Quantcast
Channel: Zehabesha Amharic » Entertainment
Viewing all articles
Browse latest Browse all 261

የጌትነት ሀለሐ እና ልማታዊ ሥነ ጥበብ

$
0
0

(ማስረሻ ማሞ)

ከኻያው ክፍለ ዘመን ታላላቅ ፈላስፎች የሚመደበው ኦስትሪያዊ ቪትገንስታይን፦ ፈላስፎችን ከማኅበረሰብ የተነጠሉ የየትኛውም “አገር” ዜጋ ያልኾኑ አድርጎ ይመስላቸዋል። የቪትገንስታይን ሐሳብ አከራካሪ ቢኾንም አስደንጋጭ አይደለም። በታሪክ ጀግኖች ፈላስፎች ብለን ከምንጠራቸው መካከል በርካቶቹ ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ሥር ነቀል በኾነ መንገድ የተነጠሉ (radical detachment) እና ማኅበረሰባቸውን ከውጭ የሚያዩ፣ የሚሄይሱ እና የሚተነትኑ ናቸው። ስለ አርቲስቶች ግን እንዲህ ዐይነት አስተያየት ሲሰጥ ብንሰማ ያስደነግጠናል። እንዲያውም ታዋቂው አንግሎ-አሜሪካዊ ገጣሚ እና ጸሐፊ ኦውደን እንዲህ ሲል ያስምጣቸዋል፤
A poet’s hope:
to be, like some valley cheese
local, but praised elsewhere
getenet eneyew
ማይክል ዋልዘር እንደሚለው አርቲስት ሊገፈተር፣ ከራሱ ማኅበረሰብ ጋራ ሊጣላ፣ እንደ ነቢይ ባገሩ ላይከበር እና ሊንገላታ ይችላል። ይኹንና ራሱን ከማኅበረሰቡ አይገነጥልም፤ እንደ ቪትገንስታይን ፈላስፋ አየር ላይ ሊንሳፈፍ አይቻለውም። ለዚህም ይመስለኛል አርቲስቶች በሚሠሩት እና በሚናገሩት በብዙዎቻችን ውስጥ ጠንካራ የኾነ አዎንታዊ እና አሉታዊ ስሜት የሚጭኑብን። በቅርቡ ጌትነት እንየው በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ በሊቢያ የደረሰውን ዘግናኝ ግድያ አስመልክቶ ስለ ስደተኝነት እና ተጠያቂነት ያቀረበውን “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” ግጥም ስመለከት እና የፈጠረውን ነውጥ ስከታተል የተሰማኝ ይህ ዐይነት ስሜት ነው። ጌትነት እንዲህ ዐይነት ነገር ሲፈጥር የመጀመርያው አይደለም። ከጥቂት ዓመታት በፊት አንዳንዶቻችን የአሁኑ ዘመን የኢትዮጵያ አምባገነንነት ኢንጂኒየር እና አንቀሳቃሽ ናቸው ብለን እየኮነንናቸው የነበሩትን አቶ መለስ ዜናዊን ግነት በበዛባቸው ቃላት በማንቆለጳጰስ ክፉኛ ድብርት (depression) ውስጥ ከቶን ነበር፤ አስቆዝሞን ነበር። ይኸው ጌትነት በምርጫ 97 ወቅት በሌላ መንፈስ እና በሌላ ነፍስ “ወይ አዲስ አበባ” የሚል መንግሥትን የሚተች ሙዚቃዊ ቴአትር ደርሶ እና አዘጋጅቶ ሊያሳይ ሲል “ተንኮለኛ” ተብሎ የመቀስ ሰለባ ኾኗል። ጌትነት ሀ፣ ጌትነት ለ፣ ጌትነት ሐ፤ ጌትነት ሲናጥ እኛን ሲያናውጥ። በጌትነት የ“ሀለሐ” ጉዞ ውስጥ የኢትዮጵያን ሥነ ጥበብ እና ግንኙነትን መዳሰስ እንችላለን።

በልጅነቴ ምራቅ የዋጡ እና ኮሌጅ የበጠሱ ታላላቆቼ የኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ መርኾ “ሶሻሊስት ሪያሊዝም ነው” ሲሉ አደምጥ ነበር። ለእኔ አእምሮ ልክ እንደ ኮሚዩኒዝም፣ ዲያሌክቲካል ማቴሪያሊዝም እና ወዘተ እነዚህ ቃላት “ከአምስት በላይ” ተብሎ የሚጠራውን ደማቅ ሰማያዊ ልብስ የሚለብሱ ሰዎች በወሬ መካከል ጣል የሚያደርጉት እና ለመናገር የሚያኮለታትፍ ከባድ የፈረንጅ ቃል ከመኾን ያለፈ ትርጉም አልነበረውም። በኋላ አድጌ በጋዜጦች የሥነ ጥበብ እና የፊልም ሂስ ጸሐፊ መኾን ስጀምር ደርግ ከተቀናቃኞቹ ዱላ ተንፈስ ባለበት ከ1972 እስከ 1980 ዓ.ም ድረስ ባሉት ዓመታት የኢትዮጵያን ሥነ ጥበብ ቀስፎ የያዘ ሐሳብ መኾኑን ተረዳሁ። ትንሽ ገፋ አድርጌ ስመረምር ደግሞ የሐሳቡን መፍለቂያ አገኘሁት።

እ.ኤ.አ በ1934 የሶቭየት ኅብረት ጸሐፍት የአንድነት-ኅብረት ኮንግረስ የመጀመርያው ስብሰባ ሲደረግ፤ የባህል አዛዡ አንድሬ ዛህዳኖቭ “ጓድ ስታሊን ጸሐፍቶቻችንን ‘የሰው ነፍስ መሐንዲሶች’ ይላቸዋል” ብሎ ነበር። ይህ ምን ማለት ነው? ይህ በጸሐፍት ላይ ሊጫን የተፈለገው “አክሊልስ” ምን ዐይነት ግዴታዎችን ያስከትላል?
ዛህዳኖቭ በጊዜው ሊያስቀምጥ የፈለገው ሐሳብ ማንም በስታሊን አመራር እና አስተዳደር ውስጥ ከፈጠራ እና ከሥነ ጥበብ ሞያ ጋራ ራሱን ያጣመረ ሰው የሶሻሊስት ሪያሊዝምን ትእምርት ተግባራዊ ማድረግ አለበት የሚል ነው። ሶሻሊስት ሪያሊዝም የዘመኑ የሶቭየት ኅብረት የባህል ፖሊስ ነበር። ማንኛውም አርቲስት እውነታውን ማሳየት ያለበት ከደረሰበት አብዮታዊ ዕድገት ጋራ በተጣጣመ መንገድ ነው። ሥነ ውበትን (aesthetics) እና ርዕዮተ ዓለማዊ ወጥነትን (Ideological uniformity) በሥነ ጥበብ ላይ ይጭናል። በርግጥ ይህ በሕግ የተደነገገ አልነበረም፤ ይኹንና በስታሊን አስተዳደር ዙሪያ ‘ሥነ ጥበብ በዘዬው ሪያሊስቲክ በግቡም ፕሮፖጋንዳዊ ነው’ የሚል ዶግማዊ እምነት ግን በእጅጉ ይቀነቀን ነበር።

የደርግ መርኾ የተቀዳውም ከዚያ ነው። ሶሻሊዝም የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ እና የማኅበራዊ ሐሳቦችን የያዘ ታላቅ የፖለቲካ ፍልስፍና እና ርዕዮተ ዓለም በመኾኑ የሶሻሊስት ሪያሊዝም ቴንታክሎች በዕለት ተዕለት (mundane) ሕይወት ላይ የሚያተኩሩ ሥነ ጥበባትን ሁሉ ይመለከት ነበር። ይኹንና እንደ ታላላቅ ፍልስፍናዎች ሁሉ ሐሳቡ ሰፊ እና ብዙ ትርጓሜ ስለነበረው ለአርቲስቶች ለመተጣጠፍ ያመቻቸው ነበር።

ከደርግ መውደቅ በኋላ ኢሕአዴግ እንደዚህ ዐይነት የሥነ ጥበብን ሚና የሚመለከት ፍልስፍናን ለመፍጠር ጥቂት ዓመታት ፈጀመበት። ኢ-መደበኛ ሳንሱሩ እና ክልከላው የሚደረገው በመርኾ ላይ ተመሥርቶ ሳይኾን በወፍ በረር ነበር። ይህ የሥነ ጥበብን ነጻነት ቢያሰፋውም የፈቃዱን ድንበር ለመገመት እና ለማወቅ እንዲያስቸግር አድርጎታል። እንደ ሶሻሊስት ሪያሊዝም ዐይነት መርኾ እንደሚመጣ ፍንጭ ያገኘነው አቶ መለስ በ1992 በፓርቲያቸውን ውስጥ ያመጹባቸውን ባለሥልጣናት ለማጥቃት በጻፉት በተለምዶ “ቦናፓርቲዝም” ተብሎ በሚጠራው ጽሑፋቸው ነው። በዚያ ጽሑፋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም ሰው ሁሉንም የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሐሳብ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሚሰጠው ጠበቅ ያለ የፍልስፍና ዐፅመ ሕንጻ (framework) ውስጥ ብቻ እንዲመሠረት፣ እንዲያሳድግ እና እንዲተረጉም ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ።

እኔ እንደዚህ ዐይነቱን የሚያቅለሸልሽ ዕይታ መጀመርያ ያነበብኹት በቼስላቭ ሚሎዥ The Captive Mind በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ነበር። መጽሐፉ የምሥራቅ አውሮፓ ኮሚኒስት ሥርዐቶች እንዴት አድርገው የአርቲስቶችን እና የምሁራንን አእምሮ ጠፍረው እንደያዙ ይተነትናል። አቶ መለስ ይኼንም አድርገው “በሐይል ሳይኾን በውድ ነው” ሲሉ ደነገጥኹ። በዴሞክራሲ ተፎካክሬ የአርቲስቶችን ጨምሮ የመላው ኢትዮጵያውያንን አእምሮ በቅጡ እንኳ ባልተተነተነው አደናጋሪ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ፍልስፍና አስረዋለሁ አሉ። “የሐሳቤ ጉልበት ፍላጎቴን ያስፈጽማል” ሲሉ ተከራከሩ። ይህን ጽሑፋቸውን ሳየው የትዕቢቱ ደረጃ ያስገርመኛል። የኖዓም ቾምስኪን Propaganda Model ያለነበበ እንኳ በዴሞክራሲያዊ ሥርዐት እንዲህ የምናብ እስራት ማምጣት ይቻላል ብሎ ለማሰብ ይቸገራል። ምርጫ 97 ደርሶም ይህን መሰከረ። አቶ መለስም በዴሞክራሲ እና በአእምሮ እስር መካከል ያላቻ ጋብቻ መመሥረት እንደሚያዳግታቸው ሲያውቁ ብዙ ጊዜ ተሞክሮ እንደሚሠራ ወደተረጋገጠው ወደ አምባገነን “ካሮት እና ልምጭ” ሄዱ። በመጀመርያ ቡትቶውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ጥለው በደቨሎፕመንታል ስቴት ሐሳብ ተኩት። ከዚያ ሥነ ጥበብ የደቨሎፕመንታል ስቴት ሐሳብ ፕሮፖጋንዳ መሣርያ እንዲኾን ከራዳር ውጭ ደነገጉ። ድንጋጌው ሥነ ጥበብ በሚሠራባቸው ቦታዎች በሙሉ ገዢ ኾነ።

“ኢሕአዴግ ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ይዞት የመጣው የልማታዊ ሥነ ጥበብ ስልት እጅግ ጽንፈኛ እና የሥነ ጥበብን ጉልበት ለማሽመድመድ ተሰልቶ የተቀመረ ነው” ይላሉ አንድ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትር ዲፓርትመንት መምህር። እንደ መምህሩ አባባል አዲሱ የሥነ ጥበባት ዩኒቨርስቲዎች አወቃቀር አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ከዚህ በፊት በራሳቸው ቆመው ይሠሩ የነበሩት የቴአትር ዲፓርትመንቱ፣ የሥዕል ትምህርት ቤቱ እና የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በአንድ ላይ ተዋቅረው “እስክንድር ቦጎስያን ኮሌጅ ኦፍ ፐርፎርሚንግ ኤንድ ቪዡዋል አርትስ” በሚለው ሥር ተጠቃለዋል። ይህ ተግባራዊ እንዲኾን ያደረጉት የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አንድርያስ እሸቴ ናቸው። “ይህ ሐሳብ አምባገነናዊ ቁጥጥር የሌለው እና ሁሉም ነገር ወደ ልማት ያተኩር የሚል ጫና ባይኖርበት ኖሮ ሠዓሊው፣ ቴአትረኛው እና ሙዚቀኛው በነጻነት አንዳቸው ከአንዳቸው ጋራ የሐሳብ ፍጭት እና ልውውጥ የሚያደርጉበት ቢኾን መልካም ነበር፤ እየኾነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው። በየዩኒቨርሲቲዎቹ የሚሠሩ ፕሮጀክቶች አብዛኞቹ በዋነኛነት ፈንድ የሚደረጉት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥር ሲኾን ዋነኛ ተግባር እና ዓላማቸው ደግሞ ሥራዎቹ በሙሉ ልማት ላይ ብቻ ያተኮሩ እንዲኾኑ ማድረግ ነው። ይህን ለማስፈጸም ትልቁን ሚና የሚጫወቱት የእስክንድር ቦጎስያን ኮሌጅ ዲን የኾኑት አቶ ነቢዩ ባዬ ናቸው። እርሳቸው ያልፈቀዱት እና ያልፈረሙበት የትኛውም ፕሮጀክት ወደ ተግባር አይለወጥም። አቶ ነቢዩ ደግሞ የአገሪቱ የባሕል ፖሊሲ ተደርጎ የተወሰደው የልማታዊ ሥነ ጥበብ ቀንደኛ አቀንቃኝ ናቸው።” ይላሉ። አቶ ነብዩ ባዬ እንደ ብሔር ብሔረሰቦች ቀን እና እንደ አባይ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች ላይ የሚያተኩሩ ድራማዎችን፣ ቴአትሮችን እና ሙዚቃዎችን በመሪነት ይጽፋሉ፤ ያሠራሉ። ኢሕአዴግ ሥነ ጥበብ ያላትን ጉልበት በመረዳት በሕዝቡ ውስጥ ተቀባይነቱን ለማስረጽ ቴአትሮቹ በየክልሉ እንዲዞሩም ያደርጋል።

ፖለቲካ እና የሙዚቃ ሥነ ውበት ላይ ጥናት የሚያደርጉት ዶክተር ሉዊስ ፐላስኮ ፕፍላዉ “ራሳቸውን ከአብዮት ጋራ አቆራኝተው መንግሥት የሚመሠርቱ አምባገነኖች ሁለት ቅድሚያ የሚሰጧቸው ነገሮች አሉ። አንደኛው፦ ብሔርተኝነትን የተላበሰ ባህላዊ ማንነት መፍጠር ነው። ሁለተኛው፦ በሥነ ጥበብ ውስጥ ፖለቲካዊ ተቀባይነታቸውን በማሰናሰል በአገር ውስጥም ኾነ ከአገር ውጪ የመንግሥታቸውን ስክነት ለማሳየት አገራዊ ጉዳዮችን በማስረግ ተቋማዊ እንዲኾን ማስቻል ነው።” ይላሉ። እንደ አቶ ነብዩ ባዬ ያሉ በሐላፊነት ቦታ የተቀመጡ ሰዎች ጠቅላይ አምባገነንነት እንዲፋፋ ሥነ ጥበብን እንደ መሣርያ በመጠቀም ማኅበረሰብን ለአንድ ዓላማ እና ለአንድ ግብ በማሰለፍ፤ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በማሳለጥ፤ የሚሠሩትን የሥነ ጥበብ ውጤቶች በሙሉ የስኬቱ ማረጋገጫ ለማድረግ ቀን ቀሌት የሚታትሩ ናቸው። “ለምሳሌ አቶ ነብዩ ከዲንነት ባሻገር በቀድሞው ኢቲቪ ባሁኑ ኢቢሲ የሚተላለፉ ድራማዎችን የመገምመገም ሥልጣን የተሰጣቸው ሰው ናቸው። ድራማው የእርሳቸውን ልማታዊ ሚዛን ካላስጎነበሰ አያሳልፉትም” ይላሉ።

እንደ አቶ ነብዩ ባዬ ያሉ ሰዎች አንገታቸውን ደፍተው የሚያገለግሉት ዴቨሎፕመንታል ስቴት እንደ ሶሻሊዝም ታላቅ የፖለቲካ ፍልስፍና ሳይኾን የተጋነነ የኢኮኖሚክ ፖሊሲ (glorified economic policy) ነው። በዴሞክራሲ አገር የምንኖር ቢኾን ኖሮ በየጊዜው ለምርጫ እንየቀረበ በመራጮች ራይት እና ኤክስ ይሰጠው ነበር። ስለዚህ በዚህ አስተሳሰብ አርቲስቶቻችን የኢኮኖሚክ ፖሊሲ ፕሮፖጋንዲስቶች ኾኑ ማለት ነው። ነፍሳችንን ይመረምሩታል፤ መንፈሳችንን ይፈታተኑታል ስንል የአቃቤ ነዋይ ሥራ ተሰጣቸው። ስለ ግድብ እና ትራንዚስተር መግጠም፣ ቴአትር መድረስ፣ ድራማ መሥራት እና መዝፈን ጀመሩ።

አልበርት ካሙ The Rebel በተሰኘ መጣጥፉ አርቲስቶች በየማኅበረሰቡ ጀግንነት እንደሚጠበቅባቸው ነገር ግን ይህ ተስፋ ሩቅ መኾኑን ታሪክን እያጣቀሰ ያወጋናል። ብዙ አርቲስቶች የጨቋኞች ጋሻ እና የፕሮፖጋንዳ መሣርያ ኾነው አገልግለዋል። ከማመጽ ይልቅ ማደርን የሚመርጡ ናቸው- እንደ ካሙ። እንዲያውም የካሙ ትችት ከዚህም ያየለ ነው፤ ዱላ አላብዛ ላለስልሰው ብዬ እንጂ። ስለዚህ “ሁሉም ነገር ወደ ዴቨሎፕመንታል ስቴት” የሚለውን መርህ ለጥ ብለው ቢቀበሉም፣ ድሮ የነበራቸውን አቋም ቀይረው ለመንግሥት ቢያጫፍሩ ለካሙም (አፈር ይቅለለውና) የሥነ ጥበብን ታሪክ ለሚያወቅም አይገርመውም። ጌትነት ሀ ወደ ጌትነት ለ ቢሸጋገር ምክንያቱ በዙርያው ያለው ያለው የፖለቲካ ኢኮኖሚ መዋቅር መለወጡ ነው። ይኹንና አርቲስቶች ላይ አብዝቶ ተጠራጣሪ መኾን ማለት ሥነ ጥበብ ላይም ተስፋ መቁረጥ ማለት አይደለም። አሪስቶትል እንደሚለው የሥነ ጥበብ መጎልበት የሰው ልጅ ማበብ ዋነኛ መለኪያ ነው። የሥነ ጥበብ መጎልበት ጥራትን፣ ብዛትን እና ስብጥርን ያካተተ ነው፤ ስለ ግድብ እና ትራንዚስተር መግጠም የሚፈልገውም፤ ትልልቅ ሐሳቦች እያነሳ ነፍሳችንን የሚጎነትለውም፤ የቀን ተቀን ሕይወታችንን የሚዳስሰውም፤ ስውሩም- ስውር ያልኾነውም፤ ሁሉም ሥነ ጥበብ የሚፋፋበት የአንድ ሺሕ ጽጌሬዳዎች ዓለም። የቴአትር ዲፓርትመንት መምህሩ እንደሚሉት “አርቲስቶች እና የሥነ ጥበብ መምህራን የራሳቸው የኾነ ግለሰባዊ ፍላጎት እና የፖለቲካ ግብ ይኖራቸዋል።” ይኹንና በግለሰብ እና በማኅበረስብ መካከል ለመምረጥ የሚያስችለው ግብ የሚመረጠው በአንድ ፓርቲ እምነት እና ዓላማ ላይ ተመሥርቶ ከኾነ “ማበብ” ገደል ገባ፤ “ይህ እንዴት ያለ አሰቃቂ እውነታ እንደኾነ እያየነው ነው።” ይላሉ መምህሩ።
teddy afro
ይኹንና በዚህ አሰቃቂ ኹኔታም ውስጥ አፈትልከው በመውጣት የሚያብቡ እና የሚያፈሩ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በፊት በነበረችው ሶቭየት ኅብረት ውስጥ ፈክተው እና አብበው መውጣት የቻሉ ሥራዎች ነበሩ። በደርግ ጊዜም በየቀበሌው ከተቋቋሙት የኪነት ቡድኖች መካከል የወጡ ግለሰቦች እና የቡድን ሥራ ውጤቶችን መጥቀስ ይቻላል፤ በሥዕል፣ በሙዚቃ፣ በቴአትር፣ በልቦለድ፣ በግጥም እና በመሳሰሉት። አሁንም የበእውቀቱ ስዩም ዐይነት አፈንጋጭ ገጣምያን፣ የቴዲ አፍሮ ዐይነት ለደቨሎፕንታል ስቴት ጽንሰ ሐሳብ የማያደገድጉ አቀንቃኞች፣ ሠዐልያን እና ሌሎች አርቲስቶች አሉ። የእነዚህ አርቲስቶች ፈተና ከባድ ነው። እንደ እነ ጌትነት ጊዜን ተገን እያደረጉ ሥነ ጥበብን የጊዜው ሥልጣን እና ሐይል (power) መሣርያ ማድረግ ቀላል ነው። ሃላፊነትን በተመለከተ ሁሉም ድርሻ ድርሻውን እንዳያነሳ “ጥፋተኞች ሁላችንም ነን” ለሚል መደበቂያ ይዳርጋል እንጂ። ይህ ደግሞ በሥነ ጥበብ ሊያብብ የሚገባውን ሕይወት ያቆረፍደዋል።

Source: 7-killo Magazine

The post የጌትነት ሀለሐ እና ልማታዊ ሥነ ጥበብ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 261

Trending Articles