(ፋርማሲስት፣ ተዋናይ፣ የማስታወቂያ ባለሙያና የፊልም ፕሮዲዩሰር)
ገመና በተሰኘውና ብዙዎች በፍቅር ይከታተሉት በነበረው የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ድንቅ የትወና ችሎታውን ያዩ በርካቶች አጨብጭበው መስክረውለታል፡፡ የቤታቸውን ሠራተኛ አፍቅሮ የሚንከራተተውን ሚኪ የተባለውን ገፀ ባህሪይ መስሎ ሳይሆን ሆኖ መተወኑ በወቅቱ ካይን ያውጣው አሰኝቶት ነበር፡፡ በዚህ ድራማ ላይ ባሳየው ምርጥ የትወና ብቃት ድራማውንና እሱን ነጥሎ ማየት እስከሚያቅት ድረስ የበርካታ ተመልካቾችን ስሜት ለመግዛት የቻለ ወጣት ተወናይ ነው፡፡ በድራማው መጠናቀቂያ ወቅት በተመልካች ምርጫ አሸናፊ የሆኑ ተዋንያንን ለመሸለም በተዘጋጀው የድራማው ምርጥ የወንድ ተዋናይ ተብሎ ለሽልማት በቅቷል፡፡ ከትወና ሙያ ጋር ከተዋወቀበት 522 በተሰኘው ፊልም በኋላም ለአባቷ ጃንደረባውና ትዝታህ የተባሉትን ፊልሞች በዋና እና በረዳት ተዋንያንነት ሰርቶባቸዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ‹‹ፍቅሬን ያያችሁ›› የተባለ አዲስ የፍቅር ፊልም ፕሮዲዩስ አድርጎ ይዞልን ብቅ ብሏል፡፡ በዚህ ፊልም ላይ ከፕሮዲዩሰርነቱ ሌላ በዋና ገፀ ባህሪይነት ተውኖበት ድንቅ የትወና ችሎታውን አሳይቶናል፡፡ ወጣቱን ፋርማሲስት፣ ተዋናይ፣ የማስታወቂያ ባለሙያና የፊልም ፕሮዲዩሰር መሐመድ ሚፍታህን አግኝተን ጥቂት አውግተናል፡፡
የመጀመሪያ ፊልምህን የሰራኸው በአጋጣሚ ነው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ስለዛ አጋጣሚ አጫውተኝ?
ፊልም መስራት ከልጅነቴ ጀምሮ በጣም እመኘው የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ እናም ፊልም ይሰራሉ የተባሉ ሰዎች ጋር ሁሉ ፎቶራፌንና አድራሻዬን እየበተንኩ ባለበት አንድ ወቅት ላይ ከጓደኞቼ ጋር ሻይ ልንጠጣ አንድ ካፌ ውስጥ ገባን፡፡ ወደ ካፌው ስንገባ ቴዎድሮስ ተስፋዬ ከሌሎች የፊልም ባለሙያዎች ጋር ቁጭ ብሎ ስገባ በጣም ያየኝ ነበር፡፡ ጓደኞቼ እሱ እኮ ብዙ ፊልሞችን ይሰራል ለምን አታናግረውም አሉኝ፡፡ ለማናገር ድፍረት ስላጣሁ በወረቀት ፅፌ ልሰጠው አሰብኩና እየፃፍኩ እያለሁ እነሱ ተነስተው ወጡ፡፡ ተከትያቸው ወጣሁና ቴዎድሮስን አስቁሜ ተዋወኩት፡፡ ፊልም መስራት እንደምፈልግም ነገርኩት፡፡ እኛም እኮ እያየንህ ነበር፡፡ እዚህ ሀገር የምትኖር ስላልመሰለን ነው እንጂ በልባችን እያጨንህ ነበር አለኝ፡፡ አመስግኜ በቀጣዩ ቀን 522 የተባለውን ፊልም ስራ ጀመርኩ ማለት ነው፡፡
522 እና ለአባቷ የተባሉት ፊልሞች በአንድ ወቅት ላይ የተሰሩ ፊልሞች ናቸው፡፡ እንደውም ለአባቷ በተባለው ፊልም ላይ ዕድሜው ለካራክተሩ አይመጥንም ተብለህ ፂምህን ለማሳደግና ትልቅ ሰው ለመምሰል መከራህን ስታይ ነበር…?
ልክ ነው፡፡ እኔ ለራሴ በዛን ወቅት ፊልም የመስራት ፍላጎቴ እጅግ ያየለበትና ለመስራት በጣም እፈልግ የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ደግሞ ይህ ለአባቷ የተባለው ፊልም ድርሰቱ የአዶኒስ ነበር፡፡ እስቲ አስቢው የአዶኒስ ድርሰት የሆነን ምርጥ ስራ ዕድሜ አይመጥንም ተብለሽ እንዳትሰሪ ስትከለከይ…? እናም ፂሜን ለማሳደግ ጉንጬን ሁሉ ፍቄው ትልቅ ሰው ለመመስል በአለባበሴ ሁሉ በጣም ጥረት አደርግ ነበር፡፡ ካራክተሩን ለመስራት ከተመረጡት ልጆች ጋር ወደ አዱኒስ ጋር ሄድንና ተፈተንን፡፡ አዱኒስ እኔን መረጠኝና መስራት ጀመርኩ ማለት ነው፡፡ ይህንን ፊልም ስንሰራ ጋሽ ሃይማኖት ዓለሙ ለ3 ወራት ስልጠና ሰጥቶን ነበረ፡፡ ጋሽ ሃይማኖት ጥሩ ነገር አለህ ጠብቀው፡፡ ከሰራህ ትልቅ ቦታ ትደርሳለህ ትልቅ ተስፋ አለህ ሲል አበረታቶኝ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጋሽ ሃይማኖትንና አዱኒስን በጣም ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡
አንድ ሰሞን ደግሞ ዕለተ ሰንበትን የብዙ ሚሊዮኖችን ዓይንና ቀልብ ስበህ በቴሌቪዥን መስኮት ላይ እንዲያፈጡ ማድረግ ችለህ ነበር፡፡ እስቲ ስለገመና ድራማ አጫውተኝ፡፡ ለድራማው እንዴት ተመረጥክ?
ወደ ገመና ድራማ የገባሁት እንደፊልሙ ሁሉ በአጋጣሚ ነበር፤ እኔ ለገመና ድራማ ካስት ከመደረጌ በፊት የድራማው ሰሪዎች ለካራክተሩ ብዙ ተዋናይ ሲያዩና ሲመርጡ ቆይተው ነበር፡፡ እኔ ጋር ተደውሎ ከገመና ድራማ ቢሮ ነው ስባል በአጋጣሚ እኔ ከጓደኞቼ ጋር ወደ ክፍለ ሀገር ለመዝናናት እየሄድን ነበር፡፡ ከዛ በፊት በቴሌቪዥን የሚታይ ረዥም ድራማ እምብዛም ባለመኖሩና ብዙም ያልተለመደ ነገር ስለሆነ ሁኔታው ብዙም አላጓጓኝም፡፡ ግን አንዳንዴ ደግሞ ደመነፍስሽ የሚግርሽ ነገር አለ፡፡ እስቲ ሄጄ ልሞክረው አልኩና ጓደኞቼን እኔ ሰዎቹን ካነጋገርኳቸው በኋላ እንደምከተላቸው ነግሬ ተሰናበትኳቸውና ወደ ገመና ቢሮ ሄድኩኝ፡፡ ገና ወደ ቢሮው ስገባ በጣም የሚያስደነግጥና የሚያስገርም ነገር አየሁ፡፡ ያም አዱኒስን ለማየት መቻሌ ነበረ፡፡ እሱም እንዳየኝ ነው ያወቀኝ፡፡ በቀድሞ ካራክተሬ ስም ናቲ ሲል ጠራኝ፡፡ ለካ ማደግም መርዘምም ይቻላል ማለት ነው አለኝ፡፡ ከዛም ስክሪፕቱን ሰጠኝና ወጣሁ፤ ስራውን ይችለዋል ተብሎ እምነት ስለተጣለብኝ በደንብ ለማጥናትና ጥሩ አድርጌ ለመተወን ጥረት ማድረጌን ቀጠልኩ፡፡ ካራክተሩ በምን ህይወት ውስጥ ነው ያለፈው? ችግሮች ሲያጋጥሙትስ እንዴት ነው የሚያልፋቸው? የሚሉትን ጉዳዮች ለማወቅና ካራክተሩን በደንብ ለማጥናት ሞከርኩ፡፡ ካራክተሩን የምገልፅበትን መንገድ ማሰብ ስራዬ አደረኩት፡፡ ሚኪ አኗኗር፣ አስተዳደግና አመለካከቱ ሁሉ በደንብ እንዲገባኝ አደረኩ፡፡ ሚኪ ያፈቀረው የቤት ሠራተኛቸውን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፍቅሩን በቀላሉ ለመግለፅ እንዳይችል እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ እናም ሚኪ ፍቅሩን ለመግለፅ የሚጠቀምበት መንገድ ለየት ያለ መሆን መቻል አለበት፡፡ ፈታኝ ነገር ነበር፡፡ ገና እኔ እንደምሰራው ተወስኖ ተሰጠኝ፡፡ በፊት ሁሉ ኦዲሽን ላይ እየሰራሁ ሳይታወቀኝ እምባዬ ሁሉ ዱብዱብ ይል ነበር፡፡ የልጁ ጉዳት ገባኝ፡፡ እናም ፈተና ላይ ስራዬን ሲያየው አዱኒስ በቃ አንተ ነህ ይህንን ካራክተር የምትሰራው፡፡ ስለዚህም ተዘጋጅ አለኝ፡፡ ማመን ሁሉ አልቻልኩም፡፡ በጣም ደስ አለኝ፡፡ አዱኒስን በሚያህል ትልቅ ሰው መመረጥና ከእሱ ጋር መስራት ለእኔ በጣም ትልቅ ነገር ነው፡፡ በወቅቱ የተሰማኝን ደስታ መግለፅ አስቸጋሪ ነበር፡፡
የገመናው ሚኪ ላንተ ምን አይነት ስሜት ነው የሰጠህ? ጥሩ ተውኜዋለሁ ብለህስ ታስባለህ?
ሚኪ ፈታኝ ካራክተር ነው፡፡ እኔ በሚኪ ታሪክ ውስጥ ያለፍኩ ሰው አይደለሁም፡፡ የሚኪን ስሜት መግለፁ ወይንም እንደሚኪ ሆኖ ህመሙን መታመሙ ለእኔ ከባድ ነገር ነው፡፡ ግን ደግሞ መሆን ነበረበት፡፡ የሚኪ ስቃይ ሊሰማኝ፤ ህመሙ ሊያመኝ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ከአንድ ተዋናይ የሚጠበቅ ጉዳይ መሆኑን አምናለሁ እና ካራክተሩን በደንብ ለመላበስ ጥረት አደረኩኝ፡፡ ያው እንግዲህ እንዳየሽው በተወሰነ ደረጃ ተሳክቶልኝ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ገመና ድራማ ለእኔ በጣም ስሜት ሰጥቶኝ ወድጄው የሰራሁት ድራማ ነው፡፡ መሆን የምመኘውን አይነት ካራክተር ነበር የሰራሁት፡፡
መሆን የምመኘው ስትል?
የሚኪ አይነት ፍቅር እንዲኖረኝ እንደ ሚኪ ማፍቀር እንድችል እመኛለሁ፡፡ ቀዝቀዝና ረጋ ያለ ባህሪይ ያለው፣ አስተዋይና በትምህርቱ ጎበዝ ነው ሚኪ፡፡ ይህ ባህሪይ የእኔም እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
አንተ በባህሪይህ ምን አይነት ሰው ነህ? አፍቃሪ ነህ?
እኔ ለፍቅር ልዩ ቦታ አለኝ፡፡ ስስ ልብ ነው ያለኝ፡፡ ለፍቅር ቶሎ የሚሸነፍና በቀላሉ የሚጎዳ አይነት ማለት ነው፡፡ እርግጠኛ ካልሆንኩኝ በስተቀር ነገሮች ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ የሚኪን ካራክተር የወደድኩትም ባመነበት ነገር ላይ የሚቻለውን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍሏል፡፡ ሲያፈቅር ያፈቀረው ከልቡ ነው፡፡ ያን ስሜቱን ስሜቴ አድርጌ ለእሱ የተሰማው እኔንም እንዲሰማኝ ሆኜ መተወን ይገባኝ ነበር፡፡ ለእኔ ፊልም ወይንም ትወና መምሰል ሳይሆን መሆን ነው፡፡ እናም ሚኪን ሆኜ ስሜቱን ስለተጋራሁት መግለፁና ለተመልካች ማሳየቱ ብዙም አላስቸገረኝም፡፡ ድራማውን ከተከታተልሽው አብዛኛውን ጊዜ በንግግር ከምገልፀው ጉዳይ ይልቅ በአስተያየቴና በሁኑታዬ የምገልፀው ጉዳይ ይበዛ ነበር፡፡ ከገመና ድራማ ላይ የማረሳው አንድ ትዕይንት ነበር፡፡ በድራማው ላይ የእኔ ሴት ጓደኛ ከዩኒቨርሲቲ ጠፍቼባት ፈልጋ አግኝታኝ የሆንከውን ነገር ንገረኝ እያለች የምትጠይቀኝ ትዕይንት ነበር፡፡ እሷ ስለእኔ የምታወቀው ጉዳይ የለም፡፡ እኔ ደግሞ በቤት ሠራተኛዋ ፍቅር ተሸንፌያለሁ፡፡ ሁለቱን ስሜቶች ማስተናገድ ነበረብኝ፡፡ ካራክተሩ የሰው ጉዳት የሚሰማው ለሰው አጥብቆ የሚያስብ አይነት ካራክተር ነው፡፡ ልጅቷ ጥሩ ፍቅር እየሰጠችው ነው፡፡ ለእሱ ጥሩ ጓደኛው ናት፡፡ እሱ ደግሞ እዚጋ በሌላ ሴት ፍቅር ተሸንፏል፡፡ እሱ እዛጋ እየሆነ ያለውን ነገር እሷ እዚህ ጋር እየሆነችለት ነው፡፡ ስለዚህ ሁለቱን ነገሮች ማቻቻልና ስሜታቸውን መጠበቅ ነበረበት፡፡ እሱ (ካራክተሩ) የወደዳት ልጅ እምቢታዋን ብትገልፅለት የሚሆነውን ያህል እዚህ ጋር ያለችው ሴትም በእሱ እምቢታ ልትጎዳ ትችላለች፡፡ እንደ ፊልም ሳይሆን እንደ ህይወትም ስታስቢው እውነታው ይኸው ነው፡፡
በድራማው ላይ ያንተ ካራክተር በጣም ተወዳጅ ካራክተር ነበር፡፡ እንደውም በኤስ.ኤም.ኤስ ከፍተኛውን ቁጥር ያገኘኸው አንተ ነበርክ፡፡ በተለይ ደግሞ በርካታ ሴቶች ናቸው ላንተ ድምፃቸውን የሰጡህ…?
ድራማው እየሄደ ባለበት ወቅት ላይ ብዙ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ስሜታቸውን ይገልፁልኝ ነበር፡፡ ጥሩ ስራ ነው፡፡ ደስ ብሎን ነው የምንከታተለው ያሉኝ ነበሩ፡፡ ይህ ለእኔ ትልቅ ነገር ነበር፡፡ ስራዬ ተመልካች ውስጥ ገብቶ መወደድ መቻሉ የሆነ ነገር መፍጠሩ ደስ ይለኛል፡፡ አንዳንዴ እኮ በሆነ ስራ ውስጥ ገብተሽ የለሽም አለሽ… ልትባይ ሁሉ ትችያለሽ፡፡ ይህ ህመም ነው፡፡ መኖርሽና አለመኖርሽ ምንም ልዩነት በማያመጣበት ሁኔታ ውስጥ መሆንሽ ስሜት ይጎዳል፡፡ ሰው አንቺን ሲያይ ደስ ብሎት አክብሮቱንና ፍቅሩን ሲያሳይሽ ትልቅ ነገር እኮ ነው፡፡ ያው የብዙ ሰዎችን ድምፅ ያገኘሁበት ምክንያትም ይኸው ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡
እስቲ ስለ አዲሱ ፊልምህ አጫውተኝ፡፡ አሁን ደግሞ ከተዋናይነት ሌላ በፕሮዲዩሰርነትም ብቅ ብለሃል፡፡ ፍቅሬን ያያችሁ እንዴት ተሰራ? ምን ያህል ገንዘብና ጊዜ ወሰደብህ?
ፍቅሬን ያያችሁ ራሴን የፈተንኩበት ስራ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከሕይወት ጋር እልህ ትጋቢያለሽ፤ እኔ ከሰዎች ጋር ተፎካክሬ አላውቅም፡፡ ሁልጊዜም ፉክክሬ ከራሴ ጋር ነው፡፡ በፊልሜ ተመልካቹ ውስጥ የሆነ ነገር መፍጠር እፈልጋለሁ፡፡ እኔ ዛሬ ላለሁበት ደረጃ እንድደርስ ያደረጉኝ ሰዎች ከእኔ ብዙ ነገር ይጠብቃሉ፡፡ ተመልካቹም ፊልሜን ለማየት ሲገባ ብዙ ነገር መስዋዕት አድርጎ ነው፡፡ ጊዜውን፣ ገንዘቡን ሁሉ፡፡ ስለዚህም ከፊልሙ የሆነ ነገር አግኝቶና ተደስቶ እንዲወጣ ነው ፍላጎቴ፡፡ እናም ያለኝን እውቀት፣ ጊዜና ገንዘብ ሁሉ ሙጥጥ አድርጌ ነው የተጠቀምኩት፡፡ ለዚህም ነው ፊልሙ የተዋጣ ጥሩ ስራ የሆነው፡፡ በገንዘብ ረገድ ምን ያህል ወጣበት ላልሽው ይህንን ያህል ነው ብዬ በቁጥር ለመግለፅ ባልችልም ብዙ በጀት ተመድቦለት የተሰራ ፊልም ነው፡፡ ከጊዜ አንፃር ደግሞ አንድ ዓመት ያህል ፈጅቶብኛል፡፡
ተሳክቶልኛል ወይም የተዋጣ ስራ ነው ብለህ ታስባለህ?
አምናለሁ፡፡ ስኬት ላልሽው ግን ለእኔ ስኬት ማለት ገና ስራውን ስጀምር እዚህ ጋ ብደርስ ብዬ ያሰብኩት ነገር ነበርና እዛ ጋ መድረስ መቻሌ ስኬት ነው፡፡ አንድን ነገር ለመስራት ስትነሺ እወጣዋለሁ ብለሽ ማመን አለብሽ ከጅምሩ አልወጣውም ብለሽ ካሰብሽ ቀሽም ነሽ፡፡ በዚህ ፊልም ላይ ብዙ አዳዲስ ነገሮች አሉት፡፡ እኛነታችንን የሚያሳዩ ነገሮችንም ለማሳየት ሞክረናል እንግዲህ ቀሪው ጉዳይ የተመልካች ነው፡፡
በፊልም ላይ ፕሮዲዩሰሩም ዋና ገፀባህሪውም አንተው ሆነህ ነው የሰራኸው፡፡ ይሄ ነገር አያስቸግርም ነበር፡፡ ፕሮዲዩሰርነቱንና ተዋናይነቱን አብሮ ማስኬዱ አላስቸገርህም?
ከባድ ነው፡፡ እውነት ለመናገር በጣም ከባድ ነው፡፡ በፕሮዲዩሰርነቴ የሚጠበቁብኝ ኃላፊነቶች አሉ፡፡ እሱን በአግባቡ መወጣት መቻል አለብኝ፡፡ ተመልካቹ ካንቺ ምንም አይነት ምክንያት መስማት አይፈልግም፡፡ የተዋጣ ስራ ማየት ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ልክ ነው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን በቀረፃ ወቅት ከካራክተሬ ውጪ ስለምንም ነገር ማሰብ አልፈልግም፡፡ ሁሉም ነገር የራሱ ሰው እንዲኖረው አድርጌ አክቲንጌ ላይ ብቻ ነው የማተኩር የነበረው በእርግጥ ተዋናይ ብቻ ሆነሽ ስትሰሪ የበለጠ ነፃነቱ ጥሩ ነው፡፡ ስለሌላው ጉዳይ የሚጨነቀው ሌላ ሰው ነው፡፡ ፕሮዲዩሰርም ስትሆኚ ግን ጭንቀትሽ ይበዛል፡፡ በሁሉም ትዕይንት ውስጥ ያንቺ ሀሳብና ስራ ሊኖር ግድ ነው፡፡ ተዋንያኑን ማስተባበር፣ የቀረፃ ቦታዎችን ምቹ ማድረግ፣ ቀረፃሽን ሳትጨርሺ ውጪ እንዳትባይ ስጋቱ፣ ሁሉም ነገር ከባድ ነው፡፡ ግን ደግሞ አክተር ሆነሽ ፕሮዲዩሰር ስትሆኚም የራሱ የሆነ ጥቅም አለው፡፡ ተዋናዩ ፊልሙ አሪፍ እንዲሆን የሚያስፈልገውን ነገር ያውቀዋል፡፡ እሱን ለማሟላት ደግሞ የማንንም በጎ ፈቃድ አይጠይቅም፡፡ ራሱ አስፈላጊ ነገር ሁሉ ያደርጋል፡፡ ይህ አሪፍ ነገር ነው፡፡
በዚህ ፊልም ስራ ወቅት በጣም ከስተህና ኪሎህን ቀንሰህ ነበር፡፡ በጤና ነው?
አዎ! ወደ 10 ኪሎ አካባቢ ቀንሼ ነበር፡፡ የቀነስኩት ግን መቀነስ ፈልጌ አልነበረም፡፡ እኔ የተጫወትኩት ካራክተር በጣም ያሳዝን ነበር፡፡ እንደ እሱ ሰው ሳያውቃቸውና ሳይረዳቸው ኖረው የሚያልፉ ሰዎች ሁሉ አሉ፡፡ እናም ለካራክተሩ ታማኝ መሆን ፈለኩ፡፡ የእሱን ኑሮ መኖር፣ እንደ እሱ ማሰብ ፈለኩ፡፡ በዚህ ጥረቴ ውስጥም አመጋገቡን እንደ ባህሪይ ውስጤ አስገብቼው ነበር፡፡ ካራክተሩ ንፁህ ነገር ይፈልጋል፣ ጥቂት ይመገባል፣ በስራው ላይ መቀለስ አይፈልግም፡፡ ለስራው ያለው ክብር የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም ራሱን ደብቆ የሚኖረው እዛው ስራው ውስጥ ነው፡፡ ማንም በዚህ ሰርክል ውስጥ ገብቶ እንዲረብሸው አይፈልግም፡፡ ይህ ነገሩ በጣም መሰጠኝ፡፡ እናም እስኪ ልኑረው ብዬ አሰብኩ፡፡ በዛ ሙከራ ውስጥ ነው ኪሎዬንም የቀነስኩት፡፡
በዚህ ፊልም ስራ ወቅት አስቸጋሪ ነበር የምትለው ጊዜ ነበር?
አዎን! 3 አስቸጋሪ ጊዜያቶችን አሳልፌ አለሁ፡፡ የመጀመሪያው ገና ስክሪፕት እየመረጥኩ ባለበት ጊዜ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ፕሮዳክሽን ከተጀመረ በኋላ ይህንን ነገር እወጣው ይሆን የሚለው ነገር በጣም ያስጨንቅ ነበር፡፡ ፊልሙ አልቆ ወደ ተመልካች ሲመጣ ደግሞ ሌላ ጭንቀት ነው፡፡
እንደተዋናይ ለዚህ ፊልም ትወና ምን ያህል ተከፈለህ? ወይንም ምን ያህል ሊከፈለኝ ይገባል ብለህ ታስባለህ?
እንደተዋናይ በዚህ ፊልም እስከ 300 ሺ ብር ድረስ ክፍያ ይገባኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ፊልም ስራ ምክንያት የመጡልኝን ሌሎች በርካታ ፊልሞች መልሻለሁ፡፡ ፊልሙ ቢዚ አድርጎኝ ነበር፡፡
አብረህ ማስኬድ አልቻልክም ነበር?
ካራክተሩ በጣም ይፈልገኝ ነበር፡፡ ከእኔ ጋር ረዥም ጊዜ መቆየት ነበረበት፡፡ ካራክተሩ ቅድም እንዳልኩሽ ከእኔ የተለየ ሰው ነው፡፡ በአስተሳሰብ፣ በአኗኗር፣ በዕድሜ፣ በአስተዳደግ፣ ባለፈበት የህይወት ተሞክሮ ሁሉ ከእኔ ይለያል፡፡ እናም ካራክተሩ ውስጥ ገብቶ መጥፋት ያስፈልገኝ ነበር፡፡ እዚህ ጋ ሌላ እዚያ ጋ ደግሞ ሌላ ሰው ሆነሽ የምትሰሪው አይነት ካራክተር አልነበረም፡፡ ሌሎች ስራዎችን መስራት አልቻልኩም፡፡
ወደ ሞዴልነትና የማስታወቂያ ስራ ባለሙያነትህ ደግሞ እንመለስ፡፡ በሞዴልነት በቋሚነት እየሰራህ ነው? ከስማደል ሞባይልስ ጋር የገባኸው የማስታወቂያ ውል እንዴት ነው? በቋሚነት…? ለአገር ውስጥ ብቻ?… እስቲ ስለሱ ደግሞ እናውራ?
በማስታወቂያ ስራ ከአስር በላይ ማስታወቂያዎች ላይ ሰርቻለሁ፡፡ ሙያውን እወደዋለሁ፡፡ ሙያሽን ወደሽ የምትሰሪው ከሆነ ታከብሪዋለሽ ካከበርሽው ደግሞ የሚፈልገውን ሁሉ ለመስጠት ጥረት ታደርጊያለሽ፡፡ በማስታወቂያ ስራዎቼ ላይ የምተገብረውም ይህንኑ ነው፡፡ ከስማደል ሞባይል ሰዎች ጋር የተገናኘሁትና ማስታወቂያዎችን መስራት የጀመርኩት በአጋጣሚ ነው፡፡ የሆነ ቦታ እራት እየበላን ሰዎች እየመጡ ከእኔ ጋር ፎቶ ሲነሱ አዩና ለማስታወቂያ ስራ እንደሚፈልጉኝ ነገሩኝ፡፡ በቃ በዚሁ መንገድ ነው የተጀመረው፡፡ አሁን ለጊዜው እየሰራን ያለነው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ወደፊት ግን ወደሌሎች ሀገራትም ለመሄድ ሀሳብ አላቸው፡፡ በሞዴልነት ሞያ ትላልቅ መድረኮች ላይ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም ሰርቻለሁ፡፡ ሸራተን፣ ሚሌኒየም አዳራሽና ሒልተን ሆቴል በሀገር ውስጥ ከሰራሁባቸው ትላልቅ መድረኮች መሀል ሲጠቀሱ ከሀገር ውጪ በአሜሪካ፣ ሜሪላንድ ውስጥም ሰርቻለሁ፡፡ አሁን በቋሚነት ከዮሐንስ ጥበብ ጋር በሞዴልነት እየሰራሁ ነው፡፡
በበጎ ፈቃድ ስራዎች ወይንም በህፃናትና አረጋውያን መረጃ ድርጅቶች ውስጥ በመግባት እንቅስቃሴ ታደርጋለህ ይባላል፡፡ ምን ያህል እውነት ነው?
የበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ መሳተፍ እወዳለሁ፡፡ ከሜሪ ጆይ የአረጋውያን እና የህፃናት መረጃ ድርጅት፣ ከመሰረት በጎ አድራጎት ጋር እሰራለሁ፡፡ አሁን ፊልሜን ሳስመርቅም አቅሜ የፈቀደውን ለእነዚህ ድርጅቶች ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ ይህንን ተግባር ወደፊትም አጠናክሬ እንደምቀጥልበት አምናለሁ፡፡
እንደው ያ የፋርማሲስትነት ሞያህ ቀረ ማለት ነው? ውሃ በላው?
አልቀረም፡፡ ወደፊት በሙያዬ አንድ ቋሚ የሆነ ነገር የመክፈት ሀሳብ አለኝ፡፡ እንደ ፋርማሲ ያለ ማለቴ ነው በትምህርቴም የተሻለ ደረጃ ላይ የመድረሱ ዕቅድ አለኝ፡፡
ዕቅዶችህ እንዲሳኩና የተሻሉ ስራዎችህን እንድናይ እንመኛለን፡፡
አመሰግናለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለተሰጠኝ ዕድል ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው፡፡