ከፍቅር ጸንሳ ልጅን ያህል ጸጋ
ወልዳ ተኝታለች ባልተቤቴ ካልጋ
ግቡና ጠይቋት አጎበር ገልጣችሁ
ሁለት ሆና ሚስቴን ታገኟታላችሁ፡፡
እኔ ሳልሳዊ ነኝ የቤቱ አባወራ
እጹብ እጹብ በሉ ይህን ድንቅ ስራ
በእናት መሬት ላይ በአባት ገበሬ ህጻን እየዘራ
ያንድ አምላክ ሚስጥሩ ሦስት ሆኖ ሲሰራ
ምሉዕ ከመ አምላክ የሚካኤል ስሙ
እንደ እግዚያብሄር ያለ ማንም ያለ ሲሆን የቃሉ ትርጉሙ
ራስን እንደ አዲስ ወልዶ ለመድገሙ
የማርያም ነው እና ሴትነት ቀለሙ፡፡
እንግዲህም አንቺ
አስመላሽ ነሽ እና ሲገሰግስ እድሜ በልጅ እያደስሽን
መልክ የምታሳዪ እንደ አዲስ ወልደሽ
እንኳን ማርያም አሜን፤
እንኳን ማርያም አሜን
ምስጋና ይድረሰው አንድ ላደረገው ስምሽና ስሜን፡፡
የውለታሽን ዳር በቃላት ለመድረስ ስላቃተው አቅሜ
ይሁንሽ ስጦታ የሚቀጥለው ዘፈን ከገለጸው ልቤን፡፡
አሜን!
ቴዲ አፍሮ ለባለቤቱ አምለሰት ሙጬ የገጠመው ግጥም –እንኳን ማርያም አሜን
ጋዜጠኛውን ደብድቧል የተባለው አርቲስት ዳንኤል ተገኝ በዋስ ተፈታ
(ሰንደቅ ጋዜጣ) ነሐሴ 20 ቀን 2006 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ገልፍ ኢዚዝ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ላይ የግል ተበዳይ በሆኑት ጋዜጠኛ ግዛቸው እሸቱ ላይ የቀላል የአካል ጉዳት አድርሰዋል ተብለው በወንጀል ተጠርጥረው ቦሌ ምድብ በመጀመሪያ ደረጃ 4 ወንጀል ችሎት ሕዳር 16 ቀን 2007 ዓ.ም ቀርበው ጉዳያቸው ተሰምቷል።
የወንጀል ችሎቱ ግራና ቀኝ አከራክሮና የሶስት ምስክሮችን ቃል ካዳመጠ በኋላ ሕዳር 30 ቀን 2007 ዓ.ም ለብይን ቀጠሮ ሰጥቷል።
ከዚህ በፊትም በካራማራ ፖሊስ ጣቢያ ለምርመራ የተጠራው አርቲስት ዳንኤል ተገኝ በቀረቡ ጊዜም በ3ሺ ብር ዋስትና መለቀቃቸው ይታወሳል።
የተወዳጁ ድምፃዊ ፀሐዬ ዮሃንስ “የኔታ” በቅርብ ይወጣል
ከኢየሩሳሌም አረአያ’
ተወዳጁ ድምፃዊ ፀሐዬ ዮሃንስ “የኔታ” የሚል ርእስ የሰጠው አዲስ አልበም በቅርቡ እንደሚለቅ ታወቀ። ከአንድ አመት ለበለጠ ጊዜ የፈጀው ይህ አልበም የሙዚቃ አድማጩ ሊወደው እንደሚችል ፀሐዬ ተናግሯል። ስለእናት አገሩ ኢትዮጵያ በየአልበሙ የሚያቀነቅነው ፀሐዬ በዚህኛው “የኔታ” አልበም እንዲሁ ማዜሙን ገልፆዋል። አቋም ካላቸውና አገርና ህዝባቸውን በማክበር ከሚወዱ ድንቅ አርቲስቶች አንዱ ፀሐዬ ዮሃንስ ነው። የፀሐዬን ዘፈኖች በፍቅር ከመውደዴ በተጨማሪ ከህይወቴ ገጠመኞች ጋር የተቆራኙ ናቸው! ከፀሐዬ ጋር ባለፈው አመት ቨርጂኒያ ተገናኝተን የተናገረውን በዚህ አጋጣሚ መጥቀስ (መድገም) ወደድኩ። « ህዝብ በጭራሽ አይሳሳትም! ሁሌም ህዝብ ትክክል ነው!» ነበር ያለው።
(በፎቶው አዲሱ የፀሐዬ ዮሃንስ አዲስ አልበም ፖስተር)
የሐበሻ ሬስቶራንት ሥራ አስኪያጅ ድምፃዊት ኢየሩሳሌም አስፋው (ጄሪን) ለምን ውስጥ እግሯን እና ታፋዋን በቢለዋ ወጋቻት? (ያንብቡ)
ድምፃዊት ኢየሩሳሌም አስፋው (ጄሪ) በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ‹ሀሎ አዲስ አበባ› በተሠኘ ተወዳጅ ዘፈኗ ትታወቃለች፡፡ እስካሁን ድረስ ሁለት የሙዚቃ አልበሞች የሠራች ሲሆን ስድስት ያህል ነጠላ ዜማዎችም አሏት፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ባደረባት የሙዚቃ ፍቅር የተለያዩ ድምፃዊያንን ዘፈኖች ትጫወት የነበረ ሲሆን ታዋቂው ኮሜዲያን አለባቸው ተካ በችሎታዋ ተደንቆ በተወዳጁ ‹‹አለቤ ሾው›› የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ ላይ እንግዳ አድርጓት ነበር፡፡ የተለያዩ ነጠላ ዜማዎች ከማውጣቷ ጎን ለጎን ሶስተኛ የሙዚቃ አልበሟን እየሠራች ባለበት በዚህ ወቅት ከሠዎች በተሠነዘረባት ጥቃት ያልተጠበቀ ጉዳት ደርሶባት ህክምና እየተከታተለች ትገኛለች፡፡ የቁምነገር መጽሔት ድምፃዊቷን ያለችበትን ሁኔታ አነጋግሯል፤ መልካም ንባብ
ቁም ነገር፡- ሙዚቃ መጫወት የጀመርሽው መቼ ነበር?
ኢየሩሳሌም፡- ወደ ሙዚቃ ህይወት የገባሁት በልጅነቴ ነው፡፡ ወላጅ አባቴ ከመሞቱ በፊት ‹‹ልጄ ዘፍና ትጦረኛለች›› ይል ነበር፡፡ አያቴ ግን አይፈቅድልኝም ነበር፡፡ ቀበሌ እሠለጥን በነበረበት ጊዜ ከሠባ አምስት ተወዳዳሪዎች መካከል አንደኛ ወጥቼያለሁ፡፡ በውድድሩ ላይ እኔ የምዘፍነው የንዋይን ነው ስላቸው ሳቁብኝ፡፡ ከዚያም የማርታ አሻጋሪን፣ የበዛወርቅ አስፋውንና የአስቴር ከበደን ዘፈኖች ዘፍኜ አሸነፍኩና እዚያ ጀመርኩ፡፡
ቁም ነገር፡-ከዚያ በኋላስ የት የት ሠርተሻል?
ኢየሩሳሌም፡- ሴሌክት የምሽት ክለብ ለሠባትና ስምንት ዓመት ያህል የሠራሁ ሲሆን ‹ሀሎ አዲስ አበባ›› የሚለው የመጀመሪያ የሙዚቃ አልበሜ ከወጣ በኋላ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ የራሴን ምሽት ክለብ ከፍቼ መስራት ጀምሬ ነበር፡፡ ግን አላዋጣኝም፡፡ ከዚያ ደግሞ ‹‹ከሚሚ መጋሎ››፣ ሐሊማ አብዱረህማን እና ከዝናሽ (ሀቢቢ) ጋር በጋራ የምሽት ክለብ ከፍተን ለመስራት ሞክረን ነበር፡፡ በመሀል ልጅ ወለድኩና አቋረጥኩኝ፡፡
ቁም ነገር፡- ወደ ሐበሻ ሬስቶራንት ገብተሽ መዝፈን የጀመርሽው መቼ ነበር?
ኢየሩሳሌም፡- ከአምስት ከስድስት ዓመት ምናምን በፊት ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም ሮዛ ግዛው በተባለች ማናጀሬ በኩል ወደ ዱባይ ሄጄ ከታንዛንያ፣ ከናይጄሪያና ከኮንጎ የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር እየሠራሁ ሙሉውን ዓመት አሣልፌያለሁ፡፡ ገራጅ የሚባል የምሽት ክበብ ነበር የምንሠራው፡፡ እንዲያውም ሌሎቹ ባለሙያዎች በየሶስት ወሩ ሲቀያየሩ እኔ ምንም ቪዛ ሳልቀይር እዚያው መቆየት ችያአለሁ፡፡ ክለቡ ከሠባት መቶ እስከ ስምንት መቶ የሚደርሡ ሰዎች ይይዛል፡፡
የጊኒ፣ የታንዛኒያ፣ የናይጄሪያ፣ የኬንያ ዜጎች እንዲሁም አረቦችና ህንዶች የሚዝናኑበት ሲሆን አንዳንድ አበሾችም አልፎ አልፎ ይመጡ ነበር፡፡ ሽልማታቸው፣ ፍቅራቸው ሁሉ ልዩ ነው፡፡ የእነሡን ሙዚቃ የምሠራላቸው ያህል በተለያየ ሁኔታ ነው የሚያዩኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ዘፋኝ አይተን አናውቅም ብለው ነበር ገንዘብ የሚሸልሙኝ፡፡
ቁም ነገር፡- ሐብታም ሆነሽ ነበራ ከውጪ የመጣሽው? (ሣቅ)
ኢየሩሳሌም፡- ብዙ ቤተሠብ ነው ያለኝ፡፡ ቤት ተከራይቼ ነው የምኖረው፡፡ ዱባይና አቡዳቢ እየተመላለስኩ ቤተሠቦቼን ነበር የምረዳው፡፡ ያስተማርኳቸው፣ የዳርኳቸው አሉ፡፡ ለእኔ ብዬ ያደረኩት ነገር የለም፡፡
ቁም ነገር፡ እስካሁን ድረስ ምን ያህል የሙዚቃ አልበሞች ሠርተሻል?
ኢየሩሳሌም፡- የመጀመሪያ አልበሜ ‹ሀሎ አዲስ አበባ› የሚለው ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም በህዳር ወር ነበር የወጣው፡፡ ‹ይጠራኛል› የሚል ሌላ አልበምም አሣትሜ ነበር፡፡ በአጋጣሚ የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ህይወት ያለፈበት ቀን ላይ ነበር ሣይታሠብ የወጣው፡፡ በዚህ ምክንያት ሣይደመጥ ቀረ፡፡ በ2006 ዓ.ም ከዱባይ የመጣሁት ለአልበም ሥራ ነው፡፡ የአልበም ሥራ መስራት ጀምሬያለሁ፡፡ የሁለት ዓመት ቪዛ እያለኝ ነው የአልበም ሥራዬን ለመጨረስ የመጣሁት፡፡ ጥሩ ጥሩ ግጥምና ዜማዎች ሠብስቤያለሁ፡፡ ከአለማየሁ ይለፍ ጋር ነው የምሠራው፡፡
ቁም ነገር፡- የተለያዩ ነጠላ ዜማዎችም አሉሽ አይደል?
ኢየሩሳሌም፡- አዎ! ከ‹ሀሎ አዲስ አበባ› አልበሜ በኋላ ያወጣሁት ‹ጀነናው› የሚል ነጠላ ዜማ አለ፡፡ የሄለን በርሄ ‹‹ኦዛዛ አሌና›› የተሠኘው ዘፈን ያለበትና የሌሎች ዘፋኞችንም ሥራዎች የያዘ ፣‹ድሪም ኮሌክሽን› የሚል አልበም ላይ የተካተተ ነበር፡፡ ‹አግባ አግቢ› የሚል ነጠላ ዜማም ሠርቼያለሁ፡፡ ‹ደቅ ላይ› የሚል የባህል ዘፈን፣ ‹ዞማ ዞማ› የሚል በኮንሶ ስልት (ሪትም) የተሠራ ነጠላ ዜማም አለኝ፡፡ የተለያዩ ቪዲዮ ክሊፖችንም እሠራለሁ፡፡ አላረፍኩም፡፡ እለፋለሁ፡፡ በጣም እለፋለሁ፡፡ የተቀመጥኩበት ጊዜ የለም፡፡ እንደኔ የሚለፋ ሠው ያለ አይመስለኝም፡፡ ለምን እግዚአብሔር ይህን እንዳደረገ አላውቅም፡፡
ቁም ነገር፡- ቅድም ልጅ እንዳለሽ ነግረሽኛል፡፡ የትዳር ሁኔታ ግን አላነሣንም?
ኢየሩሳሌም፡- ልጅ ወልጄያለሁ፡፡ አባቱ ከእኔ ጋር አይኖርም፡፡ ተለያይተናል፡፡
ቁም ነገር፡- ስንት ዓመቱ ነው?
ኢየሩሳሌም፡- እግዚአብሔር የተመሠገነ ይሁን ስምንተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ልደቱን ለማክበር ሶስት ቀን ሲቀረው ነው የታረድኩት፡፡
ኢየሩሳሌም፡- ‹እስማማለሁ አልስማማም› በተሠኘው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሆኜ ቀርቤ ነበር፡፡ እና ፕሮግራሙ በሚለቀቅበት ምሽት ቀድሜ ነው ወደ ሐበሻ ሬስቶራንት የገባሁት፡፡ ለምሽት ስራዬ ዝግጁ ሆኜ ሚኒስከርት ለብሼና ሂል ጫማ አድርጌ ነው ወደ ሬስቶራንቱ የገባሁት፡፡ ሰው ገብቷል ሙዚቃ ግን አልተጀመረም፡፡ ለባለቤቱ ደውዬ የሙዚቃ ስራ እስከሚጀመር ቴሌቪዥን እንዲያስከፍትልኝ ስነግረው እርሡ ለማናጀሯ ደውሎ ‹‹ሙዚቃ አልተጀመረም›› ሲላት ከእኔ ጋር መነጋገር ትጀምራለች፡፡ ከእሷ ጋር ስንነጋገር ሁለቱ የሬስቶራንቱ አስተናጋጆችሙዚቃ እንዳልጀመረ ለምን ነገርሽው በማለት መጥተው አንዷ ገፍታ ጥላኝ ላዬ ላይ ወጣች፤ ሌላኛዋ ደግሞ ፀጉሬን ያዘችኝ፡፡ በዚህ መሀል ማናጀሯ ቢላ ይዛ መጥታ የግራ እግሬ መሀል ታፋዬ ላይ፣ ቀኝ እግሬ መቀመጫዬ ላይ እና የቀኝ ውስጥ እግሬን ትወጋኛለች፡፡ የሠውነቴ መጋጋጥ የሚነገር አይደለም፡፡ በወቅቱ ራሴን ስቼ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ፍርድ ይስጠኝ፡፡ የደረሠብኝን ጉዳት እንደዚያ ተቀድጄ ሠውነቴ እየደማ ለሆቴሉ ባለቤት ሄጄ አሣየሁት፡፡ እሡ ሀሌሉያ ክሊኒክ ወስዶ ህክምና እንዳገኝ አደረገ፡፡ ከዚያም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ አስመዝግቤ ሁለቱ ሴቶች በቁጥጥር ስር ሲውሉ የሬስቶራንቱ ማናጀር ትጠፋለች፡፡ በቢላ የወጋችኝ የሬስቶራንቱ ማናጀር ለአሥራ ሁለት ቀናት ጠፍታ የእነርሡን መታሠር ስትመለከት ለፖሊስ እጇን ሰጠች፡፡ አሁን ሶስቱም በሦስት ሺህ ብር ዋስ ተፈትተው የፍርድ ቤት ቀጠሮ እየተጠባበቅን ነው፡፡
ቁም ነገር፡- አድናቂዎችሽስ የደረሠብሽን ነገር ሲመለከቱ ምን ተሠማቸው?
ኢየሩሳሌም፡- ማመን ከምችለው በላይ ነው የሠው ምላሽ፡፡ ‹ስንት ዓመት ጠፍተሽብን የመጣሽ ልጅ ምን ብታደርጊያቸው ነው ይህን ያደረሡብሽ› ብለውኛል፡፡ ያላዘነ፤ የማያለቅስ የለም፡፡ ከሱዳንና ከዱባይ እየደወሉ ሲያለቅሱ እኔንም ያስለቅሡኛል፡፡ ብዙ ቦታዎች ላይ መወጋቴ ነው ትልቁ አደጋ፡፡ ደም በብዛት ነበር የፈሠሠኝ፡፡
ቁም ነገር፡- አደጋውን ካደረሱብሽ ሠዎች ጋር የቆየ ቂም ነበራችሁ?
ኢየሩሳሌም፡- ማናጀርዋ ወደ ሬስቶራንቱ ከመጣች ዘጠኝ ወሯ ነው፡ ፡ ሁለቱ ደግሞ ከአስር ዓመት በላይ የቆዩ አስተናጋጆች ናቸው፡፡ መሀል ላይ ማናጀሯ ደሞዝ ስትቆርጥ፣ ሠራተኛ ስታባርር ለምንድነው ይህን የምታደርጊው እያልኩ እናገር ነበር፡፡ ያ ነገር ነው እዚህ ደረጃ ያደረሰን፡፡ ለሠሚም፣ ለተመልካችም፣ ለራሴም ነው (የደረሠብኝ ጉዳት) ትንግርት የሆነብኝ፡፡ እንደተገረዘ ህፃንነበር ቆሜ የምሸናው፡፡ ለሥራ ወጥቼ ያልሆነ ነገር ሆንኩኝ፡፡ ወይ እንደ ጓደኞቼ እንደሚካያ እና እንደ ኢዮብ መኮንን ታምሜ ሰው ሠምቶ ብሞት የተሻለ ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- አሁን ያለሽበት ሁኔታ እንዴት ነው? ጤንነትሽ?
ኢየሩሳሌም፡- ከሠባት ቀን ህክምና በኋላ የቤቱ ባለቤት እኔን ማሣከም አቁሟል፡፡ የጭንቅላቴን ውጤት መስማት አልተቻለም፡፡ ህክምና ላይ ያለው ነገር በሙሉ ቆሟል፡፡ የሁለት ወር ደመወዝም አልተሠጠኝም፡፡ ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼና እኔ ራሴ ነኝ እየተሯሯጥን ያለነው፡፡ አሁን ቤት ውስጥ ነው ያለሁት፡፡ መጥቶም፣ ጠይቆኝም አያውቅም፡፡ የውስጥ እግሬና ጭንቅላቴ አሁንም ያመኛል፡፡ አንደኛው ስካን ማድረጊያ መሣሪያ በሀገር ውስጥ የለም ተብሎ እየፈለግኩኝ ነው፡፡ እግሬ በጣም ነው የተጎዳው፡፡ ውስጥ እግሬ ድረስ ነ በር የተወጋሁት፡፡ ሌላውን የልጄ አምላክ አትርፎኛል፡፡
ቁም ነገር፡- ከዚህ በኋላ አበሻ ሬስቶራንት ተመልሠሽ የምትሠሪ ይመስልሻል?
ኢየሩሳሌም፡- በፍፁም፡ ፡ አሁን ለሦስተኛ ስራዬ ‹‹ውብ አዲስ አበባ›› የሚል ትልቅ ፖስተር (አበሻ ሬስቶራንት) ለጥፌያለሁ፡፡ ሰው እኔን ብሎ ነው የሚመጣው፡፡ ማናጀሯ ግን አርቲስትነቴን እንኳን አላየችውም፡፡
ቁም ነገር፡- ከዚህ ቀደም ‹‹ሐሎ አዲስ አበባ›› የሚል የሙዚቃ አልበም አሣትመሻል፡፡ አሁን ደግሞ ‹‹ውብ አዲስ አበባ›› የሚል አልበም ነው እየሠራሽ ያለሽው፡፡ አዲስ አበባ ላይ የተለየ ትኩረት የሰጠሽበት ምክንያት ምንድን ነው?
ኢየሩሳሌም፡- ጨርቆስ ነው ተወልጄ ያደግኩት፡፡ ከወላጅ አባቴ ቤተሰቦች ጋር ነው ያደግኩት፡፡ አዲስ አበባ አገርህ ናት፤ መለያህ ናት፡፡ ውጪ ሀገር በምሔድበት ወቅት ይከፋኛል፡፡ እዚህ ደግሞ አየሩ ያምራል፡፡ ባህል አለኝ፡፡ ያለው ለሌለው ያበድራል፡፡ እዚያ ናፍቆት አለ … ብዙ ነገር አለው፡፡
አሁን የምሠራው ‹‹ውብ አዲስ አበባ›› የሚል አልበም ደግሞ የአሁኗ አዲስ አበባ መጀመርያ ከነበረችው የተለየች መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡
ቴዲ አፍሮን ቦሌ ላይ ለምን አገቱት? –ክንፉ አሰፋ (ጋዜጠኛ)
ክንፉ አሰፋ
ወደ አውሮፓ የሚያስገባውን ቪዛ እና ትኬት ይዞ ከወዳጆቹ ጋር ጉዞውን ለመጀመር ወደ ቦሌ አለም-ዓቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ አቀና። እዚያው እንደደረሰ የተለመደው የፓስፖርትና ትኬት ቁጥጥር ተደረገ። ሁሉም የተሟላ ነበር። ቴዲ ሸኚዎቹን ተሰናብቶ ወደ ውስጥ ገባ። እለተ ሐሙስ፣ ህዳር 28 ቀን 2007 ዓ.ም.።
የአውሮፓው ኮንሰርት በፊንላንድ፣ ሄልሲንኪ ቅዳሜ፤ ህዳር 28 ቀን ይጀምራል። ፊንላንድና አካባቢው ያሉ የቴዲ አድናቂዎች ትኬት ቆርጠው አርቲስቱን በጉጉት እየተጠባበቁት ነው። የቴዲ አፍሮ ማናጀርም አቡጊዳ ባንድን ይዞ ሄልሲንኪ ላይ ለቅዳሜው ስራ በልምምድ ላይ ይገኛል።
ቴዲን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተሰናብተው የተመለሱ ወዳጆቹ አውሮፓ ደውለው አርቲስቱን ሄልሲንኪ ላይ እንዲቀበሉት ተናግረው ነበር። ነገሩ እነሱ እንዳሰቡት ግን አልነበረም። ዘግየት ብሎ ሌላ ነገር መጣ። ሰዎቹ ቦሌ ላይ አገቱት። በውድቅት ሌሊት ፓስፖርቱን ነጥቀው ወደ ቤቱ አሰናበቱትም። ይህንን ያደረጉበትን ምክንያትም አልነገሩትም። አስቀድመው ገና ከበሩ ላይ መከልከል ይችሉ ነበር።… ግን ማንገላታት ነበረባቸው። ስሜቱን ለመጉዳት መሞከር ነበረባቸው። ጉልበት እንዳላቸው ማሳየት ነበረባቸው። ፈላጭ፤ ቆራጭ መሆናቸውን ማሳወቅ ነበረባቸው። ቂመኞችና ተበቃዮችም መሆናቸውን መናገር ነበረባቸው። ….
ነገሩ ያልተጠበቀ ባይሆንም፤ ለቴዲ ጠበቆች ግራ ማጋባቱ አልቀረም። በነጋታው ጠበቆቹ ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ነበረባቸው። ከፍርድ ቤት ያገኙት ምላሽ በቴዲ አፍሮ ላይ ምንም አይነት የማገጃ ትዕዛዝ ያለመኖሩን ነው። ከዚያም ወደ ኢሚግሬሽን ጉምሩክ እና ሌሎች ጉዳዩን የሚመለከቱ ቢሮዎች ሁሉ አመሩ። እዚያም የጉዞ ማገጃ አልተገኘም። ታዲያ ማን ይሆን ያዘዘው? የካዛንችዙ ስውር መንግስት ስራውን እንደገና ጀምሮ ይሆን?
ጉዳዩ ግራ ያጋባል። እርግጥ ነው። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ አንድ ተራ ካድሬ እንዲህ አይነት ተራ ወንጀል የሚፈጽምባት ሃገር ሆናለች። አንዳንድ ቦታዎች ላይ “መንግስት የለም እንዴ?” የሚያስብሉ ወንጀሎች እንደሚፈጽሙ ይሰማል። የቀድሞው የኮሚኒኬሽን ሚንስትር ዴዔታ የነበረው ኤርምያስ ለገሰ፤ በቅርቡ ባሳተመው “የመለስ ትሩፋቶች” የተሰኘ መጽሃፉ አዲስ አበባን ባለቤት አልባ ከተማ ብሏታል።
በልማታዊ አርቲስቶች እለት-ተለት የሚወደሰው ጸሃዩ መንግስት፤ ለልማት የተጋው መንግስት፣ ጭቆናን ያቆመው መንግስት፤ ለዜጎች መብትና ነጻነት የቆመ መንግስት፣ ሃገሪቱን ወደ እድገት እና ትራንስፎርሜሽን ጎዳና ላይ ያስኬደ መንግስት፣ የመቻቻል ባህልን ያመጣ መንግስት…. እንዴት ሆኖ የጥላቻ፣ የቂም እና የበቀል እርምጃ ሊወስድ ቻለ?
ልማታዊ አርቲስቶቻችን ይቅርታ አድርጉልኝና የአስተሳሰብና የአመለካከት ለውጥ ሳይኖር ቁሳዊ ለውጥ ይመጣል ብሎ የነገራችሁ ማን ይሆን? አመለካከታችን ካላደገ፣ እድገት ይታሰብ ይሆን?
ወደ ጉዳዩ ስንመለስ፣ ከፊንላንድ በኋላ ሌሎች ስድስት የአውሮፓ ከተሞች ላይ ኮንሰርቶች ተዘጋጅተዋል። ፕሮሞተሮች ለመሰናዶው ብዙ ወጪ አውጥተዋል። የአርቲስቱ አድናቂዎችም አስቀድመው ትኬት ቆርጠዋል። ይህንን ካድሬዎቹ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ሁሉንም ማጉላላቱ፤ ከተቻለም ማደናቀፉ ደስታን ይሰጣቸዋል። እንዲህ አይነት የድፍረት ስሜት የሚመነጨው አርቲስቱን ሳይሆን ይልቁንም ሕዝብን በጅምላ ከማናቅ ነው። ሕዝብን ከመጥላት። እየገዙት ያሉትን ህዝብ መናቅና መጥላት የት ድረስ ሊያደርሳቸው እንደሚችል የምናየው ይሆናል። እንደ ሰብአዊ ፍጡር ሳይሆን እንደ እንስሳ የሚያስቡ እነዚህ የዘመናችን ጉዶች ሕዝብ የሚወደውን ነገር በሙሉ በመጥላት፤ የህዝብ አካል እንዳልሆኑ እይረጋገጡልን ነው። ከጫካ ከወጡ 21 አመታትን አስቆጥረዋል። አካላቸው ከጫካ ወጣ እንጂ አመለካከታቸው ግን እዛው እንደሆነ ድርጊታቸው ይነግረናል። ከሁለት ዓስርተ-ዓመት በኋላም ጥንት ከሚያስቡበት ከጫካው ህግ አልተላቀቁም።
ይህንን ትልቅ ሃገር እና ይህንን ትልቅ ሕዝብ እየመሩ ለምን እንደመንገስት ሊያስቡ እንደማይችሉ አይገባኝም። መንግስት ሆነው እንደግለሰብ ቂም ይይዛሉ። ቂም ይዘው እንደ ክፉ ሰው ይበቀላሉ። ሀገር ደግሞ በጥበብ እና በማስተዋል እንጂ፤ ከቶውንም በቂም እና በበቀል አትመራም። ይህንን የሚያደርጉ ሁሉ መጨረሻቸው ውድቀት፤ አወዳደቃቸውም የውርደት እንደሆነ ለደቂቃ አስተውለውት የሚያውቁ አይመስለኝም።
እንግዲህ ይህ ተራ ወንጀል በዚህ ድንቅ አርቲስት ላይ ሲፈጸም የመጀመርያ አይደለም። ከወራት በፊትም ወደ አሜሪካ ሊጓዝ ሲል የአየር መንገዱ ካድሬዎች ይዘው ብዙ አጉላልተውት ነበር። እርግጥ ነው ቴዲ አፍሮ ላይ ጥርሳቸውን ነክሰውበታል። ኤርምያስ ለገሰ፤ በ”መለስ ትሩፋቶች” መጽሃፉ ላይ የቴዲን ጉዳይ አንስቶ የገዢው ፓርቲ ሰዎች ይህንን አርቲስት እንዴት በክፉ አይን እንደሚመለከቱት ዳስሷል። ይህ አርቲስት ምናልባት በአንዲት ዜማ ተችቷቸው ይሆናል። እነሱም አላለፉትም። በፍትህ ስም የበቀል ዱላቸውን አሳርፈውበታል። ወህኒ ወርዷል። እስኪበቃቸውም ቀጥተውታል።
ቴዲ አፍሮ ግን ቂም አልቋጠረባቸውም። አሁንም የሚያቀነቅነው ስለ ፍቅር ነው። አሁንም የሚለው እንዲህ ነው። “ፍቅር ያሸንፋል!”
እነዚህ ሰዎች ሃያ ሁለት አመታት ሙሉ ከጥፋት አለመማራቸው ብቻ አይደለም የሚደንቀው። በአንድ ግለሰብ ምክንያት ከሚሊዮኖች ጋር እንደሚላተሙ አለማሰተዋላቸውም የሚገርም ነው። ለሟቹ ፓትሪያርክ ሲሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኦርቶዶክስ ምዕመናን ጋር ተቃርነው ነበር። አንድ የሙስሊም መጅሊስ መሪን ለመያዝ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሙስሊም ምዕመናን ጋር ጠፋጥተዋል።
ዛሬ አንድ ቴዲን ቢያንገላትቱት፣ ቢያግቱትም ሆነ ፓስፖርቱን ቢነጥቁት ለግዜውም ቢሆን የአድናቂዎቹን ስሜት ሊጎዱት ይችሉ ይሆናል። ይህ ድርጊታቸው ቴዲ አፍሮን ቅንጣት ያህል አይጎዳውም። ይልቁንም የበለጠ ተወዳጅ እና የበለጠ ጀግና ያደርገዋል። ከዚህ የፖለቲካ ንግድ እነሱ የሚያተርፉት ነገር ቢኖር የህዝብ ጥላቻን ነው። የቴዲን መታገት የሰሙ የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች ሳይቀሩ እንዲህ ሲሉ ተደመጡ፤ “አሁንስ አበዙት… ሃገራችንን እንድንጠላ አደረጉን….” ካድሬዎቹ ማህበራዊ ድረ-ገጾችን ቢጎበኙ የህዝቡን ስሜት ያነብቡ ነበር።
በሕዝብ አመኔታ ሳይሆን ይልቁንም በጆሮ ጠቢዎችና በመሳርያ በመተማመን እስካሁን ስልጣን ላይ ላላችሁት ገዢዎች ግን አንድ የምለው አለኝ። የፈረንሳዩ አንባገነን ናፖሊዮን ቦናፓርት የነበረውን ሰራዊት እስተውሉ። ይህ ግዙፍ እና የሰለጠነ ሰራዊት በህዝብ እንደ አሸዋ ተበተነ። የግብጹ ሆስኒ ሙባረክ ያልታሰበ እና ያልታለመ ውድቀት የመጣው እንዲሁ በመሳርያ ከመተማመን እና ህዝብን ከመናቅ ነበር። ይህ አስደንጋጭ ትዕይንት ለእናንተ ትምህርት ካልሰጣቸሁ የሱ እጣ ፈንታ ይጠብቃችኋል። መቶ አመት የቆየ አንባገነን ገዢ በታሪክ አላየንም።
የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ኢትዮጵያ
ማለዳ ፌስቡክ እንዴት አደረ? ብዬ ስከፍት የተዋናይት ሜሮን ጌትነትን ለወሊድ አሜሪካ ልትሄድ መሆኑን አንብቤ ቴዲ አፍሮ ትዝ አለኝ ። የሜሮን አይገርምም ። አሁን ልጆቻቸው ኢትዮጵያ እንዲወለዱ የሚፈቅዱ ወላጆች ጥቂት ወይም እዚያ የመውለድ እድሉ የሌላቸው ናቸው ። የባለሀብት ፣ የባለስልጣን ፣ የፓይለት ፣ የሆስቴስ ፣ ወዘተ ልጆች አሜሪካ ነው በብዛት የሚወለዱት ። ለብዙዎች ኢትዮጵያ አንደ ቀን አሜሪካ ጠቅለው እስኪሄዱ መሸጋገሪያቸው ናት ። እነዚህ ኢትዮጵያ የልጃቸው መኖሪያ እንድትሆን ያልፈቀዱ ዜጎች “ኢትዮጵያ ሀገሬ እወድሻለሁ ” ሊሉ እንዴት ይችላሉ? ሰው እንዴት በእንግድነት ካለበት ቤት ፍቅር ሊወድቅ ይችላል? ምንድነው ሀገር መውደድ? አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ እነዚህ ሀገሪቱን ጊዜያዊ መኖሪያ ያደረጉና በቀጣይ ሀገሪቱ የተሻለች መኖሪያነቷ ላይ ጥያቄ ያላቸው ዜጎች የሚበዙቱ የስርዓቱ ተጠቃሚዎች መሆናቸው ነው ።
በዚህ ስርዓት ቅጠቀጣ የበዛበት ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ከሀገር ለመውጣትና እዚያው ለመኖር በቂ ምክንያት አለው ። ድምፃዊው ግን ብልጥ ብቻ ሳይሆን ብልህ ነው ። ከሀገሩ ቢወጣ ከባህር የወጣ አሳ እንደሚሆን ያምናል ። ከነችግሩም ሀገርና ህዝብ እንደሚበልጡ ይረዳል ። ከሀገር ወጥተው ከባህር የወጡትን ያያል ። ከዚህ ሁሉ በላይ ሀገሩን ይወዳል ። ይህች የሚወዳት ሀገሩ ለእሱ ባትመቸው እንኳ ለልጆቹ የመኖሪያ ሀገር መሆኗ ላይ ጥያቄ አላነሳም ። ልጆቹን ለሀገሩ ነው የሰጣቸው ። ስለዚህም ባለቤቱ አምለሰት እርግዝናዋ ገፍቶም እዚያች ለብዙዎች ” የተስፋዪቱ ምድር ” የሆነች ሀገር ስትቆይ እዚያው እንደምትወልድ ነበር የገመቱት ። አምለሰት ግን ብዙዎች ወደዚያ በሚሄዱበት ወቅት ወደዚህ መጣች ። የቴዲ ልጅ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ተወለደ ። ይህ ብዙ ማለት ነው ። ትልቅ ውሳኔ ነው ። በሀገር ለመማረርና ሀገርን ” ለመጥላት” ፣ ቢያንስ በሀገርና በስርዓቱ (ብዙዎች ዘላቂዋን ሀገርና ነገ የሚወድቀውን ስርዓት ለይተው አያዪም) እምነት ለማጣት ቴዲ ይቀርባል ። ይህ ሁሉ ግን ልጁን አሜሪካዊ ለማድረግ ውሀ የሚቋጥር ምክንያት አልሆነለትም ። ስለዚህ የቴዲን ሀገሬ እሰማታለሁ ። ሀገሬ ሲል እውነትም ሀገሩን እያሰበ ነው ። ቴዲ ” ሀገሬ ለእኔ የሙዚቃ ግጥም ማድመቂያዬ አይደለችም ፤ ሀገሬ ናት ” ቢለኝ አምነዋለሁ ። ብዙዎች ግን አፋቸው እንጂ ተግባራቸው ይህን አይልም ። የቴዲ አፍሮ ኢትየጵያ በስሟ ግጥም የሚሰራላት ፣ ዜማ የሚንቆረቆርላት ፣ ብር የሚታፈስባት ብቻ አይደለችም ። እንደ ትናንቱ ሁሉ ዜግነቷ የሚወደድ በጭንቅ ውስጥ ያለች የተስፋ ሀገር ናት ። ቴዲ ልጆቹን በጉዲፈቻ ማሳደግ የፈቀደ ክፉ አባት አይደለም ። የሚዘፍንላትና በዘፈኑም ሀብት ያፈራባትን ሀገሩን የንግድ መደብር አላደረጋትም ። መኖሪያውና የልጆቹ ማደጊያ እንድትሆን መርጧታል ። ብዙዊች ግን ፣ የቴዲ ከሳሾችም ጭምር ይህ የሀገርን ሀገሬ የማለትና ባለሀገር የመሆን ሞራላዊ ድፍረት በውስጣቸው የለም ።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ተዋናይት አረፈች
(ዘ-ሐበሻ) ‹‹እኔ ቲያትር ከመጀመሬ በፊት፣ ወንዶች ጢማቸውን እየተላጩና ጡት እየቀጠሉ የሴትን ገጸባህሪ ይጫወቱ ነበር›› ትል ነበር የመጀምሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት ተዋናይ:: ከ1944 እስከ 1986 ዓ.ም ድረስ እጅግ በርካታ ቲያትሮችን ሰርታለች። ዳዊትና ኦሪዮን፣ አልሞትም ብዬ አልዋሽም፣ ቴዎድሮስ፣ ጦጢት፣ ፍልሚያ፣ ንግስተ-ሳባ፣ የሺ በጉለሌ እና የመሳሰሉትን በብቃት ተውናለች፡፡ ሴት ተዋናይ ባልነበረበት ጊዜ ወንዶችን ሱሪ ያስታጠቀች ቀዳማዊት አርቲስትም ናት።
አገሯንና ባህሏን ለማስተዋወቅ ሩቅ ምስራቅ፣ ሶቪየት ህብረት፣ ካርቱም ኡጋንዳና በርካታ አገሮችን ረግጣለች። በዛን ወቅት አዘጋጆቹ ለትራጄዲ ስራ እየመደቡኝ እንጂ ጥሩ ኮሜዲያን ይወጣኝ ነበር የምትለው አርቲስት በአንድ ወቅት ከጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ወደትወናው ዓለም እንዴት እንደተሳበች “ተዋናይ ለመሆን በጭራሽ ፍላጎት አልነበረኝም። በዛን ጊዜ ዘመናይ ዘለቀ ለተባለች ጓደኛዬ ስራ ፈልጊልኝ ስላት ወደዚህ ስራ ለመግባት ፍላጎት ስለነበራት መለስ ቀለስ ትል ኖሮ እኔንም ወደቴአትር ቤት ይዛኝ መጣች። እኔ ለራሴ ከዚያ በፊት ሙዚቃ አይቼ አላውቅ ሳክሲፎኑ፣ ፒያኖው ምኑ ቁጡ። የጎረምሳውስ መዓት ብትይ! ያኔ እነተስፋዬ ሳህሉ ከእኔ በእድሜ በሰል ያሉ ነበሩ። ይሄ ነገር ለእኔ አይሆንም አልኳት ለጓደኛዬ። ምክንያቱም እኔ እፈልግ የነበረው የእደ-ጥበብ ስራ ነበር፡፡ ጥልፍ መጥለፍ ዳንቴል መስራትና ሌላ ሌላውን እንጂ ጎረምሳ መሀል መዋል አልፈልግም ብዬ ወደ ቤቴ ሄድኩና በዚያው ቀረሁ:: በኋላማ መኮንን ሀብተወልድ የተባሉ ሰው ያቋቋሙት ፒያሳ ውስጥ ‹‹ዜንጎን›› የተባለ ድርጅት ነበር። ጥልፍ፣ የልብስ ስፌትና የተለያዩ የእጅ ጥበብ መማሪያ ነው። እዛ ለመማር ብዙ ደጅ ብጠናም ቦታው ሞልቷል ብለው መለሱኝ፡፡ በዚህን ጊዜ ትምህርቴን እየተማርኩ አርፌ ተቀመጥኩኝ። ታዲያ አንድ ቀን ቴአትር ቤት ያዩኝ የዘመናይ (ጓደኛዋ) ጓደኞች አኔን ፍለጋ መጥተው አገኙኝ። ብቻ ወደ ትወናው የኔን ልብ ለማሸፈት ሳይመካከሩ እንዳልቀሩ እገምታለሁ። ጋሽ ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) ጢሙን ይላጭልሽና በ‹‹ቴዎድሮስ›› ቲያትር ላይ እቴጌ መነንን ሆኖ ሲሰራ እንድመለከት ተደረገ። ይህን ስመለከት እነሱ ጡት አበጅተው፣ ቂጥ አበጅተው ሲተውኑ እኔ በተፈጥሮዬና በጾታዬ ብሰራው ክፋቱ ምንድነው አልኩና መንፈሴ ጭልጥ ብሎ ወደ ተውኔቱ ገባሁ እልሻለሁ። ” ብላለች::
ይህች ድንቅ አርቲስት ሰላማዊት ገብረሥላሴ ትባላለች:: ለመጀመሪያ ጊዜ ትያትር ስትሰራ ይከፈላት የነበረው ከወንዶቹም በላይ ነው:: በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ተከፋይ እንደሚባለው በወቅቱ ከፍተኛዋ ተከፋይ ሰላማዊት ነበረች:: 12 ብር በወር::
“በዛን ጊዜማ ዕጩ ተዋናይ ተብዬ ብርቅ ነበርኩ ሹሩባዬን እየተሰራሁ ዘናጭ ሆንኩኝ በቃ ከወንዶቹ በላይ የኪስ ገንዘብ ነበረኝ፡፡ የወንዶቹ ሰባት ብር ሲሆን የእኔ 12 ብር ነበር።”
ለዛሬዎቹ ሴት አርቲስቶች ፋና ወጊ የሆነችው አርቲስት ሰላማዊት ገብረስላሴ ፈጣሪ ገነትን እንዲያወርሳት ዘ-ሐበሻ ትመኛለች::
ቴዲ አፍሮ ፓስፖርቱ ተመለሰለት
(ዘሐበሻ) ላለፉት ፫ ሳምንታት ከሃገር እንዳይወጣ ታግዶ የነበረው ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ፓስፖርቱ ተመለሰለት። ፍርድ ቤት ሳያዝ ማን እንደከለከለው ሳይታወቅ በድህነንቶች ፓስፖርቱን ተቀምቶ ሲጉላላ የነበረው ቴዲ ኣፍሮ በዚህ የተነሳ በፊንላንድ እና በሆላንድ ኮንሰርቱን ለመሰረዝና የ፫፪ ሺ ዩሮ ኪሳራ ሊደርስበት ችሉዋል።
የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በተለይም የስርዓቱ ኣፈቀላጤ የሆኑ ሚዲያዎች ቴዲ ከሃገር አንዳይወጣ የተከለከለው ከዓመታት በፊት ይነዳት የነበረችው መኪና ታክስ ባለመክፈሉ በተከሰሰበት ክስ ነው ቢሉም ቴዲ በዚህ ክስ በዋስ የወጣና ክስም ያልተመሰረተበት ከመሆኑም በላይ ፍርድ ቤቱ ከሃገር አንዲወጣ ፈቃድ የሰጠበትን ወረቀት መያዙ ጉዳዩን ፖለቲካዊ ይዘት አንዲኖረው ኣድርጉዋል።
ቴዲ ፓስፖርቱን የያዙበት ደህንነቶች ትናንት የለቀቁለት በመሆኑ ምናልባትም ችግር ካልገጠመው ወደ ኣውሮፓ ሊጉዋዝ ይችላል ተብሉዋል፥፥ ቴዲ በኣውሮፓ ኦስሎ ነገ የሙዚቃ ኮንሰርቱንም ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። የቴዲ ባንድ ከሆላንድ ወደ ኦስሎ ትናንት ያመሩ ሲሆን በነገው ዕለት የሚደረገው ኮንሰርትም በጉጉት እንደሚጠበቅ ከኖርዌይ ለዘሐበሻ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ከ3 ሳምንት እንግልት በኋላ ቴዲ አፍሮ ወደ አውሮፓ በረረ
በክንፉ አሰፋ
ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከ3 ሳምንት እንግልት በኋላ ዛሬ ምሽት ከቦሌ አውሮፕላን ማረፍያ ተነስቶ ወደ ኦስሎ ኖርዌይ ጉዞውን ጀምሯል።
ኢትዮጵያዊው የፖፕ እና ሬጌ ሚዚቃ አቀንቃኝ በአውሮፓ ከተሞች የሙዚቃ ዝግጅቱን ለማድረግ ከአዲስ አበባ ተነስቶ የነበረው በወሩ መጀመርያ ላይ ነበር። ባለፈው ሃሙስ ዲሴምበር 4፣ 2014 ቦሌ አለም ዓቀፍ አውሮፕላን ጣብያ እንደደረሰ የደህንነት አካላት እንዳገቱት እና ፓስፖርቱንም እንደቀሙበት በልዩ ልዩ የዜና ምንጮች መዘገቡ ይታወሳል።
አርቲስቱ ለምን ወደ ውጭ እንዳይወጣ እንደታገደና ፓስፖርቱም ለምን እንደተቀማ እስካሁን በይፋ የተነገረ ነገር የለም። አንዳንድ የዜና ምንጮች ጉዳዩን ቀረጥ ካለመክፈል ክስ ጋር አያይዘው አቅርበውታል። ይህ መላ ምት ፍጹም ስህተት ነው። ምክንያቱም ድምጻዊው በጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መርማሪ ቡድን ሙሉ ቀን ታስሮ ቢውልም ያለምንም ክስ ነበር የተለቀቀው። ቴዲ አፍሮ በዚህ ጉዳይ ቢከሰስ እንኳን አገር ውስጥ ሲገባ ታክስ ያልተከፈለበት መኪና መንዳት ፓስፖርት የሚያስነጥቅ ወንጀል አይደለም። ቴዲ አፍሮ፣ የተጠቀሰውን ተሽከርካሪ የገዛው በሕጋዊ ደረሰኝ ቀረጥ ከፍሎ መሆኑን በወቅቱ ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ ነበር የተለቀቀው።
በጉዞ እገዳው ሳብያ ሁለት የአውሮፓ ኮንሰርቶቹ ተሰርዘዋል። ቀድሞ አውሮፓ የገባው የቴዲ አፍሮ ማናጀር ዘካርያዝ ጌታቸው እና አቡጊዳ ባንድ ስራቸው እንዲተጓጎል ተደርጓል። በአውሮፓ የቴዲ ኮንሰርት ፕሮሞተሮች ለአላስፈላጊ ወጪ ተዳርገዋል። የድምጻዊው አፍቃሪዎቹ ስሜት በእጅጉ ተጎድቷል።
ቴዲ አፍሮ ከጠበቆቹ እና ከስራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ላለፉት አስራ አንድ ቀናት፤ ጉዳዩን ለማጣራት እና እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ አቅሙ የሚፈቅደውን ሁሉ ሲጥር እንደነበርም ታውቋል።
ከሁለት ሳምንታት እንግልት በኋላ በትላንት ምሽት የገዛ ፖስፖርቱን አግኝቷል።
አርቲስቱ ከሃገር እንዳይወጣ መከልከል፣ ፓስፖርቱ መቀማትና እንዲጉላላ ማድረጉ በአብዛኛው ኢትዮያዊ ዘንድ ቁጣ ማስነሳቱን እና በገዥው ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዚህ ከአንድ መንግስት በማይጠበቅ ድርጊት የተነሳ የገዢው ፓርቲ አባላት ሳይቀሩ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ተስተውለዋል።
ቴዲ አፍሮ በነገው እለት ማለትም ቅዳሜ – 20 ዲሴምበር 2014 ኦስሎ ላይ ዝግጅት አለው። ሌሊቱን ተጉዞ አድሮ ምሽቱን ይጫወታል። ባንዱም ኦስሎ ላይ በልዩ ዝግጅት ይጠብቃዋል። ከዚያም በሳምንቱ ማለትም በ 27 ዲሴምበር 2014 በስዊድን ከተማ፤ በ 31 ዲሴምበር 2014 ፍራንክፈርት፤ በ 3 ጃንዋሪ 2015 በሎዛን-ስዊዘርላንድ የሙዚቃ ስራውን ያቀርባል።
ከዚያም በ ጃንዋሪ 10፤ 2015(ለኢትዮጵያ ገና) አምስተርዳም ላይ ልዩ ዝግጅቱን ይዞ ከአቡጊዳ ባንድ ጋር ይመለሳል። ከአምስተርዳም በኋላ ቀጣይ ስራዎቹ ፊንላንድ እና ዱባይ ናቸው።
በዘንድሮው የቴዲ አፍሮ አውሮፓ ኮንሰርቶች ከምንግዜውም የበለጠ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያውያን የሙዚቃ አፍቃሪዎች እንደሚገኙ ይገመታል።
አንጀሊና ጆሊ እና መልካም ሥራዎቿ –“የበጎ ፈቃድ ንግሥት”መባል ያንሳት ይሆን?
አንጀሊና ጆሊ የዛሬ የኪነጥበብ አምድ እንግዳችን ናት፡፡ ይህቺ እንስት ተዋናይት ከትወና ባሻገር በርካታ መልካም ስራዎችን በመሥራት ትታወቃለች፡፡ በኢትዮጵያም ዘሀራ የተባለች ልጅ በጉድፈቻነት እያሳደገች ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በሀገራችን በመምጣት በጎ ስራዎችን አከናውናለች፡፡
አንጀሊና ጆሊ ትውልድና እድገቷ እ.ኤ.አ. 1975 በሎሳንጀለስ ሲሆን የትወና ፍቅር የጀመራት ገና በህፃንነቷ እንደነበር ይነገራል፡፡ ወላጆቿም በትወና ሙያ ያለፉ በመሆናቸው አሁን ለደረሰችበት ከፍተኛ ደረጃ የበኩላቸውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ይነገራል፡፡
በ199ዐዎቹ በወጣትነት እድሜዋ ትወናን ጀምራለች በሊስትራስበርግ ትያትር የተማረች ሲሆን በኋላም ኒውዮርክ ዩንቨርስቲ በመግባት ትምህርቷን ተከታትላለች፡፡ በዚያው ዓመትም ጥሩ ፐርፎርማስ በማሳየቷ ከዝና ማማ ላይ ለመቀመጥ ችላለች፡፡ በዚህም በ1998 በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ እንድትሰራ እድሉን እንድታገኝ ረድቷታል፡፡ በዚሁ ዓመትም የምርጥ የጎልደን ግሎቭ አዋርድን አግኝታለች፡፡ በ1999 እ.ኤ.አ. የመጀመሪያዋን የአካዳሚክ አዋርድን በምርጥ ሴት ረዳት ተዋናይነት ልታሸንፍ ችላለች፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ የሚያግዳት አልተገኘም፡፡ የተለያዩ ይዘት ያላቸው ፊልሞችን መስራትና ብቃቷን ማሳየት ጀመረች፡፡ በዚህ ዓመትም / Lara craf, Taking lives /2004/ እንዲሁም Mrs smith የተሰኘውን ፊልም በ2ዐዐ5 ሰርታ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝታለች፡፡ 2ዐዐ7 አንጂሊና ጆሊ በጣም ምርጥ ብቃት ያሳየችበትን Mariane, pear, pregnant Widow,Mighty Heart. የተሰኙት ፊልሞችን በመስራት ለዕይታ አብቅታለች፡፡ በዚህም በሆሊውድ ምርጥ ተፅእኖ ፈጣሪ ከሚባሉት ሴት ተዋንያን ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች፡፡
አንጂሊና ጆሊ ከተዋናይነትና ከዳይሬክተርነት ባሻገር በበጎ ስራዎቿ ትታወቃለች፡፡ በ2ዐዐ2 የበጎ ፈቃድ ስራዎችን የጀመረችበት ዓመት ነበር፡፡
በዚህም ከካምቦዲያ የጉድፈቻ ልጅ በመውሰድ እንደ ራሷ ልጅ ማሳደግ ጀመረች፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ በማለት ዘሀራ የምትባል ልጅ በጉድፈቻነት ለማሳደግ ወስና ወስዳለች፡፡ በ2ዐዐ5 ባሏ ብራድ ፒት ህጋዊ በሆነ የወረቀት ሰነድ በመፈረም ሁለቱን ልጆች ተቀብሎ አብረው ማሳደግ ጀመሩ፡፡
2ዐዐ6 ለአንጀሊና ጆሊና ለብራድ ፒት ጥሩ ዓመት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የራሳቸውን ልጅ ናሚቢያ ውስጥ አግኝተዋልና ነው፡፡ 2ዐዐ7 ላይ ደግሞ አዲስ የ3 ዓመት ህፃን ከቬትናም በማምጣት የቤተሰባቸው ቁጥር አራት የደረሰበት ወቅት ነበር፡፡ 2ዐዐ8 ላይ ደግሞ የራሷን መንታ ልጆች ወለደች፡፡ በዚህ ወቅት የመንትያ ልጆቿን ፎቶ ግራፍ ለፒፕልና ለሄሎ መጽሔት 14 ሚሊየን ብር ሸጣለች፡፡ በዚህም እስከ አሁን በፎቶግራፍ ሽያጭ ክብረወሰን ለመሆንና ለመቆየት ችሏል፡፡ ነገር ግን አንጀሊና ጁሊ በ2ዐዐ7 በርካታ ስኬቶችንና ልጆችን ያገኘች ቢሆነም በህይወቷ ያዘነችበት ዓመትም ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወላጅ እናቷ በማህፀን ካንሰር በሽታ ለበርካታ ዓመታት ከታመመች በኋላ በ56 ዓመቷ ያለፈችበት ዓመት በመሆኑ ነበር፡፡ አንጀሊና ጁሊ በማህፀንና በጡት ካንሰር ህመም ምክንያት ለበረካታ ጊዜያት በሆስፒታል ቆይታለች፡ ፡ በዚህም ሰርጀሪ ተሰርቶላታል ከህመሟ እንደተፈወሰች በተደጋጋሚ በምትሰጠው ቃለ መጠይቅ ገልፃለች፡፡
ተዋናይቷ ለበርካታ ዓመታት በፍቅረኛነት ከቆየው ብራድ ፒት ጋር በ2ዐ12 ቀለበት አስረዋል፡፡ እንደገና ነሐሴ ወር 2ዐ14 በፈረንሳይ ወዳጅ ዘመድ በተሰበሰቡበት የጋብቻ ሥነ- ሥርዓታቸውን አከናውነዋል፡፡
አጂሊና ጆሊ ከትወና ባሻገር በመልካምና በበጎ ሥራዎቿ የዩናይትድ ኔሽን የበጎ ፈቃድ አምባሳደርነት ማዕረግን አግኝታለች፡ ፡ በዚህም በተፈናቃዮች ካምፖች ውስጥ በካምቦዲያ፣ዳርፉርና ጆርዳን በመዘዋወር በጎ ስራዎችን ሰርታለች፡፡ በዚህ ሥራዋም በ2ዐዐ5 የግሎባል ሂውማን ተሪያል አክሽን አዋርድ ከአሜሪካን ማህበር ለበጎ ስራዎቿ ተበርክቶላታል፡፡
በኢትዮጵያም በርካታ በጎ ሥራዎችን ሰርታለች፤ በተደጋጋሚም ከባለቤቷ ብራድ ፒት ጋር በመሆን ሀገራችንን ጎብኝታለች፡፡
በቅርብም ድፍረት የተሰኘውን በስደት ላይ የሚያጠነጥነውን ፊልም እንዲሰራ ከፍተኛ ድጋፍ ከማድረጓ ባሻገር ፕሮዲውስ በማድረግም ተሳትፋለች፡፡
የአርቲስቶቻችን ክፍያ እና ግነቱ –እውን የአርቲስቶቻችን ክፍያ እንደሚባለው ነው? ነው ወይስ ያጋንኑታል?
የቁምነገር መጽሄት ትንታኔ
መነሻ
በሀገራችን የኪነ ጥበብ ሙያ ውስጥ በሙያው አንቱ የተባለ አንድ አርቲስት ከዓመታት በፊት በአንድ ፊልም ላይ እንዲተውን ጥያቄ ይቀርብለታል፡፡ ጥያቄውን ተቀብሎ በክፍያውም ተስማምቶ ፊልም ይሰራል፡ ፡ የፊልሙ ምረቃ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ከፊልሙ ፕሮውዲውሰሮች መሀከል አንዱ ወደ እዚህ አንጋፋ አርቲስት መጥቶ ስለፊልሙ ምረቃ ሥነሥርዓት ዝግጅት ያጫውተዋል፡፡
ስለ ፊልሙ ምረቃ ዝግጅት ካብራራለት በኋላ ከፊልሙ የምረቃ ቀን ቀደም ብሎ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ስለሚደረገው የማስታወቂያና ገበያ መጥሪያ እቅድ በመንገር የእሱም ትብብር በዚህ ረገድ እንደሚያስፈልግ ይነግረዋል፡ ፡ አንጋፋው አርቲስት ስለ እቅዱ ሁኔታ በጥሞና ሲያዳምጥ ከቆየ በኋላ ‹ታዲያ እኔ በዚህ በኩል ምን አስተዋፅኦ ላደርግ እችላለሁ?› የሚል ጥያቄ ያቀርብለታል፡፡
ፕሮውዲውሰሩ ፊልሙ የተሰራው በአነስተኛ በጀት ቢሆንም ከፍተኛ ወጪ እንደወጣበትና የፊልሙ ተዋንያንም ከፍተኛ ተከፋይ እንደሆኑ የሚገልፅ ማስታወቂያ በየሬዲዮና ጋዜጣ ላይ ለማስነገር አስበናል› ይለዋል፡፡ ‹እናስ?› የአንጋፋው አርቲስት ጥያቄ ነበር፡፡ ‹እናማ አንተም የፊልማችን ዋና መሪ ተዋናይ በመሆንህ የእስከ ዛሬውን የፊልም ክፍያ ሪከርድ እንደሰበርክና ከፍተኛ ክፍያ እንደተከፈለህ አስመስለን ለማስነገር ስላሰብን በዚህ በኩል እንድትተባበረን ነው› አንጋፋው አርቲስት ሁኔታው አልገባውም፡፡ ‹ስለሁኔታው ምናልባት ጋዜጠኞች ደውለው ቢጠይቁህ ግር እንዳይልህ ብዬ ነው› በማለት ሁኔታውን ቀለል አድርጎ ነግሮት ይለየዋል፡፡ ከቀናት በኋላ እሱም ባልሰማው ሁኔታ ‹የሀገራችን የፊልም ክፍያ ሪከርድ ተሰበረ› በሚል ርዕስ በአንድ የኤፍ ኤም ጣቢያ ላይ ስሙ ተጠቅሶ ፊልሙን ከሰራበት ክፍያ በሶስት እጥፍ ከፍ ያለ ገንዘብ እንደተከፈለው ተጠቅሶ ለህዝብ ይተላለፋል፡፡ ይህንን የሬዲዮ ወሬ የሰማችው የአርቲስቱ ባለቤት በማግስቱ ባለቤቷን ታኮርፈዋለች፡፡ ‹ምነው?› ሲላት ‹ለምንድነው በየፊልሞቹ ላይ ስትሰራ የሚከፈልህን ክፍያ ዋጋ የምትደብቀኝ?› ትለዋለች፡፡ አርቲስቱ ውሸት ያደገበት ነገር ባለመሆኑ ‹እንዴት ነው አንቺን የምዋሽሽ?› በማለት ጥያቄውን በጥያቄ ይመልሳል፡፡
በሬዲዮ የሰማችውን የሪከርድ ክፍያ ዜና ዋቢ አድርጋ ስትነግረው የሰራው ስህተት ቁልጭ ብሎ ታየው ፡፡ ለማስታወቂያና ለገበያ መሳቢያ በሚል በቃል ቀለል ተደርጎ የተነገረው ነገር ውሎ ሳያድር ትዳር ለማፍረስ የሚበቃ ወሬ መሆኑ ታወቀው፡፡‹እኔስ ለባለቤቴ እውነቱን በመናገርና በማስረዳት ችግሩን ተወጣሁት፤ በሬዲዮ አማካይነት የተዋሸው የኢትዮጵያ ህዝብንስ እንዴት ብዬ ነው የማሳውቀው?› የአንጋፋው አርቲስት አቤቱታ ነበር፡፡
የአርቲስቶች ክፍያ እንደተባለው ነውን?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአንድ የጥበብ ስራን ጥበባዊ ዋጋ ከክፍያ ጋር የተያያዘ መሆኑን ለማሳየት በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ አንደ አንድ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው ለሥራው የወጣውን ወጪ ከፍ አድርጎ በማቅረብ እየሆነ ነው፡፡ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ሥራ ከፍተኛ ተመልካች አልያም አድማጭ ያገኛል በሚል ስሌት የሚቀርበው የክፍያ አሃዝ ግነት ጥበቡን ከመጥቀም ይልቅ እየጎዳው እንደውም ‹ይሄ ነው እንዴ ይህንን ያህል ወጪ ወጣለበት የተባለው ፊልም/ሙዚቃ?› እስከመባልና ለኪሳራ በር ሲከፍት ይታያል፡፡ ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸው የሚሰሩ ፊልሞችና የሙዚቃ ሥራዎች በሰለጠኑት ሀገራት ከፍተኛ ተቀባይነትና ገቢ ሲያገኙ ይስተዋላል፡፡ የወጣው ከፍተኛ ወጪም የስራውን ደረጃ ለመጠበቅ ስለመዋሉ ሌላ ተናጋሪ ሳይሆን ፊልሙ ወይም የሙዚቃ ሥራው አፍ አውጥቶ ሲናገር ይታያል፡፡ በኛ ሀገር ያለው እውነታ ግን ከዚህ በተገላቢጦሽ ያለ ይመስላል፡፡ ከፍተኛ ወጪ ወጣባቸው የሚባሉትና የሚነገርላቸው ፊልሞች እና ሙዚቃዎች ተገቢ የሆነ የተመልካችና የአድማጭ አትኩሮት ሲነፈጋቸው በአነስተኛ በጀት ብቻ ሳይሆን በጀማሪና ወጣት ተዋንያን የሚሰሩት ሥራዎች ገበያውን ሲቆጣጠሩት ይታያል፡፡
የማስታወቂያ ሥራ አንድን የጥበብ ስራ በሚፈለገው ደረጃ ወደ አድማጭና ተመልካች እንዲደርስ ለማድረግ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ ያለው ቢሆንም ሥራን በአግባቡ ሳይሰሩ በማስታወቂያ ሥራ ላይ ብቻ የማተኮሩ ሁኔታ ከፈረሱ ጋሪው እንዲቀድመው ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ የተጋነኑ አልፎ አልፎም ሀሰተኛ የክፍያ ዜናዎች በይፋ በመገናኛ ብዙሃን ማስነገር ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ጠቀሜታ እንደነበረው የሚናገሩ የፊልምና የሙዚቃ ፕሮውዲውሰሮች አሉ፡፡ በዚህ መንገድም ገና እያቆጠቆጠ ከነበረው የሀገራችን ፊልም ኢንዱስትሪ ላይ ጠቀም ያለ ገቢ የሰበሰቡ ፕሮውዲውሰሮች ስለመኖራቸው ይነገራል፡፡ ቁም ነገሩ ግን በዚህ መንገድ አንዱ ተጉዞ ተጠቃሚ ስለሆነ ብቻ ሁሉም ይህንን ጎዳና መከተል አለባቸው ወይ ? የሚለው ነው፡፡ ከዓመታት በፊት ከመቶ አስከ አምስት መቶ ሺህ ብር ወጪ እንደወጣበት ይገለፅ የነበረው የፊልም ስራ በአጭር ጊዜ ከአንድ ሚሊዮን እስከ ሃያ ሚሊዮን ብር ‹ወጣበት› ሲባል በየመገናኛ ብዙሃኑ ለህዝብ ሲተላለፍ እያደመጥን ነው፡፡ በሙዚቃው ዘርፍም እስከ አራት ሚሊዮን ብር ‹ተከፈለ› የሚሉ ዜናዎች ይነገራሉ፡፡ እውነታውስ?
ጉዳዩ በፊልምና ሙዚቃ ሙያዎች ውስጥ ጎልቶ ይታይ እንጂ በስፖርቱ ዘርፍም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ‹እከሌ የተባለው ተጫዋች በዚህ ያህል ክፍያ ወደ እዚህ ክለብ ተዛወረ › የሚሉ ዜናዎችን በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ማድመጥ የተለመደ ሆኗል፡፡ ከተጫዋቾች ዝውውር ጋር ተያይዞ ያለውን ጉዳይ አሳሳቢነት መነሻ በማድረግም መፅሔታችን የሽፋን ርዕሰ ጉዳይ አድርጋው ነበር፡፡ በቁም ነገር መፅሔት 13ኛ ዓመት ቅፅ 13 ቁጥር 185 ላይ እንደገለፅነው እስካሁን ይፋ በተደረጉት መረጃዎች መሠረት በዚህ ዓመት ክለቦቹ በአጠቃላይ ለተጫዋቾቹ ወጭ ያደረጉት የገንዘብ መጠን 28 ሚሊዮን ብር ገደማ ነው፡፡ ይህ ቁጥር ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ደደቢት ይፋ ያላደረጉትን የዝውውር ወጭ ያላካተተ ነው፡፡ የነዚህ ክለቦች ወጭ ሲደመር ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ ይሁንና ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ሀገሪቱ የምታገኘው ምንም ጥቅም የለም፡፡፡ የዝውውር (የፊርማ) ወጭ በከፍተኛ ሁኔታ (ካላቸው አቅም አንጻር) የሚያወጡት ክለቦችም ሆኑ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን የሚያጡት ክለቦች ከጥቅማቸው የባሰ ኪሳራን ያስተናግዳሉ፡፡
መንግስት በተጫዋቾቹ ላይ የሚቆርጠው ግብር እንደማንኛውም የመንግስት ሠራተኛ በደሞዛቸው ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በአሳዛኝ ሁኔታ በኛ ሀገር ለአንድ ተጫዋች የሚከፈለው ደሞዝ ከፍተኛው በወር 3ሺ 500 ብር ነው፡፡ በ2 ዓመታት ውል ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ከንግድ ባንክ እግር ኳስ ክለብ የተከፈለው ፊሊፕ ዳውዝ የወር ደሞዙ ተብሎ ፔሮል ላይ የተቀመጠው ብር 2800 ብቻ ነው፡፡ መንግስት ግብር የሚቆርጠውም ከ1 ሚሊዮን ብር ላይ ሳይሆን ከወርሃዊ ደሞዙ ላይ ነው፡፡ የሌሎቹም ተጫዋቾች ተመሳሳይ ነው፡፡ ደመወዛቸውና ለፊርማ ተብሎ የሚሰጣቸው ክፍያ የማይገናኝ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ሀገሪቱ ከእግር ኳስ ተጫዋቾች ዝውውር ማግኘት የሚገባትን ገንዘብ እያገኘች አይደለም፡፡ ለውጭ ሃገር ተጫዋቾች የሚከፈለው ገንዘብ ደግሞ ወደ ዶላር ተመንዝሮ ከሀገር የሚወጣ ብር መሆኑ ሲታሰብ ነገሩን የባሰ ያደርገዋል፡፡
የተሻለ ገቢን ለማግኘት ሲባል በማስታወቂያ ሰበብ የተሳሳተና ሀሰተኛ መረጃን ለህዝብ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን የግለሰቦችን ዝና አላግባብ መገንባትም ከሙያ ስነ ምግባር አንፃር እንዴት እንደሚታይ ግልፅ አይደለም፡፡ በተለይም ግለሰቦች ባገኙት ልክ ግብር መክፈላቸው ተዘንግቶ ያላገኙትን ገቢ እንዳገኙ አስመስሎ ማስነገር ከህግ አንፃር እንዴት እንደሚታይ ያነጋግራል/ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የስራ ኃላፊ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ በገፅ 8 ላይ ይመልከቱ /፡፡
የቁም ነገር መፅሔት የጋዜጠኞች ቡድን ባለፉት ዓመታት በመገናኛ ብዙሃን ስም ተጠቅሰው የተላለፉ የአርቲስቶች ክፍያ ዋጋዎችን ለመመርመርና እውነተኛነቱን ለማረጋገጥ ሙከራ አድርጓል፡፡ ሙከራው ራሳቸው አርቲስቶቹ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርበው የተናገሩትና በይፋ ያረጋገጡትን ይጨምራል፡፡
አርቲስት ሔለን በድሉ
ይህቺ ወጣት ተዋናይት በተለያዩ ፊልሞች ላይ ስትሰራ ትታወቃለች፤ በቅርቡም በተጠናቀቀው ሰው ለሰው ድራማ ላይ ስትተውን የነበረችው ሔለን በቅርቡ ይወጣል ያለችው አዲስ ፊልም ላይ እንድትተውን 80ሺህ ብር እንደተከፈላት መፈራረሟን በጥር ወር 2006 ከታተመው ላይፍ መፅሔት ጋር ያደረገችው ቃለ ምልልስ ላይ ተናግራለች፡፡
አርቲስት መሐመድ ሚፍታ
መሐመድ ቀደም ሲል በሞዴሊንግ ሙያ ላይ የተሰማራና በተለያዩ መድረኮች ላይ የሚታይ ወጣት ነው፡፡ የዛሬ ሶስት ዓመት የተጠናቀቀው ገመና የቲቪ ድራማ ላይ በመተወን ወደ ፊልሙ ዓለም የተቀላለቀለው መሐመድ ወደ እውቅና ማማ ላይ የወጣው ወዲያውኑ ነው፡፡ መሐመድ ከፊልም ስራው በተጨማሪም የተለያዩ ድርጅቶችን ምርት ለማስተዋወቅ የማስታወቂያ ሞዴል ሆኖ የሚሰራ ሲሆን የዛሬ ዓመት ገደማ ‹ስማድል› ለተባለው ሞባይል ለሁለት ዓመት የማስታወቂያ ሞዴል ለመሆን 400 ሺህ ብር እንደተከፈለው በመጋቢት ወር በተላለፈ የታዲያስ አዲስ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ቀርቦ ተናግሯል፡፡
ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ደግሞ ተቀማጭነቱ ሳውዲ አረቢያ የሆነ አንድ የንግድ ተቋም መሀመድን በ30 ሺህ ዶላር /600ሺህ ብር/ የማስታወቂያ ሞዴል ሆኖ እንዲሰራ መፈራረሙ በኢትዮፒካ ሊንክ ፕሮግራም ላይ ለህዝብ ተላልፏል፡፡
አርቲስት ሚኪያስ መሐመድ
ባለ ታክሲው በተሰኘው የመጀመሪያ ፊልሙ ተቀባይነትን ያገኘው ወጣቱ ተዋናይ ሚኪያስ መሐመድ በቅርቡ ተመርቆ ለእይታ በበቃው የመቅደስ በቀለ ማክዳ ‹ሊነጋ ሲል› ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት ይሰራል፡፡ ከዚሁ ፊልም ምረቃ ጋር ተያይዞ በታዲያስ አዲስ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ የተላለፈው ዘገባ እንደሚያመለክተው ከሆነ ሚኪያስ መሐመድ በዚህ ፊልም ላይ ለመስራት ብር 400 ሺህ ተከፍሎታል፡፡ ይህንን ክፍያ ስለማግኘቱም ሚኪያስ በፕሮግራሙ ላይ ቀርቦ አረጋግጧል፡፡
ድምፃዊት ሔለን በርሄ
ወጣቷ አቀንቃኝ ሔለን በርሄ የመጀመሪያ አልበሟን ተከትሎ የተለያዩ ፊልሞችን የማጀቢያ ሙዚቃ እንድትሰራ ጥያቄ የቀረበላት አርቲስት ነች፡፡ በ2003 ዓ.ም ተመርቆ ለእይታ የበቃውን ‹ፔንዱለም› ፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ የሰራችው ሔለን ለዚህ ነጠላ ዜማዋ ብር 100 ሺህ ከፕሮዲውሰሩ ቶም ፊልም ፕሮዳክሽን እንደተከፈላት በኢትዮፒካ ሊንክ ፕሮግራም ላይ ተናግራለች፡፡
ዝናህ ብዙ ፀጋዬ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በልዩ ልዩ ፊልሞች እና የቴሌቪዥን ድራማ ላይ በመስራት የሚታወቀው አርቲስት ዝናህብዙ በሙያው የፊልም ባለሙያ ባይሆንም በየተሳተፈባቸው ፊልሞች ላይ ብቃቱን እያሳየ ያለ አርቲስት ነው፡፡ ዝናህብዙ በፊልም ሥራ ላይ ብቻ ሳይሆን በማስታወቂያ ሥራዎች ላይም ከፍተኛ ተከፋይ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ በቅርቡም
መስከረም 10 ቀን 2007 ዓ.ም በኢትዮፒካ ሊንክ ፕሮግራም ላይ በቀጥታ ስልክ ላይ ቀርቦ ዘሚሊ ለተባለው ፋብሪካ ለአንድ ዓመት ማስታወቂያ ለመስራት አንድ መቶ ሺህ ብር፤ ለካንጋሮ ጫማ ፋብሪካ ማስታወቂያ ደግሞ ለሁለት ዓመት ኮንትራት 200 ሺህ ብር እንደተከፈለው ተናግሯል፡፡
ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ/ ጆሲ/
ዮሴፍ ገብሬ ጆሲ ኢን ዘ ሀውስ/ዮሴፍ በቤት ውስጥ/ የተሰኘ ፕሮግራም በኢቢኤስ ቲቪ ላይ የሚያቀርብ አርቲስት ሲሆን በቅርቡ ‹መቼ ነው› የተሰኘውን ሁለተኛ አልበሙን ለአድማጭ አቅርቧል፡ ፡ ጆሲ ይህንን አልበሙን ሰርቶ ለአድማጭ ለማቅረብ ከፍተኛ ወጪ ማውጣቱንና ከአልበሙ ሽያጭ ላይም 193ኛ ዕትም የተወሰነ ገቢውን የበጎ አድራጎት ስራ ለሚሰራ ድርጅት ለመስጠት መወሰኑን በገዛ ፕሮግራሙ ላይ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ ተናግሯል፡፡ መስከረም 24 ቀን 2007 ዓ.ም በተላለፈው በታዲያስ አዲስ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሆኖ ቀርቦም ‹ዳሽን ቢራ› አልበሙን ሁለት ሚሊዮን ብር ስፖንሰር እንዳደረገውና እንደከፈለው ተናግሯል፡፡
አርቲስት /ሞዴል ሳያት ደምሴ
ሳያት ደምሴ ወደ ኪነጥበቡ ዓለም ከመግባቷ በፊት የምትታወቀው በቁንጅና ውድድር
ላይ ተሳትፋ ‹ሚስ ኢትዮጵያ› የተሰኘውን ውድድር በማሸነፏ ነው፡፡ ሳያት ከቁንጅና ውድድሩ በኋላ መጀመሪያ ፊልም ከዚያም ወደ ሙዚቃው ዓለም ገብታ የመጀመሪያ አልበሟን ከሶስት ዓመት በፊት ለአድማጭ አቅርባለች፡፡ ህዳር 13 ቀን 2007 ዓ.ም የወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ በፊት ለፊት ገፁ ላይ የሳያት ደምሴን ፎቶግራፍ በማድረግ ከአንድ የጀርመን ኩባንያ ጋር እጅግ ከፍተኛ በሆነ ክፍያ ፊልም ልትሰራ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ሳያት (የጋዜጣው ዘገባ እውነት ከሆነ) በዚህ ፊልም ላይ በመስራቷ በሀገራችን ታሪክ ከፍተኛዋ የፊልም ተከፋይ ትሆናለች ይላል ጋዜጣው፡፡ ነገር ግን ሳያት በፊልሙ ላይ በመስራቷ ከፍተኛ ክፍያ ታገኛለች ተባለ እንጂ ምን ያህል ክፍያ እንደምታገኘ ጋዜጣው አልጠቀሰም፡፡ ክፍያውን የተመለከተ ህጋዊ የውል ስምምነት ከፊልሙ ፕሮውዲውሰሮች ጋር ስለማድረጓም የተባለ ነገር የለም፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ አርቲስት ሳያት ደምሴን አግኝተን የተባለው ነገር እውነት ስለመሆኑና ስለ ውል ስምምነቷ ለመጠየቅ ያደረግነው ሙከራ/ ስልኳ ከአገልግሎት ውጪ ነው ስለሚል/ ለጊዜው አልተሳካልንም፡፡ ሳያት በማንኛውም ጊዜ የዜናውን ትክክለኛነት ሊያረጋግጥ የሚችል ህጋዊ መረጃ ካላት ለአንባቢያን ለማቅረብ የምንችል መሆኑን እንገልፃለን፡፡
የአርቲስቶቹ ምላሽ ምንድነው?
በጉዳዩ ዙሪያ ስማቸው የተጠቀሱ አርቲስቶችን በተመለከተ አግኝተን ለማነጋገር ሙከራ ያደረግን ሲሆን የአንዳንዶቹ ስልክ ዝግ ሲሆን የሌሎቹ ስልክ ምላሽ አይሰጥም ወይም አያነሱትም፡ ፡ ካገኘናቸው አርቲስቶች መሀከል የአንዳንዶቹ ምላሽ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
አርቲስት ዝናህብዙህ ፀጋዬ ከሁለቱ ድርጅቶች ጋር የተደረገው ስምምነት ትክክል እንደሆነና የውሎቹ ማለቂያ ቀን ጊዜ በቅርቡ የሚጠናቀቅ በመሆኑ በስራውም ለውጥ እየታየበት በመሆኑ ከዚህ የተሻለ ክፍያ ለማድረግ እየተነጋገረ እንደሆነ ለቁም ነገር መፅሔት ተናግሯል፡፡ ያልተከፈለን ክፍያ አጋኖ ማቅረብ ህዝብን መዋሸት እንደሆነ የገለፀው ዝናህብዙ ከድርጅቶቹ ጋር የተደረገውን የውል ስምምነት ለማሳየት እንደሚችልና ከአንድ ሳምንት በኋላ ለመገናኘት ቀጠሮ ጠይቋል፡፡
አርቲስት መሀመድ ሚፍታ ከሁለቱ ድርጅቶች ማለትም ከስማድልና ከሳውዲው ኩባንያ ጋር የማስታወቂያ ስራ እንደሚሰራ አረጋግጦ ዝርዝር ምላሽ ለመስጠት ግን የፊልም ቀረፃ ላይ በመሆኑ መልሶ እንደሚደውል ገልፆ ስልኩ ተዘግቷል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊነት
መገናኛ ብዙኃን በእውነት ላይ የተመሰረተ መረጃ ለህዝብ ማቅረብ ዋና ስራቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር በጋዜጠኞች አማካይነት ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ዘገባዎች በመረጃ ላይ የተመሰረተና ተአማኒነት ያለው መሆን እንዳለበት መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው፡፡ በጓደኝነትም ሆነ በትውውቅ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚቀርቡ ተመሳሳይ መረጃዎች እውነት ሆነው ካልተገኙ የተአማኒነት ችግር እንደሚፈጥሩ ግልፅ ነው፡፡ በመሆኑም ትክክለኛና ህጋዊ አሰራሮች በተግባር መመልከት የማንኛውም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑ ሳይዘነጋ ገንዘብንም ሆነ ሌሎች የግል ዝናን የሚያገዝፉ ዘገባዎች ለህዝብ ሲተላለፉ በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ሊሆኑ ይገባል፡፡
ህብረተሰቡ በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርብለትን ዘገባ አምኖ የሚቀበለው ጋዜጠኞች ሁኔታውን ‹አረጋግጠው ነው› በሚል እምነት በመሆኑ ከክፍያ ጋር የተያያዙ ዘገባዎች በውሎች የታሰሩ መሆኑን ማረጋገጥ የጋዜጠኞች ሃላፊነት ነው፡፡ አለበለዚያ ለማስታወቂያና ለግል ዝና መገንቢያ በሚል ‹እከሌ ይህን ያልህ ተከፈለው› የሚለው ዜና የተአማኒነት ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርምና ጋዜጠኞች ለሙያቸው ክብር ሊሰጡ ይገባል፡፡
በነገራችን ላይ እስከ ዛሬ ድረስ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ከክፍያ ጋር ተያይዞ ስማቸው የተጠቀሱ አርቲስቶች የተባለው ነገር እውነት መሆኑን በማስረጃ ለማቅረብ ፍላጎቱ ካላቸው ዝግጅት ክፍላችን አሁንም በሩ ክፍት እንደሆነ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
አንድ ምሽት ከቴዲ አፍሮ ጋር በፍራንክፈርት
የቴዲ አፍሮ ዝግጅት በፋራንክፈርት ሲደረግ በቦታው ተገኝቼ ነበር ። ብዙ ጊዜ ዘፋኝ ሲመጣ አልገኝም ። ዘንድሮ ግን ወያኔ በእሱ ላይ ያደረገውን ተንኮል መቃወም የሚቻለው በዝግጅቱ በመገኘት በመሆኑ ሰብሰብ ብለን ተገኝተን ነበር። ሰልፉ ሳይጠነክር ቀደም ብለን ለመግባት በጊዜ ነበር የደረስነው። ሰዓቱን ጠብቀን ከፍለን ገባንና ጥግ ላይ ወንበር ፈልገን መጠበቅ ጀመርን ። እሱ ወደ መድረክ እስከሚወጣ በልዩ ልዩ ዘፈን እየተዝናናን ቆየን ። ወጣት ይጎርፋል፣ አለባበስ ይታያል፣ ዓመት በዓሉን ዓመት በዓል አስመስለውታል። የአዲስ ዓመት ዋዜማ . . . ለቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ዝግጅቱ ተጠናቋል። አዳራሹ እኩለ ሌሊት ላይ እየሞላ መጣ።
የሚጠበቀው ቴዲ አፍሮ ወደ መድረክ ሲወጣ ወጣቶች ያብዱ ጀመር። እሱ “ፍቅር ያሸንፋል“ ይላል። ወጣቶቹ ይጮኻሉ። “እወዳችኋለሁ“ ሌላ ጩኸት። አዳራሹ ድብልቅልቅ አለ ! ደስታና ጩኸት ይፈራረቁ ጀመር። ለአንድ ጊዜ እንኳን ቢሆን ይህንን ዓይነት አቀባበል የኢትዮጵያ ገዥዎች መቼ ይሆን የሚያገኙት ? ብዬ አሰብኩ። በ2015 ይኽንን ብመኝ የተጋነነ ይሆናል?
በተከታታይ አራት ዘፈን ተዘፈነ ። ልዩ ልዩ ዓይነት ጭፈራ ታየ ፣ ውስጥ ሙዚቃ ፣ ደጅ ርችት ፣ መድረኩ ላይ ጭፈራ ቀለጠ ። 2015 በደስታ ተጀመረ ። ለዛሬም ቢሆን ችግራችንን ሁሉ ልንረሳ የተስማማን ይመስላል። ተስፋችንን አንግበን ለፍቅር የተነሳን ሆንን። ፍቅር ያሸንፋል ቴዲ ፣ እኛም ያሸንፋል . . . ። አጠገቤ የነበረው ጓደኛዬ ግን ዘመን መቀየሩን ረስቶት ያሸንፋል እያለ ግራ እጁን ቡጢ ጨብጦ መፈክር ያሰማል። ሌላው አውርድ እጅህን እዚህ ቡጢ አያስፈልግም ይለዋል። የፍቅር ጠላቶችን አደቅበታለሁ ሲል ተሳሳቅን። ወጣቱ መድረኩ አካባቢ እኛ ጥግ ጥጉን ይዘን እስክስታውን ወረድነው።በቴዲ ዘፈን ምንጃርኛም ይሞከራል። ያልተሞከረ አልነበረም። ፍራንክፈርት ቀለጠች . . . ቤት የቀረም ሰው ያለ አይመስልም . . . አዳራሹ ምንም ትልቅ ቢሆን ተጨናንቋል። አዲስ ዘመን በአዲስ ተስፋ ተጀመረ።
እንደ ድንገት አንድ ወጣት ከጭፈራው ብዛት ደክሞት አጠገቤ ተቀመጠ።
ደከመህ ? ብዬ ጠየቅሁት ።
ጭንቅላቱን በማወዛወዝ አዎን አለኝ።
ትንሽ ትንፋሽ እሲከያገኝ ጠበቅሁና ቴዲን ትወደዋለህ ? መልሱን በአማርኛ ስጠብቅ በትግርኛ ቀጠለ። በንግግር ልንግባባ አልቻልንም። አማርኛ አይችልም። ቴዲ አዲስ ዘፈን ሲጀምር ወጣቱ አብሮት ይዘፍናል። ወጣቱ የቴዲን ዘፈን በቃሉ ያወርደዋል። ከቴዲ አፍሮ ጋር በዘፈን ይግባባሉ። ከእኔ ጋር ግን በቋንቋ ልንግባባ አልቻልንም። ለዘመናት የቆየው ጦርነት ምክንያት የወጣቱን ቋንቋ አለመናገራችን ይሆን?? ሃሳብ መጣ ። አሁን ስለ ወጣቱ የማወቅ ፍላጎቴ ጨመረ ።
ሁሉን ዘፈን ታውቀዋለህ ?
አሁን ገባው መሰለኝ አዎ ሁ.. ሉ ን አለኝ በአማርኛ በትግርኛ አነጋገር ። ገና ዘፈኑ ከማለቁ በፊት ልጁ እየሮጠ ወደ ዳንሱ ገባ ። እኔን ጥሎ ከቴዲ ጋር በሙዚቃ ሊግባባ ከነፈ . . . ።
ከጎኔ የነበረው ለጭፈራ የሄደው የጓደኛዬ ትርፍ ቦታ ለወጣቶች መተዋወቂያ ጠቀመኝ ። አንዲት በረጅም ጫማ ላይ የቆመች ወጣት መጣች ።
“መቀመጥ ይቻላል?“ እየተቅለሰለሰች ጠየቀችን ። ባለቤቱ እስከሚመጣ ፈቀድኩ ።
“ይህ ጫማ እግርሽን አያደክመውም?“ ወሬ መጀመሪያዬ ሆነ ።
“ትለምደዋለህ ፤ ከዚያ ብዙም አይሰማህም።“ ስለ ጫማው አስረዳችኝ።
“እዚህ ሃገር ቆይተሻል?“ የሚቀጥለው ጥያቄ ነበር ።
“ ገና አራት ወሬ ነው ?“
“ገና አዲስ ነሻ ? ”
” አዎ ነኝ።”
“የት ነው የተመደብሽ ? ” ከፍራንክፈርት ራቅ ያለ ቦታ ጠራችልኝ ።
“እና ለቴዲ አፍሮ ብለሽ ነው ከዛ ድረስ የመጣሽው ? ”
“ታዲያስ!” አለችኝ በመደነቅ ። አመላለስዋ ለቴዲ ያልተመጣ ለማን ይመጣል? የሚል ጥያቄ ያዘለ ይመስላል።
ቴዲ አዲስ ዘፈን ጀመረ ። ጥያቄዬን ሳልጨርስ ጥላኝ ነጎደች። ጫማዋን ግን እዛው ጥላው በረረች።
እኔም በተራዬ መድረኩ ጋር ብቃ አልኩ። ከዘፈኖቹ ማህል ቴዲ መፈክሩን ያሰማል። “ ፍቅር ያሰኝፋል“ ወጣቶቹ በሞላ በአንደነት እንደ መፈክር ይደግሙታል ። ሲዘፍን ይከተሉታል ፣ ቴዲ አውቆ ማሕል ላይ ሲያቆም እነርሱ ይሰማሉ ። በዚህ ምሽት ሁሉም ደናሽ ፣ ሁሉም ዘፋኝ ሆኗል ። ጩኸቱ ስለበዛ ለዕረፍት ወደ ውጭ ወጣ አልኩ ። አዳራሹ ውስጥ አንድ ሺህ የሚሆን ሰው አለ ። ደጅ ከ200 -300 የሚሆን ሰው ለመግባት ቆሟል። ይህ ሁሉ ሰው እንዴት ሊሆን ነው ራሴን ጠየቅሁ ። ሕዝብ እንደ ጉድ ይጎርፋል። ይዘፈናል ይጨፈራል፣ ይፈከራል ፣ ቴዲ እውዳቸኋለሁ ይላል፣ ወጣቶቹም በጩኸት ፍቅራቸውን ይገልጹለታል።
ተመልሼ ቦታዬ ተቀመጥኩ ። አሁን ከብዙ ወጣቶች ጋር ተዋወቅሁ። ቦርሳና ጫማ እኔጋ እያስቀመጡ መሄድ ተጀመረ ። ለዚህ የታማኝነት ሥራ በመብቃቴ አልከፋኝም ። ወጣት ሲደሰት ከማየት በላይ ምን የሚያስደስት ነገር አለ ። ኢትዮጵያ ፣ ኤርትራ የሚለው ነገር ቦታ አልነበረውም ። ቴዲም ያውቅበታል፣ ፍቅር ያሸንፋል ! እያለ ፍቅርን ይዘራዋል። ወጣት በቡድን ሆኖ አብሮ ይጨፍራል። የመግባቢያ ቋንቋ የቴዲ ዘፈን ሆኗል። እኔም ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ የጫማና የቦርሳ ጥበቃዬን በሰፊው ይዠዋለሁ። ተስማምቶኛል። አይሆንም ብዬ በዘመኑ ቋንቋ አላካብድም ።
ሌላ መጣ ቦታ ጠየቀኝ ። የተለመደው መልስ ተሰጠው ። ኤርትራዊ እንደሆነ ገብቶኛል። ቀስ በቀስ ተግባባን። ለምንድነው ቴዲን የምትወዱት ?
“ቴዲ እንደ ሌሎቹ አያካብድማ ? ኤርትራ ፣ ኢትዮጵያ ገለመሌ ፣ ገለመሌ አይልም ። ይመቻል። ዛሬ እዛ ፍራንክፈርት ሌላም ዘፈን አለ ። “ማህበረኩም“ ያዘጋጀው ነው ። ከአስመራ የመጡ ታዋቂ ዘፋኞች አሉ። እዛ ማንም አልሄደ ፣ እዚህ ነው የመጣነው።” ብዙ ነገር አስረዳኝ ። እኔም “ማህበረኩም“ ምን እነደሆነ ማጣራት ጀመርኩ ። የሻብያ እጅ ያለበት ድርጅት እንደሆነ ሰማሁ። ገረመኝ ሻዕብያን በዘፈን ማሸነፍ ተቻለ ማለት ነው ? “ቦለኛ“ የሚተሰኘ የቀድሞ የኤርትራውያን የዘፈን ዝግጅት ታሰበኝ ። ያኔ ወርቅና ጌጥ ሳይቀር የሚሰጥበት ዘመን ነበር ። የዛን ጊዜ ማነው ከቦለኛ የሚቀር። አሁን ግን ቴዲ በዘፈን አሸነፈ ። የወጣቱን ፍላጎት የወያኔም፣ የሻዕብያም እንዳልሆነ ታዬ . . . የምን ጦርነት ፣ የምን የሕዝብ እልቂት ፍቅር ያሸንፋል ። ወጣት ተሰብስቦ አንድ ላይ ይጨፍራል ፣ ይፋቀራል፣ ይዝናናል . . . የጦርነት ጡሩምባ ለዛሬም ቢሆን ቆሟል . . . የክፍፍል አባዜ ቆሟል ቴዲ የፍቅር ጦሩን ይዞ ዘመቻውን ካለውጊያ ቀጥሏል።
በዚህ ምሽት አንድ ነገር ተመኘሁ በሚቀጥለው ዓመት እነዚህን ወጣቶች የሚያፋቅር ፣ የቴዲ አፍሮን ጥሪ ቀጣይነት ተመኘሁ። ፍቅር የሚያሸንፍበት ቢሆን ብዬ ተመኘሁ። እነዚህ ወጣቶች የሚያፍሩበትን ሳይሆን የሚኮሩበትን ሃገር ተመኘሁ። ቴዲ አፍሮን አሥመራ ንግስት ሳባ ስታዲዩም ውስጥ መድረክ ላይ ሆኖ ፍቅር ያሸንፋል ሲል መስማትን ተመኘሁ። ከሁሉ በላይ ግን ማካበድን የማያውቅ የወጣትነትን ዘመን ተመኘሁ። . . . በወያኔና በሻብዕያ ትምክህት ሊገዳደሉ የሚችሉ ወጣቶች በአንድነት ሲጨፍሩ ማየትን የመሰለ መልካም ስጦታ ከቴዲ አፍሮ 2015 ተሰጠን። እኛም በደስታ ተቀበልነው ።
ስለ ሕዝብ ፍቅር የሚዘፍኑ በሰላም ይክረሙ !
01.01.2015
ፍራንክፈርት
ሳይንስና ሙዚቃ
ከኢሳያስ ከበደ
‹‹ይህ ሰው እጅግ ብዙ ጥልቅ አሳቦችንና ጠንካራ ስሜቶችን በአንድ የሙዚቃ ሥራ ውስጥ መክተብ ችሏል፣ ለዛውም በአንዲት ትንሽ የሙዚቃ መሳሪያ ይሞዝቁ ዘንድ፡፡ ይህ ድንቅ ድርሰት በሚወለድበት ወቅት በፀሐፊው ቦታ ራሴን ከትቼ ሳስበው ከአቅሜ በላይ የሆነ ልዩ የሀሴት ስሜት ራሴን ሲያስተኝ ይታየኛል›› ይህ ጥቅስ ጆሃነስ ብራሃምስ የተባለ የ19ኛው ክፍለ ዘመን እውቅ ሙዚቀኛ የጆሃን ሰባስቺያን ባህ (በልዩ ተሰጥኦው ከምን ጊዜም የዓለም የሙዚቃ ሃያላን አንዱ) ድርሰት የሆነውን partita in D minor for Solo Violin አስመልክቶ የተናገረው ነው፡፡
ቻኮን የዚህ ድርሰት የመጨረሻ ክፍል ስያሜ ሲሆን ብራሃምስ ለግራ እጅ ብቻ የፒያ ጨዋታ እንዲሆን አድርጎ እንደገና አዘጋጅቶታል፡፡ ቻኮን ተጫዋቹን እጅግ በጣም የሚፈትንና አድማጩን በከፍተኛ የስሜት ማዕበል የሚያናውጥ ቅንብር ነው፡፡ ታዲያ ይህንኑ ውብ ስራ ለአዲስ አበባ ጆሮ ለማድረስ ኒኮላ ስታቪ የተባለ የተካነ ፈረንሳዊ ፒያኒስት ከጥቂት ወራት በፊት በጣልያን የባህል ማዕከል ተገኝቶ ነበር፡፡ ጣዕመ ሙዚቃውን በቦታው ተገኝቼ ካደመጥኩ በኋላ ሳይንቲስቶች የሚሰሩት ሥራ አርቲስቶች ከሚሰሩት ስራ ጋር ያለውን አንድነት የበለጠ ለማስተዋል ችያለሁ፡፡
መጀመሪያ ፈጠራን እንመልከት፡፡ ቻኮንን ለመድረስ ዓመታት ፈጅቷል፤ ምክንያቱም ጥልቅ አሳቦችንና ስሜቶችን የሚወክል ሙዚቃዊ መግለጫ ከራስ ጭንቅላት ማፍለቅ ጊዜ የሚወስድ፣ ትዕግስትንና ልዩ የፈጠራ ችሎታን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አንድን ንድፈ ሃሳባዊ ፊዚሲስት (Theoretical physicist) ለምሳሌ ብናነሳ፣ ውስብስብ የሆነ መስተጋብር ካላቸው ብዙ የተፈጥሮ ገፅታዎች መካከል ውስን የሆኑትንና ተፅዕኗቸው ተነጥለው መታየት የሚችሉትን ገፅታዎች መወከል የሚችሉ ሒሳባዊ ሞዴሎች አስሶ ማግኘት አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሌሎች ያላዩትን አድማስ ከተለመደው የአስተሳሰብ አጥር አሻግሮ ለማየት የሚያስችል አይነ ህሊና ይጠይቃል፡፡
አካባቢን ያለምንም መርጃ መሳሪያ (በአሁኑ ማሳያ፣ ያለ ሙዚቃ ወይም ያለ ሳይንስ) አተኩሮ በመመልከትና በማሰብ ብቻ ለመረዳት አዳጋች የሆኑ የተሸፈኑ ምስጢሮች ጊዜም ቦታም ሳይገድባቸው በብዛትና በየዓይነት ይገኛሉ፡፡ የሰው ልጅ ድንቅ የሆነ አዕምሮውን ተጠቅሞ ይኸው የራሱ አዕምሮ በሚገባ ማገናዘብና ማላወስ የሚችላቸውን ሞዴሎች (በአሁኑ ማሳያ፣ የሙዚቃ ድርሰት ወይም ሒሳባዊ ቀመር) ፈልስፏል፡፡ ይህ የፈጠራ ስራ ጥግ ነው፡፡ የፈጠራ ስራው አቀማመር ልቀት ደግሞ ለሰዎች ስሜት ቅርብ የሆነ ውበት አለው፡፡ ይህ ሃሳብ ውበትን ወደሚመለከተው ሁለተኛው ነጥብ ያሻግረኛል፡፡
ሊ ስሞሊን (ሳይንቲስትና የኖቤል ሽልማት ባለቤት) ‹‹The life of the cosmos›› በተሰኘው መፅሐፉ ውስጥ ሳይንቲስቶችና አርቲስቶች በውበት ላይ የሚጋሩትን አቋም እንዲህ ፅፎታል፡፡ ‹‹ሳይንቲስቶች ልክ እንደ አርቲስቶች ሁሉ ስለ ስራቸው ውበት ይጨነቃሉ፡፡ በተለይም ንድፈ አሳባዊ ፊዚሲስቶች እና የሒሳብ ሊቆች ተፈጥሮን በደፈናው በድጋሚ ከሚያስቀምጡና ከሚዘግቡ መግለጫዎች ይልቅ ተፈጥሮን በልዩ ልዩ መንገዶች መወከል የሚችሉ ፈጠራዎች ለስራቸው ድንቅ ውበት እንደሚያጎናፅፉላቸው ያምናሉ፡፡ አርቲስቶችም ይህንን ሀሳብ ይጋራሉ››
ሳይንስና ሙዚቃን የሚያዋድደው ሶስተኛው እሴት ስርዓት ይመስለኛል፡፡ ሰባስቺያን ባህ የሙዚቃ መሳሪያ ድምፅን በመጠቀም ልዩ ስሜት እና አስተውሎት ወደ አድማጭ አሻግሯል፡፡ ይህንን አይነት ስራ ለመስራት ሙዚቃው ከስሜት ጋር ያለውን ቁርኝት በሚገባ ከማወቅ ባሻገር ሙዚቃውን ለመናገር የሚያስችል ልዩ ቋንቋ አቀላጥፎ ማወቅ ያሻል፡፡ አንድ የልብ ወለድ ደራሲ ያዳበራቸው ብዙ የቋንቋ ክህሎቶችና የሚከተላቸው የሰዋሰው ህጎች እንዳሉ ሁሉ ሰባስቺያን ባህ ቻኮንን በዘፈቀደ አልደረሰውም፡፡
ለፒያኖ አጨዋወት የተመቸ፣ በዓመታት የሚዳብር የጣት ቅልጥፍና የስርዓቱ አንድ አካል ነው፡፡ የሞት፣ የቅኝት ወዘተ የሙዚቃ ለዛ መገለጫዎችን ሳያዛቡና በዘመኑ ከነበረው የባሮክ የሙዚቃ ስልት ህግጋት ሳይፈነግጡ የፈጠራ ስራ ማመንጨት መቻል ሰባስቺያን ባህ ጠንቅቆ ያከበረው ሌላኛው የስርዓቱ አካል ነው፡፡
ሪቻርድ ፋይንማን (ምናልባትም ከአልበርት አይንስታይን ቀጥሎ በንድፈ አሳባዊ ፊዚክስ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሮ ያለፈ) እንዳለው ከሆነ ‹‹ሳይንሳዊ ፈጠራ በመገደቢያ እርከን ውስጥ የሚገኝ አይነ ህሊና›› ነው፡፡ አሁንም እንደገና ከንድፈ አሳባዊ ፊዚክስ ሳንወጣ የዚህን ጥቅስ አንድምታ ማጤን እንችላለን፡፡ የመገደቢያው እርከን በቀጥታ ስርዓትን ይመለከታል፡፡ በምስልና በሀተታ አካባቢን የመግለፅ ችሎታ የሳይንስ ቋንቋ አጋዥ ክህሎቶች ቢሆኑም ቅሉ ዋናው መሳሪያ ሒሳብ ነው፡፡ ሒሳብ በተጠየቃዊና ምክንያታዊ አካሄድ ወይም ስነ አምክንዮ የተዋቀረና ተፈጥሮን የሚወክል ሞዴል ለመገንባት ፍፁም ተስተካካይ ያልተገኘለት የሰው ልጅ ድንቅ የፈጠራ ውጤት ነው፡፡ በሒሳብ ክህሎት በሚገባ ያልተካነ ግለሰብ ስኬታማ ፊዚሲስት መሆን አይችልም፡፡
ሰባስቺያን ባህ የሞት፣ የቅኝት ወዘተ የሙዚቃ ለዛ መገለጫዎችን ሳያጣርስና ከባሮክ የሙዚቃ ስልት ማዕቀፍ ሳያፈነግጥ ድንቅ ሥራዎችን በሙዚቃ መስራት እንደቻለው ሁሉ አንድ ንድፈ አሳባዊ ፊዚሲስት፣ እንበል አልበርት አይንስታይን፣ አዲስ ግኝት ለማድረግ ሲነሳ ቀደም ሲል ትልቁን የሳይንስን የእውቀት ማህደር መቀላቀል የቻሉ ንድፈ አሳቦችን በዘፈቀደ መናድ አይችልም፡፡
አልበርት አይንስታይን የሳይንስ የእውቀት ማዕቀፍን ሳይተላለፍ፣ አስገራሚ የዓይነ ህሊና ተሰጥኦውን ተጠቅሞ፣ ተፈጥሮን መወከል የሚችሉ ልዩ ሒሳባዊ ሞዴሎችን አበርክቷል፡፡ የብርሃን ጨረር በውስን ፍጥነት እንደሚጓዝ የሚገልፀው የማክስ ፕላንክ ንድፈ ሐሳብ በአንድ ወገን፣ በሌላ ወገን ደግሞ ጋሊለዮ ጋሊለይ ያዊት (constant) ንፅፅራዊ ፍጥነት ያላቸው አካላት ተፈጥሮን ለመለካት ቢሞክሩ አንድ አይነት ልኬት እንደሚኖራቸው ያስረዳበት ንድፈ ሐሳብ፣ እርስ በእርስ የሚጣረሱ ቢመስሉም ሁለቱም በየፊናቸው ተፈጥሮን በትክክል መወክል የሚችሉ ንድፈ ሀሳቦች መሆናቸውን የሚያወላውል አልነበረም፡፡ ታዲያ አይንስታይን በዚህ ጨቋኝ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ሁለቱንም ውብ ሒሳባዊ ሞዴሎች ሳይሽር፣ በተቃራኒው ሁለቱንም ሞዴሎች አንድ ላይ ያዋሃደበት ‹‹Special Theory of Relativity›› የተሰኘው ንድፈ ሃሳብ ለሳይንስ ስርዓት የበላይነት ግሩም ማሳያ ነው፡፡
በሳይንስና በሙዚቃ ውህደት ላይ አራተኛና የመጨረሻ የማሰቢያ ነጥብ ልወርውር፡፡ እንደ ጆሃነስ ብራሃምስ ላለ የሙዚቃ ባለሞያም ሆነ እንደ እኔ ላለ ባለሞያ ያልሆነ ቀንደኛ የሙዚቃ አፍቃሪ ቻኮን በሁለት ደረጃ ትርጉም ይሰጣል፡፡ ሳባስቺያን ባህ እንዲህ አቀላጥፎ የሚያንበለብለው የሙዚቃ ቋንቋ የአድማጩን ስሜት እስር ድረስ ዘልቆ ይኮረኩረዋል፡፡ ይህ የሚሆነው የአድማጩ ጭንቅላት ቋንቋውን በሚገባ መረዳት በመቻሉ ነው፡፡ ይህ የመጀመሪያው ደረጃ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በዚህ የሙዚቃ ቋንቋ የተወከለውን የሰባስቺያን ባህ ልዩ ስሜት፣ አስተሳሰብ፣ አስተውሎት ወዘተ… መረዳት በመቻል የሚገኝ ልዩ ደስታ አለ፡፡ የእነዚህን ሁለት ደረጃዎች ተዛማጅ መገለጫዎች በሳይንስ ውስጥ ለመመልከት ወደ ሊ ስሞሊን ‹‹The life of the cosmos›› እንመለስ፡፡
‹‹የሰው ልጅ አዕምሮ የወለደውን ሒሳባዊ ሞዴል በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሞዴሉ የተወከለውን ገሃዳዊ ሁኔታ በተመሳሳይ ሰዓት መረዳት መቻል የሚያስገኘው አንዳች ሀሴት አለ›› ምንም እንኳን እስከ አሁን ድረስ ከሙዚቃ አቻው ጋር ሲነፃፀር በስሱ የተስተዋለ ክስተት ቢሆንም ሊ ስሞሊን የሚያወራለት ሃሴት ለሳይንቲስቱም ለሳይንስ አፍቃሪውም ስሜት ቅርብ ነው፡፡ ቀላል ምሳሌ፡- የፓይታጎራስን መክስት (pythagorean theorem) አመጣጥና ማረጋገጫ በተረዳንበት ቅፅበት መክሰቱ በዓለም ላይ ላሉ ቀጤ ጎን ሶስቶች (Ritht triangles) በሙሉ መስራት መቻሉን መገንዘብ ከቻልን የተባለው ልዩ ደስታ ይጎበኘናል፡፡
The post ሳይንስና ሙዚቃ appeared first on Zehabesha Amharic.
የማለዳ ወግ…አርቲስት ሜሮንና አስቴር ተናገሩ ፣ እኛስ ! * በስደት የግፉአኑን መከራ ለመቅረፍ ምን እየሰራን ነው ? * የውዴታ ግዴታ የለብንምን?
የማለዳ ወግ… አርቲስት ሜሮንና አስቴር ተናገሩ ፣ እኛስ !
* በስደት የግፉአኑን መከራ ለመቅረፍ ምን እየሰራን ነው ?
* የውዴታ ግዴታ የለብንምን?
ነቢዩ ሲራክ
ሜሮንና አስቴር …
ያን ሰሞን አርቲስት ሜሮን ጌትነት ” አትሂድ ” ባለችው የተዋጣለት ግጥሟ ታሸበሽብ ታረግድለት የነበረውን የኢህአዴግ አመራርና ስርአቱን በሰላ ብዕሯ መሸነቋቆጧ ከጫፍ እስከ ጫፍ የሃበሻ መነጋገሪያ ሆኖ ከርሟል ። የሜሮን ፋና ወጊ ፣ በጥበብ የተከሸነ ፣ ነፍስ አሽር ግጥም በድምጽ ብቻ ሲሰራጭ ገዥውን ፖርቲ የመከላከያ ሰራዊት መለዮ ከነኮፊያው ሳይቀር እየደነቀረች የተለያዩ ወቅታዊ ደጋፊ ዝግጅቶችን ስታቀርብ የምናውቃት አርቲስት ሜርን ጌትነት ድምጽ መሆኑን ለማመን ቸግሮንም ነበር ። ብዙም ሳይቆይ ግን ዛሬ በእሳት ዶግ አመድ በሆነው የጣይቱ ሆቴል ጥበብ ይዘንብበት በነበረው የጃዝ አንባ ዳራሽ መድረክ ላይ ግጥሙን ስታነብ የተቀረጸችው ፍንትው ያለ መረጃ ቀረበ ።
“ጉድ ” አልን … ” እውነት ሜሮን ናትን ” ስንል አይሆን መስሎን የተጠራጠርነው ገሃድ ሆኖ እውነቱ ተገለጠ ፣ ጥበቧን የወደዱላት ” ጥበብ የህዝብ ስሜት ጉዳት ሲገልጥበት እንዲህ ነው ፣ አበጀሽ ሜሮናችን ” በሚል የቆየ ብሽቀታቸውን ትተው የአድናቆት ፍቅር ስሜት ቀየሩት ፣ በቅኔ በውዳሴም በክብር ” ሜሮን ሜሮን ” እያሉ ከፍ ከፍ አደረጓት ! ሜሮን ጨክና ትደግፈው ይደግፉት የነበረውን የኢህአዴግ መንግስት ቅኔ ዘርፋ መሸንቆጧን ያልወደዱላት ምላሽ ቅኔ ሳይቀር ተቀኘን ብለው ትንታጓን ሜሮንን የስድብ ውርጅብኝ አወረዱባት ! ” ይህች ደግሞ ምን ጎደለብኝ ብላ ነው? ” ሲሉ የህዝብ ህመም ፣ የህዝብ ሮሮና ዋይታን የህዝብ ልጆች ጥበበኞች የመግለጽ ሃላፊነት እንዳለባቸው እያወቁት እንዳላቀቁ ሆነው ዘለፏት ፣ ተሳለቁባት !
የጥበብ ሰዎች እንደ ሃገሬው በከፋው የእኛ ፖለቲካ ዘባተሎ እየተገፉ ” ሃብታችን የህዝብ ፍቅር ነው! ” እንዳላሉ መሸነጋገላቸው አስተዛዛቢ ሆኖ መንጎድ ያዘ ፣ ህዝብና ጥበብ በፖለቲካ ቅኝት ተለያዩ ! አርቲስቱ ትዝብት ላይ ወደቁ … ይለይለት ያላ የሚመስለው መንግስት ያን ሰሞን ህወሃት ኢህአዴግ ያለፈበትን የትግል ጉዞውን ያዩለት ዘንድ አርቲስት የጥበብ ሰዎችን ወደ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የትጥቅ ትግል መጠንሰሻ ወደ ደደቢት ሲወስዳቸው ነገሩ ሁሉ ግልጥልጥ ማለት ያዘ !
በጉዞው ጉብኝቱ ስለሆነው ሁሉ አናወጋም …በዚያው በጉብኝቱ በተደረገው ውይይት የተነሱ በርካታ ውይይቶች አንዱ ግን እናነሳለን ! ቀልብ ሳቢ ከነበሩት ውይይቶች መካከል የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣኖች በተካፈሉበት አንድ ውይይት የሰላ ጥያቄ ለመከላከያ የበላይ ለጀኔራል ሳሞራ የኑስ የሰላ ጥያቄ ያቀረበችውን የአስቴር በዳኔ ጥያቄ ይጠቀሳል ፣ በእርግጥም የአስቴር በደኔ ጥያቄ ፍጹም ይሆንል ያልተናል ፣ ያልተጠበቀና ያልታሰበ ነበር ፣ የአስቴር ይህን ሁሉ አመት አውራ ሁናችሁ መግፋታችሁ ያዋጣ ይሆን የሚል አንድምታ ያለው ምክር የተቀላቀለበት ጥያቄ ለጀኔራል ሳሞራ ቀርቦ ምላሽ የተባለው ምልሽ ተሰጠው …
እናም የአስቴር ጉዳይ ፣ የአስቴርን እያንሾካሾከ ከራሱ ጋር የሚፋተገው የእኔ ቢጤ ፈሪ ጥያቄው የእሱ ጭምር ሆኖ እያለ የህዝብ ልጇ የብርቱዋ አርቱስት አስቴር በዳኔ ጥያቄ እያለ እንደ ሜሮን ሾተላይ ግጥም እየተቀባበለ መመልከቱ እውነት ነው ፣ በእርግጥም ጥያቄው የብዙሃን ጥያቄ ነበርና የአርቲስት አስቴር በዳኔ ጥያቄና መልስ የያዘው ተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ መረጃ እንደ ሜሮን ግጥም ከጫፍ እስከ ጫፍ በሰፊው ተናኘ !
እኛስ እንደ ዜጋ !
ከሜሮን ሰሞነኛ መነጋገሪያ ግጥም ለጥቆ አርቲስት አስቴር በዳኔ ለኢህአዴግ መንግስት ቁንጮ ባለስ ልጣናት ያቀረበችው ጥያቄ እንደ ሜሮን ሁሉ በድጋፍና በጥላ ቻ የታጀበ ነበር ። እኔ የምለው እኛስ የት ነው ያለነው ነው? ይህን ብየ የማጠይቀው ! መልስም አለኝ !
አዎ አርቲስት አስቴርና አርቲስት ሜሮን ያሻቸው የፈቀዱትን ተናግረዋል ፣ በቃ ! ሁለቱም እህቶች ስሜታቸውና ማስተላፍ ያለባቸው መልዕክት ያመኑበትን ሲሆን በአደባባይ ነው የተናገሩት ! እኛ ግን እነሱ ያመኑበትን ለመቀበል ምክንያቱ ግልጽ ሆኖ እያለ አግድመን እየተራኮትን ያለነው ! አርቲስቶች ባነሱት በብዙሃን የሃገሬ ሰው ውስጥ የሚንቀለቀል መሰረታዊ እውነትና ጥያቄ ውስጥ ራሳችን ማየት ተስኖናል ። እንደ ዜጋ በከባቢያችን ከእኛ የሚገባውን ጥቂቱን ሃላፊነት ሳንወጣ ማግለል ፣ ማንቋሸሽ ፣ ማጥላላትና መኮፈስን ለምደነዋል ! ግን ለምን ? አልልም ! እስከ መቸ እንዲህ ሁነን እንቀጥላለን ? ግን እላለሁ !
የሃገር ቤቱ ፖለቲካ እሳት ሆኖ ይፋጃል ቢባል ፣ በአረቡ አለም በስደት የሚገኙ እህቶቻችን መከራ እንዲያቆም በስደት ያለን የተሻለ ኑሮ የምንገፋው እንደ ዜጋ ለግፉአኑ የቻልነውን ማድረግ የሞራል ግዴታ እያለብን ለማድረግ ፈቃደኞች አይደለንም ! መከራና ሰቆቃው ከቀን ወደ ቀን እየከፋ መጥቷል ፣ የመንግስት ሹማምንት ከሞቀው ወንበራቸው ተነስተው ለተጎጅ ወገኖቻቸው እንዲተጎ እንኳ የሰላ ሂስ ሰንዝረን ቀርቶ ተሽቆጥቁጠን በየበአላቱ ስናጅባቸው ለተገፊው ወገን እንዲደርሱለት አንመክራቸውም ! በስደት የግፉአኑን መከራ ለመቅረፍ ምን እየሰራን ነው ? የውዴታ ግዴታ የለብንምን ?
አንዳንዶቹም ሹሞቻቸን ከማስተማር ከምመከር ወጥተን ጥሩ ነገር እንደሰሩ እናሞካሻቸዋለን ፣ የሰላ ሂስ የምናቀር በውን ” የግንቦት 7 ፣ የኦነግ ፣ የአረናና የማንቴስ ተቃዋሚ አባላት ” እያልን ለጥቅም ማግበስበሱ እኩይ ምግባር መትጋት ይቀናናል ፣ አድርባይ አጎብዳጅነቱን ትተንና ላንመለስበት ንስሃ ገብተን ፣ መቸ ይሆን ወደ ትክክለኛው መንገድ የምንጓዘው? መቸ ነው ለፖለቲካ ወገንተኛነትን ፈንግለን ለወገናችን መከራ መቆም ፣ ለሰብዕና ብለን እውነትን የምንከተለው ?
ከሰብአዊ ሰው በወጣ የአድርባይነት ካባ ደርበን የሚ ገፋውን ህይዎታችሁን መታዘብ ዘልቆ ያማል ! እንደ አርቲስት ሜሮን እውነትን ሸፋፍነን ብንከርምም ቀኑ ሲደርስ ፣ ውስጥ አልቀበል ሲል ለእውነት መስዋዕት ለመሆን የምንተጋበት ውበትን እውነት ብለን የምንገልጥበት ቀን ናፍቆኛል ። እንደ አርቲስት አስቴር ደፍረን የህዝብ የወገናችን “የህሊና ድምጽ ” መሆኑ ቢሳነን ፣ የሚፈሩትን ሹሞች ሳንፈራ በግምባር የምናጠይቅበት ስለ እውነት የምናፈጥበት ሞራል ባይኖረን … እንደ አቅማችን ፣ እንደ ራሳችን ፣ እንደ ቤታችም ፣ እንደ ጉዳታችን ሆነን የግፉአን ስደተኛ እህቶ ቻችን መከራ እንዲያቆም የምተጋበት ቀን ናፍቆኛል ! እውነቱን በገሃድ መገላለጥ ፣ ለየቸገረው ስደተኛ እርዳታን ድጋፍ የማድረጉ ሃላፊነት ከማናችንም የሚጠበቅ የውዴታ ግዴታ መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል ! ያ ሲሆን ማየት ደግሞ በጣሙን ናፍቆኛል !
እስኪ ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
ጥር 12 ቀን 2007 ዓም
The post የማለዳ ወግ… አርቲስት ሜሮንና አስቴር ተናገሩ ፣ እኛስ ! * በስደት የግፉአኑን መከራ ለመቅረፍ ምን እየሰራን ነው ? * የውዴታ ግዴታ የለብንምን? appeared first on Zehabesha Amharic.
የቦብ ማርሌይ ሐውልት በአዲስ አበባ ሊቆም ነው
ጥር ፲፪(አስራ ሁለት ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከሐውልቱ ስራ አስተባባሪዎች መካከል የጃኖ ባንድ መስራች የሆነው አርቲስት አዲስ ገሰሰ ለታዲያስ አዲስ እንደገለጸው፤ የቦብ ማርሌይ ሐውልት ከሶስት ሳምንት በሁዋላ በገርጂ ኢምፔሪያል ሆቴል ፊት ለፊት ይቆማል።
በምርጫ 97 ዋዜማ የቦብ ማርለይ 60ኛ አመት በመስቀል አደባባይ ሲከበር፤ በወቅቱ የመዲናዋ ከንቲባ የነበሩት አቶ አርከበ እቁባይ በበአሉ የተገኙትን የቦብ ማርለይ ቤተሰቦችን ሐውልቱ ይቆምበታል ወደተባለው ስፍራ በመውሰድ፦<በሲህ ቦታ የቦብ ማርለይ ሐውልት እንዲቆም ወስነናል”በማለት ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
አቶ አርከበ ከአስር ዓመት በፊት ቃል ቢገቡም፤ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ሐውልቱ ሳይቆም መቆየቱን የገለጸው አርቲስት አዲስ፤ ከሶስት ሳምንት በሁዋላ በተባለው ቦታ በይፋ እንድሚቆም አሳውቋል።
The post የቦብ ማርሌይ ሐውልት በአዲስ አበባ ሊቆም ነው appeared first on Zehabesha Amharic.
የደደቢት ጉዞ መዘዝ፤ ከሰራዊት ፍቅሬ እስከ ታገል ሰይፉ
ክንፉ አሰፋ (ጋዜጠኛ)
በመጀመርያ ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ደጋፊና ተደጋፊ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን በሙሉ ጠሯቸው። ሰበሰቧቸው። እንዲህም አሏቸው። “ወደ ደደቢት አብራችሁን ትሄዳላችሁ፤ እዛ እንደደረሳችሁም አመጣጣችንንና አካሄዳችንን በደንብ አድርጋችሁ ታጤናላችሁ። ከዚያ ስትመለሱ ሁሉንም ነገር ለህዝቡ ትናገራላችሁ።…”
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የሃገር መሪ ሆነው የሚሰሩት እኝህ ሰው መልዕክታቸውን በዚህ አላበቁም። አይናቸውን ፈጠጥ፤ ጉሮሯቸውንም ጠረግ-ጠረግ አደረጉና ንግግራቸውን ቀጠሉ “ስለረጅሙና መራራው ትግላችን፤ ከጅምራችን እስከ አያያዛችን የታዘባችሁትን ሁሉ ንገሩን። ጥሩውንም ይሁን መጥፎውን ነገር ሳትደብቁ ተናገሩ።…”
ድምጻዊው በዝማሬ፣ ጸሃፊው በድርሰት፣ ተዋንያኑ በተውኔት ስለ ህወሃት የአርባ አመት ጉዞ እንዲመሰክሩ የተሰጠች ትእዛዝ መሆንዋ ነው። አጭር፣ ግልጽ እና ቀጭን መልዕክት ነበረች።
የስርዓቱ ደጋፊ ሳይሆን ይልቁንም ተደጋፊ የሆኑት ሁሉ የዘመቻውን ጥሪ በደስታ ተቀበሉ። ወደ ደደቢትም አመሩ። የታዘቡትንም ነገር ሲናገሩ ሰማን።
ልብ እንበል! እነዚህ የጥበብ ሰዎች ናቸው። ጥበብ ደግሞ የሕዝብ አገልጋይ ናት። ጥበብ ለእውነት የምትቆም ዘብ ናት። ጥበብ አንድን ህብረተሰብ የመቅረጽ እና የመለወጥ ሃይል አላት።
በአለማችን የጥበብ ሰዎች ሚና ጎልቶ የሚታየው ተፈጥሮ ባደላቸው የጥበብ ስራ ብቻ ሳይሆን፤ እነዚህ ሰዎች በጥበብ ስራቸው ውስጥ ለህዝብ በሚያስተላልፉት እውነተኛ መልእክትም ጭምር ነው።
አርቲስቶች አክቲቪስቶች መሆን አለባቸው ብሎ መከራከር አይቻልም። ይህ የራሳቸው ምርጫ ነው። መሆን ካለባቸው ግን የህዝብን እንባ ማበስ ነው የሚገባቸው። ወቅቱን ጠብቆ እንደሚቀየር ድሪቶ መንግስት ሳይሆን ከህዝብ ጎን መቆም ያስከብራቸዋል።
ጥበብ ቆራጥነትን ትጠይቃለች። መስዋዕትነትን ልታስከፍልም ትችላለች። ፍሬዋ ግን ሁል ጊዜ ጣፋጭ ነው። እውቁ ቻይናዊ አርቲስት አይ ዌዊ እዚህ ላይ ይጠቀሳል። አሜሪካዊቷ ጁዲ ችካጎም እንዲሁ። ጃማይካዊው ቦብ ማርሌይ እና የናይጄርው ፌላ ኩቲ በአለማችን ላይ ለውጥ ያመጡ የጥበብ ጀግኖች ናቸው። የኛዋ አርቲስት አስቴር በዳኔም ለዚህ ዋቢ ነች። ማህበራዊ ድረ-ገጾች ይህንን አስረግጠውልናል።
“ህዝቡ አጎብዳጆች ይለናል።” አለች አርቲስት አስቴር በዳኔ ከዚያ ሁሉ መንጋ ተነጥላ። ‘እውነት ነጻ ያወጣችኋል!’ የሚለው ክርስቶሳዊ አባባል የተዋሃዳት ወጣት። እውነትን ተናግራ ራስዋን ነጻ አወጣች። እርግጥም የህሊና ነጻነትዋን ለማወጅ መድፈር ነበረባት። ማማጥም ነበረባት። አርቲስትዋ እንደጦር የፈራችው ከፊትዋ ተደርድረው የነበሩ ጉምቱ ባለግዜዎች አልነበሩም። ምክንያቱም ጉዳዩን ለነሱ አስቀድማ ተናግራ ነበርና። ይልቁንም ከአጠገብዋ የነበሩ የስራ ባልደረቦችዋ እና የሙያ አጋሮችዋ እንደጦር ያስፈራሉ። እንደ ይሁዳ አሳልፈው ሊሰጧትም ይችላሉ። ደደቢት ላይ ሲደርሱ ሁሉም በአንድ ማሰብ ጀመሩ። ደደቡ… አንድ ግዜ ተኑሮ ለሚሞትበት አለም ሁሉም ከራሱ ተጣላ። ሁሉም ከህሊናው ሸሸ። ሁሉም ለማደር አጎብዳጅ ሆነ። በመጨረሻም ሁሉም አስቴርን በአርባ ክንድ ራቁዋት። ግና እስዋ ጣርያ ስትነካ እነሱ ደግሞ ሲዘቅጡ አየን።
የኪነ-ትበብ ሰዎቻችንን መፈተኛ ግዜ ብቅ አለ። ግን ይህ ሁሉ ወጪ እና ሽርጉድ ለምን አስፈለገ?
ጉዞውን ከመጪው ምርጫ ጋር የሚያያይዙ ወገኖች አሉ። ጉዞውን እንደምርጫ ዘመቻነት ለመጠቀም…። ይህ የዋህነት ይመስላል። ምክንያቱም ህወሃት አንድም ግዜ በምርጫ ዘመቻና ግልጽ በሆነ ውድድር ምርጫ አሸንፎ አያውቅም። ነብሳቸውን ይማርና አቶ መለስ ከነ ስዬ ቡድን ጋር በተለያዩ ግዜ ተናግረውታል። “ህወሃት በስብሷል!” ነበር ያሉት። ላለፉት ፪፫ አመታት ይህ የበሰበሰ ስርዓት ነው ሃገሪቱን እየገዛ ያለው። ይህ የበሰበሰ ስርዓት በምርጫ ሳይሆን የህዝብን ድምጽ በመስረቅ ነው እስካሁን ያለው።
ከምናከብራቸውና ከየምናደንቃቸው የኪነጥበብ ስዎች ውዳሴዎች ሰማን። ነዋይ ደበበም እጅግ አድርጎ ሲረግመው በነበረው ደደቢት ላይ ዘፈነ። እንዲያውም በስሜት ዘፈነ። “የሃገር ነቀርሳዎች” ሲላቸው የነበሩትን እነ ሳሞራን፣ እነ አባዱላን፣ … እያቀፈ … አልረሳም እያለ አቀነቀነ።
በዚያ የቀውጢ ወቅት ከሰለሞን ተካልኝ ከተቃዋሚ ወገን ወጥቶ ህወሃትን ሲቀላቀል ድምጻዊው ነዋይ ደበበ እንደ እብድ ነበር ያደረገው። ያዙኝ፤ ልቀቁኝ አለ። የንዴት ቃላትን ሁሉ በዘፋኙ ላይ አዥጎደጎደው። “ማሰብ የማይችል ደደብ ሰው!” አለ ነዋይ። ቀጠለናም “ሰለሞን ተካልኝ ስጋ የሚበላ በሬ ነው።” ሲል ድምጻዊውን ከሰብአዊ ፍጡርነት ወደ እንስሣነት ጎራ መድቦት ነበር።
ዛሬ በዚያው መድረክ ላይ አዲስ ትእይንት እያየን ነው። የግዜ ሃዲድ ላይ ሆኖ የሚመለከተው ሁሉ በትዝብት የሚያስቆዝም አሳዛኝ ድራማ፤ አርቲስት ብለን የምንጠራቸው ወገኖቻችን የሚፈጽሙት የፖለቲካ ዝሙት። ነዋይ ደበበ በግዙፉ የሰለሞን ተካልኝን ትከሻው ላይ ለመጠምጠም እጆቹ በጣም ሲረዝሙ በመገናኛ ብዙሃን ተመለከትን። … አጃኢብ አለ ያገሬ ሰው!
አዕምሮ ማሰብ ሲያቆም፣ አንገታቸው አዙሮ ማየት ሲሳነው፣ ልቦናችን የቅርቡን ክስተት ሲዘነጋ፣ የስነ-ልቦና ችግር ነው ከማለት ውጭ ምን ይባላል?
የሰራዊት ፍቅሬ ማጎብደድ ደግሞ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም። ይህ ሰው በ ፩፱፹ዎቹ በነበረው የርስ በርስ ውግያ ወታደር ሆኖ ከደርግ ወገን ነበር የተሰለፈው። ዛሬ በሽሬ ሽንፈቱ ላይ ጥሎት የሸሸው የጦር ታንክ ላይ ቆሞ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እጆቹን እያወጣ ደግም ቀለደ። ለካስ ደርግ እንደዚህም አይነት ወታደር ይዞ ነበር ህወሃትን ይፋለም የነበረ? ሰራዊት ፍቅሬ ዛሬ ዝናው ሳይሆን ሃብቱ ጣርያ ነክቷል። አሰልቺ ድምጹና ምስሉ እጅ-እጅ እስኪል በቴለቭዥን እንዲቀርብ በገዢው ፓርቲ ተፈቅዶለታል። ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚውሉ የስርዓቱ በዓላት ቁጥር እጅግ በዝተዋል። የብሄር ብሄረሰቦች ቀን፣ የከተሞች ቀን፣ የአርሶ አደሮች ቀን፣ የአርብቶ አደሮች ቀን፣… ባዛር ለልማት ወዘተ። የማስታወቂያ ወጪው ከዝግጅቱ ወጪ አይተናነስም። ሁሉንም የማስታወቂያ ስራ ለሰራዊት ፍቅሬ ሰጥተውታል። ታዲያ እሱም ገሚሱን ለባለስልጣናቱ ማካፈሉ የግድ ነው። የዚህ ሰው መንቀልቀል ምስጢር ይህ ብቻ ነው። ሰራዊት ፍቅሬ በዚህ ሁኔታ የማስታወቂያ ስራውን በሙስና መስመር ውስጥ አዝልቆታል።
አንደኛው ተደጋፊም ተነስቶ “ይህ ነገር በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ፊት ለፊት ሃውልት ሊሰራለት ይገባል።” ሲል ተደመጠ። ሰውዬው ይህንን አምኖበት እንዳልተናገረ ሰዎቹም ይገምታሉ። መቼም ለእለት ጉርስ ሲባል እንደዚህ አይነት ለህሊና የሚጎረብጥ ነገር እያደረጉ ከመኖር፤ በልመና መተዳደር ክብር ነው።
ከጅምሩ የስርዓቱን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ሂደት ለመገምገም ወደ ደደቢት በረሃ መሄድም አያስፈልግም። ኢትዮጵያ ዛሬ ከገባችበት መከራ ለማውጣት የህወሃት አነሳስን ማጥናት ምንም ፋይዳ የለውም። መነሻው ጥሩም ይሁን መጥፎ፣ መድረሻው ግን አላማረም። ይህ ስርዓት ሃገሪቱን ባህር አልባ አገር አድርጓታል። የባህር በር የአንድ ሃገር ምስጢርም ነው። ኢትዮጵያ እንደ ማንኛውም ሉአላዊ ሃገር ምስጢር እንኳን የላትም።
ህዝቧም ከአፈናው ሰንሰለት ገና አልወጣም።
በአመለካከት ልዩነታቸው ብቻ ወገኖቻችን እንደ ጥጃ ሲታሰሩ የደደቢት ተጓዦቹ ይመለከታሉ። ሃሳባቸውን በነጻ የገለጹ ዜጎች የሽብርተኛነት ታርጋ ተለጥፎላቸው በግፍ ሲፈረድባቸው ይሰማሉ። ኢትዮጵያውያን እንደ ምጽዓት ሲሰደዱ በአይናቸው ይመለከታሉ። ለነጻነትና ለእኩልነት ታግለን መጣን የሚሉን ደግሞ በአንዲት ጀንበር ሚሊየነር ሲሆኑ ይታዘባሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ እንደሙያቸው አንዲት ቃል እንኳን ተንፍሰው አያውቁም። ወደ በረሃው መጓዙ እንደ ሲሲሊው የማፍያ ቡድን ከደደቢት ምሽግ ውስጥ ቃል-ኪዳን ለመግባባት ካልሆነ በቀር ፋይዳው አይታይም።
“ህዝቧ አጎብዳጆች ይለናል።” አለች አስቴር በዳኔ። ህዝብ ምን እንደሚላቸው የምትሰማው እስዋ ብቻ አይደለችም። ጆሮ ያለው ሁሉ ይሰማዋል። ይህን እያወቁ ግን አጎብዳጅ ምሆናቸውን ጭራሽ በብሄራዊ ቴሌቭዥን ወጥተው አሳዩን።
ህዝቡ ብቻ አይደለም። በእርግጠኝነት ለመናገር እነዚያ ባለ-ስልጣናትም አድርባዮቹን ይንቋቸዋል። በባህር ዳሩ የኢህአዴግ ጉባኤ “የኢህአዴግ አባል ለመሆን አንዱና ዋናው መስፈርት አድርባይነት ነው” በማለት አድርባይነትን የፈጠረውና ያስፋፋው ራሱ ህወሃት እንደሆነ ተናግረው ነበር። “አድርባይነት” ስርዓቱን በሚፈታተን ደረጃ መስፋፋቱን ከመግለጻቸውም በላይ አድርባዮቹን እንዴት እንደሚበቀሏቸውም ባህርዳር ላይ መክረዋል።
ደብረጽዮን ትእዛዙን ሲሰጡ ትንሽም ቢሆን ዲፕሎማት ነበሩ። ከትእዛዞቻቸው መሃል እንዲት እንዲህ የምትል መልእክት ነበረች። “…ችግሮቻችንንም ንገሩን።”
ይህች ሃረግ የኪነ-ጥበብ ሰዎቹ የህዝብን ብሶት በአደባባይ እንዲናገሩ በር ከፋች ነበረች። እነ አበበ ባልቻ ይህችን እድል ተጠቅመው ስለ-ኪነጥበብ መውደቅ እንኳን ትንሽ መልእክት ከማስተላለፍ ይልቅ ልወደድ ባይነትን መረጡ። ይህን ጥሬ ሃቅ የመናገር ድፍረት ያለው አንድ ሰው ጠፋ። ሁሉም ምስጋናና ውዳሴውን አበዛ። ለማደር የሚደረግ ካንገት በላይ ውዳሴ… መቼም ያሳዝናል።
በጭምጭምታም እንደሰማነው፤ በደደቢት አንዳች የተለወጠ ነገር የለም። ደደቢት ድሮም በረሃ – አሁንም በረሃ ነው። የአካባቢው ህዝብ ላይም ምንም የሚታይ ለውጥ የለም። ይህ ህዝብ ከሃያ አመታት በፊት የመናገር በብት አልነበረውም። ይህ መብት አሁን ብሶበት ሕዝቡ የመናገር ብቻ ሳይሆን የውጭ ራዲዮ እንኳን የመስማት መብቱን ተነፍጓል።
ይህችን ሃቅ የጎበኘ አንድ የኪነ-ጥበብ ባለሞያ እንዴት አስችሎት ዝም ይላል? ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነበር። “ስለ እውነት የቆመ አንድ ሰው ይጥፋ?” የሚለው ጥያቄ በህዝብ ዘንድ እየተብላላ እያለ ነበር አስቴር በዳኔ ብቅ ያለችው። ይህች አርቲስት የህዝቡን ጥያቄ ይዛ በድፍረት ወረወረችው። መገናኛ ብዙሃንና ማህበራዊ ገጾችም በዚሁ ጉዳይ ተጨናንቀው ከረሙ።
ለድቅድቅ ጨለማ ትንሽ የብርሃን ፍንጣቂ ትበቃለች እንዲሉ የዚያን ሁሉ የውሸት ክምር አንድ እውነት አፈራረሰው። ህዝብ ያከብራቸው የነበሩ የኪነጥበብ ባለሞያዎች ሁሉ ወረዱ። የማያልፈውን የህዝብ ፍቅር በሚያልፍ ነገር ቀየሩት።
ጥሪ የተደረገላቸው አርቲስቶች ሁለት አማረጮች ነበራቸው። ጥሪውን ተቀብሎ ሄዶ እውነትን መመስከር አሊያም እንደ ገጠሚ ታገል ሰይፉ ጥሪውን አለመቀበል። ገጣሚ ታገል ሰይፉ በኤፍ ኤም ፱፯ ራዲዮ ሲናገር እንዲህ ነበር ያለው።
“ባለፈው የመቀሌ ጉዞ ላይ እኔ አልሄድኩም። አርቲስቶች ሲሄዱ ጥሪ ተደርጎልኛል። ነገር ግን የደደቢቱን ጉዞ ስላላመንኩበት ቀርቻለሁ። ስለማልፈልገው ማለት ነው። …ለነሱም የምለው ነው። በተለይ ባለፉት 15 አመታት ብዙ ነገር አልተሰራም። ለስነ ጽሁፍ የሚመች ግዜ አይደለም። ስነጽሁፍን ትኩረት አልሰጡትም። እያየን ነው።”
ታገል ሰይፉ ቀደም ሲልም በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሃሳቡን ተቆርጦ እንዳስቀረበት ተናግሯል። ደደቢት ድረስ ሄዶ ሃሳቡን የማያስተላልፉለት ከሆነ መቅረቱ አይነተኛ አማራጭ ነው። አበበ ባልቻን፤ ሙሉ አለምን፣ ነዋይ ደበበን፣ … አርቲስቶች እና የኪነጥበብ ሰዎች ብለን ጠርተን፤ አስቴርንና ታገል ሰይፉን ምን ልንላቸው ይሆን?… ማህበራዊ ፍርዱን ከህዝቡ ያገኙታል።
ህወሃት ግን አንድ መልዕክት ለማስተላለፍ ነበር አርቲስቶቹን ወደ ደደቢት የወሰዳቸው። አዚህ ተነስተን፣ አፈር ለብሰን፣ አፈር በልተን፣ የፈረስ ሽንት ጠጥተን የያዝናት ስልጣን ናት። ይህችን ስልጣን በምርጫ እንደማናስረክብ እናንተም አረጋግጡልን… እንዲሁ ተቃጥላችሁ ታልቃላችሁ እንጂ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ አታስቡ… የሚል መልዕክት።
እኔም በዚህች ቀልድ ጽሁፌን ልቋጭ። አንድ የህንድ ኢንቨስተር አዲስ አበባ ዬሴፍ ቤተ ክርስቲያንን የቀብር ስፍራ አይቶ በሊዝ ሊገዛ ፈለገ። የአዲስ አበባ ባለስልጣናትን ጠርቶ እንዲሸጡለት ጠየቀ። ባለስልጣናቱም መልሰው ሌሎች ቦታዎች ሳያልቁ የቀብር ስፍራ ለግዜው እንደማይሸጡለት ነገሩት። ህንዱ መለሰና መከራቸው። “እኛ አገር ሰው ሲሞት እናቃጥላለን እንጂ አንቀብርም። ለምን ይህን ለም ቦታ ታባክናላችሁ?”
ባለስልጣናቱ መለሱ፣ “እኛ አገር ደግሞ ሰውን በቁሙ ነው እንጂ ሲሞት አናቃጥልም!“
The post የደደቢት ጉዞ መዘዝ፤ ከሰራዊት ፍቅሬ እስከ ታገል ሰይፉ appeared first on Zehabesha Amharic.
በኢትዮጵያ መንግስት በጥብቅ የሚፈለጉ 3 አርቲስቶች
እንዳለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብን በነፃነት ያለመግለጽ መብት አለመከበሩ ያጠቃው ጋዜጠኞችን ብቻ አይደለም። አርቲስቶችም ጋዜጠኞች ከሚከፍሉት መስዋእትነት ያልተናነሰ ትግል እያደረጉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለመታደል ሆኖ የሃሳብን የመግለጽ ነጻነት በመገደቡ ዛሬ እንደ ታላቁ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙና ተመስገን ደሳለን ያሉ ጋዜጠኞች ያልሆነ ክስ ተልጠፎባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ። የእነዚ ታላላቅ ጋዜጠኞች ‘ወንጀል’ መንግስት እንደሚለው ሳይሆን የሕዝብን በደልና ብሶት ማሰማታቸው ብቻ ነው።
ዛሬ ዛሬ ደግሞ ላለፉት 23 ዓመታት ሃሳባቸውን በነጻነት ከሚገልጹት ጋዜጠኞች ባልተናነሰ በመንግስት ጥርስ እየተነከሰባቸው የሚገኙት የጥበብ ባለሙያዎች እየሆኑ ነው።
እንደሚታወቀው በስደት ዓለም ከ150 በላይ ጋዜጠኞች እንዳሉ ሁሉ ዛሬ ቁጥራቸው በዛ ያሉ አርቲስቶችም በስደት ይህንን ስርዓት በመሸሽ በስደት ላይ ይገኛሉ። ከነዚህ መካከልም የኢትዮጵያ መንግስት እንደታላቁ እስክንድር ነጋ አስሮ ለማሰቃየት ከሚፈልጋቸው ታላላቅ አርቲስቶች መካከል 3ቱ ዋነኞቹ ሲሆኑ ሌሎቹ ሁለቱ ደግሞ ገና መንግስት እያጎበጎበባቸው በመሆኑ የ3ቱን ገድል አሳይቻችሁ የሁለቱን እንስት አርቲስቶችን ማንነት አስተዋውቃችኋለሁ።
1ኛ. ታማኝ በየነ
ብዙዎች እንደስሙ ነው ይሉታል። አክቲቪስት ሆኗል ከአርቲስትነቱ በተጨማሪ። አላሙዲ ካደረገለት በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያደረገልኝ ይበልጣል በሚል ዛሬም ድረስ የያዘውን አቋም ባለማዋዠቅ ይህን ተራ መንግስት ማንነቱን በማጋለጥ ላይ ይገኛል። በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ “የሕዝብ ልጅ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ታማኝ በየነ አሁን በስልጣን ላይ ያለው አንባገነን ስርዓት ከዚህ አርቲስት ጎን ፎቶ የተነሳ፣ የታየ፣ ሻይ የጠጣ አሸባሪ ነው የሚል ክስ እንደሚመሰርት አስታውቋል። ታማኝ በየነ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ክብርን ያገኘ በመሆኑና ክብሩንም ለገንዘብም ይሁን ለታይታ ያልቀየረ በመሆኑ ብዙዎች የሚያከብሩት ሲሆን የሕወሓት መንግስት ይህን ታላቅ አርቲስት በቁጥጥሩ ስር ለማዋል የማፈነቅለው ድንጋይ የለም።
ታማኝ የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሳይሆን በግሉ በሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ በነፃነት እያጋለጠ ዘረኛውን ስርዓት እርቃኑን እያስቀረው ሲሆን በተለይም መንግስትን የሚያጋልጠው ራሳቸው የመንግስት ባለስልጣናት በሚሰጡት እርስ በእርሱ በሚጣረስ በቪድዮ የታጀበ ቃለምልል መሆኑ በብዙሃን ዘንድ ተወዳጅነትን በሥርዓቱ ዘንድ ደግሞ ለመታሰር ከሚፈለጉ 3ቱ አርቲስቶች መካከል አንዱ ሆኗል።
2ኛ. ፋሲል ደመወዝ
አርቲስት ፋሲል ደመወዝን የማውቀው አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ የሚባል ሰፈር በተለምዶው ሸለቆ የሚባል አካባቢ ነው። በሸለቆ አካባቢ ሲራመዱ ፋሲል ሙዚቃ በመለማመድ ላይ እያለ የሚያሰማውን እንጉርጉሮ ማድመጥ የተለመደ ነው። ይህ ታላቅ ድምፃዊ የጎንደር መሬት ለሱዳን ተላልፎ በሕወሃት/ኢሕአዴግ መንግስት በተሰጠበት ወቅት “አረሱት” የሚል ዘፈን ካወጣ በኋላ በስር ዓቱ ሰዎች ወፌ ላላ ተገርፏል። ፋሲል ታዝሎ እስኪሄድ ድረስ በዚህ ፋሽስት መንግስት የተገረፈ ከመሆኑም በላይ የዳነው በህክምና ብቻ ሳይሆን በጸበልም ጭምር ነው።
ፋሲል ደመወዝ አሁን ሰሜን አሜሪካ ከመጣ በኋላ ‘እንቆልሽ” በሚለው አልበሙ ‘ያውላችሁ’ የሚል ዘፈን ያወጣ ሲሆን በዚህም ዘፈኑ ሃገሪቱን ካለምንም ተቀናቃኝ በአፓርታይድ ስርዓት ለሚመሩት ሰዎች “ሰው አስተዳደራችሁን እና በደላችሁን ጥሎ ጥሏችሁ እየሄደ ነው” ሲል ነግሯቸዋል። ፋሲል ደሞዝ በአሁኑ ሰዓት በሕወሓት አስተዳደር ከሚፈለጉ ዋና አርቲስቶች መካከል አንዱ ነው።
3ኛ. ክበበው ገዳ
ኮሜዲያን ነው። በጣም ይወደዳል። በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያም ይቀልዳል – ክበበው ገዳ። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ እሱን የሚያል ኮሜዲያን አለ ብሎ ለመናገርም ይከብዳል ይላሉ በሙያው ውስጥ ያሉ ሰዎች እና ባለሙያዎች። ክበበው ገዳ በማንኛውም ማህበራዊ ሕይወት ዙሪያ በመቀልድ ይታውቃል። ይህ ኮሜዲያን ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ በመመላለስ የተለያዩ የኮሜዲ ሥራዎችን አቅርቦ ተመልሷል። የዘንድሮው ግን ለጉድ ነው። የሥርዓቱን ሰዎች በእጅጉ እስቆትቷል።
ባለፈው ኦገስት 2014 ላይ ክበበው ገዳ በዳላስ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ በዓል አስተናጋጅነት ትልቅ በዓል ላይ ተገኝቶ ነበር። ይህ ኮሜዲያን አሁን ባለው የኢትዮጵያውያን ነባራዊ ሁኔታ ዙሪያ በርካታ ቀልዶችን አቀረበ። በተለይም አሁን ባለው ስርዓት ዙሪያ ልክ እዚህ ሰሜን አሜሪካ ኮሜዲያን በመሪዎቻቸው እንደሚቀልዱት ሁሉ ቀለደ። የሕዝቡን ብሶትም በቀልዱ አሰማ። ስለሟቹ ጠ/ሚ/ር፣ ስለሟቹ ፓትሪያሪክ፣ አሁን ስላለው የመንግስት አካሄድ በቀልድ አዋዝቶ አቀረበ። ለዚህ ኮሜዲያን ከሕዝብ የቀረበለት አድናቆትን ቢሆንም ከ ስርዓቱ ግን የቀረበለት ማስፈራሪያና ዛቻ ነው። እንደውም ‘ሃገርህ ትገባታለህ” የሚሉ ዛቻዎች ከስርዓቱ ደርሶታል። ክበበው ሙያውን ተጠቅሞ ባስተላለፈው መልዕክት ከኢትዮጵያ መንግስት ተላላኪዎች የሚደርስበት ማስፈራሪያ ሃገርህ ብትገባ አለቀልህ የሚል ብቻ ሳይሆን አሁን ባለበት ሃገር ሳይቀር እንደማይለቁት የሚገልጹ ናቸው።
ማነህ ባለሳምንት?
ሜሮን ጌትነትና አስቴር በዳኔ።
ሁለቱም ሴት አርቲስቶች ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደርሰውን የሴት ልጅ ተጽ ዕኖ ተቋቁመው አደባባይ የወጡ ሴቶች። ሁለቱም ያመኑመትን ይናገራሉ። ሁለቱም በተለይ ሃገር ቤት ካሉ አርርቲስቶች የሚለዩበት ነገር አላቸው። እነዚህ አርቲስቶች ስለ እውነት እውነትን ስለመሰከሩ ዛሬ በ ሥ ር ዓቱ ሰዎች እየተነከሰባቸው ያለውን ነገር አብረን እያየነው ነው።
The post በኢትዮጵያ መንግስት በጥብቅ የሚፈለጉ 3 አርቲስቶች appeared first on Zehabesha Amharic.
ኢቢሲ የዳና ድራማ አዘጋጆችን እናንተ ድራማውን የማትጨርሱት ከሆነ እኔ እጨርሰዋለሁ ሲል አስፈራራ
በአዲስ ስሙ አጠራር ኢቢሲ እየተላለፈ የሚገኘው ዳና ድራማ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊቋረጥ እንደሆነ ተሰማ::
ከኢቢሲ አካባቢ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከዚህ ቀደም ‹‹ዳና›› የተሰኘው የቴሌቪዥን ድራማ በተለይ አርቲስት ሜሮን ጌትነት መንግስትን የሚቆነጥጥ ግጥም ከለቀቀች በኋላ ድራማ ሊቋረጥ ነው ተብሎ በሰፊው የተወራ ሲሆን ለሁለት ሳምንት ተቋርጦ እንደገና መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ከኢቢሲ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ዳና ድራማ በድጋሚ ከተቋረጠበት እንዲጀመር የተደረገው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ታሪኩን ጨርሶ እንዲያጠናቅቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶትና በዚህ ቅድመ ሁኔታ ተስማምቶ ነበር፡፡ ይሁንና ታሪኩን ከመቋጨት ታሪኩን እየሳቡት በመገኘቱ በዚህ የተነሳ በቴሌቪዥን ጣቢያው በኩል ከባድ ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ አልሰማም በሚል ተስጥቶት የነበረ ሲሆን በመሆኑም ጣቢያው ‹‹እነሱ ካልጨረሱት እኛ እንጨርሰዋለን›› የሚል አቋም በመውሰዱ ‹‹ዳና›› ያለው ዕድሜ ከ3 ሳምንት በላይ እንዳይሆን ሆኗል::
ኢቢሲ ዳና ድራማን አዘጋጆቹ የማይጨርሱት ከሆነ ራሱ አቋርጦት በምትኩ ከ3 ሳምንት በኋላ ‹‹መለከት›› የተሰኘ አዲስ ተከታታይ ድራማ ዘወትር ዕሁድ ማስተላለፍ እንደሚጀምር ምንጮቻችን አስታውቀዋል::
The post ኢቢሲ የዳና ድራማ አዘጋጆችን እናንተ ድራማውን የማትጨርሱት ከሆነ እኔ እጨርሰዋለሁ ሲል አስፈራራ appeared first on Zehabesha Amharic.
“በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል ባይ ሰው ነኝ”–አርቲስት አስቴር በዳኔ (ቃለምልልስ ከቁምነገር መጽሔት ጋር)
ሰሞኑን በማህበራዊ ድረገፆች እና አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ላይ ስሟ በተደጋጋሚ የሚነሳው አርቲስት አስቴር በዳኔ የሀገራችን ‹ታዋቂ› አርቲስቶችን ባሳተፈውና ህወሃት የተመሰረተበትን 40ኛ ዓመት ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የጉብኝት ፕሮግራም በጠየቀቻቸው ጥያቄዎች መነጋገሪያ አጀንዳ ሆና ሰንብታለች፡፡ አስቴር ለመከላከያ ሚኒስትር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ለሆኑት ለጄኔራል ሳሞራ የኑስ ባቀረበቻቸው ጥያቄዎች የደነገጡ አንዳንድ የሙያ ጓደኞቿ ሳይቀሩ ‹ማግለልና መድልዎ› ለመፍጠርም ሲሞክሩ ስለመታየታቸው ይነገራል፡፡ የራሷን አቋም በግልፅና በድፍረት በዚያ መድረክ ላይ ካቀረበችው አስቴር በዳኔ ጋር አዲስ አበባ ላይ አጠር ያለ ቆይታ ከቁምነገር መጽሄት ጋር አድርጋለች – ለግንዛቤ እንዲረዳዎ ዘ-ሐበሻ እንደወረደ አስተናግዳዋለች::፡
ቁም ነገር፡- ሰሞኑን በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ ስምሽ በስፋት እየተነሳ ነው፤ ምንድነው?
አስቴር፡- እንግዲህ ከሰሞኑ የደደቢት ጉዞ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል፡፡ በጉዞው ላይ ለየት ያሉ ጥያቄዎች
ጠይቃለች በሚል መሰለኝ የተለያየ ነገር እየተባለ ያለው፡፡
ቁም ነገር፡- አንቺስ የተለየ ጥያቄ ጠይቄያለሁ ብለሽ ታስቢያለሽ?
አስቴር፡- ያሉና ሁሉም የሚያውቀውን ህዝቡ ውስጥ ያሉ ጥያቄዎችን ነው የጠየቅሁት፤ አዲስ ነገር አለው ብዬ አላስብስም፡፡
ቁም ነገር፡- በመጀመሪያ እስኪ በጉዞው ላይ እንዴት እንድትሳተፊ እንደተጠራሽ ንገሪኝ?
አስቴር፡- እንደማንኛውም አርቲስት ነው የተጠራሁት፤ ጉዞው እንዳለ የነገረኝ አርቲስት መለሰ ወልዱ ነው፡፡ የህወሃትን 40ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ አርቲስቶችን ወስደው ሊያስጎበኙ አስበዋል አንቺም ተጋብዘሻል ሲለኝ ደስ አለኝ፡፡ እንደ ፊልም ሰሪ ታሪካዊ ፊልም የመስራት ፍላጎት ልቤ ውስጥ ስላለኝ ለወደፊቱ የሚሰራ ነገር አይጠፋም ብዬ ሄድኩ፡፡ወደ እዛ ስንሄድ በቲቪ ብቻ የምታያቸው ባለስልጣኖች ከእኛ ጋር ጃኬት አድርገው መንገድ በመንገድ ሲሄዱ ሳይ ገረመኝ፡፡
ቁም ነገር፡-እነማን እነማን ነበሩ?
አስቴር፡- ዋና ዋናዎቹ ባለስልጣናት ነበሩ፤ እንግዲህ ሁሉንም ላላውቃቸው እችላለሁ፤ ግን የማውቀውን ያህል ጥሪ ካልከኝ፤ አቦይ ስብሃት፤አቶ በረከት ስምኦን፤አቶ አዲሱ ለገሰ፤ አቶ ስዩም መስፍን፤ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ፤ አቶ አባዱላ፤ ዶ/ር ካሱ ኢላላ ነበሩ፡፡
ቁም ነገር፡- ለጄኔራል ሳሞራ ያነሳሽው ጥያቄ ምን ነበር?
አስቴር፡- ከስብሰባው በፊት በአውቶብስ ስንሄድ አብረን ካለን አርቲስቶች ጋር ያው የተለመደ ወሬ እናወራለን፡፡ ሁሉም የመሰለውን ነው የሚናገረው፡፡ እኔ ደግሞ የምናገረው የማምንበትን ነው፡፡ የማስበውን እግዚአብሔር ያውቃል፤ ኑሮዬ ካሜራ ፊት ለፊቱ እንደተደቀነበት ሰው መሆን አለበት ብዬ ነው የማስበው ፡፡ ማስመሰል አልወድም፡፡እና እዛ አውቶብስ ውስጥ ስናወራ የምናወራውን የሰማ አንድ የኢህዴግ አባል የሆነ አርቱስት ‹ለምን ይህንን እዚህ የምታወሩትን መድረክ ተዘጋጅቶ አትናገሩም?› አለ፡፡ እኔ ደስ ይለኛል አልኩና በማግስቱ ነው መሰለኝ የደርግ 604ኛ ክፍለ ጦር የተደመሰሰበትን ቦታ አስጎብኝተውን ስንመለስ ስብሰባ ተጀመረ፡፡አዳራሹ በሙሉ ሰው ሞልቷል፤ፖሊሶች ጠባቂዎች አሉ፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላትም አሉ፡፡ እና ስብሰባው ተጀምሮ ጄኔራል ሳሞራ ገለፃ ሲያደርጉ አንዳንድ ማስታወሻዎችን እየፃፍኩ ነበር፡፡ ለምሳሌ እሳቸው ሲናገሩ ምን አሉ ‹ለአስር ዓመታት ያህል ስንታገል ቆይተን ውጤት አልመጣ ሲል በአዲስ አስተሳሰብ ነው ለውጥ ያመጣነው› ብለው ነበር፡፡እንደውም ምንድነው ያሉት ‹አሮጌ አስተሳሰብ አዲስ አስተሳሰብን ለመቀበል ይጎትታል› ብለው ነበር፡፡እንግዲህ እስከ እዛ ቀን ድረስ የተለያዩ የትግሉን ቦታዎች ተመልክተናል፡፡ እና ከእሳቸው ገለፃ በኋላ መድረኩ ለጥያቁ ክፍት ሲሆን አርቲስት አበበ ባልቻ መጀመሪያ ጠየቀ፤ ከዚያ ሳምሶን ማሞ ጥያቄ ጠየቀ/እናንተ እንደውም ባለፈው እትማችሁ ላይ አውጥታችሁታል/ ከዚያ ጥያቄ የሚጠይቅ ጠፋ፤ ቤቱ ፀጥ አለ፡፡ጠይቁ እየተባለ በየሻይ ቤቱና በየምግብ ቤቱ ባለስልጣናቱን በጀርባ ከማማት አሁን ነው መጠየቅ ያለብኝ ብዬ አሰብኩ፡፡ግን ፈራሁ፤ከዚያ ለአቶ በረከት በትንሽ ወረቀት ላይ ‹ ጥያቄ መጠየቅ ፈልጌ ነበር፤ ግን ፈራሁ› ብዬ ላኩላቸው፡፡›
ቁም ነገር፡- እንዴት ለእሳቸው ለይተሽ ይህንን ጥያቄ ጠየቅሽ?
አስቴር፡- ምን ሆነ መሰለህ? ከዚያን ቀን ቀደም ብሎ፤ እዚህ አዲስ አበባ ኤፍኤም ላይ ተንሻፎ ስለእኔ የተወራ ወሬ ነበር፤ በጉዞው ላይ በነበርኩበት ጊዜ ትንሽ አሞኝ ነበር፤ መንገዱም ሙቀቱም በሰዓቱ ምግብም ስለማንበላ አንዳንዴ ከጉብኝት በኋላ በ10 ሰዓት ነበር ምሳ የምንበላው በዚህ በዚህ የተነሳ ታምሜ በየቦታው እቀመጥ ነበር፡፡ የሆነ ቦታ ተቀምጬ ሳለ ከጀርባዬ አንድ ሰው ትከሻዬን መታ መታ አድርጎ ‹ውሃ ጠጪ የእኔ እህት› ሲለኝ፤ ‹እሺ የኔ ወንድም› ብዬ ቀና ስል አቶ በረከት ናቸው፡፡ እንዴት እንደደነገጥኩ ልነግርህ አልችልም፡፡በስመ አብ ሁሉ ብዬ አማትቤ ነበር፡፡ ከዛ በየመንገዱ ላይ ሌሎቹም ባለስልጣናት ሲያገኙን ‹.አስቴር እንዴት ነው? በርቺ› ይሉኝ ነበር፡፡ ያ ስብሰባ የተካሄደው ከዛ በኋላ ስለነበር ለአቶ በረከት ወረቀቷን ስልክ አንብበው ‹የፈለግሽውን ጠይቂ› ብለው ምልክት ሰጡኝ፡፡ በወቅቱ ለሴቶች
ዕድል ይሰጥ ሲባል ሌላ ሰው ስላልነበረ ለእኔ ተሰጠኝ፡፡ የተቀመጥኩት ከበስተኋላግራ ወንበር ላይ ነበር፡፡ የመጠየቅ ዕድሉ ሲሰጠን ግን ማይክ ስለማይደርስ ወደፊት ነይ ተብዬ ፊት ወንበር ላይ ተቀምጬ ነበር የጠየቅሁት፡፡ እንዴት እንደፈራሁ
ልነግርህ አልችልም፡፡ አንዳልኩህ ቤቱ በሙሉ በባለስልጣናት ተሞልቷል፡፡ግን እንደምንም ብዬ የፃፍኩትን ወረቀት እያየሁ ጠየቅሁ፡፡
ቁም ነገር፡-ምንድነው የጠየቅሽው?
አስቴር፡-ለምሳሌ ደርግን ለምን ጠላት ብለን እንጠራለን? ከደርግ ውስጥ ያሉ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው፤ በአይዲዮሎጂ ልዩነት ነው እንጂ በአብዛኛው ንፁህ የኢትዮጵያ ልጆች አሉበት፤ አሁንም ጠላት ማለት ተገቢ ነው ወይ? የሚለው የመጀመሪያ ሲሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ለሀገር ለመስራት ብለው የሚወዳደሩ በመሆናቸው ተፎካካሪ ፓርቲ ለምን አይባሉም? ተቃዋሚ የሚባለው ግን ከስሙ ጀምሮ የግድ መቃወም ያለበት ይመስለዋል፤ ግንቦት ሲመጣ 24 ዓመት ይሆናችኋል፤ እና ከዚህስ በኋላ በአዲስ አስተሳሰብና ፍልስፍና ሌላ የፖለቲካ ፖርቲ በምርጫ አሸንፎ ሀገሪቱን ሲመራ ልናይ እንችላለን ወይ? የሚልም አለ፡፡መንግስት ለመቀየር ከዚህ በኋላ የግድ ጦርነት አያስፈልግም፤ ስለዴሞክራሲ ስታስቡ ልባችሁ ምን ይላችኋል? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ነው የጠየቅሁት፡፡
ቁም ነገር፡- ምላሹስ?
አስቴር፡- ጄኔራል ሳሞራ የተቻላቸውን ያህል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ደርግን በተመለከተ ጠላት ያልኩትን ይቅርታ አድርጊልኝ ነው ያሉት፡፡ ትክክል ነው የደርግ ወታደር ተገዶ የሚዋጋ ነው፤ ነገር ግን ምን አለ መሰለሽ በወታደራዊ ውጊያ ውስጥ መጀመሪያ ላይ ተዋጊን ሞት ሞት እንዲሸተው ማድረግ ያስፈልጋል› ሲሉ አርቲስቱ ሁሉ አጨበጨበ፤ ተቃዋሚ ፓርቲን በተመለከተ ተፎካካሪ በሚለው ቢተካ እኔ ተቃውሞ የለኝም ግን አንዳንድ ተቃዋሚ የሀገሩን ጥቅም ለውጪ ሁሉ አሳልፎ የሚሰጥ አለ ብለዋል፡፡
አስቴር፡- ከጥያቄሽ በኋላ በአርቲስቶች በኩል የነበረው ስሜት ምን ይመስላል?
ቁም ነገር፡- ብዙዎቹ ሸሹኝ፤ከእኔ ጎን መሆን ራሱ የፈሩ ነበሩ፤ ትተውኝም የሄዱ አሉ፡፡ የሚገርምህ ግን ባለስልጣናቱም ሆነ የእነሱ ደጋፊዎች እኛ እኮ የታገልነው ማንም ሰው የመሰለውን እንዲናገር ነው፤ ጥሩ ጥያቄ ነው የጠየቅሽው፤
ነበር ያሉኝ፡፡
አስቴር፡- ከዋናዎቹ ጥያቄውን ከተጠየቁት ሰዎች ሳይመጣ ከሙያ ጓደኞችሽ መምጣቱ ምን ስሜት ፈጠረብሽ?
ቁም ነገር፡-አላውቅም፤ እንግዲህ ምናልባት እንደዚህ ብላ ትጠይቃለች ብለው አስበው ላይሆን ይችላል፡፡ ግን ውስጤ አንድ ነገር ነግሮኛል፤ አንዳንዶቹ ደስተኛ ላይሆኑ እንደሚችሉ፡፡ ምናልባትም ትንሽ ደፋር ሳልሆንባቸው አልቀረሁም/ ሳቅ/ አንድ አርቲስት እንደውም ማታ ራት ከበላን በኋላ አጠገቤ መጥቶ ምን አለኝ መሰለህ? አንቺ ምን ይሁን ነው የምትይው?› አለኝ፤ ምን ይሁን አልኩኝ? አልኩት ‹ኢህአዴግ ህዝብ እስከመረጠው ጊዜ ድረስ ሺ ዓመትስ ቢነግስ ምን አለበት?› አለኝ፡፡ እኔ ታዲያ ምን ቸገረኝ፤ እኔ እኮ ስለዲሞክራሲ ስለተነሳ ነው ጥያቄ የጠየቅሁት እንጂ ‹አንድ ሰው ተነስቶ እኔ ንጉስ ነኝ› ቢለኝ ሺ ዓመት ንገስ ነው የምለው› አልኩት፡፡ይሄ ግን የብዙዎቹን አስተሳሰብ የሚወክል አስተያየት እንዳልሆነ ይገባኛል፡፡ በነገራችን ላይ እኔ የተለየ ነገር ፈጥሬ የተናገርኩ ሰው አይደለሁም፡፡ የተሰማኝን ነው የተናገርኩት፡፡እውነት ነው ብዬ የያዝኩት ነገር ካለ በድፍረት እናገራለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- በየማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ ስላንቺ እየተባሉ ያሉትን ነገሮች ተመልክተሻቸዋል?
አስቴር፡- እኔ ብዙ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ አይደለሁም፡፡ በሳምንት አንድና ሁለት ጊዜ ባይ ነው፡፡ ለምሳሌ የእኔን ፎቶና የባለስልጣናትን ፎቶ አድርገው ስድብ በመፃፍ የሚያሰራጩ አሉ፤ ይሄ ትክክል አይደልም፤ የእኔ አላማ መሳደብ አይደለም፤ በመሳደብም ሆነ የሰውን ክብር በመንካት የሚመጣ ለውጥ አለ ብዬ አላምንም፡፡ እነዚህ ሰዎች እኮ ከፋም ለማም ሀገሪቱን እያስተዳደሩ ያሉ ሰዎች ናቸው፤ ያለፉበትንም የትግል ሂደት ሄደን ተመልክተናል፡ ፡ የሚካድ አይደለም፡፡ ያሉትን ጠንካራ ጎኖች አጠንክሮ ችግሮቹንም መንገር ነው የሚያስፈልገው፡ ፡እኔ በአሁኑ ወቅት ጊዜ የለኝም፤ ብዙ ስራ አለኝ፤ አራት መፅሐፍ ላሳትም ያዘጋጀኋቸው አሉ፤ አንድ ግጥም ሲዲ ጨርሻለሁ፤ የቤተሰብ ሀላፊ ነኝ፡፡ የልጆች እናት ነኝ፡፡ ፌስቡክ በሚሰጠው አፍራሽ አስተያየት ላይ ምንም ልል አልችልም፤ አልሞቀኝም አልበረደኝም፡፡ ከዚህ ይልቅ ፊልም ሰርቼ ብታወቅ ነው የምመርጠው፡፡ የሚገርምህ ቤተመንግስት ሁሉ ተጠራች ብለው የሚያወሩ አሉ፡፡
ቁም ነገር፡- ጉዳዩ ከፖለቲካ ጋር መያያዙ አስጨንቆሻል?
አስቴር፡- ለምን ያስጨንቀኛል? የፖለቲካ ጥያቄ ስትጠይቅ ጉዳዩ ወደ ፖለቲካ እንደሚሄድ እገምታለሁ፡፡ግን እኔ የጠየቅሁት ጥያቄ ካየሁት ከሰማሁት፤ሰው ከሚያወራው ተነስቼ በመሆኑ ያን ያህል አነጋጋሪ መሆኑ አስገርሞኛል፡፡
ቁምነገር፡- አስቴር ፖለቲከኛ ናት?
አስቴር፡-አይደለሁም፤
ቁምነገር፡-ፖለቲካ ትወጃለሽ?
አስቴር፡- ማለት.. የሚያናድዱኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ በዚያ በኩል ያለውን ሁኔታ ለማወቅ የምቆፍር አይነት ሰው ነኝ፡፡ ግን የፖለቲካ ጋዜጣና መፅሔት የምከታተል ሰው አይደለሁም፡፡ እርግጥ ነው በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል ባይ ሰው ነኝ ፡፡
ቁምነገር፡- አርቲስት ከፖለቲካ ነፃ መሆን ይችላል ብለሽ ታስቢያለሽ?
አስቴር፡- አርቲስት ፖለቲከኛ ሳይሆን መስታወት ነው፡፡ መስታወት ደግሞ ያለውን ነገር በግልፅ ነው የሚያሳየው ብዬ ነው የማምነው፡፡
ቁም ነገር፡- በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለችው አስቴር ምን አይነት ሴት ናት?
አስቴር፡- አስቴር በጣም ቆንጆ፤ በንጉሱ ፊት ሞገስ ያገኘች፤ ለህዝቧ ምህረትን ያመጣች ብልህ ሴት ናት፡፡እናትም አባትም ሆኖ መርዶኪዮስ ነው ያሳደጋት፡፡መርዶኪዮስ ከህንድ እስከ ኢትዮጵያ ነበር የሚያስተዳድርው፡፡ ንጉሱ ሲያገባት አይሁዳዊ መሆኗን አያውቅም፡፡ መርዶኪዮስ ሐማ ለሚባለው የንጉሱ ባለሟል አልሰግድም በማለቱ እንዲገደል ይወሰናል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን መላ ዘሩ ሁሉ እንዲጠፋ ይፈረድበታል፡፡ ይህን ጊዜ መርዶኪዮስ አስቴርን በዚህ ጊዜ ህዝብሽን ማዳን አለብሽ ይላታል፡፡ንጉሱ ብዙ ሚስቶች ስላሉት የሚፈልጋትን ካላስጠራ በቀር እሱ ጋር መቅረብ አይቻልም፡፡ አስቴር ግን ህዝቡ ለሶስት ቀን ፆም ፀሎት ይያዝ አለች፤ ከሶስት ቀን በኋላ ንጉሱ ሳያስጠራት ቢገድለኝም ይግደለኝ ብላ ንጉሱ ፊት ሄዳ ቆመች፡፡ ንጉሱ ዘንጉን ከዘረጋላት አለፈች ማለት ነው፤ ዝም ካለ ግን ያው ትገደል ነበር፡፡ ግን አስቴር በንጉሱ ፊት ሞገስ አገኘች፡፡ ምንድነው የምትፈልጊው? ሲላት ስለህዝቧ ተናገረች ፤ ስለህዝቧ የተጻፈው የሞት ደብዳቤ ለጠላቶቿ ሆነ፤ህዝቧንም አዳነች ማለት ነው፡፡ በጣም ነው አስቴርን የምወዳት፤
ቁም ነገር፡- በመጨረሻስ?
ቁም ነገር፡-ለሁሉም አስተያየት ለሰጡኝ ሰዎች ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡ አድናቆታቸውን ለሰጡን ብቻ ሳይሆን ለተቹኝም ለሰደቡኝም አመሰግናለሁ፡፡ ምክንያቱም ሰው ሁልጊዜ የሚናገረው በአዕምሮውና በአስተሳሰቡ በእውቀቱ ደረጃ ነው፡፡ ሁሉም ሰው እንደእኔ ያስብ ለማለት አይቻልም፡፡የተነገረውን ነገር የምትቀበልበት ልብ ነው አንተን የሚገልፅህ፡፡ ቀና አስተሳሰብ እንዲኖረን ነው የምፈልገው፡፡አንድ የሚያደርገን ነገር ላይ ብናተኩር ነው ደስ የሚለኝ፡ ፡ በፖለቲካ ልዩነት ሳቢያ እንደ ጠላት ባንተያይ እላለሁ፡፡ፖለቲከኛነትና እንጀራም ቢለያይ ጥሩ ነው፡ ፡ እኔ ለማንም ጥላቻ የለኝም፤ ማንንም አልቃወምም፡ ፡ሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያለችውን ኢትዮጵያ እንፍጠራት ነው የምለው፡፡ እየተፈራራን የትም አንደርስም፡፡የመሪዎቻችንን ልብ በፍቅር መማረክ ይቻላል፤ፈሪ ህዝብ ለምንም አይጠቅምም ፡፡ መንግስትም ፈሪ ህዝብ ይዞ ልማቱን መቀጠል አይችልም፡፡ ከዚህ ፍርሃት እንደ ህዝብ ተላቀን በፍቅርና በሰላም ለሀገር ይጠቅማል የምንለውን አሳብ እየሰጠን እንድንኖር ነው የምምኘው፡፡
ቁም ነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡
The post “በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል ባይ ሰው ነኝ” – አርቲስት አስቴር በዳኔ (ቃለምልልስ ከቁምነገር መጽሔት ጋር) appeared first on Zehabesha Amharic.
ፋሲል ደሞዝ አይኑን በአይኑ አየ
በሰሜን አሜሪካ ነዋሪነቱን ያደረገው ድምፃዊ ፋሲል ደሞዝ የወንድ ልጅ አባት ሆነ:: ፋሲል የመጀመሪያ ልጁን ከወ/ሮ መቅደስ ያገኘ ሲሆን በተደጋጋሚ በሚሰጠው ቃለምልልስ ሚስቱ ሁሉ ነገሩ እንደሆነች እና አሁን ላለበት ደረጃ ያበቃችውም እርሷ መሆኗን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር::
ፋሲል ደሞዝ የመጀምሪያ ልጁን ስሙን ቴዎድሮስ ሲል ስም አውጥቶለታል::
ለድምፃዊው እና ለባለቤቱ እንኳን ደስ ያላችሁ እንላለን::
The post ፋሲል ደሞዝ አይኑን በአይኑ አየ appeared first on Zehabesha Amharic.