገባለች የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ አልነበረም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ መሠረት ቀደም ሲል በተመሳሳይ ውድድሮች ላይ አለመታየቷ ነው፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በአቴንስ ኦሎምፒክ ላይ ተሳትፋ ለሀገሯና ለራሷ የወርቅ ሜዳልያ የ5ሺህ ሜትር ርቀት ስታስመዘግብ አዲስና ፈጣን አትሌት ኢትዮጵያ ማፍራቷን ግልፅ ሆነ፡፡ ሁሌም ፊቷ ላይ የእልህና የአልበገርባይነት ስሜት የሚነበብባት መሰረት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት በ5 ሺህ ሜትር የወርቅ የኦሎምፒክ አሸናፊ በመሆን የማይደበዝዝ ታሪክ አስመዝግባለች፡፡ ውጤቷ ከእሷ ቀደም ብላ በኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ የተከፈተው የሴቶች አትሌቶቻችን የአሸናፊነት ስሜት መስመር እየያዘ መምጣቱን የሚያረጋግጥ ሆኗል፡፡
ሪኮርዶቿ
መሠረት ከኦሎሚፒክ ድሏ በተጨማሪ የተለያዩ የሶስት ርቀቶች ሪኮርዶች በእጇ ነበሩ፡፡ በ2007 ካደረገቻቸው በርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮች መካከል የሶስቱን ሪከርዶ በመስበር ብቃቷን አስመስክራለች፡፡ የመጀመሪያው ሪከርዷን የሰበረችው በየካቲት 3 ቀን 2007 እ.ኤ.አ በጀርመን በርሊን በተካሄደው የ3 ሺህ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር በ8 ደቂቃ 23 ሰከንድ በመግባት አሸናፊ ሆናለች፡፡
ከሶት ወራት በኋላም ሜይ 20 ቀን 2007 እ.ኤ.አ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ በተዘጋጀው የ2 ማይል ውድድር ላይ 9 ደቂቃ 10 ነጥብ 47 ሰኮንድ በመግባት ተጨማሪ ድልን ተጎናፀፈች፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ሰኔ 15 ቀን 2007 እ.ኤ.አ በኖርዌይ ኦስሎ የ5ሺህ ሜትር ርቀትን ሪከርድ 14 ደቂቃ 26 ነጥብ 63 በሆነ ሰዓት በመግባት ኦሎምፒክ ድሏን አድሳለች፡፡ ይህ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የያዘቻቸው ሪከርዶችና ያሳየቻቸው ብቃቶች ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጣት የሚገባ አትሌት መሆኗን አመላክቷል፡፡
መሠረት ከ2007 እ.ኤ.አ በፊትም ባደረገቻቸው ውድድሮች ማንነቷን አሳታለች፡፡ ከ2003 ጀምሮ እስከ 2006 እ.ኤ.አ ድረስ በበርሊን፣ በአቴንስ፣ በቡዳቬስት፣ በሄልሲንኪ፣ በሞኮና በኦሳካ ተደራራቢ ድሎችን በ3 ሺህ እና በአምስት ሺህ ሜትር ርቀቶች ተቀዳጅታለች፡፡ የ5 ሺህ ሜትር የዓለም ሪከርድን በኦስሎ የሰበረችው መሠረት ከውድድሩ በኋላ እንደተናገረችው ‹‹የዓለም ሪኮርድን በሁለት ወይም በሶስት ሰኮንዶች አሻሽላለሁ የሚል እምነት ነበር የነበረኝ አሁን ግን በ8 ሰኮንዶች ነው ያሻሻልኩት ይህም አስደናቂ ነው ብላለች፡፡ መሠረት የ5ሺህ ሜትርን የኦሎምፒክ ውድድር በአሸናፊነት ካጠናቀቀች በኋላ በተደረጉት ውድድሮች ሁሉ የበላይነተቷን እንዳስጠበቀች ሲሆን በ5ሺ ሜትር ውድድር የተሸነፈችው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ መሠረት የ5 ሺህ ሜትር ርቀትን ተወዳድራ የተሸነፈችው በ2005 እ.ኤ.አ በሄልሲንኪ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ በሀገሯ ልጅ በጥሩነሽ ዲባባ ነው፡፡
የበጎ አድራጎት ተሳትፎ
መሠረት በአትሌቲክስ ካላት ተሳትፎ በተጨማሪ በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ ተሳትፎ ታደርጋለች፡፡ በ2005 እ.ኤ.አ የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የበጎ ምግባር አምባሳደር አድርጎ የሰየማት ሲሆን በዚሁ ዙሪያ በህፃናት ክትባትና በህፃናት የጉልበት ብዝበዛ ላይ በሚዘጋጁ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰሚናሮች ላይ በመገኘት ተሳትፎ አድርጋለች፡፡
‹‹ሴቶች ከድህነት ራሳቸውን ማላቀቅ እንዲችሉ የበኩሌን ጥረት አደርጋለሁ›› የምትለው መሠረት በተለይ እንደ ኤች አይ ቪ ባሉ ህመሞች የሚጠቁ ህፃናትንና እናቶችን በመርዳት ከወገኖቻቸው ጋር መቀላቀል እንደሚገባ ተናግራለች፡፡ አትሌት መሰረት ደፋር የዩኒሴፍ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር በመሆን ታገለግላለች፡፡
ሽልማቱ
በ2007 ማብቂያ ላይ በፈረንሳይ ሞናኮ በሚገኘው ባለ አምስት ኮከብ ሞንቴ ካርሎ ልዩ ሆቴል ውስጥ በ2007 እ.ኤ.አ ባሳየችው ምርጥ ብቃት የዓመቱ ምርጥ አትሌት የተባለችውን መሠረት ደፋር ስሟ ሲጠራ ‹‹ይገባታል›› በሚል ስሜት አዳራሹ በጭብጨባ ተሞላ፡፡ ወደ መድረክ ያመራችው መሠረት ደፋር የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊትና አፍሪካዊት የዚህ ክብር ባለቤት ሆነች፡፡ አስቀድማም መሰረት ታሪክ ሠርታለች፡፡ በአቴንስ ኦሎምፒክ በአምስት ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ በማግኘት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ኢትዮጵያዊ አትሌት ነች፡፡ የአቴንስ ኦሎምፒክ በኋላ 5ሺህ ሜትር ርቀትን የግል ሀብቷ አድርጋ ይዛዋለች፡፡ በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ የ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤትም ነች በየተወዳደረችባቸው ቦታዎች ሁሉ የ5ሺ ሜትር ወርቅ የመሠረት ደፋር ብቻ መሆን ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡
በ2008 የፈረንጆች ዓመት ባሳየችው ድንቅ ብቃት የዓመቱ ኮከብ አትሌት ተብላ የተመረጠችው መሠረት ደፋር ሽልማቱን ለመቀበል ወደ መድረክ በወጣችበት ወቅት ያደረገችው ንግግር የብዙዎችን ትረኩረት ስቧል፡፡ ‹‹ይህንን ሽልማት በማግኘቴ የተሰማኝን ደስታ ለመግለፅ ቃላት የሉኝም፡፡ ሽልማቱ የእኔ ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ነው፡፡ ይህንን ሽልማት ወደ አትሌቲክስ መንደር ለማምጣት ለሚጣጣሩ ወጣት ሴቶች መታሰቢያ እንዲሆንልኝ እፈልጋለሁ›› ብላለች፡፡
ከረዥም ጊዜ ፍቅረኛዋ ቴዎድሮስ ሀይሉ ጋር ትዳር የመሰረተችው መሠረት በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያ ልጇን ለመውለድ በአሜረካን ትገኛለች፤ ትዳሯ ለስኬቷ አስተዋፅኦ እንዳደረገላት ትናገራለች፡፡ ጊዜና ቦታ ሳይመርጡ ለዚህ ስኬት እንድበቃ ላደረጉኝ ሁሉ ምስጋናዬ አቀርባለሁ ያለችው መሠረት ሽልማቱ የባለቤቷና የእሷ የጋራ ሊሆን እንደሚገባ መስክራለች፡፡
አትሌት መሠረት ደፋር ከ3ሺ ሜትር ጀምሮ እስከ ግማሽ ማራቶን ድረስ ሻምፒዮን በመሆን በርካታ ስኬቶች ያስመዘገበች ሲሆን ገና በወጣትነቷ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷታል፡፡ ወጣቷ አትሌት መሰረት ደፋር ቀደም ሲል ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለሁለቱ አንጋፋ አትሌቶች ሀይሌ ገ/ስላሴና ደራርቱ ቱሉ ከሰጠው የአትሌቶች የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ቀጥሎ ሶስተኛዋ አትሌት ናት፡፡
የክብር ዶክትሬት ድግሪ መጠሪያ ይሆናል?
የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በአንድ ተቋም የሚሰጥ እውቅና ይሁን እንጂ ይዞት የሚመጣው የሞራል ጥያቄ አለ፡፡ የዩኒቨርሲቲ በር የመርገጥ ዕድሉ የሌላቸው ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ተምረው ዲግሪ ያገኙ ግለሰቦችም በዚህ ስም ለመጠራት ፍላጎት ሲያጡ በተለያየ ጊዜ ተስተውሏል፡፡ ያም ሆኖ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ያገኙ ግለሰቦች ክብሩንና እውቅናውን ያገኙት በስራቸው መሆኑን በማመን በየትኛውም ቦታ ከስማቸው በፊት ሲጠሩበት ይታያል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በትምህርት እንደተገኘ የአካዳሚክ ማዕረግ ለመቁጠር በመቸገር በመደበኛ ስማቸው ብቻ እንዲጠሩ ያደርጋሉ፡፡
ሳሙኤል ጆንሠን በችግር ምክንያት የኮሌጅ ትምህርቱን ያቋረጠ ደራሲ ነው፡፡ ጆንሰን በፃፋቸው የድርሰት ሥራዎች መሠረት እ.ኤ.አ በ1965 የTrinity college of Dubline የህግ የዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቶት ነበር፡፡ ጆንሠን ከዚህ ጊዜ በኋላ በማንኛውም ህዝባዊ የስብሰባዎችና የሚዲያ መድረኮች ላይ ራሱን እንደ ዶክተር ነበር የሚያስተዋውቀው፡፡ ቤንጃሚን ፍራንከሊንም ራሱን ‹‹ዶክተር ፍራንክሊን›› ብሎ ይጠራ እንደነበር መዛግብት ያወሳሉ፡፡
የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሚሰጠው ከነሙሉ ክብሩ ጥቅሙና መብቶቹ ጋር እንደሆነ ህግ ይደነግጋል፡፡ መብቶቹ በስያሜው መጠራትን ያካትታል፡፡ በእርግጥ በክብር ዶክትሬት ዲግሪ መጠራት የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ሰዎች በዚህ የማዕረግ ስም የሚጠሩት እስከፈለጉ ድረስ ብቻ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል፡፡
ከኢትዮጵያ መሪዎች መካከል የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በማግኘት በኩል ቀዳሚው አፄ ሀይለስላሴ ናቸው፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ሀይለስላሴ እ.ኤ.አ በ1964 ከሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢ ጥበቃና በደን ጥበቃ ላይ ላደረጉት አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷቸዋል፡፡ ፕሬዚዳት መንግስቱ ኃ/ማርያምም ከሞስኮ ዩኒቨርሲቲ ተመሳሳይ ዲግሪ ደርሷቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከኮሪያ ሀናን ዩኒቨርሲቲ በ1994 ዓ.ም በፖለቲካል ሳይንስ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሲቀበሉ ፕሬዚዳት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ (እሳቸው ስሙን ከማያስታወሱት ) አንድ የአሜሪካ ዩነቨርሲቲና ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ሆኖም ሁሉም መሪዎች በኦፊሻል በዚህ ማዕረግ ሲጠሩ አይሰማም፡፡፡ ከፕሬዚዳት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በስተቀር ለምን እንደማይጠሩበት የተናገሩ ስለመኖራቸው መረጃ የለኝም፡፡ ፕሬዚዳት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ግን በህዳር ወር 2000 ዓ.ም ለቁም ነገር መፅሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ‹‹ዶክተር ተብዬ መጠራት አልፈልግም፤ ተምሬ ስላላገኘሁት ደስታ አይሰማኝም›› ብለው ነበር፡፡
በክቡር ዶክትሬት ዲግሪ መጠራት የምርጫ ጉዳይ ነው ብለናል፡፡ የምርጫ ጉዳይ ቢሆንም ግለሰቦቹ ፈልገውም ሆነ ሳይፈልጉ እንዴት ነው መጠራት ያለባቸው የሚለው ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በተለይ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የክብር ዶክትሬት ዲግሪና ፕሮፌሽናል ዲግሪን ባለመለየት አንዱን ከሌላው ጋር ቀላቅሎ የማቅረብ ሁኔታ ይታያል፡፡ የጥላሁን ገሠሠን የሙት ዓመት መታሰቢያን በተመለከተ ፕሮግራም የሚመራ የአንድ ኤፍ ኤም ጋዜጠኛ ‹‹ የዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ 1ኛ ዓመት የመታሰቢያ ዝግጅት በሙዚቃ ኮንሰርት ይካሄዳል›› ሲል ማድመጤን አስታውሳለሁ፡፡ አሁንም ድረስ በተመሳሳይ መልኩ የሚጠሩ ጋዜጠኞች አሉ፡፡ የክብር ዶክትሬት ዲግሪውን ያገኙ ግለሰቦች የሚጠሩበትን አግባብ በተመለከተ ቁም ነገር መፅሔት የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴን ጠይቃ ነበር፡፡ (ደብዳቤውን ይመልከቱ) ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ እንዳሉት የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ያገኙ ግለሰቦች የክብር ዶክተር ተብለው መጠራት እንደሚችሉ በምሳሌ አስደግፈው አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ያገኙ ሰዎችን በትምህርት የዶክትሬት ዲግሪ እንዳገኙ ሰዎች አስመስለን መጥራት ተገቢ እንዳልሆነ (ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ማለት ይቻላል፤ ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ ማለት ግን እንደማይቻል፤ጥላሁን የሚጠራው የክብር ዶ/ር ተብሎ እንደሆነ) መረዳት ያስፈልጋል፡፡
‹‹በጥርጣሬ ውስጥ የወደቀው ክብር››
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ከሠጣቸው ሰዎች መካከል በአንዳንዶቹ ላይ ጥያቄዎች እያሳረፈ ነው፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ድረገፆች ላይ አስተያየታቸውን የሚሠጡ ሰዎች በአቶ ተፈራ ዋልዋ የክብር ዶክትሬት ላይ ተገቢነቱን የተጠራጠሩ ስለመሆናቸው ሲገልፁ ነበር፡፡ እኝህ ሰው ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከተሰጣቸው ክብር ጋር የሚጣጣም ስለመሆኑ ጥርጣሬ አላቸው፡፡ ለአቶ ተፈራ ዋልዋ የተሰጠውን የክብር ዶክትሬት ፖለቲካዊ ትርጉም በመስጠት ተገቢነት የሌለው ብለውታል፡፡ በርግጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዩኒቨርሲቲዎቹ የክብር ዶክትሬት የሚሰጧቸው ሰዎች ፖለቲካዊ አንድንድምታ ያላቸው ይመስላሉ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለቀድሞው ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ለታቦ ምቤኪ የሰጠውና ዘንድሮ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ለኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ክብሩን መስጠቱ ለዚህ ሃሳብ መነሳት አንዱ ምክንያት ነው፡፡ቁ
ምንጭ በአዲስ አበባ የሚታተመው ቁምነገር መጽሔት