Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Entertainment
Viewing all articles
Browse latest Browse all 261

የምስጢራዊው ድምፃዊ ‹አዳዲስ› ምስጢሮች

$
0
0

ጥላሁን ገሠሠ የዛሬ ስድስት ዓመት በፋሲካ ዋዜማ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ ህዝብና መንግስት እንደ አንድ ሆነው ቀብሩን እንዳደመቁትና በጋራ እንደሸኙት እናስታውሳለን፡፡ጥላሁን በህይወት በነበረባቸው ዘመናት በህይወቱ ውስጥ ያሉ ብዙ አነጋጋሪና ምስጢራዊ ጉዳዮችን ሳያብራራና ግልፅ ሳያደርግ ማለፉን ተከትሎ በዓመቱ የወጣው የህይውት ታሪኩን የያዘው መፅሐፍ ነገሮችን አፍረጥርጦ ይፋ ያደርጋል የሚል ግምት ነበር፡፡ ያም ሆኖ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ‹ደራሲያን› በቡድን ተፅፎ የታተመው መፅሐፍ በጥላሁን ዙሪያ ያሉና የሚነገሩ ምስጢሮችን ሳያፍታታም ሆነ ሳይነካ የወጣ መፅሐፍ መሆኑ በወቅቱ አነጋጋሪ ነበር፡፡ ጥላሁን ገሠሠ በሕይወት በነበረበት ወቅት ለመጨረሻ ጊዜ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ ተመስርቶ ተዘጋጀ የተባለው መፅሐፍ አንድ የህይወት ታሪክ መፅሐፍ መያዝ ያለበትን መሠረታዊ ደንቦችን ያልተከተለና ጥላሁን ገሠሠን የማይመጥን መፅሐፍ መሆኑን ቁም ነገር መፅሔት በወቅቱ አስተያየቷን አስፍራለች፡፡
tilahun
ጥላሁን ገሠሠ የሚሊዮኖችን ስሜት የመቆጣጠሩን ያህል፤ ከ50 ዓመታት በላይ የማንጎራጎሩን ያህል፤በሀገር ፍቅር ስሜት ህዝቡን ያነደደ ሰው የመሆኑን ያህል የግል ህይወቱና ማንነቱም ለብዙዎች ምስጢር ነው፡፡ በትውልዱ፤ በዕድገቱ፤ በቤተሰቦቹ ፤ በትዳር ህይወቱና በልጆቹ ዙሪያ የሚታወቁ ነገሮች የጠለቁ አይደሉም፡፡ይህንኑ መነሻ በማድረግ ይመስላል ሰሞኑን በጥላሁን ገሠሠ ዙሪያ አንድ መፅሐፍ ታትሞ ለአንባቢያን ቀርቧል፡፡‹ጥላሁን ገሠሠ የሕይወቱ ታሪክና ምስጢር› በሚል ርዕስ በጋዜጠኛ ዘከሪያ መሐመድ የተፃፈው መፅሀፍ ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ በቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ በተገለፀው መፅሐፍ ላይ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡ ከአስተዳደጉ፤ከቤተሰቡ ማንነት፤ከሙዚቃው ስራው አንፃር ሳይንሳዊ የህይወት ታሪክ አፃፃፍን ተከትሎ እንደተዘጋጀ የሚናገረው ጋዜጠኛ ዘካሪያ ጥላሁን ገሠሠ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ከሁለት ወራት በኃላ ስራውን መጀመሩንና አምስት ዓመታት እንደፈጀበት ይናገራል፡፡ በአራት ምዕራፎች የተከፋፈለው መፅሐፉ 448 ገጽ ያለው ሲሆን ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በተፃፈው መፅሀፍ ላይ የተገለፁ የሀቅ መፋለሶችን እንደሚያስተካክልና ለዓመታት ምስጢር የነበሩ ጉዳዮችን ‹ሆድ ይፍጀውን › ጨምሮ ለአንባቢያን ይፋ ያደርጋል፡፡ ከቤተሰቡ በተገኘ መረጃ ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀው ይህ መፅሐፍ እስከዛሬ ድረስ በየትኛውም ሚዲያ ላይ ያልታዩ ጥላሁን ገሠሠ የአንድ ዓመት ህፃን ሳለ ጀምሮ ያሉ ፎቶግራፎችን አካቶ ይዟል፡፡
ያልተፈቱት ምስጢሮች
በጥላሁን ህይወት ብዙ ያልተፈቱ ምስጢሮች አሉ፡፡ በ1985 ዓ.ም ከተፈጸመበት የግድያ ሙከራ ጀምሮ የቤተሰባዊ ህይወቱና የውልደት ቦታው ምስጢር ሆነው ወይም በተዛቡ መረጃዎች ታጅበው አመታትን ዘልቀዋል፡፡
የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ጋዜጠኛ ዘከርያስ መሃመድ ከአቶ ፈይሣ ሃሰና ሃይሌ ማስታወሻ ላይ ያገኛቸውን መረጃዎች መነሻ በማድረግ እውነቱን ላሳያችሁ ይለናል፡፡ በመጽሐፉ እንደቀረበው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉሥ የሚል ካባ የተደረበለት ክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ የተወለደው አዲስ አበባ ሳይሆን ወሊሶ አካባቢ ሶየማ በተባለ ቦታ ነው፡፡ ከአቶ ፈይሣ ሃሰና ማስታወሻ የተገኘው ጽሑፍ እንዲህ ይላል፡-
‹‹በወረራው ምክንያት ተበታትኖ የነበረው ቤተሰባችን ሶየማ በሚገኘው የቤተሰብ ርስት ላይ ዳግም ተገናኘ፤ በዚህ ጊዜ ጌጤነሽ (የጥላሁን እናት) መውለጃዋ ተቃርቦ በጣም ከብዳ ነበር፡፡
… መስከረም 17 ቀን 1933 ዓ.ም የመስቀል በዓል ዕለት መላው ቤተሰባችን በወላጅ አባቴ በአቶ ሃሰና ቤኛ እልፍኝ ተሰብስበን ነበር፡፡ ከዕኩለ ቀን በኋላ በትልቁ እልፍኝ ጌጤነሽ በምጥ ተያዘች፤ ፅንሱ በሆድዋ ውስጥ ፋፍቶ ስለነበር ምጧ ረጅም ሰዓት ወሰደ፤ በዚህም ምክንያት ጌጤነሽ ደካክሟት ምጧ በተራዘመ ቁጥር ድካምዋ በርትቶ አቅም እያጣች በመሄድዋ ለእሷም ሆነ ለልጅዋ ህይወት በጣም ሰጋን፤ ቤተሰቡ በሙሉ ፀሎትና ልመና ያደርግ ጀምር፤ በመጨረሻም ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ሲሆን ጌጤነሽ ወንድ ልጅ ተገላገለች፤ የጌጤነሽ እናት ነገዬ አብደላ ዲንሳሞ ለተወለደው ልጅ ደገፋ ስትል ስም አወጣችለት፡፡›› (ገፅ 29-30)

ጥላሁን ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ከተለያዩ ሴቶች ጋር ጋብቻ የፈፀመ ሲሆን የመጀመሪያ ባለቤቱ መሆናቸው የሚነገረው ወ/ሮ አሥራት አለሙ ቢሆንም ጋዜጠኛ ዘከሪያ በአዲሱ መፅሐፉ ይህንን እውነት ያፈርሰዋል፡፡ የመጀመሪያ ባለቤቱ ፊት በር አካባቢ ትኖር የነበረች ፈለቀች ማሞ የተባለች ሴት ናት ይለናል፡፡ ከፈለቀች ጋር በሰርግ መጋባታቸውም ይነገራል፡፡ በወቅቱ ካሳ ተሰማ፣ እሳቱ ተሰማ እና ሸዋንዳኝ ወልደየስ የጥላሁን ሚዜዎች ነበሩ፡፡ (ገፅ 352)፡፡

ይሁን እና ከወ/ሮ ፈለቀች ጋር ረጅም አመታትን በትዳር አልቆዩም፡፡ በቅናት ምክንያት ፈለቀች ጥላው ጠፋች፡፡ ከዚያ በኋላ ሁለቱ ሰዎች ለረዥም ጊዚያት በአካል እንኳ ተገናኝተው አያውቁም ነበር፡፡ ዘከርያ የፈለቀች ጥላሁንን ባዶ ቤት ጥላው መጥፋት ከሌላ የልጅነት ታሪኩ ጋር አዛምዶ ይተነትነዋል፡፡

አቶ ፈይሳ ማናቸው?

አቶ ፈይሳ ሃሰና ሐይሌ የጥላሁን ገሠሠ አጎት ናቸው፡፡ ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ የግል ታሪካቸውን ጨምሮ የጥላሁን እና የቤተዘመዶቹን ታሪኮች በመፃፍና ፎቶግራፎቹን በማንሳት ታሪክን ለትውልድ ያስቀመጡ ታሪከኛ ሰው ናቸው፡፡ ጋዜጠኛው ዘከርያ መሐመድ አሁን በመፅሐፍ መልክ ላሳተመው አዲስ የጥላሁን ታሪክ መነሻ የሆኑት እርሳቸው ናቸው፡፡ ይህ የአቶ ፈይሳ ማስታወሻ በጥላሁን ዘንድም የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁን እና እሱ በሕይወት እያለ እንዲታተም አይፈልግም ነበር፡፡ ለአመታት ከጋዜጠኞች ደብቋቸው የነበሩት ታሪኮች ተገልጠው ከአዲሱ እውነት ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥን አይፈልግም ነበር፡፡ ይሁን እና ህይወቱ ካለፈ በኋላ እንደሚታተም እርግጠኛ ነበር፡፡ ለአቶ ፈይሳ ልጆችም ማንቂያ የሚመስል ሀሳብ ሹክ ብሏቸዋል፡፡ ‹‹እኔ ስሞት ይህን ታሪክ አትተኙበትም›› የሚል፡፡

የ22 ዓመታት እንቆቅልሽ

ጥላሁን ‹‹ሆድ ይፍጀው›› በሚል ያለፈው የ1985ቱ የግድያ ሙከራ በማን እና ለምን እንደተፈፀመ ጥርት ያለ መረጃ አሁንም ድረስ ባይገኝም ዘከርያ በመፅሐፉ ውስጥ ያስቀመጣቸው ትንታኔዎች ሁለት ድምዳሜዎች ላይ ሊያደርሱን ይታትራሉ፡፡ የመጀመሪያው ድምዳሜ ጥላሁን እራሱን ለማጥፋት ሙከራ አድርጓል የሚል ነው፡፡ አደጋው ከደረሰበት በኋላ ለንደን ለህክምና በሄደበት ወቅት ከቅርብ ጓደኛውና የጀርመን ሬድዮ ጋዜጠኛ ከነበረው ጌታቸው ደስታ ጋር ሲያወሩ እንደቀልድም ቢሆን ራሱን ለመግደል መሞከሩን ነግሮታል፡፡ ‹‹ስማ ጥላሁን ያኔ የጀመረህ ሰውዬ ሳይጨርስ አይተውህም፤ ወንድምህ ነኝ፡፡ ነገ ብትሞት በሚቻለው በማንኛውም መንገድ ገዳይህን እፋረደዋለሁ…. ንገረኝ… ማነው የወጋህ?››
‹‹ ራሴ ነኝ››
‹‹ሂድ ባክህን… ይሄን ሂድና ለምታወራለት አውራ እኔ አለቀበልህም›› (ገፅ 290)

ጌታቸው የጥላሁንን መልስ ያመነ አይመስልም፡፡ ነገር ግን ከዚህ የጥላሁን መልስ ተነስተን ሊሆን የሚችልበትን እድል ስንገምት አንድ ጥያቄ ማንሳት ጥሩ ይሆናል፡፡ ጥላሁን በርግጥ የመግደል ሙከራ የተደረገበት በሰው ከሆነ ከዚያ በኋላ በነበሩት እነዚያ ሁሉ አመታት ያ ሰው ጥላሁንን ለምን አልተተናኮለውም፡፡ መቼም አንድ ሰው በጊዜያዊ ንዴት ያን ያህል ጥቃት ይፈፅማል ተብሎ አይታሰብም፤ ከዚያ በተጨማሪ ግን በፖሊስ የምርመራ ውጤት ሊረጋገጥ አልቻለም፡፡ ወይም ተረጋግጦ ቢሆን እንኳን በድብቅ ቀርቷል፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ጥላሁን እራሱን ለማጥፋት ሞክሯል ወደሚል ጫፍ ይወስዱናል፡፡ ዘከርያ በመጽሐፉ ከልጅነቱ ጀምሮ የነበሩትን የጥላሁን ህይወት በሰፊው በመተንተን እንቆቅልሾቹን ሊፈታልን ሞክሯል፡፡

በሌላኛው ጫፍ ደሞ ጥላሁን ላይ ጥቃት የፈፀመ ሰው እንዳለ እንድናስብ ይገፋናል፡፡ ሰውዬው አቶ አወቀ መንገሻ ይባላል፡፡ ከገፅ 292 – 293 ድረስ በሰፈረው ፅሁፍ የቀደሙ መፅሔቶች ላይ የወጡትን መረጃዎች መሠረት በማድረግ ስለ ጉዳዩ ተተንትኖ ቀርቧል፡፡

ጥላሁንና አቶ አወቀ የሚቀራረቡ ጓደኛሞች ቢሆኑም በመጨረሻ ግን ተኮራርፈው ነበር፤ በዚህ ምክንያት አቶ አወቀ ወይም በአቶ አወቀ የታዘዘ ሰው ጥላሁን ላይ ጥቃቱን ፈፅሞ ሊሆን ይችላል ወደሚል ሀሳብ ይገፋናል፡፡ ተከታዩን ፅሁፍ እንመልከት፡-
‹‹ በ1990ዎቹ አጋማሽ አካባቢ አንድ እለት መሻለኪያ በሚገኘው የጥላሁን ሼል ነዳጅ ማደያ ቢሮ የስልክ ጥሪ አቃጨለ፡፡ የጥላሁን ፀሐፊ ስልኩን አንስታ ‹‹ጤና ይስጥልኝ አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ቢሮ›› አለች፡፡

… ‹‹አወቀ የሚባል ሰው ሞቷል፡፡ እንኳን ደስ አለህ በይው፡፡››
‹‹እንዴ! ሰው ሲሞት እንዴት ለሰው እንኳን ደስ ያለህ ይባላል?!››
‹‹ግዴለም ለእርሱ ስትነግሪው ይገባዋል፡፡ አንቺ የማታውቂው ነገር ስላለ ነው፡፡››
በማግስቱ ይሁን በሳልስቱ ጥላሁን ከአሜሪካ ስልክ ደወለ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ፀሐፊዋ ሌሎች መልዕክቶችን አስቀድማ ‹‹አወቀ የሚባል ሰው ሞቷል የሚል መልዕክትም ተቀብያለሁ›› አለችው፡፡ የቀረውን መልእክት ግን ማስተላለፍ አልፈለገችም፡፡ … ምንም እንኳ በዛች ሰዓት የጥላሁን ገፅታ ባይታያትም ፀሐፊዋ ከምትሰማው የጥላሁን ድምፅ ሁለመናው ወለል ብሎ ይታያት ነበር፡፡ ከዚያ ለራሱ የሚያወራ ያህል ‹‹ ህም እርሱ ሞተና… እኔ ነዋሪ ሆንኩኝ?!›› አለ፡፡ (ገፅ 297)

መጽሐፉ ለምን?

የመጽሐፉ አዘጋጅ ዘከርያ መሐመድ በመቅድሙ ላይ እንዳሰፈረው እስካሁን በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን የሰማናቸውና ያነበብናቸው እንዲሁም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በ2002 ዓ.ም ለህትመት ባበቃው መፅሐፍ የሰፈሩት የጥላሁን ገሠሠ ታሪኮች በመሠረታዊ ሀቅ ደረጃ ጉድለት አለባቸው፡፡ ‹‹ ጥላሁን ወደ ሙዚቃ ዓለም ከገባበት ዘመን አንስቶ እስከ ህልፈቱ ማግስት፣ ሕይወትና ሥራዎቹን የሚመለከቱ አያሌ ዘገባዎች በመገናኛ ብዙሀን ቀርበዋል በ2002 የህልፈቱ 1ኛ ዓመት በተከበረበት ወቅት ደግሞ ጥላሁን ገሠሠ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉስ የሚል ርዕስ ያለው መፅሐፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ ነገር ግን በዚህ መፅሐፍ ውስጥ የምናነበው የጥላሁንን የሕይወት ታሪክ እና ርዕሱ ከተጠቀሰው መፅሐፍ መሆኑ ከዚህ ቀደም ሲል በመገናኛ ብዙሀን ሲተረክ የኖረው የጥላሁን ሕይወት ታሪክ በመሠረታዊ ሀቅ ደረጃ ለየቅል ናቸው፡፡ ጥላሁን ገሠሠ የህይወቱ ታሪክ እና ሚስጢር የተሰኘውን ይህን መፅሐፍ የወለደው ከዚህ ልዩነት ጀርባ ባለው በጥላሁን ህይወት እና በስብዕናው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳደረ በምንም አጋጣሚ ያልተነገረ ቤተሰባዊ ክስተት ነው፡፡
ባለፉት 50 ዓመታት ስናነብና ስንሰማ የኖርነው የጥላሁን የትውልድ፣ የልጅነትና የቤተሰቡ ታሪክ ጥላሁን እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ ድረስ ሚስጥር አደድጎ የያዘው የልጅነት ዘመን ቤተሰባዊ ጠባሳ የወለደው የተቀየረ ታሪክ ነው፡፡ ይህ መፅሐፍ በጥላሁን የሕይወት ታሪክ ውስጥ ያሉ መሠረታዊ ሀቆች እንዴትና ለምን እንደተቀየሩ፣ እንዲሁም በጥላሁን ስብዕና ላይ ያሳደረው አንድምታ ምን እንደሚመስል ይተርካል፣ ይተነትናል፡፡›› ይላል፡፡
ዘከርያ መጽሐፉን ለማዘጋጀት የተነሳበትን አላማ ሲገልጽም፡- ‹‹ የተዛቡ ታሪኮችን ማስተካከልና የተዛቡ እይታዎችንና ግንዛቤዎችን ማስተካከል፣ ሰውዬውን መረዳት፣ ከሱ ህይወት መማር እንድንችል ነው፡፡ ለኛም እኮ ይጠቅመናል የሱ ህይወት ምን አይነት ምስቅልቅል ውስጥ እንደነበር እናያለን፡፡ እኔ ጥላሁን ገሰሰ ዝም ብሎ ተረት እንዲሆን አልፈልግም፡፡ ማንም የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ ጥላሁን የተለያየ ሰው በሚያነሳው ብጥስጣሽ አሉባልታ መካከል እንዲቆም አልፈልግም፤ ይሄ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ምን አይነት ስብዕና ነበረው፤ ከህዝቡ ጋር ምን አይነት መቀራረብ ነበረው፤ የልጅነት ህይወቱ ምንድነው የሚሉትን ነገሮች መለስ ብለን ብናውቅ እንማርበታለን፤ እንጠቀምበታለን፤ እሱንም ደግሞ ከተዛቡ ግንዛቤዎች እናጠራዋለን፡፡››ይለናል፡፡

ጥላሁን በህይወት ዘመኑ የደበቀን የግል ምስጢሮች እንዳሉትም ዘከርያ ይናገራል፡- ‹‹ እኛም አላወቅንለትም እሱም ደብቆናል፡፡ ሁለቱም ነው የሚባለው እሱ ስለደበቀን ነው እኮ እኛም ያላወቅነው፡፡ ነገር ግን ስለደበቀንና ሌላ ታሪክ ስለነገረን ውሸታም ነው ልንለው አንችልም፡፡ በርግጥ ውሸት ነው፡፡ ግን ለህልውናው ሲል እራሱን ለማቆየት ሲል ስሜቱን ለማጠገግ ሲል በሰቀቀን ላለመሞት ሲል አንድ ሰው ይዋሻል፡፡ ይሄ የሁላችንም ጉዳይ ነው ይሄ መፅሐፍ እኮ የጥላሁንን ታሪክ ለመናገር የወጣም አይደለም፡፡ ብዙ ሰዎችን ያክማል ብዬ አስባለሁ እኔ፡፡ ጥላሁን ያደረገውን ማድረግ ጉዳትም ጥቅምም ይኖረዋል፡፡ ወደኋላ ያሉ መጥፎ ትውስታዎችን እንሸሻቸዋለን፤ ማስታወስ አንፈልግም፤ ስለዚህ ከዚያ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ማውራት ካለብን ከዚያ ሸሽተን ሌላ ታሪክ ጨምረንበት እንናገራለን፡፡ ጥላሁን ዝነኛ ባይሆን ኖሮ እኮ ሁሉም ሰላም ይሆን ነበር፡፡ ዝነኛ የሆነውም ያንን ታሪክ በመሸሹ ነው፡፡ ጥቅምም ጉዳትም ነበረው፡፡ ጥላሁን ደስተኛ ሰው አልነበረም፤ ለራሱ ሆኖ አይደለም የኖረው፡፡ እነዚያ የሚጎዱት ነገሮች ደግሞ በቀላሉ የሚታረቁት አይደሉም፡፡ እና ለምን ለህዝብ ያንን ታሪኩን አልተናገረም ልል አልችልም፡፡ ግን ስነልቦናውን ጎድቶታል፡፡ የተረጋጋ የትዳር ሕይወት እንዳይኖው አድርጎታል፡፡ የሆነ አቅሙን ነስቶታል፡፡ የሚፈጠሩ አደጋዎችን የመጋፈጥ አቅሙን ሸርሽሮታል፤ በዚህ ምክንያት ቤተሰቡ ይፈርሳል፡፡ ምክንያት አለው ሰዎች እንዲረዱት እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ለምሳሌ ጥላሁን ብዙ ስለማግባቱ አንስተው በመጥፎ ሁኔታ የሚተረጉሙት አሉ፡፡ ለምንድነው ብለው ግን አይጠይቁም፡፡ ዝም ብለው ‹አለሌነት› አድርገው ይወስዱታል፡፡ አይደለም / ላይሆን ይችላል፡፡ መጀመሪያ ለምንድ ነው ብለን ጠይቀን ትክክለኛውን ነገር መረዳት አለብን››

Source: ቁም ነገር ቅጽ 13 ቁጥር 201 ሚያዝያ 2007

The post የምስጢራዊው ድምፃዊ ‹አዳዲስ› ምስጢሮች appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 261

Trending Articles