ተወዳጁ ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ስለብሄራዊ ቡድናችን “መሬት ሲመታ” የሚል ወቅታዊ ዜማ ለቀቀ። ዜማውን እነሆ ለዘ-ሐበሻ አንባቢያን ብለናል።
ዋልያ፣ ዋልያ፣ ዋልያ፣ ዋልያ
ዋልያ ብቁ፣
ይታይ ሰንደቁ፣
ወኔ ታጠቁ፤
. . .ባና ባና ሳተናው ዋልያ
የኮርብታው ብርቱ
የዳሸን ተራራ ጫፍ ላይ ያረገው
እንዲታይ ሰንደቁ . . .
ቴዲ አፍሮ አዲስ ነጠላ ዜማ ለቀቀ
ቴዲ አፍሮ በማርፈዱ ሸራተን እንዳይገባ ተከለከለ
አዲስ አድማስ
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ሰሸዋንዳኝ የአልበም ምርቃት የተጋበዙት ሠራዊት ፍቅሬና ሰይፉ ፋንታሁንም ተከልክለዋል
በሸራተን አዲስ ጋዝ ላይት ክለብ ከትናንት በስቲያ ሰተካሄደው የድምፃዊ ሸዋንዳኝ ኃይሉ “ስጦታሽ” አልበም ምርቃት በክብር እንግድነት የተጠራው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፤ ሰዓት አርፍዶ በመድረሱ እንዳይገባ ተከልክሎ ከበር ተመለሰ፡፡
ቴዲ አፍሮ ከምሽቱ 5፡30 ላይ የምርቃት ስነስርዓቱ ወደሚካሄድበት ጋዝ ላይት ክለብ ሊገባ ሲል የጥበቃ ሰራተኞች “ጥሪው 4 ሰዓት እንጂ 5፡30 ሰዓት አይደለም” በማለት እንዳይገባ እንደከለከሉት ለማወቅ ተችሏል። አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬና ሰይፉ ፋንታሁንን ጨምሮ በርካታ ያረፈዱ እንግዶች ወደ ጋዝ ላይት ክለብ እንዳይገቡ መከልከላቸውን የዓይን እማኞች ገልፀዋል፡፡ ሸዋንዳኝ፤ ቴዲ አፍሮ እንዳይገባ መከልከሉን የሰማው መድረክ ላይ ሆኖ እንደሆነ የገለፁት ምንጮች፤ በዚህም ማዘኑን ተናግረዋል። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፤ ሁለቱ እንዳላቸው ቅርበት ቴዲ አፍሮ በፕሮግራሙ ላይ ቀድሞ መገኘት ነበረበት ብለዋል፡፡ ድምፃዊ ሸዋንዳኝን ስለ ጉዳዩ በስልክ ጠይቀነው፣ መልስ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
ከትላንት በስቲያ ምሽት በተካሄደው የምርቃት ስነ ስርዓት ላይ ሸዋንዳኝ ከአዲሱ አልበም አስር ዘፈኖችን የተጫወተ ሲሆን የተዘጋጀለትን አዲካ እና ኤም ጂ ፕሮሞሽን ያዘጋጁለቱንም ኬክ በዚያው ፕሮግራም ላይ ቆርሷል፡፡ ሸዋንዳኝና ቴዲ አፍሮ በአንድ የሙዚቃ ባንድ ውስጥ ለረጅም አመታት አብረው የሰሩ ሲሆን ቴዲ አፍሮ ሲያገባ ሸዋንዳኝ ሚዜው ነበር፡፡
ማርፈድ የስንፍና ምልክት መሆኑን የተናገረው አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ፤ሸራተን ስንደርስ የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ በሩን ዘግተው እንደሄዱ ተነግሮናል ብሏል፡፡ “በሌሎች አገሮችም የተለመደ ነው፤ናይት ክለብ ከሞላ ሰው እስኪቀንስ መግባት አይቻልም” ያለው ሰራዊት፤ “እኛ ታዋቂ ስለሆንን ለምን ተከለከልን የሚል ቅሬታ አላደረብንም” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
addis admas
“ለሳቅ ባይተዋሩ”–ገጣሚ ፋሲል ተካልኝ ለኮሜዲያን አብርሃም አስመላሽ የቋጠረው ስንኝ
ታሞ..ታሞ..ታሞ..ታሞ
ሰው ድኖ ይታያል..ከሕመሙ አገግሞ::
ታሞ..ታሞ..ታሞ..ታሞ..
ሰው ይሞታል ደግሞ::
ለምን?..ለምን?..እኮ ለምን?..
ምነዋ ተገኘሁ?..መዳንህን ሳምን::
…ታሞ መሞት አለ!
ድንገት ወጥቶ መቅረት
…በአንተ አልተጀመረ::
የቆየ ሐቅ ነው..ያለ..የነበረ..
በዘመናት ብዛት..ለአፍታ እንኩዋ ያልተሻረ
ዛዲያ ለምን ልቤ?
ነባሩን ሐቁን ስቶ..
ሞትህን መቀበል..ማመን ተቸገረ::
አዲስ ሆኖ ዛሬ..የተለየው አንተ
ስንታለ የኖረ?!?..ሳይኖር እኮ የሞተ::
ሰው ሟች ፍጡር ነው..ድንገት ወጥቶ ቀሪ
በምድር ላይ ነግሶ..
ለካ ሞት ብቻ ነው..ሕያው ሆኖ ኗሪ::
ተዘልፍልፎ ሲታይ..
የተኛ ቢመስልም..ጣምኖና ደክሞት
ሲያዘናጋ ነው..
ከቶ አያንቀላፋም..ለካ አጅሬ ሞት!!
ድንገት ወጥቶ የቀረ.. ላይመጣ የሔደ
ቅኔ እንደተቀኘ..
“አንቱ” የተሰኘ..
ዘመኑን በሙሉ..ችሎ እንደኮመደ
ለሳቅ ባይተዋሩ..ሕይወትን ያሳቀ
ሕይወት ያደመቀ..
በኑሮው የነፈዘ..በኑሮው ያለቀሰ
ቅኔውን..ምፀቱን..
ቧልቱና ዘበቱን..ጀምሮ ያልጨረሰ
ተፈጥሮው የረቀቀ..በፈጠራው የላቀ
እንደማሾ በርቶ..
ብርሐን ለግሶ..ነዶ ነዶ ያለቀ
ሞት ላይ የቀለደ..ሞት ላይ የዘበተ
ሞትን ያሳቀቀ..ሞትን የገዘተ
ማናለ እንዳንተ?!?..
ቀልዶ የኖረ..ቀልዶ የሞተ::
* * *
ፍልፍሉ በአዲስ አበባ ክፉኛ ተደበደበ
(ዘ-ሐበሻ) በረከት በቀለ ወይም በገጸ ባህሪይ ስሙ “ፍልፍሉ” በሚል የሚታወቀው ኮሜዲያን ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ለሥራ ከተመለሰ በኋላ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ድብደባ እንዳጋጠመው የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች ከአዲስ አበባ ዘግበዋል።
ኮሜዲያኑ በሰሜን አሜሪካ በተለያዩ ከተሞች እንዲሁም በ እስራኤል ሃገር የኮሜዲ ሥራዎቹን አቅርቦ በቅርብ የተመለሰ ሲሆን ከ2 ቀናት በፊት ድብደባ የተፈጸመበት በፒያሳ አካባቢ መሆኑን ዘጋቢዎቻችን ገልጸዋል። ኮሜዲያኑ ወደ ፒያሳ የሄደው ከባለቤቱ እና ከባለቤቱ እህት ጋር እንደነበር የገለጹት ዘጋቢዎቻችን ፊቱ ላይ ጭምር ሳይቀር ድብደባ ፈጽመውበት ጥርሱ ሌላኛው ጥርሱ መውለቁንም ገልጸዋል።
በፍልፍሉ ላይ ጥቃት ያደረሱት ሰዎች እነማን ይሁኑ የታወቀ ባይሆንም ኮሜዲያኑ ለፖሊስ ከህክምና ካገገመ በኋላ ቃሉን መስጠቱ ታውቋል። እነዚህ ዘራፊዎች ምናልባትም በኮሜዲያኑ ድብደባ የፈጸሙት በቅርቡ ከአሜሪካ በመመለሱ ገንዘብ ይዞ ይሆናል በሚል ሊሆን ይችላል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ኮሜዲያኑ በቅርቡ ከሰይፉ ፋንታሁን ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “ክበበው ከአሜሪካ ሲመለስ ቤት ሲገዛ፤ እኔ ግን አደብ ገዝቼ ተመለስኩ” ሲል ገንዘብ እንዳልያዘ በቀልድ መናገሩ አይዘነጋም።
ፍልፍሉ በሰሜን አሜሪካ ቆይታው ያልፈረምኩበትና፤ ያልተከፈለኝ ሲዲ በስሜ ወጥቷል ሲል ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቀው በዘ-ሐበሻ በኩል አስተላልፎት የነበረው ቪዲዮን ለግንዛቤ ይመልከቱት።
በአንድ ወቅት በዘ-ሐበሻ ድረገጽ ላይ የፍልፍሉ እና የቁልሉ ጨዋታ በሚል የቀረበውን ቃለምልልስ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ
የማለዳ ወግ:- ስቀው ያሳሳቁን ፣ በርተው የጠፉ የጥበብ ሰዎች እና ልናሽረው የምንችለው ቁስል!…
ቀልድ ሲነሳ አስቂኝ ሶስቱ ድንቅ ተዋናዮች አለባቸው ተካ ፣ ልመንህ ታደሰና አብርሃም አስምላሽ በልዩ ችሎታቸው ለእኔ እና ለብዙዎች ከፍ ያለ ቦታ አላቸው። ነፍሱን ይማረው አለባቸው ተካ ድሃ እንደደገፈ በአሳዛኝ የመኪና አደጋ አለፈ! ህይወቱን ለጥበብና በፋና ወጊ መልካም ተግባር ተሰልፎ ሲያሳልፍ ተስገብግቦ ሃብት አላካበተምና ለእሱና ለቤተሰቦቹ የረባ ጥሪት ሳይጥል አለፈ … መልከ መልካሙ ልመንህ ከምድረ አሜሪካ አዕምሮውን ስቶ ከሞቱት በላይ ካሉት በታች ሆኖ በአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎች ይንከራተታል … የሙያ አጋሮቹ ከምድረ አሜሪካ ያደረጉት ሁሉ ትብብር ቢሳካ ኖሮ ልመንህ ዛሬ ድኖ እናየው ነበር ፣ ግን አልሆነምና በናኘበት ከተማ ራሱን ጥሎ ነሁልሎ ማየቱ ልብ ይሰብራል ፣ ያሳዝናል! አንዳንድ ወዳጆቸ ልመንህን ለመደገፍ በግል ከሚደረገው ጥረት ባለፈ በተቀናጀ መልኩ እርዳታ እንደማይደረግለት አጫውተውኛል ፣ ለዚህም ምክንያቱ የህምሙ ክፋት እንደሆነ የገለጹልኝ ሃገር ቤት ያሉ የሙያ አጋሮቹም ቢሆንም ለከፋው ህመም መላ ማጣታቸውን ይናገራሉ … ብቻ ልመንህም እንዲህ ሆኗል … አዕምሮውን የሳተ በየጎዳናው ተንከራታች … ክፉ ጊዜ ….
አዱ ገነት ተወልዶ አድጎ ለዛ ያለውን የሃገር ቤት የገጠር ቃና ንግግርን በግ ለመሸጥ ወደ አዲስ አበባ ከሚመጡ ከበግ ነጋዴዎች ተለማምዶ ሲናገረው ገጠር ተወልደው ያደጉትን ያስንቅ ነበር ፣ ከገጠር መጥተው የገጠሩን አነጋገር ወደ ከተምኛው ለመቀየር ሲደነባበሩ አዲስ አቤው የተገላበቢጦሽ የእንሱን የአነጋገር ዘይቤ ተክኖና ተውቦ አገር ምድሩን በፈጠራው ሲያስቀው ድንቅ ችሎታ ነበረው ። አብርሃም አስመላሽ …በአንድ ወቅት ከአብርሃም ጋር ተገናኘተን ከቀልድ ያለፈ የጨዋታውን ለዛ ኮምኮሜዋለሁ! መልካም ሰብዕናም እንደ ነበረው ወዳጆቸና ወዳጆቹ አጫውተውኛል ! አብርሃም አስመላሽ …
አብርሃም ወደ ጀርመን ሃገር ሄዶ ህክምና እንዲያገኝ ትልቁን ድርሻ ለተወጡት የሙያ አጋሮቹ ላደረጉት ትብብር አድናቂዎቹ ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው … ዛሬ አንድ መረጃ ደረሰኝና ከምስጋናው አልፊ ብዙውን አውጥቸ አወረድኩ …አብርሃም የመሞቱን መሪር መርዶ ከሰማን እያለፈ ባለው ሳምንት ውስጥ ጥቅምት 21 በእለተ ማርያም 2013 ዓም ነው ! ከዚያች ቀን ወዲህ የአብርሃምን ሬሳውን ወደ ሃገር ቤት ለመውሰድ የገንዘብ ድጋፍ እርዳታ መጠየቁን ሰምቻለሁ … እናም የጥበብ ሰዎች መጨረሻ አሳሰበኝ! … ወገን ለወገን ነውና የአብርሃም ሬሳ የሚወዳት ሃገሩ አፈር ትቀምስ ዘንድ ሁላችንም የእርዳታ እጃችን ብንዘረጋ መልካም ነው በሚል በሳውዲ ነዋሪ አሳሳቢ ከሆነው የምህረት አዋጅ ማለቅ ስጋት ወጣ ብየ ይህችን ማስታወሻ ሞነጫጨርኩ …
ከአብርሃም ሳልወጣ ቀጠልኩ. .. ከሬሳው ማመላለሻው እርዳታ በኋላስ ? ብየ ለራሴ አልጎመጎምኩ… እሱም እንደ ኮሜዲ አለባቸው ከወደ ኋላ ጥሏቸው የሄዱ ቤተሰቦች እንዳሉት ሰምቻለሁ … እናም የእነሱም መጻኤ እጣ ፋንታ በእኛው ካልተደገፈ መላ አይኖረውም …በሚል ጀመሬ ምናል የኪነ ጥበብ ሰዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች እንዲህ እያለፉ ስላሉ ብርቅየ የሃገራችን ልጆችን እና ቤተሰቦችን ቢታደጓቸው? ቢያንስ ለኪነ ጥበብ አፍቃሪ አድናቂዎቻቸውን በተነሳሽነት በማሰባሰብ የድጋፍ እርዳታ ቢያሰባስቡላቸው ስል ማሰቤ አልቀረም! ቅድሚያ ድጋፉ ከሙያ አጋሮች ቢጀምር አልኩና ራሴን ያዝ አደረግኩት … ብዙ ከእርዳታ ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ታወሱኝ!
የእርዳታ ነገር ሲነሳ በርካታ የከሸፉ ሙከራዎችን አይረሱኝም ፣ አለም ደቻሳ ሊባኖስ በኢትዮጵያ ቆንስል በር በአንድ አረብ “ጀብራሬ” እየተጎተተች ባየናት በጥቂት ቀናት ልዩነት ራሷን ገደለች አሉን … ከወራት በኋላ ጥላቸው የሔደቻቸውን ልጆች ለመርዳት በተጠራው አለም አቀፍ አርዳታ ለተጠራው እርዳታ የተገኘው ምላሽ አያኮራም! እዚህ ሳውዲ በርካቶች ለከፋ ችግር ሲዳረጉ በግል የሚደረጉትም ሆነ በማህበራዊ ገጾች ለሚጠራ እርዳታ የሚሰጠው ምላሽ ያሸማቅቃል … ያን ሰሞን ለአመታተ በብዕራቸው አገር ያስደመሙ ሁለት ኩሩ የስነ ጽሁፍ ሰዎች በየተራ መታመማቸውን በሰማን … የጋዜጠኛ ጸሃፍት ባልደረቦዎቻችን መታመም ካንገበገባቸው ወንድሞች እርዳታ ይሰበስቡ ከነበሩት መካከል አንዱ ወዳጀ እንደ ጨው የተበተንን የዚያች ሃገር ጋዜጠኞች ዘንድ እርዳታና ድጋፍ አገኝ ብሎ ከአውሮፖ አሜሪካ በመላላክ ሲባትል ያተረፈው ድካም ብቻ ሳይሆን የሰውን ጭካኔ መሆኑን አጫውቶኛል። ይህንን አሳዛኝ ገጠመኝ ያጫወተኝ ወዳጀ መጨካከናችን አስታውሶ ያቀበለኝ መረጃ ተስፋ ባያስቆርጠኝ ሳያሳዝነኝ አልቀረም! ብቻ ጊዜው ተበላሽቶ ጨካኞችን እያወገዝን ጨቋኞች መሆናችን ዘልቆ ቢያደማም ተስፋ መቁረጥ ከቶ አይገባም …
አዎ ካለፈው ልንማር ከቻልን ዛሬ በመልካም ነገር ማስቀጠል እንችላለን! ዛሬ የብርቅየውን ኮሜዲ የአብርሃም አስመላሽን ነፍስ ይማር ስንል በስሙ ለተጠየቅነው እርዳታ እጃችን እንዘርጋ ዘንድ ግድ ይለናል ! አስተባባሪዎችም ግልጽ የሆነ እርዳታ ማሰባሰብ አድርጉ ፣ የስልክ የባንክ አድራሻና ሌላም ተገቢ መረጃዎችን ስጡ! አበው ” ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ፣ ለሃምሳ ሰው ጌጡ ነው!” እንደሚሉት ነውና የቻለ እንዳቅሙ ይርዳ … ይህ መሰሉ እርዳታ ወገንተኛነታችን እና ሰብዕናችን እናሳይበት እንደሁ ማለት እንጅ ሰው ሰጥቶ ፣ ደግፎ አያጠግብም … ሰጥቶ እና ደግፎ የሚያጠግብ አንድ ፈጣሪ አምላክ ብቻ ነው … የቻልን እንለግስ …አንድየ ሁሉንም ያያል ለሰጭ ይስጠዋል እናም እንረዳዳ ! ስቀው ያሳሳቁን ፣ በርተው የጠፉ የጥበብ ሰዎች እና መጨረሻቸው እንዲህ ሲሆን ማየቱ ቢያምም ከታደግናቸው ልናሽረው የምንችለው ቁስል እንዳለ አንዘንጋ ስል የማለዳ ወጌን ቋጨሁ!
ለቤተሰቦች መጽናናትን እመኛለሁ … የሟችን ነፍስህን ይማር !
ጥጋበኞቹ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሱማሊኛ ሙዚቃ በሸራተን ሲደንሱ የሚያሳይ ቪድዮ
“ሁለቱም ባዶዎች ነበሩ!”/ለዘመኑ የሀገራችን “ቦለቲከኞች”/ –ከፊሊጶስ (ግጥም)
እ’ስራና ቅል ……..
አፈጣጠራቸው፣ ቢሆንም ለየቅል፤
እንደ አቅማቸው፣ ሠርተው
በሀሳብ – ተግባር፣ ተግባብተው፤
ሰላም አግኝተው፣ አንድነት
ይኖሩ ነበር፣ በአንድ ቤት።
በፍቅራቸው፣ የሚቀናው
ዱባ ግን፣ ጉረቤታቸው፤
ያሴር ነበር ሴራ፣ የሚያሥር
ይሸርብ ነበር ነገር፣ የሚያደናግር፤
ያጠምድ ነበር፣ ወጥመድ
ባረፉበት ቤት፣ ሳይቀር በመንገድ።
እ’ሰራን ሲያገኘው፣ ብሎ ጎንበስ – ቀና
የሰላምታ አይነት፣ ያዥጎደጉድና፤
በማር የተቀባ፣ የመርዝ ቃላት
ይነግረው ነበረ፣ መስሎ ተቆርቅሪ፣ ለሱ ያዘነለት።
ቅልንም ሲያገኘው ወይም ቤቱ ሄዶ
ከአስረደው በኋላ፣ እንደሚፈልግው በፍቅሩ ተገዶ፤
ምክር ነው እያለ፣ ነገር ይነግረዋል
በማያውቀው ጉዳይ፣ ደሙን ያፈለዋል።
ከለ’ታት አንድ ቀን፣ ሥራ በፈቱበት
በነገር ተይዘው፣ ”በተሰለቡበት”፤
እ’ስራ ተክዞ፣ ወደ ቤት ሲሄድ
ቅልም በበኩሉ፣ ሲያስብ በምንገድ፤
ዓይን – ለዓይን ተጋጩ፣ እጅግ ተፋጠጡ
በሰላምታ ፋንታ፣ ንትርክ መረጡ።
ቅል ኮራ ብሎ፣ ምላሱና ሳለና
ዱባ ከነገረው፣ ብዙ አስታወሰና፤
”እኔ ከ’ንተ አላንስም፣ እንዲያው ባልበልጥህ ”
በማለት ጀመረ፣ “አንተ እ’ስራ ሆድ ነህ!”።
“ለሰው ልጅ አገልጋይ፣ ወሃ ለመያዝ፣ ተመራጭ እኔ ነኝ
እንደ አስፈለጋቸው፣ የሚሽከረክሩኝ።”
”እኔ ቅል ብቻ ነኝ፣ ቶሎ ውሃ በመሙላት የሚመርጠኝ ሰው
ይዘውኝ ቢዞሩ፣ የማልከብዳቸው፣ የምመቻቸው።”
ነገሩ ተካሮ፣ ዱላ መረጡና
ይጣለዙ ጀመር፣ በሰፊው ጎዳና።
ገላጋይ መስለው፣ የቀረቡት ሁሉ
ዘወር ብለው ሄዱ፣ ዱላ እያቀበሉ።
እነሱም ቀጠሉ፣ ቀጠሉ…. ቀጠሉ
እስቲ እናስብበት፣ ለነገም አላሉ
ጎዳናውን አልፈው፣ ሜዳውንም ሞሉ።
የመደባደቡ፣ ኃይል ቢያጥራቸው
ተያይዘው ወደቁ፣ ‘ርስ – በ’ርሳቸው
ብትንትንም አሉ፣ መሬት ብትነካቸው።
የእ’ስራና ቅል፣ ዱባ ጉረቤት
ጠቡን ሲከታተል፣ ቁጭ ብሎ በ’ርቀት፤
”ከቶ ማን ያሸንፍ፣ ፈሪ ማን ይሆን”
እያለ ሲደሰት፣ በማየት ፍልሚያውን፤
ወድቀው፣ ተበታትነው፣ ተፈረካክሰው
ሜዳውን ሞልተውት፣ ሲያስታውላቸው
”ለካስ ሁለቱም ባዶዎች ነበሩ!” በማለት ሳቀና
ቤታቸውን ሊወርስ፣ ሄደ እየተዝናና።
—–//——-
ፊልጶስ / 2006 / E-mail: philiposmw@gmail.com
*”ለካስ ሁለቱም ባዶዎች ነበሩ!” የሚለውን የወሰድኩት ከኮንፊሽዬስ አባባል ነው::
ጃኪ ጎሲ በሳዑዲ ላሉ ወገኖቻችን መታሰቢያ ነጠላ ዜማ ለቀቀ
በኢትዮጵያ ሙዚቃ እንደነገሠ 50 ዓመት የደፈነው አሊቢራ
በሚኒሶታ የኦሮሞ ስፖርት ፌስቲቫልን አስታኮ ባለፈው ጁላይ ላይ 50ኛ ዓመት የሙዚቃ አገልግሎቱ ቢከበርም፤ አሁን ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዚህ ብርቅዬ አርቲስት 50ኛ ዓመት በዓል እየተከበረ ነው።
ግንቦት 18 ቀን 1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ የተወለደው የክብር ዶ/ር አሊ መሐመድ ብራ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ድሬዳዋ ከተማ በቀድሞዎቹ መድረስ ጅዲዳ እና በልዑል ራስ መኮንን ት/ቤቶች፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ አበባ ካቴድራል ት/ቤት ተከታትሏል። በኋላም ካሊፎርንያ በሚገኘው ሳንታ ሞኒካ ኮሌጅ በሙዚቃ የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ትምህርት ተከታትሏል። አሊ ብራ 8 ቋንቋዎችን አቀላጥፎ መጠቀም ይችላል።
የፈረንጆቹ አመት 1963 አሊ ብራ ሙዚቀኛ ሆኖ ዳግም የተወለደበት ዓመት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ይህ ዓመት አሊ ብራ በድሬዳዋ ከተማ ከነበረው የአፈረን ቀሎ የሙዚቃና የባህል ቡድን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረክ ላይ ሙዚቃ የተጫወተበት ነበር።
አሊ ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረክ የተጫወተው “ብራዳ በርሄ – Birraadahaa Barihee” የተባለውን እጅግ ተወዳጅ ዘፈኑን ነበር። ቤተሰቦቹ ያወጡለትን ስም አሊ መሐመድ ሙሳን በመቀየር አሁን ሁለተኛ ስሙ የሆነውና (Second name) በጊዜው ቅፅል ስሙ የነበረውን “ብራ”ን ከህዝብ ያገኘው ከዚሁ ዘፈኑ መሆኑ አመቱ አርቲስቱ አሊ የተወለደበት አመት የመሆኑን ነገር ያጠናክራል፣ ከዚህ በኋላ አርቲስቱ የተጓዘባቸው ሃምሳ አመታት በሀገራችን ሙዚቃ ታሪክ የራሱን ጉልህ ምዕራፍ የፃፈባቸውና፣ በዚህም ሂደት በርካታ ውጣ ውረዶችንና ፈተናዎችን አልፎ ለታላቅ ስኬት የበቃባቸው አመታት ናቸው።
የክብር ዶ/ር አሊ ብራ በተፈጥሮው ተሰምቶ የማይጠገብ፣ ሁሌም የሚወደድ እጅግ ማራኪ ድምፅን የተለገሰና ከፍተኛ የዜማ ተሰጥዖን የታደለ ነው። በዚህ ችሎታውና በብርቱ ጥረቱ እስከ አሁን ከ260 በላይ ድንቅ ዘፈኖችን ዜማዎችን ለሕዝብ አቅርቧል። አሊ ያለውን ቋንቋ የመማር ከፍተኛ ክህሎት በመጠቀም በኦሮምኛና በ8 የተለያዩ ቋንቋዎች (ሶማልኛ፣ አማርኛ፣ አፋርኛ፣ ሀረሪኛ፣ አረብኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ኪስዋሂሊ እና ስፓንሽ) ሥራዎችን አቅርቧል። በሥራዎቹም በርካታ የሕይወትን ገፅታዎችን ዳሷል።
አሊ ጊታር፣ ፒያኖ፣ ኡድ እና ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎችን የሚጫወት ሲሆን፣ ለራሱና ሌሎች በርካታ ግጥምና ዜማዎችን ደርሷል። የራሱን ለየት ያሉ የዜማ ቅንብርና የአዘፋፈን ስልቶች የፈጠረ አርቲስትም ነው።
አሊ በሀገራችን ታሪክ ታላላቅ ከሚባሉ የሙዚቃ ቡድኖች ጋር ሰርቷል። ከአርባ በላይ ሀገራት (በሁሉም አህጉራት) እጅግ በርካታ በሆኑ መድረኮችም ላይ ተጫውቷል። የአሊ ስራዎች አፋን ኦሮሞንና ሌሎች የዘፈነባቸውን ቋንቋዎች ለሚሰሙ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሙዚቃ አፍቃሪ ዘንድ እጅግ የሚወደዱ ትውልድና ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች ናቸው።
ዶ/ር አሊ ብራ የዘመነኛ (contemporary) ኦሮምኛ ሙዚቃ አባት ሲሆን ለሀገራችን ሙዚቃ፣ ባህል እና ስነ ጥበብ ማንሰራራት፣ እድገትና መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው የኦሮምኛ አልበም የአሊ ብራ ነበር። የእርሱን ፈለግ ለተከተሉ በርካታ ድምፃዊያን አርአያና መምህር በመሆንም አገልግሏል። በርካታ ወጣት ድምጻውያን ስራ ሲጀምሩ፣ ዘፈኖቹን፣ ለልምምድ እንደ አፍ መፍቻ፣ ስራቸውን ለማድመቅ እንደ ማጣፈጫ ሲገለገሉባቸው ኖረዋል። አሊ ምርጥ አርቲስቶችን ያፈራ የአርቲስቶች አባት ነው።
ዶ/ር አሊ ብራ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ሙዚቃዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በስፋት ያስተዋወቀና ለተለያዩ ሕዝቦችና ባህሎች መገናኛ ድልድይ የሆነ የባሕል አምባሳደርም ነው። በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ምሁራን ሙዚቃዎቹን አጥንተዋል፣ ስለ ሙዚቃዎቹም በርካታ ጽሁፎችን ጽፈዋል።
አሊ ብራ፣ በሙዚቃ ዓለም በቆየባቸው ዘመናት በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደር የሌለው የሕዝብ ፍቅርና አክብሮትን ተቀዳጅቷል። በሚሊዮኖች ሕሊና እና ልብ ውስጥም ልዩ ቦታ አለው።
ለስኬቶቹና ለአስተዋጽዖዎቹ እውቅና ከሰጡ የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተቋማትም ከሃምሳ በላይ ታላላቅ ሽልማቶችንም አግኝቷል። ከጅማ ዩኒቨርስቲ ያገኘው የክብር ዶክትሬት ዲግሪ በእነዚህ ሽልማቶች አንዱ ነው።
አሊ ትምህርትና ጥበብ የዕድገትና የስኬት መሰረቶች መሆናቸውንና፣ አለመማር ሕሊናን እንደሚያሳውር በጽኑ ያምናል። ለአሊ፣ ትምህርት በመደበኛ ትምህርት ቤት የሚገኝና አእምሮን ብቻ የሚያሳትፍ ሂደት ሳይሆን፣ የሰው ልጅ እድሜ ልኩን በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው የሚያካሂደውና ሁለመናን (አካልን፣ አእምሮን፣ መንፈስንና፣ ልቡናን) የሚያሳትፍ ሰፊና ረጅም ሂደት ነው።
አሊ ብራ፣ እነዚህን እምነቶቹን በዘፈኖቹ ውስጥ በማስተላለፍ ብዙዎችን እንዲህ ላለ የትምህርት ጉዞ አነሳስቷል፣ ራሱም እምነቱን በተግባር በመኖር አርአያና ምሳሌ ሆኗል።
አሁንም የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓሉ መሪ ቃል “Barnootaa ammas Barnootaal -መማር አሁንም መማር!” እንዲሆን የወሰነ ሲሆን፤ መሪ ቃሉን በመከተል በበዓሉ አከባበር ዝግጅቶች ላይ በሙሉ ስለ ትምህርት የተለያዩ መልዕክቶች ይተላለፋሉ።
ዶ/ር አሊ ብራ ለሀገራችን እድገትና አዲሲቱንና የበለፀገችውን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በተለይ በትምህርት ዘርፍ የሚያደርገው አስተዋፅዖ ስለ ትምህርት በማስተማር ብቻ የተወሰነ አይደለም።
አሊ “Birra Children’s Education Fund” የተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ከባለቤቱ ጋር አቋቁሞ ለሕፃናት ትምህርት ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛል። ድርጅቱ አሁን በድሬዳዋ አካባቢ ባሉ ትምህርት ቤቶች ላይ እየሰራ ሲሆን፤ በቀጣይነት በመላው የሀገራችን ክፍሎች የተጠናከረ ሥራ ለመስራት እቅድ አለው።
በቀጣዩ የህይወት ክፍለ ጊዜው፣ አሊ ብራ፤ በዋነኝነት በሚከተሉትን ተግባራት ለማከናወን አቅዷል።
- የጀመረውን የበጎ አድራጎት ስራ ማስፋፋትና ማጠናከር፣ ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም እንዲደርስ መስራት፣
- ፈለጉን የተከተሉ አርቲስቶችን በአማካሪነት በመደገፍና፣ እውቀትና ልምዱን በማካፈል ለኪነጥበቡ እድገት ሲያደርግ የቆየውን አስተዋጽዖ መቀጠል፣
የዚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ የሃምሳኛ ዓመት ክብረ በዓልን የሚያዘጋጀው የፕራክሲስ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆነው ወጣት ዘላለም ቻላቸው በአሉን ለምን ማክበር እንዳስፈለገም ይገልፃል።
አንደኛው አሊ ብራ ለሀገራችንና ለሙዚቃው ዓለም ትልቅ ስጦታ ነው። የአርቲስቱ ሕይወት፣ ስራዎቹ እና ያስመዘገባቸው ውጤቶች የታሪካችንና የትውፊታችን ጉልህ አካላት ስለሆኑ፣ ሊዘከሩ፣ ክብር ሊሰጣቸውና ሊጠበቁ ይገባል። እርሱም ላደረገው ሁሉ ተገቢው ክብርና ምስጋና ሊሰጠው ይገባል። ይህ የወርቅ ኢዩ ቤልዩ በአል እነዚህን በይፋና በተደራጀ መልኩ እንደሚደረግ ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
ሁለተኛው፣ አሊ ብራ በሃምሳ ዓመታት ጉዞው ላስመዘገባቸው ስኬቶች ዋነኛው መሰረት ከአፍሪቃዎቹ፣ ከአድናቂዎቹና ከህዝብ የተደረገለት ድጋፍና እርዳታ መሆኑን በፅኑ ያምናል። ስለዚህም በአሉ አሊ ለተዋለለት ውለታ ለእነዚህ ሁሉ ምስጋናውን የሚያቀርብበትና የደስታው ማዕድ ከሌሎች ጋር የሚቋደስበት መድረክ ነው ይላል አዘጋጁ ዘላለም ቻላቸው።
ሶስተኛው ደግሞ፣ ታላላቆችን የማያከብር ማህበረሰብ ተተኪ ታላላቆችን አያፈራም ሲልም ተናግሯል። እንደ ዘላለም ገለፃ በዚህ በአል ለአሊ ቢራ የሚሰጠው ክብርና ምስጋና ፈለጉን ለተከተሉ አርቲስቶችና በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ለሚገኙ ሁሉ መነቃቃትን፣ መነሣሣትን እና ብሩህ ተስፋን ይፈጥራል፤ ነገ በየዘርፉ ብዙ አሊ ብራዎች እንዲኖሩ መንገድ ይጠርጋል። በሙያቸው ለሕዝብና ለሀገር ታላቅ ውለታ የዋሉ አንጋፋዎችን የማክበርና የማመስገን ባሕላችንን የምናዳብርበትም ይሆናል።
በአራተኛነት የገለፀው ደግሞ፣ በአሉ አሊ እምነቱን፣ ዕውቀቱን፣ እቅዱን፣ ተስፋውን፣ ራዕዩን በተለያዩ መድረኮች ለሌሎች በማካፈል እስከ ዛሬ ይዞት የመጣውን ችቦ ለሌሎች የሚያስተላልፍበት መድረክም ይሆናል ብሏል ዘላለም ቻላቸው። በመጨረሻም በአሉ፣ አርቲስቱ በቀጣይነት ሊሰራቸው ላሰባቸው ሥራዎች መሠረት የሚጥልበትም ይሆናል።
የአሊ ብራ የሃምሳኛ አመት የመድረክ ውሎው በአል በምን አይነት መልኩ ይከበራል የሚል ጥያቄም ተነስቶ ነበር። እንደ ወጣት ዘላለም ቻላቸው ገለፃ የበዓሉ አከባበር፣ የሚከተሉትን ዋና ዋና ዝግጅቶችና ተግባራት ያካተተ ይሆናል ብሏል።
ይህ ዝግጅት ሃምሳኛ አመት በአሉ በይፋ የሚጀመርበትና የሙያ አጋራቱ፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት፣ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆች እና ሚዲያ የሚገኙበት ዝግጅት ነው። ዝግጅት ስለ አሊ ብራ ሕይወትና ሥራዎቹ የሚቀርቡ ጥንታዊ ጽሁፎችን፣ ንግግሮችን እና የሙዚቃ ድግስን ያካትታል።
የአሊ ብራን ህይወትና ሥራዎች የሚያሳዩ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች እንዲሁም የተሸለማቸውን ሽልማቶች የሚቀርቡባቸው ኤግዚቢሽኖች በአዲስ አበባና በአደማ ከተማዎች ይካሄዳሉ።
በአዲስ መልክ የተቀናበሩ 10 የተመረጡ የአሊ ዘፈኖችን የያዘ አልበም ለወርቅ ኢዩቤሊዩው ይለቀቃል ሲል ወጣት ዘላለም ቻላቸው ተናግሯል። ከዚህ ሌላም ኮንሰርቶች እንደሚቀርቡም ገልጿል። ኮንሰርቶቹም የሚካሄድባቸው ከተሞችም ይፋ ሆኗል።
1. አዲስ አበባ
2. ድሬዳዋ
3. ሌሎች የክልል ከተሞችና የኦሮሚያ ከተሞች
4. በውጭ ሀገራት (አውሮፓ፣ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅና እስያ፣ አውስትራሊያ)
አሊ ቢራ በእስከዛሬ ህይወቱ ከ40 በላይ ሀገራት እየተዘዋወረ ሙዚቃዎቹን አቅርቧል። ስለዚህ አለማቀፋዊ ተቀባይነቱ ሰፊ እና ተወዳጅ በመሆኑ በየሐገሩ በጉጉት እንደሚጠበቅ ተናግሯል።
(ዘገባ ከሰንደቅ ጋዜጣ)
ወጣቷ ድምፃዊት ስለሳዑዲ አረቢያ የወገኖቻችን ስቃይ “ይጣራል በርቀት”ስትል አቀነቀነች
(ዘ-ሐበሻ) “ይጣራል በርቀት የወገን ድምጽ ስሙኝ ይላል” ስትል ወጣቷ ድምፃዊት ሰላማዊት አበባየሁ በሳዑዲ አረቢያ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተሰቃዩና እየሞቱ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን አቀነቀነች። ልብ በሚነካ ድምጽ፣ ለኢትዮጵያውያኑ በዋሽንግተን ዲሲ የተደረገውን ሰላማዊ ሰልፍና አርቲስት ታማኝ በየነ በሳዑዲ አረቢያ ኢምባሲ ደጃፍ “shame on you” ሲል የተናገረውን በዘፈኗ ውስጥ ያካተተችው ይህች ወጣት ድምፃዊት ምንም እንኳ ዜማው ከጥላሁን ገሰሰ “ይህች አጋጣሚ” ዘፈን ጋር ቢመሳሰልም፤ በዚህ ‘ይጣራል በርቀት’ ዘፈን ያሳየችው ብቃት ወደ ፊት ተስፋ እንዲጣልባት አስችሏታል። ዘፈኑ የሚከተለው ነው፦
አፍሪካዊው ኮከብ
ጀግናው አሸለበ፣ ደከመው ተረታ
ሞት አይቀርምና፣ የማታ የማታ፤
ምን ብርቱ ቢሆኑ፣ ሺ መካች ቢሆኑ
ሰው አያልፍ አይገደፍ፣ ተዛቹ ተቀኑ፤
አፍሪካ ሆይ መጥኔ፣ አንድ ወልደሽ ላጣሽው
ተንግዴ መሸበሽ፣ በማን ትዘከሪው? በማንስ ትጠሪው?
ማንዴላ ብረቱ፣ የሮቢን ደሴቱ
የዘረኞች ዋግምት፣ የጥቁር ኩራቱ-
ተንግዲህ የለህም፣ ታሪክ ነበርክና
ታሪክ ነህ ተንግዴ፣ ላትመጣ እንደገና፤
ዓለም አሸርግጂ፣ ቱቢት አስመቺና
ደረት እየመታሽ፣ ”ወይ ልጄን…” በዪና፤
አንበሳሽ ቀን ጣለው፣ ይውጣልሽ ሀዘንሽ
ሙሾሽን ደርድሪ፣ ማቅ ልበሽ እባክሽ
ማንዴ እኮ ነው ሃጁ፣ ሌላው እንዳይመስልሽ፤
ባፍሪካ ሰማይ ላይ፣ የበራው ኮከብ
ተወርዋሪ ነበር፣ ዐይንን የሚስብ፤
ባፍሪካ ሰማይ ላይ፣ የነጋው ጀምበር
ለወገኑ ነበር፣ ብርሃንና አድባር
ለጠላቱ ነበር፣ መራር እንደ ኮሶ
ገፍናኝ እንደንቆቆ፣ ጠላትን አድብኖ-
ጠላትን አጢሶ፤
ማንዴላ አባ ቢያ፣ ደከመኝ ባይል
በቀን ተሸንፎ፣ ኑ ሸኙኝ ባይል-
የኮከቡን ኮከብ፣ ማን እሱን ሊያህል?!
ባፍሪካ ሰማይ ላይ፣ የታየው ፀዳል
ጌጣችን ነበረ፣ ተመሃል ባይጎል፤
-በአበራ ለማ
(ኦስሎ፣ 06.12.13፣ 01፡06 ሰዓት)
ቢሞትም አይሞትም! (ግጥም ስለማንዴላ) –ከፋሲል ተካልኝ (አደሬ)
ቢቢሲ..አልጀዚሪያና ኤፒ የመሳሰሉ መገናኛ
ብዙኃን..በሰበር ዜናነት..የታላቁን የዓለማችን
ተምሳሌ – ተአርአያ የሆነውን የኔልሰን
ማንዴላን (የማዴባን) ዜና ዕረፍት እየዘገቡ ነው::
የዜናው እውነትነት ቢረጋገጥም..ቀደም ብዬ
በስንኞቼ..አጽንኦት ሰጥቼ እንደገለጽኩት..
የማዴባን ሕያውነት አይለውጥም::
ለማንኛውም..በሥጋዊ ዕረፍቱ የተሰማኝን ሐዘን በመግለጽ..ነፍስ ይማር እላለሁ::
የመታሰቢያ..ስንኞቹንም እነሆኝ ብያለሁ!!!
____ ቢሞትም አይሞትም ____
ከዳር እዳር ይናኝ..
ላለም ሁሉ ያስተጋባ
ስሙ የተቀደሰ ነው..
ለዘላለም ማዴባ!..ማዴባ!..
ማዴባ!..ማዴባ!..
ታቦት ተቀርጾ ለግብሩ..
ቢጠራ በቀንም ሆነ በሌት
ቢያሞጋግሱት ደጋግመው ቢቀኙለት..
ቢቆሙለት ቅኔ ማሕሌት
እማይበዛበት..
እማያንስበት..
ለሔደበት ፍኖተ-ነጻነት..
የመለኮታዊ ብርሐን ነጸብራቅ ነው!..
እሚያወጣ ተጭቆናዊ ቅሌት
ለቅኖች ሁሉ አብነት..
ለመላው ዘረ-አዳም ተምሳሌት::
ተሥጋዊ መሻቱ ‘ርቆ..ያለትዕቢት..ያለአመፃ..
በቅዱስ ውስጣዊ ሃይሉ..
የበደሉትን ይቅር ብሎ..በነጻ መንፈሱ ያነፃ
ተክፋታቸው እግረ-ሙቅ አላቆ..
በእርቀ-ሰላም በምህረትና በይቅርታ
የትም’ክታቸውን ሠንሰለት በጥሶ..
ያሰሩትን በትህትናው የፈታ
ለጨቁዋኞች ነጻ አውጪ ነው..
ለተጨቁዋኞችም እንደጌታ::
የተንኩዋሰሰው..
የዘረሰው መንፈስ..
ተዘር..ተቀለም ልቆ..በፅኑ መንፈስ ገዝፏል
ሕያው የሆነ ታሪኩን..በበጐ ምግባሩ ጽፏል
ምድረ-ደንብን ተቃርኖ..
ሕገ-ተፈጥሮን ተላልፏል
የዕድሜ ልክ ጽልመቱን እንኩዋ’..
በብሩህ ብርሐኑ ገፏል
ማዴባ ቢሞትም አይሞትም!..
ሞትን ቀድሞ አሸንፏል..
ተሚኖርበት በላይ ኖሮ..
ተሚሞትበትም ቀን አልፏል!!!
የቂም..የበቀል..የክፋት..
እሾህ እሾሁን ነቃቅሎ..
በእርቅና ሰላም ያስተቃቀፈ..
…ያበረከተ የፍቅር አበባ
ስለራሳችሁ ኑሮ ፀልዩ..
ቢሞትም እኮ አይሞትም!..
…ዘላለማዊ ነው ማዴባ::
* * *
___ፋሲል ተካልኝ አደሬ___
“የምኒልክ ተግባር ዛሬ ያለንበትን ሀገር መዋቅር የሠራ በመሆኑ፤ የተዘፈነው ዘፈን ለክብራቸው ቢያንስ እንጂ የሚበዛ ሊሆን አይችልም”–ቴዲ አፍሮ (አዲስ ቃለምልልስ)
(እንቁ መጽሔት) ተወዳጁን ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሣሁንን በዚህ የመጽሔታችን ልዩ ዕትም፤ የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን 100ኛ የሙት ዓመት… በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለመከበሩን ጉዳይ በተመለከተ ጥያቄዎች አቅርበንለታል። ቴዲም በምላሹ “በማንኛውም ሁኔታ ጥሩ የሠራን ሰው ማመስገን፣ ማክበር ጠቃሚ ባህል መሆኑን ተረድተን፤ በዚህ በኩል እስከዛሬ ያለውን ስሕተት ማረም አለብን” ብሏል። ሌሎች መሰል ሐሰብ አስተያቶችንም ሰንዝሯል። ሁሉንም ከቃለ-ምልልሱ ዝርዝር ይዘት ያገኙታል። መልካም ቆይታ!
ዕንቁ፡- የዳግማዊ ዐፄ ምንሊክ 100ኛ የሙት ዓመት በብሔራዊ ደረጃ አለመከበሩን እንዴት አየኸው?
ቴድዎሮስ፡- በቅድሚያ ከአከባበሩ አግባብነት ተነስተን ለይተን ልናስቀምጠው የሚገባ ነጥብ መኖር አለበት። ይከበራል የሚባለው ቀን የሞቱበት ይሁን፤ ሥርዓተ ቀብራቸው የተፈጸመበት ወይስ ምኒሊክ በሠሯቸው አገራዊ ቁም ነገሮች ላይ ያአተኮረ ይሁን የሚለው ሀሳብ እራሱን የቻለ ውይይት የሚፈልግ ነው። እንዲህም ሆኖ ግን በግሌ የምኒልክ ማንነትም ይሁን ለኢትዮጵያ ያበረከቱት አስተዋፅኦ በብሔራዊ ደረጃ አለመከበሩ ያሳስበኛል።
ዕንቁ፡- በአንተ ግንዛቤ ከኢትዮጵያ ባሻገር ባለው ዓለም ብሔራዊ ኩራት የሆኑ ሰዎች ስለምንድነው የሚታሰቡት? አያይዘህም ምኒልክን በማክበር ሊገኝ ይችላል ብለህ የምታምንበትን ብሔራዊ ጥቅም ብትገልጽልን?
ቴድዎሮስ፡- ግለሰቦች እንዲታወሱ የሚደረግበትም ምክንያት፤ መሻሻልና መደገም ያለባቸው ጥሩ ታሪኮች ወደ አዲሱ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ስለሚፈለግ ነው። እነዛ ብሔራዊ ኩራት መሆን የቻሉ ሰዎች ሲታሰቡ ወይም የመልካም ስምና ተግባራቸው ማስታወሻ ዝግጅት ተደርጎ ክብራቸው እንዲገለጥ ሲደረግ፤ ሌሎች መልካም የሚሠሩ ሰዎችን ማፍራት የሚያስችል መነሣሣትን ይፈጥራል። በመሆኑም ነው ክብረ በዓሎች በታላላቅ ግለሰቦች ስም እየተሰየሙ፣ የእነሱም መልካምነት እየታሰበ የሚወሱበት አንድ ብሔራዊ ዝግጅት የሚከናወንበት ሥርዓት የሚያስፈልገው።
ዕንቁ፡- ዳግማዊ ምኒልክ ስለዛሬይቱ ኢትዮጵያ መፈጠር ሲሉ የገቡበትን ጦርነት እንዴት ነው የምትመለከተው?
ቴዎድሮስ፡- ምንጊዜም ሰዎች የሚበጃቸውን ነገር እስኪገነዘቡት ድረስ ያለመግባባቱ መጠን ይሰፋል። ያም ግጭት ሊፈጥር ይችላል። ይህም ደግሞ በእኛ ሀገር ሁኔታ ብቻ የተከሰተ ሳይሆን በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሆነም ነው። እንዲህም ሆኖ ግን ለምሳሌ ምኒልክ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ዘምተው ንጉሥ ጦናን ማረኩ። ከማረኳቸውም በኋላ እግራቸውን እያጠቡ ‹‹የእኛ አንድ አለመሆን፣ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት አለመመሥረታችን፤ የጋራ ለሚሆነው ጠላታችን ጥቃት አሳልፎ የሚሰጠን አደገኛ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። በዚህ ምክንያት ነው ወደ አንተ ጦር ያዘመትኩት እንጂ ሥልጣንህን ለመቀማትና በአንተ ላይ ለመግነን… ፈልጌ አይደለም። ማእከላዊ መንግሥታችንን ማጠናከሩ ግን ሁላችንንም የሚጠቅመን ነው። አገራችንን፣ በሕላችንን፣ ታሪካችንን፣ ቋንቋችንን ጠብቀንና ድንበራችንን አስከብረን ለመኖር ይረዳናል›› ነበር ያሏቸው።
ለምንጊዜውም ነገሮችን በቀና ማየትና የጎደለውን ሞልቶ፣ ያለውን ጥሩ ነገር እንዳለ ይዞ መሄዱ፤ ለተሻለ ሀገራዊ ርምጃ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ። ይህን የመሰለው አካሄድ ደግሞ በሌሎች አገሮች አልተሠራበትም የሚል ቅንጣት ዕምነትም የለኝም። ወቅቱ በረዳቸው መጠን የነበረውን የአንድነት ክፍተት ሞልተውና አመጣጥነው ማእከላዊ መንግሥቱን ከነበረው የግንዛቤ ማነስ ሁሉ… ቀድመው፤ በተቻለ መጠን በትህትና ዝቅ ብለው እግር በማጠብ ጭምር የነበረውን መጥፎ ሁኔታ መልክ ለማስያዝ ደክመዋል። ዛሬ ያለው ኢትዮጰያዊም ከተለያየ የኢትዮጵያ ብሔሮች ምንጭ ፈልቆ ይኸው በአንድነት ‹‹ኢትዮጵያዊያን ነን›› ለማለት ችሏል። ስለዚህ የምኒልክ ስም ብሔራዊ አክብሮት ማግኘት የሚገባው፣ በሕልውናችንም ላይ ከፍተኛ የሆነ ሚና ያለው፣ የተባበታተነውን ሰብስበው ያቆዩ በመሆናቸው ነው።
ዕንቁ፡- “በዐፄ ምኒልክ ዘመነ-መንግሥት የተጀመሩት ሥልጣኔን የመከተል ጉዞዎች እንደጅምራቸው ቀጥለው ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ያደጉትን ሀገራት ጎራ ለመቀላቀል በቻለች ነበር” በማለት የሚቆጩ ወገኖች አሉ። አንተስ ምን ትላለህ?
ቴዎድሮስ፡- ያንን የሥልጣኔ ጅምር ከነበረው የኋላቀርነት ሁኔታ ጋር ሲመለከቱት ለመቀበል በጣም ከባድ ነበር። ለምሣሌ ‹‹ ስልክ ማነጋገር የሰይጣን ተግባር ነው…›› በማለት የተቃውሞ ሃሳባቸውን የሚሰነዝሩ ሰዎች ነበሩ። እንደዚህ ያለውን አመለካከት እና አስተሳሰብ አሸንፎ ለመሄድ ምኒልክ ብዙ ደክመዋል። ከዚህ ተነስተን የመሄዱ ጉዳይ በእሳቸው ተነሳሽነትና አስተማሪነት የተጀመረ ቢሆንም ቀዳማዊ ሀይለስላሴ በስልጣን ዘመናቸው ትምህርትን በማስፋፋት የተወሰነ ደረጃ ለማስኬድ መሞከራቸው የስልጣኔ ምንጩ ትምህርት መሆኑን ያገናዘበ ቀጣይ እርምጃ ነው ለማለት ያስደፍራል።
ዕንቁ፡- አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ባለታሪክ የሆኑ አርዓያዎቻቸውን ያለማክበራቸው ችግር ከምን የመነጨ ነው?
ቴዎድሮስ፡- የችግሩን ምንጭ አጠር አድርጎ ለመግለጽ ያስቸግራል። ነገር ግን ምንግዜም ቢሆን ለጥሩም ይሁን ለመጥፎው ድርጊት፤ መንግሥትም በመንግሥትነቱ፣ ሕዝቡም በሕዝብነቱ የየራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል። እንዲያም ሆኖ ለሀገርና ለወገን የሠራን ሰው ማክበር ጠቃሚ ባሕል ነው። ምንግዜም ቢሆን ጥሩ ተምሳሌት በማይኖረው ማኅበረሰብ ውስጥ ጥሩ የሚሰራ ዜጋ ለማፍራት አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ በማንኛውም ሁኔታ ጥሩ የሠራን ሰው ማመስገን፣ ማክበር ጠቃሚ ባህል መሆኑን ተረድተን፤ በዚህ በኩል እስከዛሬ ያለውን ስሕተት ማረም አለብን። ጥሩን ነገር ማየትና ማክበር መቻል፤ ጥሩ ነገር በራስ ውስጥ እንዲሰርጽ መፍቀድ ማለት ስለሆነ፤ ከሞቱት ሰዎች ሕይወት ያለው ሥራቸዉን ወስዶ መራመድ የሚገባን ይመስለኛል።
ዕንቁ፡- እስቲ “ምኒልክ ተወልዶ…” ስለሚባልበት ምክንያት የሚሰማህን ግለጽልን?
ቴድዎሮስ፡- አዎ ‹‹ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፣ ግብሩ ዕንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ›› ተብሏል። ለእኔ ዕንቁላሉ የምዕራባውያንን ባሕልና ቋንቋ፣ በመውሰድ የራስን ባህል እና ማንነት ለማስጣል የተሞከረውን ሀሳብ ይወክላል።ዕንቁላሉ ውስጥ ተደብቆ የመጣው የተገዥነት አስኳል ሌላው ምስጢር ነው። የዚህ ጥቅስ ወርቁ በራሱ ባለብዙ ትርጉም ነው። ምኒልክ በራስ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ፍልስፍና… የመመራት አስተሳሰብ እንዳይጠፋ ያደረጉትን አስተዋፆም ደርቦ ይገልፃል።
ዕንቁ፡- “የምኒልክ ታላቅነት መከበር የነበረበት በኢትዮጵያ ብቻ አልነበረም። በአፍሪካም ደረጃም ነው እንጂ” የሚሉ ወገኖች አሉ። ለዚህም አባባላቸው አስረጅ የሚያደረጉት የዓድዋን ድልና የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎውን ነው። የአንተ እስተያየትስ?
ቴዎድሮስ፡- በስፋት እንደሚታወቀው የዓደዋ ድል፤ ለመላው አፍሪካውያን ወንድሞቻችን…. ነጻ መውጣት ታላቅ የሞራል ስንቅ መሆን የቻለ ነው። የኢትዮጵያ አርበኞች ትግል ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው የመሰከረ ነው። ነገር ግን ይህን ታሪክ አፍሪካዊ በዓል አሳክለን ከማክበራችን በፊት ትርጉሙን ባገናዘበ መልኩ ኢትዮጵያዊ በዓል አክሎስ ይከበራል ወይ የሚለዉን ጥያቄ በቅድሚያ ለራሳችን መመለስ ያለብን ይመስለኛል።
ዕንቁ፡- ከዚሁ ወቅታዊነት ያለው ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ይኖረዋል የሚል ግምት አለንና … “ጥቁር ሰው ” የተሰኘውን ዜማ ለመሥራት ምን አነሣሣህ?
ቴዎድሮስ፡- አንድ ሰው ከፍላጎቱ፣ በውስጡ ከሚፈጠረው ስሜትና ከተፈጥሮአዊ ዝንባሌው በመነሳት ሥራዎችን ይሠራል። አንድ ሰው ማንን ይመስላል? ቢባል፤ እናቱንም አባቱንም ከመምሰሉ በላይ አነጋገሩን ይመስላል እንደሚባለው እኔም የምጫወተው ሙዚቃ የምናገረውን ይመስላል ማለት ነው። ከምንምና ከመቼውም ጊዜ በላይ ለእነዚያ ታሪክ የሠሩ ሰዎች አክብሮት መጠስት ተገቢ ነው የሚል ስሜት በውስጤ ይመላለስ ስለነበር፤ ያንን ስሜት ለመግለፅ ስል የሠራሁት ሙዚቃ ነው።
ለምሣሌ የምኒልክ ተግባር ዛሬ ያለንበትን ሀገር መዋቅር የሠራ በመሆኑ፤ የተዘፈነው ዘፈን ለክብራቸው ቢያንስ እንጂ የሚበዛ ሊሆን አይችልም። እንዲህም ሆኖ መቼም የሰው ልጆች አመለከካከት እና ስሜት የተለያየ ስለሆነ ዳግማዊ ሚኒልክ ያበላሹት ተግባር አለ ብለን የምናምን ወገኖች ካለን እንኳ የተበላሸውን ነገር ለማስተካከል በተበላሸ መንገድ መሄድ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። በተበላሸው መንገድ የሚኬድ ከሆነ ምንጊዜም በዚህ ምድር ላይ ዕዳ ተከፍሎ ሊያልቅ አይችልም።ዕዳ ተከፍሎ የሚያልቀው በፍቅር ብቻ ነው። ጥቁር ሰውንም የፈጠረው ‹‹ፍቅር ያሸንፋል›› የሚለው መንፈስ ነው። ። በዳህላክም ላይ የምናየው ይሄንኑ ነው። ስለዚህ ዕዳ የመሰረዝ ጉዳይ ከአበዳሪ አገሮች የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከእየራሳችንም ህሊና የሚጠበቅ ተግባር ነዉ።
ዕንቁ፡- የምኒልክ የመሪነት ጥንካሬ ከራሳቸው ብቻም ሳይሆን ከዕተጌ ጣይቱም አጋርነት የሚመነጭ ስለመሆኑ የታሪክ መዛግብት ላይ ሠፍሮ ይነበባል። አንተስ ስለጣይቱ ምን ትላለህ?
ቴዎድሮስ፡- ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ አንዲት ሴት አለች እንደሚባለው የምኒልክ ጥንካሬ የጣይቱም ነው። ከዚህም በዘለለ ልናየው ስንሞክር የጣይቱ ሚና ሲመዘን አንደኛ የምኒልክን የልብ ሥፋት የምንረዳበት ነው። በጊዜው እንደማንኛውም ኋላቀር አስተሳሰብ ለሴቶች ከሚሰጠው ግምት አንፃር ምኒልክ ሚስታቸውን በነበሩበት ደረጃ ኃላፊነት የሰጡ፣ ምክራቸውንም ለመቀበል የማያመነቱ ሰው ሆነው እናገኛቸዋለን። ዛሬ ስለሴቶች ጥንካሬ ለማወራት፤ ጣይቱ በጣም ጥሩ ምሣሌ ናቸው። ይሄ የጣይቱ ብልሀት፣ የጣይቱ መንፈሳዊ ጥንካሬ፣ የአመለካከት ሥፋትና ጥልቀት… ምኒልክን ‹‹ዕምዬ›› እስከማሰኘትና አልፎ ተርፎም በዓድዋ ጀግንነታቸው ጎልቶ እንዲዋጣ የወኔ ኃይል እስከመሆን ደረጃ የዘለቀ ነው። የሁለቱ የመቻቻልና የመደማመጥ መጠን በራሱ፤ በተለይ አሁን አሁን… ለሚስተዋለውና ‹‹የሴቶች የበታችነት፣ የወንዶች የበላይነት…›› ለሚባለው አጀንዳ ጥሩ ማጣቀሻ ነው። ከዚህም ባሸገር ጣይቱ በብዙ መመዘኛ ትልቅ ሥራ የሠሩ ሴት ናቸው።
ዕንቁ፡- ምኒልክን በተመለከተ እንደ ሙዚቃው ሁሉ ፊልም ሠርቶ ሕያው ሥራዎቻቸውን ማክበር አይቻልም?
ቴድዎሮስ፡- አንተ ያላከበርከውን ሌላው ሊያከብርልህ አይችልም። አፍሪካዊያን ወገኖቻችን የእኛን አባቶችና አያቶች ዋጋ ያውቃሉ። እኛ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ላይ ለመድረስ ገና ጭቅጭቃችንን አልጨረስንም። ስለዚህ በፊልምም ሆነ በሙዜቃ መደገፎ ጠቃሚነቱ በአያጠያይቅም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እኛ በታሪካችን ላይ ያለንን ግንዛቤ የማስፋት ደረጃና ጥልቀቱ በቂ ሆኖ መገኘቱ ላይ ነው።
ዕንቁ፡- የምኒልክ ማንነት በብሔራዊ ደረጃ መከበር ይገበዋል… ከመባሉ አኳያ ለወጣቱ ትውልድ የምታስተላልፈው መልዕክት ይኖርሃል?
ቴዎድሮስ፡- ቅንነት ከሌለ ጥሩ ነገር ማየት እንደማይቻል አውቆ። ታሪኩንም በቅንነት ስሜት መመርመር ይኖርበታል። የባለታሪክ ሰዎችን ጥሩ ነገር መውሰድና ጥሩ ያልሆነ ነገራቸውን ደግሞ እንዳይደገም ለማረም መትጋት ከኛ ከወጣቱች ይጠበቃል። ትልቁና ቁልፍ ነገር የማንነትን መሠረታዊ ጥያቄ ከመገንዘብ ይመነጫል። ሕይወትም የሚጀምረው ራስን ከመሆን ነው። ሰው ራሱን ሲያክል ሌላ ብዙ ነገር ማድረግ ይቻለዋል።… ስለዚህ የነገር ሁሎ ምንጭ ፍቅር ስለሆነ ከፍቅር የሚጀምረውን ህይወት በፍቅር ለመጨረስ ቅንነት ያስፈልጋል። አመጣጡን ያዬ አካሄዱን ያዉቃልው ምክኒያቱም ታሪኩን እየዞረ የማያይ ተጋዥ የኋላ መመልከቻ መስታወት የሌለው መኪናን ይመስላልና።
ያ’ገሬና የኔ –አትክልት አሰፋ (ጋዜጠኛ) –ከቫንኩቨር
እናቴና አገሬ ሙግት ገጠሙና፣
ሚስቴና እናት አለም ተወዳደሩና፣
ልጄ እና እማምዬ ፉክክር ገቡና፣
አንዱን ምረጥ ብለው ድርቅ ሲሉብኝ፤
እናቴም ውዴ ናት፣
ሚስቴም የኔ ፍቅር፤
ልጄም ንጉሴ ነው፤
የሚጣፍጥ ከማር፤
የግሌ የራሴ የማ’ለውጣቸው፣
በሰላሳ ዲናር የማልቀይራቸው፤
እናት፣ ሚስት፣ ልጄ፤ ሁሉም የኔ ናቸው።
እኔ ግን ያገሬ፤
እኔስ የ ‘ማምዬ…
የግል ንብረት ነኝ ብዬ መለስኳቸው።
ዲሴምበር 15/2013- ቫንኩቨር (በርናቢ)
ኮሜዲያን ዶክሌ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ታወቀ
(ዘ-ሐበሻ) በቅርቡ ወደ ሰሜን አሜሪካ የመጣው እና ከስራ ባልደረባው ከኮሜዲያን ተመስገን ባትሪ ጋር በመሆን የኮሜዲ ሥራውን እየተዟዟረ በማቅረብ ላይ የሚገኘው ኮሜዲያን ዶክሌ (ወንደሰን ብርሃኑ) በቨርጂኒያ አሌክዛንደሪያ ሆስፒታል ኢመርጀንሲ ሩም ገባ በሚል የተሰራጨው መረጃን ተከትሎ ዘ-ሐበሻ ባደረገችው ማጣራት ኮሜዲያኑ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ አረጋግጣለች።
ይህ ወሬ እንደተሰማ ዘ-ሐበሻ ኮሜዲያኑን ወደ አሜሪካ ወዳስመጣው ያቆብ ፕሮሞተር ደውላ የፕሮሞተሩ ስልክ ባይነሳም ከአዲስ አበባ አብሮት ወደመጣውና በቨርጂኒያ አንድ ቤት ውስጥ አብሮት ወደሚኖረው የሥራ ባልደረባው ኮሜዲያን ተመስገን ባትሪ ጋር በመደወል እንዳረጋገጠችው ኮሜዲያን ዶክሌ ትናንት ምሽት ከገባበት የኢመርጀንሲ ሩም በመውጣት አሁን እቤቱ ይገኛል። እንደ ኮሜዲያን ተመስገን ባትሪ ገለጻ በዶክሌ ላይ በ እግሩ ላይ በወጣች እባጭ የተነሳ አላራምድ ብላው ወደ ኢመርጀንሲ ሩም ሄዷል። ሆኖም ግን በተደረገለት ህክምና አርቲስቱ በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል።
ለኮሜዲያን ተመስገን ዘ-ሐበሻ ‘እንደሚታወቀው በሰሜን አሜሪካ እየተዟዟራችሁ ከዶክሌ ጋር ሥራችሁን እያቀረባችሁ ነው፤ ይህ አደጋ ከሥራችሁ ያቆማችሁ ይሆን?” በሚል ላቀረበችው ጥያቄ “አሁን ዶክሌ በመልካም ሁኔታ ላይ ስለሚገኝከሥራችን የሚያግደን ነገር የለም” ብሏል።
ከኮሜዲያን ተመስገን ጋር በስልክ ያደረግነው ምልልስ የሚከተለው ነው፦
[jwplayer mediaid="10960"]
ቴዲ Vs ምኒልክ፡ ስለ ጥቁር ሰው ወይንስ ስለ ጥቁር ገበያ? –ከታምራት ነገራ (ጋዜጠኛ)
ቴዲ አፍሮ ዳግማዊ ምኒልክን አስመልክቶ ለዕንቁ መጽሄት የሰጠውን ቃለ መጠይቅ ተከትሎ ሱናሚ ሊባል የሚቻል ንትርክ ስለ ቴዲ እና ስለ ዳግማዊ ምኒሊክ በሶሻል ሚዲያ ተናፍአል፡፡ ሰሞኑ ደግሞ የዳግመዊ ምኒልክ ያረፉበት መቶኛ ዓመት የሚታሰብበት መሆኑ ለሱናሚው ትልቅ ድምቀት ሰጥቶታል፡፡
ቴዲ አፍሮ ጥቁር ሰው ከሚለው አልበሙ ወዲህ ስለዳግማዊ ምኒልክ በተለያዩ ቦታዎች ተናግሯል፡፡ እኔን ግን ከቴዲ አፍሮም ፣ ከዳግማዊ ምኒሊክም፣ ከጥቁር ሰው አልበምም በእጅጉ የሳበኝ የዳግማዊ ምኒልክ ተዋስዖ (Discourse) ነው፡፡ በተለይም ተዋስዖው እየተካሄደ ያለበት ገበያ በእጅጉ ስቦኛል፡፡ አንድን ተዋስዖ ስናስተውል የተዋስዖውን በርካታ ክፍሎች ለያይተን ልናይ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ የአንድን ተዋስዖ ይዘት የሚያጠና ሰው በተዋስዖው ውስጥ ጎልተው በተደጋጋሚ የሚታዩ ሐሳቦች፣ ቃላት፣ እና ዝንባሌዎች ያጠናል፡፡ በተያያዥነትም በተዋስዖው ዙሪያ ወሳኝ የሚባሉትን መልዕክት አስተላላፊ ምርቶች ለምሳሌ ዘፈኖች፣ ፊልሞች፣ አልበሞች፣ መጽሐፍትን፣ መፈክሮች፣ እና ፖስተሮች ሊያጠና ይችላል፡፡ በተዋስዖው ዙሪያ ያሉ ተዋናዮች ላይ ማተኮር የሚፈልግ ሰው ደግሞ ተዋስዖውን የሚያንቀሳቅሱትን የሐሳብ አመንጭ እና አከፋፋይ ጋዜጠኞች፤መጽሄቶች፤ ፀሐፍት፤ ምሁራን ፤አርቲስቶች ዙሪያ ጥናቱን ያተኩረል፡፡ ልክ እንደዚሁ አንድ ሰው አንድ ተዋስዖ የሚካሄድበትን ገበያ አተኩሮ ማየት ይችላል፡፡
ገበያ የሚለውን ቃል የምጠቀመው በተዋስዖው ውስጥ ያለውን ትርፍ ወይንም ኪሳራ ብቻ ለማሳየት ሳይሆን ተዋዖውን በሚያካሂዱት ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ ቡድኖች እና ሐሳቦች መካከል የሚደረገውን ግብይት የሚካሄድበትን ሥርዓት (System) ለማመላከት ነው፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ ወቅታዊው፣ ትልቁ፣ እና እውነተኛው ጥያቄ ቴዲ፣ ጃዋር፣ በቀለ፣ ጫልቱ፣ እና አብደላ ስለ ዳግማዊ ምኒልክ ምን አለ? ምን አለች? ምን አሉ? አይደለም፡፡ ስለ ዳግማዊ ምኒልክ በክፉም ኾነ በደጉ መናገር እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ እንዴት ሱናሚ ማስነሳሳት ቻለ ? ስለ ዳግማዊ ምኒልክ እገሌ ገለመሌ ቢል ስለለምን ይኼን ያህል ያወዛግበናል? ይኼ ለእኔ ትልቁ እና ዋነኛው ጥያቄ ነው፡፡ ሱቅ በደረቴዎች የዳግማዊ ምኒልክ አድናቂዎችም ኾኑ ተቺዎች ስለ ዳግማዊ ምኒልክ የሚያስደስታቸውን፣ የሚያምኑበትን፣ እንደውም ሕይወታቸውን እስከሚሰጡለት ድረስ የሚያምኑትን ነገር እየተናገሩ፣ እያደረጉ እንደኾነ ሊወተውቱን ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በዳግማዊ ምኒሊክ አድናቂዎችም ሆነ አውጋዦች መካከል በሚደረገው ምልልስ ከመሳተፍ በመጠኑም ራቅ እና ከፍ ብለን ለማየት ከሞከርን ግን የዳግማዊ ምኒልክን አድናቂዎችም ኾነ ተቺዎችን የሚያስተዳድረውን ገበያ ለማየት እንችላለን፡፡ የዳግማዊ ምኒልክ ደጋፊዎችም ኾነ ተቺዎች በዳግማዊ ምኒልክ ተዋስዖ ዙሪያ ያላቸውን ሐሳብ በተገኘው አጋጣሚ እና ሥፍራ ከማስተላለፋቸው አልፈው በዳግማዊ ምኒልክ ዙሪያ አለኝ የሚሉትን ዕውቀት እና ግንዛቤ እንዴት እንደ ጨበጡት፣ ማን እንደሰጣቸው፣ ከየት እንዳገኙት፣ እና እንዴት እንደ ቀረበላቸው የሚኖራቸው ግንዛቤ እጅግ ውሱን ነው፡፡ አንድ ባለሱቅ በሱቁ ውስጥ ስላለው እቃ እና ዋጋ መጠነኛ ግንዛቤ ይኖረዋል ሊኖረውም ይገባል፡፡
ከዛ ባለፈ ግን አገሪቷን ወይንም ዓለምን ስለሚያንቀሳቅሰው የገበያ ሥርዓት፣ የገበያ መርህ፣ የገበያ ተቋማት፣ እና የገበያ ሕግጋት ኃይል ያለው ግንዛቤ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ጩኸት፣ ትርምስ፣ምሥጢር፣ ግርግር፣ ፍርሀት… ዳግማዊ ምኒልክ እና ሥርወ መንግሥታቸው በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ካላቸው ሰፊ ተጽዕኖ ተነስተን ከተወያየን እስከ ዛሬ አይደለም ገና ለሚቀጥሉት ብዙ መቶ ዓመታት የማንግባባቸው በርካታ ነጥቦች ይኖራሉ፡፡ ለእኔ አሳሳቢው ጉዳይ ስለዳግማዊ ምኒልክ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ሙሉ ስምምነት ላይ መድረስ አይደለም፡፡ አሳሳቢው ጉዳይ ለምን በውይይቱ መካከል ስክነት፣ እርጋታ፣ ዕውቀት፣ እና እውነት ጠፍተው በሥፍራቸው ጩኸት፣ ትርምስ፣ እና ድንቁር እንደ ምን ነገሡ ነው፡፡ እንደ እኔ እምነት በዳግማዊ ምኒልክ ዙሪያ የሚደረገው ተዋስዖ ከስክነት ትርምስ እንዲበዛው፣ በምክንያት ከሚናገሩ ሰዎች ጯኂዎች መድረክ እንዲያገኙ፣ አዋቂዎች ከአላዋቂዎች እንዳይለዩ፣ እውነት የያዙ ፈርተው ሐሰተኞች እንዲዳፈሩ ነገር ዓለሙ በአጠቃላይ ትርምስ እንዲበዛበት ሆን ተብሎ እተደረገ ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ ርዕሰ ጉዳዩ የምኒልክ ተዋስዖ ስለኾነ እንደ ምሳሌ ልጠቀመው ብዬ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ እና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ስላለው ማንኛውም ተዋስዖ በእርጋታ፣ በአመክንዮ እና በዕውቀት መናገር አይቻልም፡፡ ይህ ትርምስ የተፈጠረው ደግሞ በአብዛኛው ኾን ተብሎ በተገነባ የተዋስዖ ገበያ ሥርዓት እንጂ ዝም ብሎ በአጋጣሚ ከሰማይ ዱብ ያለ ክስተት አይደለም፡፡ የዳግማዊ ምኒልክን ተዋስዖ በምናየው እጅግ አጨቃጫቂ በኾነ መልኩ በመላው አገሪቷ እንዲተዋወቅ የተማሪዎች ንቅናቄ እና የሕወሃት መንግሥት ዋነኛውን ሚና ተጫውቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዳግማዊ ምኒልክ ዙሪያም ኾነ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ዙሪያ የምንሰማቸውን በርካታ ሀሳቦች ጥንስሳቸው በ1966ቱ የተማሪዎች ንቅናቄ ነው፡፡ በተማሪዎች የተነሱትን አንዳንድ ሐሳቦች ለምሳሌ መሬት ላራሹ የደርግ መንግሥት በከፊል ተግባራዊ ተደጓል፡፡ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል እና ሌሎች መሰል ሐሳቦችን ግን እንኳን ሊተገብር መኖራቸውንም እንኳ በአግባቡ ሳይናገር ዘመኑን ጨረሰ፡፡ በ1983ዓ.ም ሕወሃት ሥልጣን እንደያዘም ሻዕቢያን እና ኦነግን በግራ እና በቀኝ አስከትሎ በተማሪዎች ንቅናቄ የተጠነሰሱ በርካታ ሐሳቦችን በመላው አገሪቷ አወጃቸው፡፡ የፈለገውን ሕግ አደረገ ያልፈለገውን ችላ አለ፡፡ ሌዋታን፤ የገበያው ጌታ ማንኛውም መንግሥት በሚያስተዳድረው አገር ላይ በሚካሄደው ተዋስዖ ላይ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር የታደለ ማንም ግለሰብ እና ቡድን ደግሞ በኢትዮጵያ ተዋስዖ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ በእጅጉ ኃያል ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ኋይት ኃውስን ለመቆናጠጥ እድል የቀናው ፓርቲ በአሜሪካ ላይ በተለያዩ ጉዳዮች ተዋስዖውን ሊያነቃንቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን አሜሪካንን የሚገዛው ፓርቲ በአሜሪካ ተዋስዖ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው ፓርቲ በኢትዮጵያ ተዋስዖ ላይ ከሚኖረው ተጽዕኖ ጋር ሲነጻፀር አቅሙ እጅጉን ውሱን ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ፓርቲ ዋይት ኃውስን ያዘ ማለት ኮንግረስ በእጁ ነው ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ በፖሊሲ እና በጀት መሰል ጉዳዮች ላይ ያለው ተጽዕኖ ይወሰናል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ተዋስዖን በመቅረጽ፣ በማዳበር፣ እና በማከፋፈል ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ሚዲያ፣ የሕትመት ቤቶች፣ እና መሰል ተቋማት በዋይት ኃውስ እጅ ውስጥ አይደሉም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንድ ቡድን በድንገት ተነስቶ ወዲያውኑ የአገሪቷን ተዋስዖ ወደ ፈቀደው ርዕዮተ ዓለም (Ideological) ዝንባሌ መንዳት እንዳይችል የሚያደርጉት ዘልማዶች እና ሕግጋቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካን ዶላር እና ሳንቲሞች ላይ የሕያው ፕሬዝዳንት ምሥል እንዳይቀረጽ ህግ አለ፡፡ ይህ ሕግ እንደ አሁኑ በይፋ ሕግ ሆኖ ከመጽደቁ በፊት የሕያው ፕሬዝዳንት ምሥል በዶላር ላይ እንዳይቀረጽ ያልተጻፈ ስምምነት ነበር፡፡ የኛ ብር መልኩ ስንቴ ተለዋወጠ? እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ማንበብ እና መፃፍን የመሰለ ዝቅተኛው የተዋስዖ መሳተፊያ ክህሎት ጭራሹኑ በሌለበት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ገደብ የሌለው ሥልጣን በእጁ ላይ የወደቀ ቡድን በአገሪቷ ተዋስዖ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ልክ የለውም፡፡
በዚህ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚኖረው ጉልበትም የተዋስዖውን ይዘት ከመቆጣጠርም አልፎ ተዋስዖው የሚካሄድበትን ገበያ ሕግጋት እንደ ፈለገው መቆጣጠር እንዲችል አቅም ይሰጠዋል፡፡ ሕወሃት ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ በዳግማዊ ምኒልክ ዙሪያ የለኮሰውን ተዋስዖ ለአጃንዳ አጠር ሎሌዎች በሊዝ አኮናትሮ ገበያውን በጌታነት ከላይ ሆኖ እየዘወረው ነው፡፡ በአንድ አገር የተዋስዖ ገበያ ላይ እጅግ ተፈላጊው ግብ እውነትን ማግኘት ነው፡፡ እውነት በአንድ ጉዳይ ላይ የሚኖረንን የመረጃ ትክክለኝነት እና ሐሰትነት ላይ ብቻ የተገደበ ግንዛቤ አለመኾንኑ፤ በተዋስዖ ትንታኔ ውስጥ በአብዛኛው እውነት ስንል ከመረጃው ትክክለኝነት እና ስህተትነት ባሻገር ያሉ ሐሳቦችንም ይዳስሳል፡፡ በተዋስዖ ትንታኔ ውስጥ እውነት የተዋስዖው ተሳታፊዎች በመረጃው ላይ የሚኖረቸውን ትርጓሜ፤ በትርጓሜው ላይ ያላቸውንም ስምነት ሊያካትት ይችላል፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ዘመቱ የሚለውን አረፍተ ነገር እንውሰድ፡፡ ይህኑ አረፍተ ነገር አንድ የዳግማዊ ምኒልክ ነገር ሲነሳ ሆዱን ባር ባር የሚለው ወዳጃችን ብድግ ብሎ ዘመቻው ከእግዚአብሄር ለኢትዮጵያ የተሰጠ ቅዱስ ስጦታ ነው ብሎ ይህንኑ አረፍተ ነገር ሊተረጉመው ይችላል፡፡ የዳግማዊ ምኒልክ ነገር ሲነሳ የሚያንገሸግሸው ሌላኛው ወዳጃችን ደግሞ ብድግ ይልና ዘመቻው የተካሄደው ዳግማዊ ምኒልክ አያቶቼን እንዲያጠፏቸው በሰይጣን ስለታዘዙ ነው ብሎ ትርጓሜውን ይሰጠናል፡፡ እነዚህም ሆኑ ሌሎች በርካታ ትርጓሜዎች በዳግማዊ ምኒልክ ተዋስዖ ዙሪያ ይኖራሉ፡፡ እያንዳንዱ ቡድን የራሱን ትርጓሜ ይዞ ወደ ገበያው ይመጣል፡፡ ትርጓሜ ሊሸጥ፣ ትርጓሜ ሊገዛ፡፡ ሕወሃት ግን ገበያው ውስጥ ትርጓሜ ይዞ ከመቅረብ የተዋስዖ ቸርቻሪነት ከወጣ ሰነበተ፡፡
እጅግ የሚያዋጣው የገበያውን ሥርዐት እና መዋቅር መቆጣጠር እንደ ሆነ ስለገባው ችርቻሮውን ለጉልቶች ሰጥቶ ኪራይ ይሰበስባል፡፡ ሕወሃት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የተዋስዖ ገበያ በነጻ ገበያ መርህ እንዲመራ ፈጽሞ አይፈልግም፡፡ ይልቁኑ የተዋስዖው ገበያ የሚያስተዳደረው ሻጭንም ሆነ ሸማችን በሚያደናብረው የጥቁር ገበያ መርህ ነው፡፡ በነጻ ገበያ መርኾዎች የሚንቀሳቀስ የተዋስዖ ገበያማ እውነትን ያገኛታል፡፡ እውነትን ያገኛት እርሱ ደግሞ አርነት ይወጣል፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በገበያው ካሉን እልፍ አዕላፍ የምኒሊክ ትርጓሜዎች በተደጋጋሚ ጮክ ብለው የሚሰሙት ሁለቱ ጽንፈኞች ብቻ ናቸው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የተዋስዖ ገበያ የሚመራበት ሥርዐት የገበያው ተሳታፊዎች ወደግራም ሄዱ ወደቀኝ ወደ አንድ ትርጓሜ እንዲሰባሰቡ፤ በዚያ ትርጓሜ ዙሪያም አዲስ እውነት ቀርጸው የጋራ አገር እንዲገነቡ የሚፈልግ የገበያ ሥርዓት አይደለም፡፡ ሕወሀት ምን ዐይነት ሚዲያ፤ በምን ያህል መጠን እንደሚኖር ይወስናል፡፡ ያለማንም ሀይ ባይነት የትምህርት ሥርዐቱን ወደ ፈለገው የትርጓሜ አቅጣጫ ያሳልጣል፡፡ የአደባባዮች፣ የመንገዶች፣ የሀውልቶች፣ አስፈላጊ ከኾነ ደግሞ የከተሞችን ስም እርሱ ወደፈለገው የተዋስዖ ትርክት እንዲያፈገፍጉ በማድረግ ገበያውን እንዳፈተተው ያቆማል፣ ይበትንማል፡፡ የብሔራዊ መዝሙር፣ የባንዲራ፣ የብሔር ብሔረሰብ ክብረበዓላት ይቀርጻል፣ ያውጃል፣ ይበጅታል፣ ያስፈጽማል፡፡ የአየር በአየር ነጋዴዎች ለጥቂት ደቂቃ አገሪቷ ውስጥ ያሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከፓርቲው ገለልተኛ ቢሆኑ፤ ነፃ ሚዲያ በብዛት እና በጥራት ቢስፋፋ፤ የትምህርት ሥርዓቱ የሚቀረጸው አሁን ከሚታየው ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት በተለየ መልኩ ቢኾን ኖሮ ምን አይነት የተዋስዖ ገበያ በኢትዮጵያ እንደሚኖር ለመገመት አያዳግትም ፡፡ በምናባዊቷ ኢትዮጵያም እንኳን ስለዳግማዊ ምኒልክም ኾነ ስለጨለንቆ ሙሉ በሙሉ አንስማማም፡፡ ነገር ግን ውይይቱን የሚያስተናብሩት የጥቁሩ ገበያ የአየር በአየር ነጋዴዎች ፤ ውይይቱንም የሚመሩት ለጥቁር ገበያው የተመረቱ አልበሞች፣ መጽሐፎች፣ ድግሶች እና ሰልፎች አይሆኑም፤ የውይይቱ ይዘትም ልክ 1983 ዓ.ም እንደ ነበረው እጅ እጅ አይልም ነበር፡፡ ያልጨረቱ ሀልዮቶች፣ ያልነፈሰባቸው ትችቶች፣ አዳዲስ ዘርፎች በየጊዜው እየበቀሉ እያደጉ ስለዳግማዊ ምኒሊክም ሆነ ስለ ኢትዮጵያ የሚደመጡት ትንታኔዎች እና ትርጓሜዎች ለተዋስዖው ሞገስ ይሆኑት ነበር፡፡ የገበያው የበላይ ጠባቂ ሕወሃት እጅጉን የሚጠነቀቀው ስምምነት እንዳይፈጠር ነው፡፡ በየትኛውም ተዋስዖ ላይ የሰከኑ አስታራቂዎችን ሳይሆን ስምምነት ላይ ለመድረስ ይቅር እና ለመደማመጥ የማይችሉትን ያበረታታል፡፡
በዚህ ድቅድቅ ጭለማ ውስጥም ሁሉም በእውር ድንብር ይተራመሳል፡፡ ጥቂት ትንሽ ሻል ያሉ አራዶች በየጥጋጥጋቸው ርዕስ እና ትርጓሜ እየመረጡ ቢጫ ሰው ፣ ሰማያዊ ዶሮ፣ ሲያዴ ፈረስት፣ እና ሚያዚያ 9 ምናምን የሚል የአየር በአየር ቡቲክ ይከፍታሉ፡፡ ከዚህም ከዚያም የለቃቀሙትን የትርጓሜ ሰልባጅ አዲስ ልብስ አስመስለው ይሸጣሉ፡፡ እነዚህ የአየር በአየር ነጋዴዎችም የገበያውን ሕግ አይቀይሩም፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም የገበያው መሰረታዊ ሕግ ከተቀየረ ሕልውናቸው አደጋ ላይ እንደሚኾን ስለሚገነዘቡ ከጥቁር ገበያነት ወደ ነጻ ገበያነት እንዲለወጥም አይፈልጉም፡፡ ገበያውን እንዴት አድርጌ ነው የምጠቀልለው ብለው ሁሉ የሚገዛው ትርጓሜ ለማምጣትም አፈልጉም፡፡ የአየር በአየር ነጋዴዎች ናቸው እና ቶሎ ቶሎ ከግርግሩ አትርፈው ሽል እና ሽብልል ከማለት ውጪ ገበያውን ሙሉ ለሙሉ ለመማረክ ወገቡም የላቸውም፡፡ To be fair ለሕወሀት ሳይሆን ለእውነት ‘ፌር’ ለመሆን የኢትዮጵያ ተዋስዖ ገበያ የጥቁር ገበያን መርህ መከተል የጀመረው ግንቦት 20/1983 አይደለም፡፡ ከሕወሀትም በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የትርጓሜ ገበያው በገዢው ቡድን ተፅዕኖ መሆኑ አይካድም፡፡ የወቅቱ ትክክለኛ መረዳት ተዋስዖው የጥቁር ገበያ ሥርዐት መኾኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ እንዴት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ትርጓሜዎች በሰላም ሊንሸራሸሩ የሚችሉት ? በእርጋታ እና በስክነት የሚንቀሳቀስ የተዋስዖ ገበያ ሥርዐት መመስረቻ ቁልፎቹ ምንድን ናቸው ? በባህሎቻችን እና በቋንቋችን ውስጥ ምን ያህል ሀብት ምን ያህል ድህነትስ አለ ? አሁንም ስለጥቁር ሰው ማሰብ ይፈልጋሉ ? I don’t .
ዝነኛው አርቲስት ቴዎድሮስ ምትኩ አረፈ
(ዘ-ሐበሻ) አርብ ሴፕቴምበር 7 ቀን 2013 ታዋቂው የሙዚቃ ሰው ቴዲ (ቴዎድሮስ) ምትኩ በሜሪላንድ ግዛት ሆስፒታል መግባቱ ተገለጸ በሚል ዘ-ሐበሻ ዘግባ ነበር። ይህ ዜና እንደተሰማም በርካታ የኢትዮጵያ ሙዚቃ አፍቃሪያን ይህን ዝነኛ አርቲስት ፈጣሪ ምህረቱን እንዲሰጠው ሲጸልዩ ቆይተው ድምጻዊው ከሆስፒታል ተሽሎት ወጣ።
ሆኖም ግን ዛሬ ጠዋት ዲሴምበር 22 ቀን 2013 ዓ.ም 4፡06 ላይ ኢትዮጵያውያንን ከ1960ዎቹ ጀምሮ ሲያዝናና የነበረው ቴዎድሮስ ምትኩ ማረፉ ተሰምቷል። የድምጻዊው የቀብር ቦታ እና የፍትሃት ሁኔታው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ባይሰማም፤ የፊታችን ማክሰኞ ሊሆን ይችላል የሚል መረጃ ግን ለዘ-ሐበሻ ደርሷል። ሁኔታውን ተከታትለን እንዘግባለን።
ዝነኛው ቴዎድሮስ ምትኩ የጥላሁን ገሰሰ ባለቤት እህት ከሆነችው ወ/ሮ መአዛ በዙ ጋር ላለፉት 22 ዓመታት በትዳር ዓለም ቆይቷል።
ዘ-ሐበሻ በዚህ ታዋቂ የሳክስፎን ባለሙያ የተሰማትን ሃዘን እየገለጸች ታዋቂው ጸሐፊ ዳግላስ ጴጥሮስ እንደ አርቲስት ቴዎድሮስ ምትኩ ያሉ ዝነኞችን ለማስታወስ የጻፈውን ለግንዛቤ አስተናግዳለች።
ከዳግላስ ጴጥሮስ
የአንድ ጐልማሳ ዕድሜን ያህል ወደ ኋላ ዞር እንድንል የዛሬው ርዕሰ ጉዳዬ ትዝታ ይቀሰቅሳል – ከ1960ዎቹ ዓመታት በፊት፡፡ በእነዚያ ዓመታት ውስጥ በትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ በድንቅ ባህልነቱ የሚጠቀስ አንድ ጥበብ በተለየ ሁኔታ አብቦ ነበር፡፡ ያውም የሙዚቃ ጥበብ፡፡
ይሁን እንጂ ይህን መሰሉ ባህል ከዘመን ዘመን የሚሸጋገር ፍሬ እንዳያፈራ «የሥርዓቶች ዋግ መትቶት» በአበባ ብቻ ሊቀር ግድ ሆኗል፡፡ በጭንገፋ ተመትቶ «ግባ መሬቱ» የተፈፀመው ይህ የጥበብ ቡቃያ ፍሬው ከትውልድ ትውልድ እንዳይተላለፍ በእሸትነቱ ስለ ተቀጨ እነሆ የዛሬው ጥበብ ነክ ችግራችን ገዝፎና ሥር ሰዶ «ለወይነዶ!» ቁጭት ዳርጎናል፡፡
«ዛሬ» የሚለው ቃል በጽሑፌ ውስጥ መደጋገሙ አለብልሃት አይደለምና አንባብያን እንድትታገሱኝ በመቅድም አቤቱታ እማፀናለሁ፡፡
እናም የዛሬን አያድርገውና ለልዩ ልዩ ሕዝባዊ ክብረ በዓላት በመዲናችን አዲስ አበባና በዋና ዋና የሀገራችን ከተሞች በዓላቱን የሚያደምቁት የማርች ባንድ (በተለምዶ ማርሽ ባንድ የሚባለው) ሙዚቀኞች ከወታደራዊ ክፍሎች የተገኙት ብቻ አልነበሩም፡፡ ከእነርሱ ባልተናነሰ ደረጃ ያውም በተሟላ ዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ተደራጅተውና ማራኪ የደንብ ልብስ ለብሰው ጥዑም ዜማቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡ የትምህርት ቤት የሙዚቃ ባንዶች ያበቡበት ወቅት ነበር፡፡ ወጣትነት በለገሳቸው መለሎ ቁመት እየተውረገረጉ የተመልካችን ቀልብ ይስቡ የነበሩት እኒያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ታዳጊ የሙዚቃ ጠበብት ዘግይቶ በተፈጠረው ትውልድ ይዘነጉ ካልሆነ በስተቀር በታሪክ መዝገብ ውስጥ ግን ህያው እንደሆኑ መቆየታቸውን የሚደልዝ የተሟጋች ብዕር አይኖርም፡፡
ዳግማዊ ምኒልክን፣ ኰከበ ጽባሕን፣ የደሴው ወ/ሮ ስሂንና የናዝሬቱን አፄ ገላውዲዎስ ትምህርት ቤቶች ብቻ ለጊዜው በክብር ልዘክር፡፡ እነዚያ ትምህርት ቤቶች የነበራቸው የሙዚቃ ባንዶች (ኦርኬስትራና ማርቺንግ ባንድ) በወቅቱ ለተደረሰበት የሙዚቃ ዕድገት ከፍታ ብቻ ሳይሆን በእነዚያ የሙዚቃ ባንዶች ውስጥ ተፈጥረው፣ አድገውና በጥበቡ ተራቅቀው ከሙዚቃ ጋር ነፍስና ሥጋቸው እንደተቆራኘ የሚገኙ ባለሙያዎች ቁጥር ቀላል የሚሰኝ አይደለም፡፡ ሌሎቹን ጥበባት ወቅትና ጊዜ ሲፈቅድ አስታውሳቸዋለሁ፡፡
«ክርስቶስ ለሥጋው አደላ” እንዲሉ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ዕውቀት የተጐነጨበትን የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ባንድ የሚያስታውሰው በትልቅ አክብሮት ነው፡፡ ልዩ ልዩ ክበረ በዓላት ሲመጡ አዲስ የሙዚቃ ቅንብር ለመፍጠር ቀን ከሌት ይደረግ የነበረው ኃላፊነት የተሞላበት የተማሪ ጓደኞቹ የሸብ ረብ ዝግጅት አስደናቂ የሚሰኝ ብቻ ሳይሆን ከግምት በላይ ሊነገርለት የሚገባ ነው፡፡ በወርቃማ ጐፈርና በቀይና ቢጫ ቀለማት የተዋበው የተማሪዎቹ የሙዚቃ ባንድ ገና የትምህርት ቤቱን በር አልፎ ወደ ዋናው የአራት ኪሎ አውራ ጐዳና ሲገባ በዕልልታ ይቀርብለት የነበረው የሕዝብ አቀባበል ወደር አልነበረውም፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ባንዶች ውስጥ ያገለግሉ የነበሩት የያን ጊዜዎቹ ተማሪዎች በኋለኞቹ የጉልምስና ዕድሜያቸው ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ዕድገት የተጫወቱት ሚና እንዲህ በዋዛ በቀላል የሃሳብ ጥቅሻ የሚታለፍ ስላይደለ ጥቂቶቹን ብቻ ለአብነት በመጥቀስ ዝርዝሩን በይደር ማስተላለፉ ይበጃል፡፡
ወደ ኰከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት እስኪዛወር ድረስ የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ማርቺንግ ባንድ ታንቡር መች የነበረው የሙዚቃው ሊቅ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደና በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ ከከፍተኛ የሥራ መሪነት እስከ መምህርነት እያገለገለ የሚገኘው አቶ ሰሎሞን ሉሉን ብቻ ለአብነት አስታውሼ ልልፍ፡፡ አቶ ሰሎሞን ሉሉ አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ መዝሙር የዜማ ደራሲ እንደሆነም ማስታወሱ አስፈላጊ ነው፡፡
እኒህን መሰል ጐምቱ የሙዚቃ ጠበብት ተኰትኩተው ያደጉት በአንጋፋው የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ባንድ ውስጥ ነው፡፡ እኒህንና ሌሎች በርካታ ወጣቶችን ሲያሰለጥኑ የነበሩት አቶ ዘውዱና አቶ መብራቱም የማይዘነጉ የጥበቡ ፊታውራሪዎች ነበሩ፡፡
የኰከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ባንድም ልክ እንደ ትምህርት ቤቱ ስም ሁሉ በወቅቱ የፈካ አጥቢያ ኰከብ ነበር፡፡ በዚያ የሙዚቃ ባንድ ውስጥ አድገው የወጡት ወጣቶችም በሀገራችን የሙዚቃና የቴአትር ጥበብ ላይ ያሳረፉት በጐ አሻራ ሊዘነጋ ከቶውንም አይችልም፡፡ ጥቂቱቹን ልዘክር፡፡ የትምህርት ቤቱ ዘንግ ወርዋሪ፣ ትራንፔት ተጫዋችና ድምፃዊ የነበረው ዓለሙ ገብረአብ እንዴት ይረሳል፡፡ ዓለሙ ገብረአብ ሕይወቱ እስካለፈ ጊዜ ድረስ የብሔራዊ ቴአትር ቤት ፈርጥ ተዋናይ ነበር፡፡
ዛሬ በውጭ ሀገራት ኑሮአቸውን የመሠረቱት ዝነኞቹ የሙዚቃ ባለሙያ ወንድማማቾቹ ተሾመ ምትኩና ቴዎድሮስ ምትኩ የኰከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት የሙዚቃ ባንድ አባላት ነበሩ፡፡ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ከዲሬክተርነት እስከ መምህርነት የዘለቀው አቶ ተክለ ዮሐንስ ዝቄ የዚሁ ትምህርት ቤት ፍሬ ነው፡፡ ታምራት ፈረንጅ፣ ተስፋዬ መኰንን፣ ታምራት ሎቴ፣ ሞገስ ሀብቴ ብዙዎቹ በሕይወት ባይኖሩም በተነደፉበት የሙዚቃ ፍቅር እስከ መጨረሻ የዘለቁት የኰከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት ባንድ ከጥበቡ ፍቅር ጋር ስላቆራኛቸው ነበር፡፡ የእነዚህ ወጣቶች አሠልጣኝ የነበሩት አቶ ማሞ ደምሴና አቶ ጌታነህ ታደሰም አይዘነጉም፡፡ በምሥረታውና በማጠናከሩ ሂደት ላይ የጐላ ድርሻ የነበራቸው ዳኒሻዊውን ፓል ባንክ ሃንሰንን የመሳሰሉ የውጭ ሀገር መምህራንን ለጊዜው በማስታወስ ብቻ እናልፋቸዋለን፡፡
የዝነኛው የደሴው ወ/ሮ ስሂን ትምህርት ቤት የወጣቶች ፖለቲካዊና ሁለገብ ገናና ተሳትፎ በታሪክ የከበረ ቦታ እንዳለው አይደለም የሰው ምስክርነት ሣር ቅጠሉም ቢሆን እኔ ልናገር ብሎ ለዋቢነት መሽቀዳደሙ አይቀርም፡፡ በተለይ ግን የወ/ሮ ስሂን ትምህርት ቤት የሙዚቃ ባንድ በወቅቱ የነበሩትን ወታደራዊ የሙዚቃ ባንዶችን ብቃት በከፍተኛ ሁኔታ ይፈታተን እንደነበር ዕድሜውን የታደሉት ሁሉ የሚያስታውሱት ነው፡፡
የናዝሬቱ ዓፄ ገላውዲዎስ፣ የሐረሮቹ መድኃኒዓለም ትምህርት ቤት እና የመምህራን ማሠልጠኛ ተቋም የሙዚቃ ባንዶችም የነበራቸው ዝና እንዲሁ በጥቂት ቃላት እየታወሰ የሚታለፍ ባይሆንም ዝርዝሩን ለታሪክ ጸሐፍት በመተው ለዝክር ያህል ስማቸውን አስታውሰን እናልፋለን፡፡ የአዲስ አበባዎቹን መድኃኒዓለም ትምህርት ቤትና ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤትን በተመለከተ ግን ንባቤና መረጃዬ ስላልዳበረ እንዲህ ነበሩ ለማለት ድፍረት አጥቻለሁ፡፡ እነዚህን ሁለት ትምህርት ቤቶች በተመለከተ አዋቂዎች ቢያስተምሩን ነበርኩበት ባዮች ቢያሳውቁን ለዕውቀታችን በእጅጉ ይጠቅመናል፤ ከስህተትም ይታደገናል፡፡ መድኃኒዓለም ትምህርት ቤትን ካነሳሁ አይቀር ብዕረ መንገዴን በትምህርት ቤቱ ዋና መግቢያ ላይ ይነበብ የነበረውንና በፍፁም ከህሊናዬ ሊወጣ የማይችለውን ጥቅስ አስታውሼ ልለፍ፤ «ከዚህ ከማይሞተው የሰው ልጅ ማደጊያ ሥፍራ ግቡ» የሚለውን፡፡ ዛሬስ ያ ጥቅስ በቦታው ይገኝ ይሆን?
በውስን የጋዜጣ ገጽ ግዙፍ ሃሳቦችን ማስተናገድ ፈተናው የትዬለሌ መሆኑን አንባቢያን እንደሚረዱት ተስፋ በማድረግ ወደ ማጠቃለያው ሃሳብ ብዕሬን በፍጥነት ማንደርደሩን መርጫለሁ፡፡
ዛሬን ከቀዳሚ ዘመናት ጋር እያስተያዩ ይህ ጐደለ ይህ ሞላ ማለቱ አግባብ ባይሆንም ትናንትን ከዛሬ ጋር እያነፃፀሩ መልካሙን ማስታወሱ ግን ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ ለምን ቢሉ፤ «ብልህ ከትናንት ይማራል፣ ሞኝ ግን ዕለት በዕለት ይሳሳታል» እንዲሉ መሆኑ ነው፡፡
ከላይ በተዘረዘሩት ትምህርት ቤቶች የሙዚቃ ባንድ ውስጥ አባላት የነበሩት ወጣት ተማሪዎች ትምህርት ቤታቸውን ከተሰናበቱ በኋላ ምን ሠሩ? ምን ፈፀሙ? ዛሬስ የት ናቸው? ተገቢ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
በታዳጊነት ዕድሜ ከመደበኛው ትምህርታቸው ጐን ለጐን በሙዚቃ ፍቅር የወደቁት እኒያ ወጣቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሸናፊነት ተወጥተው በልዩ ልዩ ሙያቸው ለሀገራቸው ኩራት እንደነበሩና እንደሆኑ ሥራቸውና ስማቸው ምስክር ነው፡፡
ለአብነት ያህልም በዘመኑ ዝነኛ ባንድ የነበረውን «ሶል ኤኰስ» በመባል ይታወቅ የነበረውን ባንድ የመሠረቱት በኰከበ ጽባሕ የሙዚቃ ባንድ ውስጥ የነበሩት ተስፋዬ (ሆዶ) መኰንን (ከበሮ መቺ)፣ ታምራት ፈረንጅ (ትራምፔት ተጫዋችና ድምፃዊ)፣ ተክለ ዮሐንስ ዝቄ (ትራምፔት)፣ ተሾመ ምትኩ (ጋራ ሥር ነው ቤትሽ፣ ሞት አደላድሎን፣ ሃሳቤን የመሳሰሉት ዝነኛ ዜማዎቹ ይጠቀሳሉ) እና ቴዎድሮስ ምትኩ (ሳክሲፎኒስት) የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ የኰከበ ጽባሕ ፍሬዎች ከሶል ኤኰስ በፊትም ዙላ ባንድን መሥርተው ነበር፡፡ «ሶል ኤኰስ» ባንድን ወደ «አይቤክስ ባንድ» ከዚያም «ሮሃ ባንድ» ወዘተ. እየተባለ የስም ሽግግር በሚደረግበት ጊዜ ሁሉ እነዚያ ወጣቶች በንቃት ተሳታፊ ነበሩ፡፡
በዚያ ዘመን የነበሩት ብዙዎቹ የትምህርት ቤቶቹ የሙዚቃ ባንድ አባላት በሀገራችን የሙዚቃ ጥበብ ውስጥ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ዛሬም ድረስ የደበዘዘ አይደለም፡፡ እንዲያውም ብዙ ታላላቅ የጥበቡ ሰዎችን አሁን ድረስ ለደረሱበት ደረጃ መሠረት የሆናቸውን መደላድል ጥቀሱ ቢባሉ ያለጥርጥር ምሥጋና የሚያቀርቡት ላሳደጋቸው የየትምህርት ቤቱ የሙዚቃ ባንድ እንደሆነ መገመት አይገድም፡፡
ይህ ታላቅ የጥበብ መክሊት በዛሬዎቹ ትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ አለወይ? ርግጥ የዕውቀትና የጥበብ ሁሉ መፍለቂያው ትምህርት ቤት መሆኑ መስካሪ አያሻውም፡፡ ግን ግን በየትምህርት ቤቱ ለዛሬውም ሆነ ለነገው ሙዚቃችን መሠረት ሊሆን የሚችል ሥራ እየተሠራ ነው? ከመደበኛው ሥርዓተ ትምህርት ጐን ለጎን ለሙዚቃ ጥበብ እየተሠጠ ያለው ትኩረት ምን ያህል ነው? የትምህርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን «የተቀበረውን ውጤታማ መክሊት» ቆፍሮ ለማውጣት ምን እየሠራ ይሆን? ዳግማዊ ምኒልክ፣ ኰከበ ጽባሕ፣ ወ/ሮ ስሂን … ትምህርት ቤቶችስ «ነበር» ታሪካቸውን ማደስ አይገባቸውምን? የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወድቋል ወይም ተነስቷል እያልን መከራከራችን ብቻ በራሱ በቂ ይሆናልን? ምን ያህሉን መክሊቶቻችንስ አርቀን በመቆፈር ያለማስተዋል ቋጥኝ ጭነንባቸው ቀበርናቸው ይሆን? እንወያይበት፣ እንምከርበት፡፡ ከንባቤ ጎን ለጎን ለዚህ ጽሑፍ በቂ ግብዓት በመስጠት የተባበሩኝን አርቲስት እሸቱ ጥሩነህ፣ ደራሲና ሃያሲ አስፋው ዳምጤና አቶ ተክለዮሐንስ ዝቄን ክብረት ይስጥልኝ በማለት በአንባቢያን ስም የማመሰግነው በታላቅ አክብሮት ነው፡፡ ሰላም፡፡
ቴዲ አፍሮ እና ጥሬ ጨዋዎች
ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በብዙዎች ሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ትልቅ ስፍራየሚሰጠው ወጣት ከያኒ ነው፤ በሙዚቃዎቹ በሚያነሳው ሀገራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ታሪካዊና ወቅታዊ ጉዳዮች የተነሳ የብዙዎችን ቀልብ ለመግዛት የቻለ ይመስለኛል፡፡ የእርሱን ታላቅነት መግለፅ የዚህ ጹሑፍ ዓላማ፣ ጥያቄም፣ የማወቅም ፍላጎት አይደለም፡፡
ይልቁንም ለዚህ አጭር መጣጥፍ መነሻ የሆነኝ ከሰሞኑ በአንዳንድ ጥቃቅን እና አነስተኛ ካድሬዎች እንዲሁም መንግስትን ለምን እንደሚቃወሙ እንኩአን በማያውቁት እንደ እነ ጃዋር መሀመድ የመሳሰሉ ሰሞንኛ ትችታቸውን በመሰንዘራቸውን ምክንያት እኔም የተሰማኝን ልጨምር በሚል ነው፡፡
እንደምናውቀው ቴዎድሮስ ካሣሁን በዚህች የሙዚቃ ህይወቱ ከዛቻ እስከመታሰር ድረስ የደረሰ መሆኑ እሙን ነው ይህም የደረሰበት የተለየ ሰው ስለሆነ ነው
ቴዲ ሺህ ዘመናት ስልጣኔያችንና ታሪካችን፣ ጥበባችን በፍቅር፣ ፍቅራችን በጥበብ የተገመደበት ውሉ ከየት ተጀምሮ የት እንደተቋረጠ ታሪክንእንጠይቅ ዘንድ እንዲህ ሲል በቅኔው ተመራምሮ ያመራምረናል፡-
ብራናው ይነበብ ተዘርግቶ ባትሮኖሱ ላይ፣
የእነ ፋሲለደስ የእነ ተዋናይ፣
የት ጋር እንደሆነ ይታይ የእኛ ጥበብ መሰረቱ…፡፡
እናም እስቲ ታሪክ ይታይ፣ ይመርመር፣ ዘመናትን ያስረጁና የተሻገሩ ብራናዎቻችን ይውጡ፣የሺህ ዘመን የሃይማኖት፣ የጥበብ፣ የታሪክ፣ የሥልጣኔና የፍልስፍና ድርሳኖቻንን ይታዩይመርመሩ… በአክሱም ስልጣኔ፣ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ትንግርት፣ በጎንደርበእነ ፋሲለደስ የስልጣኔ አየር ዝናዋ የናኘላት፣ እነዛ ፍቅርን በጥበብ አስውበው በቅኔያቸውናበማኅሌታቸው ሰማይ ሰማያትን ሰንጥቀው በመንፈሳቸው ጸባዖት የደረሱ፣ በፍቅር ጧፍ የነደዱበማሕሌታዩ ያሬድ መንፈስ የተነሱ እንደ ተዋናይ ያሉ የቅኔ የጥበብ ጉልላቶች እንደ አጥቢያኮከብ በደመቁባት ምድር ዛሬን ፍቅር የተራብን፣ ጥበብን የተራቆትን፣ ስለ ፍቅር የደከመንምንድነው ምክንያቱ የሚል ይመስለኛል ቴዲ…፡፡
ቴዲ በሙዚቃው ለታሪክ ያለውን ስሱነትና (sensitivity) እውቀትም (Indigenous Knowledge)አሳይቶናል፡፡ ተዋናይን ስንቶቻችን እናውቀዋለን ተብለን ብንጠየቅ የሚያስተዛዝበን ሳይሆንይቀራል፡፡ በተለይ ደግሞ ለዘመናችን ትውልድ ለአፉም ለልቡም ቅርቦቹ እነ አርሴናል፣ቼልሲ፣ ሜሲ፣ ሮናልዶ፣ እነ ፊፍቲ ሴንት እነ ቢዮንሴ፣ ወዘተ… የባሕር ማዶዎቹ ዝነኞች ናቸውእንጂ እነ ተዋናይን እነ ቅዱስ ያሬድን፣ እነ አጼ ፋሲልን ሊያስባቸው ወኔው ያለውአይመስልም፣ ኅሊናውንም ይደክመዋል እናስ እንዴት፣ ምን ሲደረግስ ሊያስባቸው ይችላል የኔትውልድ፡፡ በቅኔው የተራቀቀና በመንፈሳዊ እውቀቱ አንቱ ስለተባለው ስለ ተዋናይለመስማትም ሆነ ለማወቅ የታሪክ መዛግብትን ማገላበጥ ግድ ይላል፡፡ አሊያም ከቤተክርስቲያን ሊቃውንት አባቶች እግር ስር ቁጭ ማለት ያስፈልግ ይመስለኛል፡፡
ቴዲ በየትኛው መንገድ የሀገሩንና የቤተ ክርስቲያኑን የጥበብ እና የሥልጣኔ ከዋክብቶችንሊያውቅ እንደቻለ ባይነገረንም የትናንትናዎቹን የሀገራችንን ባለውለታዎችና የዘመንፈርጦች ማንነት ለማወቅ እና እንዲሁም ታሪኩን ለመመርመር ግን የተጋና የሰላ አእምሮእንደተቸረው/እንዳለው የግጥሞቹ መልእክቶች ይነግሩናል፡፡ እናም ከታሪካችንናከስልጣኔያችን መሰረት ከአክሱም ተነስቶ በጊዜና በታሪክ ሃዲድ ላይ አሳፍሮን በትላንትታሪካችን ውስጥ ራሳችንን እንድንመረምር፤ ራሳችንን እንድናይ ይወተውተናል፡፡ ለዚህደግሞ ምክንያቱ ይለናል ቴዲ ስለ ፍቅር ዜማው ውብ የግጥሞቹ ስንኞች፡-
. . .የኋለው ከሌለ የለም የፊቱ፣
ሳይራመድ በታሪክ ምንጣፍ፣
ሰው አይደርስም ከዛሬ ደጃፍ፡፡
በማለት ከታሪካችን ጋር እጅ ለእጅ በምናብ ሊያጨባብጠንና ሊያስተያየን ይፈልጋል፤ እናምያለ ትላንት ዛሬ የለም፣ ያለ ዛሬ ደግሞ ነገ አይታሰብም በሚል የመጣንበትና የተጓዝንበትንአኩሪና አሳፋሪ የታሪካችንን ምእራፍ ለማገላበጥ ለደከምን ለእራሱ እና ለእኛ ትልቅ ቁም ነገርያለው ምክር ያስተላልፋል፡፡ ይህ የከያኒው የግጥም ስንኝ የሮማውን ታላቅ የሕግ ሊቅ፣ፈላስፋና አስተማሪ የሆነውን የሲስሮን አባባል አስታወሰኝ፡- ‹‹ከመወለዳችን በፊት ያለውንታሪክ ካላወቅን ዕድሜ ልካችንን ሕጻን ሆነን እንቀራለን፡፡›› ታሪካችንን ለመመርመር እናከታሪካችን ለመማር የደከምን እኛ ዛሬም እንደ አዲስ ሰናፈርስ ስንጀምር ከመጀመር ሀ ሁሳንወጣ እንደ ህጻን ባለህበት እረገጥ የሆንበትና ታሪክን እንድንደግም የተፈረደብን ምስጢሩምን ይሆን በማለት ታሪክ ጠያቂ፣ የታሪክ ወዳጅ፣ ከታሪክ የምንማር እንድንሆን ያተጋናል፡፡
ከምንኮራበት ታሪካችንና ስልጣኔያችን ባልተናነሰ አንገት የሚያስደፋ ስማችንና ማንንታችንበዓለም ፊት በቀየረብን በበርካታ የራብ፣ የእርስ በርስ ጦርነትና መበላላት ታሪክ ዘመናትንውስጥ አልፈናል፡፡ እናም የመጣንበት መንገዱ ረጅም ዘመናቶቻችንም መከራ ሰቆቃና ዋይታ የነገሰባቸው ናቸው ሲል የትናንቱን ታሪክ ለመድገም የተፈረደብን ይመስል ታሪክ ደጋሚዎች እንድንሆን የሆንበትን እውነታ መመርመርና ማየት እንችል ዘንድ ትልቅ ጥያቄያጭርብናል፡፡ ዛሬም እግራችን መሄድ ተስኖት ቆመናል
የእርሱ ደጋፊዎች እንዳሉ ሁሉ የእርሱ ተቃዋሚዎች መኖራቸው ተፈጥሮአዊ ነው ነገር ግን በአሉባልታ የቴዲን ስራዎች ጥላሸት ለመቀባት የሚደረግ ትግል ወይ ቅናት ነው አልያም ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው እንደሚባለው ይሆናል፡፡
ለእምዬ ምንሊክ ያላቸው ጥላቻ ሰሞኑን ተቀስቅሶባቸው ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ ከርመዋል አስገራሚው ነገር ምንሊክን ለመሳደብ ቴዲን ሰበብ ማድረጋቸው ነው ሌላው ደግሞ መረጃውን እኔ ለቅቄዋለው ብሎ ማንም ኃለፊነቱን እሰከዚች ሰዐት ድረስ ሳይወስድ እነርሱ ቴዲን እና ምንሊክን መዝለፍ የየእለት ተግባራቸው አድርገውታል፡፡
ምንሊክን ህዝቡ እምዬ ብሎታል ቴዲን ደግሞ የዘመናችን የሙዚቃው ንጉስ ብሎ ሰይሞታል
ደበበ ሰይፉ ጥሬ ጨው በሚለው ግጥሙ እንዲህ ነበር ለነፈዞች የገጠመው
ጥሬ ጨው – ደበበ ሰይፉ
————
መስለውኝ ነበረ ፣
የበቁ የነቁ
ያወቁ የረቀቁ
የሰው ፍጡሮች ፣
ለካ እነሱ ናቸው ፣
ጥሬ ጨው..ጥሬ ጨው
ጥሬ ጨዋዎች ፣
መፈጨት-መሰለቅ-መደለዝ-መወቀጥ-
መታሸት-መቀየጥ
ገና እሚቀራቸው ፣
“እኔ የለሁበትም !”
ዘወትር ቋንቋቸው ።
ለማንኛውም እኔም እንደ ደበበ ሰይፉ ሰሞንኛ የቴዲ ተቺዎችን ጥሬ ጨው ብዬ ሰይሜያቸዋለው፡
የዝነኛው አርቲስት ቴዎድሮስ ምትኩ (ቴዲ) የቀብር ሥነ-ስርዓት የፊታችን ቅዳሜ በሜሪላንድ ይፈጸማል
(ዘ-ሐበሻ) ከቀናት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ታዋቂው የሙዚቃ ሰው ቴዎድሮስ ምትኩ (ቴዲ) የቀብር ስነሥርዓት የፊታችን ቅዳሜ በሜሪላንድ እንደሚፈጸም ቤተስቦቹ ለዘ-ሐበሻ ድረ ገጽ ገለጹ።
ኖቬምበር 11 ቀን 1955 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለደው ይኸው ታዋቂ የሳክስፎን ሙዚቃ ባለሙያ ህይወቱ ያለፈችው ባለፈው ቅዳሜ ዲሴምበር 22 ቀን 2013 በዋሽንግተን ዲሲ መሆኑን ዘ-ሐበሻ ከቀናት በፊት መዘገቧ ይታወሳል።
በሕዝብ ዘንድ እንደተወደደ የኖረው ቴዲ የፊታችን ቅዳሜ ጸሎተ ፍትሃቱ እና የቀብር ስነ ሥርዓቱ በሜሪላንድ ስለሚፈጸም አድናቂዎቹ በብዛት ወጥተው እንዲሸኙት ቤተሰቦቹ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የጸሎትና ፍትሃቱ የሚደረገው ቅዳሜ ከጠዋቱ 9:30 በር ዕሰ አድባራት ደብረሰላም ቅድስት ማርያም ቤ/ክ ሲሆን አድራሻውም የሚከተለው ነው።
Re’ese Adbarat Debre Selam Kidest Mariam
The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church
1350 Buchanan St. NW, Washington, DC 20011
ከዚያም የቀብር ስነሥርዓቱ በThe Gate of Heaven Cemetery 13801 Georgia Ave. Silver Spring, MD 20906 ይፈጸማል።
ቴዲን ለመሸኘት የወጣው ፕሮግራም የሚከተለው ነው፦
Saturday, December 28, 2013
5:15 AM
Teddy Mitiku’s Hearse Arrives at Re’ese Adbarat Debre Selam Kidest Mariam The Ethiopian Orthodox Tewahedo Church. The church is located on 1350 Buchanan St. NW, Washington, DC 20011.
6:00 AM
The procession of Teddy Mitiku’s casket (carried by six Ethiopian Artists) and family into the church will take place from the entrance on Buchanan Street.
6:00 AM – 9:15 AM
Regular church service will be conducted
9:30 AM – 10:45 AM
Wake ceremony
10:45 AM – 11:15 AM
Memory sharing from family and friends in attendance.
11:15 AM – 11:45 AM
Various Ethiopian artists honor Teddy Mitiku
11:45 AM – 12:00 PM
Preparation to commence procession. Teddy Mitiku’s final resting place will be at The Gate of Heaven Cemetery at 13801 Georgia Ave. Silver Spring, MD 20906
12:05 PM
The Procession will start from the intersection of 16 Street and Buchanan Street, the Procession will turn right onto 16th St
The Procession enters next roundabout and take the 3rd exit onto 16th St/MD-390 N (Crossing into Maryland)
The Procession then turn right onto Georgia Ave and arrives its destination at the Gate of Heaven Cemetery on the right.
Attention: Maryland and the District of Columbia law require that all drivers who participate in a procession must turn both their headlight and hazard lights
1:30 P.M.
Once Teddy Mitiku’s casket arrives at the Gate of Heaven Cemetery, burial ceremony begins.
After we finally lay to rest Teddy Mituku, Funereal Reception takes place at The Blair Apartment -East (next to Giant) 1220 East-west Hwy, Room # 119 (Hospitality Suite), Silver Spring, MD 20910
Place of Mourning until Sunday, December 29, 2013:
The Blair Apartment (East)
1220 East-west Hwy,
Room #119 (hospitality suite)
Silver Spring, MD 20910
የዘፋኞቻችን ሞራልና ስብእና
ከጥበቡ ተቀኘ
የሃገራችንን የሙዚቃ ስራ ድሮ በሽክላ ኋላ ላይ በካሴት አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሲዲ ታትሞ ገበያ ላይ ሲቀርብ እንገዛና ከማዳመጥና ከማጣጣም አልፈን እንደ ቅርስ በየቤታችን የምንወዳቸውን ዘፋኞች ስራ እናስቀምጥ ነበር:: ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የለመድናቸው የሙዚቃ ቤት ስሞችም ነበሩን ታንጎ ፣ አምባሰል ፣ ሶልኩኩ ፣ ኤሌክትራ ፣ ዜድ… አድራሻችን ከመርካቶ ዝቅ ብሎ፣ ከአውቶቡስ ተራ አጠገብ ፣ አንዋር መስጊድ ፊት ለፊት… ግጥም ይልማ ገብረአብ ፣ ዜማ አበበ መለሰ ፣ ከመድረክ የቀረጸው ከድር ጭቅሳ… የሚሉ ጽሁፎች በየካሴትና ሲዲው ላይ ይታይ እንደነበር ካስታወስኩኝ በኋላ ወደ ዛሬ ዋናው ጉዳዬ እገባለሁ::
ኣሁን በተለይ ያለፉትን ሶስትና አራት አመታት ትላልቅ የማስታወቅያ ባነሮች ላይ የዘፋኙ ፎቶ አጠገብ በጣም በትልቁ ሜታ ቢራ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ፣ በደሌ ቢራ፣ ባቲ ቢራ፣ ሐረር ቢራ… የሚል ማስታወቅያ ማየት የተለመደ ነገር ሆኗል::በጣም የሚገርመው ደግሞ ዘፈኖቹን ልንሰማ ሲዲውን ስንገዛው ከሲዲው ጀርባ ይሄንኑ የቢራ ማስታወቅያ ቤታችን ይዘነው እንመጣለን:: እኔ ይሄንን ካየሁ በኋላ ለልጆቼማ ኑ በቢራ ተደሰቱ የሚል ማስታወቅያ ያለበት ሲዲ ይዤ ላለመግባት ወስኜ መግዛቱንም ትቼዋለሁ:: ሙዚቃው በሙዚቃ ቤት ብቻ ሳይሆን በቢራ ፋብሪካዎች ስፖንሰርነት እየወጣ እንደሆነም በሰፊው ማየት ይቻላል:: ለመሆኑ ሙዚቃው ካለ ቢራ ማስታወቅያ መሰራት አይችልም? ዘፋኞቹስ ለልጆች እና ለሚያድጉ ወጣት ጎረምሶች የወደፊት እጣ እንዳይናጋ ወይ እንዳይበላሽ በመቆርቆር ይሄ የሚያስነውር አካሄድ አይሆነንም ፣ አይበጀንም አይሉም እንዴ? ነፍሱን ይማርና ተፈራ ካሳ ለህዝብ ትምህርቱን በዘፈን እንዲ ነግሮን አልፏል:
በመጠጥ ደስታ ይገኛል ብላችሁ
መጠን አትለፉ ትቃጠላላችሁ
ለነገሩ ቴዲ አፍሮ ወዶ ከፈረመና ከሰራ በኋላ እኔ አልፈልግም ፣ ይሄንን ጉዳይ እቃወማለሁ ፣ እንደውም እከሳለሁ ብሎ ቡራ ከረዩ አብዝቶ እንደነበር ይታወቃል ግን የፈጠረው ምንም ነገር እንደሌለ መገንዘብ ችያለሁ:: ይልቁንስ አሁን ከቅርብ ቀን በፊት ልጆች የኔን ፎቶ ከቢራ ጋር እንዲያዩት አልፈልግም ፣ ለወጣቶች ጥሩ አርአያ መሆን እፈልጋለሁ ሲል የነበረው እራሱ ቴዲ ለቢራ ፋብሪካ ፈረመ የሚል ዜና አንብቤ ወይ ስብ እና እያልኩ ነበር:: ዘሪቱ ከበደ በዚህ ከቢራ ፋብሪካ ስፖንሰርነት ጋር በተያያዘ ጉዳይ በጣም ጠንካራና የምትመሰገን ሴት ዘፋኝ እንደሆነች አስመስክራለች::
ግን ይሄ ሁሉ የሞራል ድቀትና አደገኛ ግድየሌሽነት በሃገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ በተለይ በዘፋኞቻችን ላይ እንዴት ሊመጣ ቻለ? ኪነጥበባውያንስ ነፍሳቸው ምን ያህል ብትደነድን ነው ይሄንን ኑ በቢራ ተደሰቱ የሚል መአት ሲዲያቸው ላይ ለጥፈው ግዙን የሚሉት? መጠጥን ማስተዋወቅ ከስነ ጥበብና ትውልድን ከማስተማር ጋር ምን አያያዘው? ከሰፊው ህዝብ በፊት እንዲህ አይነት አካሄድ ለአገር ጥሩ እንዳልሆነ የሙዚቃ ሰዎቻችን እንዴት ማወቅ ተሳናቸው?
አቤት ጥያቄዎቼ ብዛታቸው በዚህ ጉዳይ ላይ ትንሽ ነገር መጻፍ አስቤያለሁ ያልኩት ወዳጄ ‘አንተ እኮ በጣም የምትገርም እውነቱን አልቀበልም ብለህ ዝም ብለህ የምትንገላወድ ምስኪን ፍጡር ነህ:: እዚ አገር ዘፋኙ እንዴት ሞራሉና ስብእናው ወርደ ትለኛለህ? የዚ አገር ዘፋኝ አይደለም እንዴ እየዘመረ አምባገነኑን መለስ ዜናዊን ነቢይ ነው ሲለን የነበረው? የዚ አገር ዘፋኝ አይደል እንዴ የማያቀውን ታሪክ አዋቂ ነኝ እያለ የሚዘላብደው? የዚ አገር ዘፋኝ አይደል እንዴ በመሃይምነቱ ዘሎ ፓርቲዎች አስታርቃለሁ የሚለን? የዚ አገር ዘፋኝ ሲጀመር ምን አይነት ሞራል እና ስብእና አለው እና ነው አሁን ሞራሉ ወደቀ ምናምን እያልክ የምትቀባጥረው? የበውቀቱ ስዩም እና የሌሎች ታላላቅ ደራስያን መጽሃፍ ምረቃ ላይ የማይገኙ ዘፋኞችና የኪነጥበብ ሰዎች አይደሉም እንዴ በሚኒስትሩ በረከት ስምኦን መጽሃፍ ምረቃ ምሽት እንግዳ ከበር ከመቀበል አንስቶ እስከ ዝግጅቱን መምራትና ማድመቅ ሲያሽቃብጡ የነበሩት? የዚ አገር ዘፋኝ እና የኪነጥበብ ሰዎች ያለ ምንም እውቀት የሚሰብኩን ሁሉ ስለ አባይ፣ ስለ ህዳሴ፣ ስለ ትራንስፎርሜሽን እና ስላለው የሃገሪቷ እድገት አይደለም እንዴ? የህዝብ መበደል፣ የኑሮ መወደድ፣ የህዝብ በህግ ጉዳይ ያላግባብ መንገላታት መቼ ተሰምቷቸው ያቃል እና ነው ዛሬ ሞራላቸው ወደቀ የምትለኝ? ‘ ብሎ በቁታ እየገነፈለ ተወኝ አለኝ:: ወድያው ደግሞ “ግን ደሞ” ብሎ ጀመረ “ግን ደሞ አንዳንድ በጣት የሚቆጠሩ ነፍሳቸውን ጊዜያቸውንና ሁለመናቸውን ለኪነ ጥበብ የሰዉ እንዳሉም የማላቅ አልምሰልህ እኔ እነዛን ጥቂቶችን እጅግ በጣም አከብራቸዋለሁ” ብሎኝ ሌላ ጨዋታ አውግተን ተለያየን:: እኔም ብዙ ማሰብ ጀምሬ አውጥቼና አውርጄ…..
እውነትም ከዘፋኞች ሞራል ዝቅጠት ጀርባ የሚታይ ወይ አላዋቂነት ፣ ወይ ጥቅም እስካገኘሁ ምናገባኝ ማለት ፣ ወይ ደግሞ ትልቅ ድንቁርና አለ በሚለው ተስማማሁ:: እንደዚህ ያልኩበት ምክንያት ምንድነው? ነጥቦቼንም በዚህ መልኩ አስቀመጥኩ
- ኮፒ ራይቱ አላሰራ አለን፣ ተቸግረናል፣ በጣም ተቸገርን፣ እየተዘረፍን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መፍትሄ ይፈልግልን በማለት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር ጋር ስብሰባ ሲያደርጉ አምሽተው ተቸግረናል እየተዘረፍን ነው ባሉበት አፋቸው ዝግጅቱ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በስጦታ መልክ የወርቅ ብእር እንደሰጡዋቸው ሳስታውስ፣
- ባደባባይ ሰው እንዲገደል ያደረገ መሪ ሲሞት ከተከበረው ብሄራዊ ቲያትር እስከ ቤተመንግስት ምነው ተለየኸን መስከረም ሳይጠባ የሚለውን ዘፈን እየዘፈኑ ነጠላ አደግድገው (ለቅርብ ዘመዶቻቸው የማያደርጉትን) እያለቀሱ መሄዳቸውን ሳስብ፣
- ከእንግዲህ ሻማ ለልደት ነው እያሉ የማያቁትን የኢንጅነሪንግ ሙያ እየተጨማለቁበት ሳይ ከአንድ ግድብ ምረቃ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ ችግር እንደማይኖር ማብራሪያና ዲስኩር የሰጡትን ሳስበው፣
- ታላቅ የኦርቶዶክስ አማኝ ነኝ በማለት የማያቁትን የቤተ ክርስቲያንን ህግና ቀኖና ባልተከተለ መልኩ በድፍረት መዝሙር ዘምረው ማሪያም ማርያም የሚል ነጠላ ዜማ በለቀቁ ማግስት ዳንኪራና አስረሽ ምቺው ማድረጋቸውን ሳስበው፣
- እንኳን ሌላ ሰው ያላግባብ ታሰረ ሊሉ እራሳቸው ያላግባብ ታስረው ያለ ወንጀሌ ነው የታሰርኩት በጣም ተበድያለሁ ለማለት ድፍረትና ብቃት የሌላቸው እንደሆኑ ሳስበው፣
- ዘፈን እምቢ ሲላቸውና ከገበያ ሲወጡ በመሃይምነት እንዲሁም በከባድ ድፍረት ጌታ ጠርቶኝ ነው ብለው ለሃይማኖትም ለህዝብም ክብር ሳይሰጡ የስብከትንና የዝማሬን ተአምራዊ ጥበብ ምንም ሳይማሩ የፕሮተስታንት ዘማሪ ሲሆኑ ሳይ፣
- እከሌ ሮጦ ሲያሸንፍ ሲዘፍኑ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሲዘፍኑ ለአባይ ግድብ ሲዘፍኑ ሳውዲ ለሞቱት ሲዘፍኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሞቱ ሲዘፍኑ ጥበብን ከውስጣዊ ስሜታቸው ሳይሆን ከጊዜውና ከሰሞኑ ወሬ ጋር ሊወስዷት ሲፈልጉ ዜና የሚመስል ዘፈን አቅርበው ስሰማ፣
- በመሃይምነትና በድንቁርና ታውረው ያልሰሩበትንና ያልለፉበትን የሌላ ሰው ዘፈንና ዜማ ከአገር ውስጥም ከውጭም ወስደው በማስረጃ ሲቀርብባቸው ይቅርታ በስህተት ባለማወቅ ነው እንደማለት ይህንን ፕሮግራም ይሰራ የነበረውን ለምን ይዋሻል ራዲዮ እስከማዘጋት መድረሳቸውን ስሰማና ሳይ፣
እነዚህንና ሌሎች ብዙ ያልዘረዘርኳቸውን ነጥቦች ካየን የኢትዮጵያ ኪነጥበብ በተለይ ሙዚቃ ከባለሙያ የእውቀት ማነስ ችግር የተነሳ ወርዶ በዚህ ባለንበት ዘመን እንኳን ራሱን መደገፍ እንዳቃተው ግልጽ ይሆንልናል:: ግን ዘፋኞቻችንና የኪነጥበብ ሰዎች ይህንን ችግር በጣም በሰለጠነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ እራሳቸውን አዋርደው ያለቢራ ፋብሪካዎች ማስታወቅያ ካሴታቸውን ማሳተም ከማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን በግልጽ የተናገሩ አይመስለኝም:: እንደውም ጥሩ ነገር በመስራት ያለብን ችግር ሊቀረፍ ይችላል ብለው ከማሰብ ከባለስልጣን ጋር፣ ከካድሬ ጋር፣ ከባለሃብት ጋር በመሞዳሞድ ሊያልፉ ያሰቡ ይመስለኛል:: ይህ ደግሞ በጣም አስነዋሪና ከኪነጥበብ ሰው ሳይሆን ከአየር በአየር ነጋዴ የሚመነጭ ተራ ውርደትና ስግብግብነት ነው::
ጊዜውን በውል ባላስታውሰውም በዚህ ሶስት አራት አመት ውስጥ የኢህአዴግ ባለስልጣኖች ያሳተሙትን የህዳሴ ዋዜማ የተሰኝውን DVD አባዝቶ በህገ ወጥ መንገድ ሲሽጥ የተያዘ ሰው 15 አመት እንደተፈረደበት ሰምተን ማንም እየተነሳ የድምጻዊያኖቻችንን ካሴት እና ሲዲ ለዘመናት በህገ ወጥ መንገድ ሲሸጥ ምንም አለመደረጉ ከዘፋኞቻችን በላይ እኔን ለምን እንዳስቆጨኝ አላውቅም::
የራሳቸውን መብት ሳያስጠብቁና ኮፒ ራይታቸውን ታግለው ሳያስከብሩ ዘፋኞቻችን ለኛና ለመጪው ትውልድ ያስባሉ ማለት ዘበት ነው ግን ቢሆንም ካለባቸው ችግር ለመውጣት የጀመሩት መንገድ ትክክል እንዳልሆነና ነገ ሁላችንም በልጆቻችን ፊት ሊያሳቅቀን የሚችል የሞራል ዝቅጠት መሆኑን ሳልጠቁም አላልፍም:: አርአያ የሚለው ቃል ለነገ ከማሰብና ለመጪው ትውልድ ከመጠንቀቅ ጋር አብሮ የሚሄድ ትርጉም ያለው ትልቅ ቃል ነው:: ይሄ ቃል ተረስቶ ወይ ደግሞ የሰው ስም ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ካለኝ ስጋት ይቺን ጽፌያለሁ ደህና ሁኑ::