ከዘከሪያ መሀመድ
ጥላሁን ገሠሠ በሕይወቱ ሳለ ያደንቃቸው ከነበሩ ታላላቅ ድምጻውያን መካከል፣ የዓረቡ ዓለም ድምጻውያን ንግሥት የምትሰኘው ዑም ኩልሡም አንዷ ነበረች፡፡
ዑም ኩልሡም እ.አ.አ. ሜይ 4, 1904 ገደማ ግብፅ ውስጥ ቱማይ አል-ዘሃይራህ በሚባል አውራጃ ተወልዳ፣ ፌብሯሪ 3፣ 1975 ከዚህ ዓለም ተለይታለች፡፡ ሥርዓተ ቀብሯም ከአንድ ሚሊዮን የማያንስ ሕዝብ በተገኘበት ካይሮ ውስጥ ተፈጽሟል፡፡ እ.አ.አ. በ2001 የግብጽ መንግሥት ለዑም ኩልሱም ‹‹ከውከብ አል-ሸርቅ›› (“የንጋት ኮከብ” ማለት ይመስለኛል) እየተባለ የሚጠራ በተለይ ዑም ኩልሱምን የሚዘክር ሙዚየም ያቋቋመላት ሲኾን፣ በዛማሊክ ሐውልት ቆሞላታል፡፡ የዑም ኩልሱም አልባሳት፣ እንዲሁም በኋለኛ ዕድሜዋ መድረክ ላይ ሳይቀር ታደርገው የነበረው መነጽሯን ጨምሮ በርካታ የግል መጠቀሚያዎቿ በስሟ በተሰየመው ሙዚየም በቋሚነት ለዕይታ በቅተዋል፡፡ …
እንደ ጥላሁን ሁሉ፣ ዑም ኩልሡም ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል የዐረቡን ዓለም በዜማዎቿ እየመሰጠች ኖራለች፤ ዛሬም በተመስጦ ትደመጣለች [ከነምስሏ በመድረክ ላይ ስትዘፍን ማየት የፈለገ፣ “ሩታና ክላሲክ” ጣቢያ ላይ ያገኛታል፡፡] ዑም ኩልሡም በዓረቡ ዓለም እጅግ ተወዳጅ የነበረችውን ያህል፣ አድናቂዋ ጥላሁን ገሠሠ በእኛ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ነበረው፡፡ በሀገራችን ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው ጥላሁን ገሠሠ፣ አንድ ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ኃውልት እንደሚቆምለት ተስፋ ማድረግ እንችላለን፡፡ አልባሳቶቹ እና አንዳንድ የግል መጠቀሚያዎቹ በስሙ በሚሰየም ሙዝየም የመቀመጣቸው ነገር ግን ያጠራጥራል፡፡ ይህን የሚያስብለን ሰሞኑን የተወሰኑ የጥላሁን አልባሳት ለመቄዶንያ የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማኅበር መሰጠታቸውን መስማታችን ነው፡፡
የጥላሁን አልባሳት ለመቄዶንያ የተለገሱት ለምን ዓላማ እንዲውሉ ታልሞ እንደሆነ አላወቅሁም፡፡ እንደኔ እንደኔ፣ የመቄዶንያ መሥራች የታላቁ ድምጻዊ አልባሳት ትልቅ ታሪካዊ ዋጋ ያላቸው መሆኑን በመገንዘብ፣ ለበጎ አድራጎት ተቋማቸው ቋሚ ገቢ ሊያስገኝ በሚያስችል መልኩ ቢጠቀሙበት መልካም ነው፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድር በሰጣቸው ሰፊ መሬት ላይ ለሚገነቡት ግዙፍ የአዕምሮ ህሙማን መንከባከቢያ ማዕከል ግንባታ የሚውል ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚያስፈልጋቸው የድርጅቱ መሥራች የጥላሁንን አልባሳት ለጎብኝዎች በሚመች መልኩ በማስቀመጥ፣ ለጥላሁን ገሠሠ ሙዝየም መሠረት የሚጥሉበትን አንድ ርምጃ ቢራመዱ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ እርሳቸው አንድ ርምጃ ሲራመዱ፣ ሙዝየሙን ለማጠናከር ሕዝብ የየድርሻውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጀምራል፡፡ ማን ያውቃል የተቀሩት የጥላሁን ገሠሠ አልባሳትም ወደ ‹‹መቄዶንያ የጥላሁን ገሠሠ ሙዝየም›› ይመጡ ይሆናል፡፡
ለማንኛውም፣ በአዲስ አበባ ‹‹የጥላሁን ገሠሠ መታሰቢያ ሙዝየም›› ተቋቁሞ እስክናይ ድረስ፣ ካይሮ የሚገኘውን የዑም ኩልሡም ሙዝየም ከፊል ገጽታ በፎቶግራፍ እንጎብኝ፡፡ …